ዳንኤል ዘነበ
ኤች ፓይሎሪ የሚባለው ባክቴሪያ ለጨጓራ ህመም መከሰት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ዘጠና በመቶ ያህሉ የጨጓራ ህመም በዚሁ ባክቴሪያ አማካኝነት ይከሰታል። ይህ የጨጓራ ባክቴሪያ ወይም ሄሊኮባክተር ፓይሎሪ ከሄሊኮባክተር ዝርያዎች ሰውን በመያዝና በማጥቃት የታወቀው ነው።
ከ50 በመቶ በላይ የዓለማችን ሰዎች በዚህ ኢንፌክሽን እንደሚያዙ ጥናቶች ያሳያሉ። ነገር ግን ብዙዎቹ ላይ ምልክት ስለማያሳይ ኢንፌክሽኑ እንዳለባቸው ብዙ ሰዎች አያውቁም።
ባክቴሪያው ወደ ሰውነታችን በምግብ አማካኝነት በመግባት ጨጓራ ውስጥ መኖር የሚችል ነው። እነኝህ ባክቴሪያዎች መላ ሳይባሉ ለብዙ ዓመት ከቆዩ አልሰር የተባለ ቁስለት በጨጓራ ላይና በትንሹ አንጀት የላይኛው ክፍል እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
ሂደቱ ደግሞ ከፋ ካለ አንዳንድ ሰዎች ላይ ካንሰር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
የጨጓራ ባክቴሪያ ከምንበላው ምግብ፣ ከምንጠጣው ውኃና ከምንጠቀማቸው በባክቴሪያው ከተበከሉ ቁሶች ሊያገኘን ይችላል። በሽታው አብዛኛውን ጊዜ ፅዳት በሚጎድልባቸው አካባቢዎች የሚከሰት ሲሆን ባክቴሪያው በምራቅ ንክኪና ባክቴሪያው ካለበት ሰው ጋር በሚኖር የፈሳሽ ንክኪ ሊተላለፍብን ይችላል። በሽታው ታዳጊ በሚባሉ አገሮች በስፋት የሚከሰት ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ባክቴሪያው ወደ ሰውነታችን ገብቶ የሚጠለለው በልጅነት ጊዜ ሲሆን ምልክት መታየት የሚጀምረው ግን ለዓመታት ከቆየ በኋላ ነው። ክሮኒክ የሚባለውም ለዛ ነው።
ይሁን እንጂ አብዛኛው ባክቴሪያው ያለባቸው ሰዎች ቁስለት አያጋጥማቸውም። ተመራማሪዎች የጨጓራ ባክቴሪያ አንዳንዶች ላይ ለምን ቁስለት ፈጥሮ እንደሚጠና ሌሎች ላይ ደግሞ ያን ያህል ችግር የማይፈጥረው ለምን እንደሆነ ብዙ ያረጋገጡት ነገር የለም።
ባክቴሪያው የጨጓራ ሕመም እንዴት ይፈጥራል?
የጨጓራ ባክቴሪያ ወደ ሆዳችን ከገባ በኋላ በጨጓራ ንብርብር ሽፋን ላይ በተለያዩ መንገዶች ጥቃት በማድረስ ጨጓራችንን ለቁስለት ተጋላጭ ያደርገዋል። እንደሚታወቀው ጨጓራችን ምግብ ለመፍጨት አሲድ ይጠቀማል፤ ይህ አሲድ በጨጓራችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያደርገው ይህ የጨጓራ ንብርብር አካል ነው።
ይህ አካል ከተሸረሸረ፤ ጨጓራችን ለአሲዱ የተጋለጠ ስለሚሆን ከፍተኛ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል።
ጉዳቱ የደም መፍሰስ ጨምሮ አካሉ ማመርቀዝ ወይም ቁስለት፤ እንዲሁም የበላነው ነገር እንዳይፈጭና እንዳይረጋ ሊያደርግ ይችላል፤ በዚህ ሁኔታም ሕመሙ መፍትሔ ካላገኘ እስከ ነቀርሳ ወይም ካንሰር የሚደርስ ወደ ተወሳሰበ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል።
ባክቴሪያው ህመም የመፈጠር አቅም የሚሰጡት ነገሮችን በሶስት ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን የመጀመሪያው አካባቢያው ሁኔታዎች፣ ሁለተኛው የግለሰቡ በሽታን የመከላከል አቅም፤ እንዲሁም የባክቴሪያው የራሱ የተፈጥሮ በሽታ አምጭነት ጉልበቶች ናቸው።
ባክቴሪያው የራሱ ብዙ በሽታ አምጭነት አቅሙን የሚያጎለብቱለት ተፈጥሮዎች አሉት።
ፍላጀላ እንደፈለገ ለመንቀሳቀስ ይረዳዋል፤ ቫይኩዬላቲንግ ቶክሲን የተባለው መርዛማ ንጥረ ነገር ቀጥታ ህዋሶችን በማጥቃት መግደል ይችላል። ይህም የተለያዩ ጎጂ ኢንዛይሞች አሉት።
ዩሬዝ፣ ሙሲኔዝ፣ ፕሮቲየዝ (ፕሮቴዝ)፣ ላይፔስ ሲሆኑ፤ እነዚህ ኢንዛይሞች የጨጓራን ድርብርብ መረብ ለመበጣጠስ እና ቁስለት ለመፍጠር በቂ መሣሪያዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
የጨጓራና የጨጓራ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ምልክቶች
በባክቴሪያው አማካኝነት በጨጓራችን ላይ ቁስለት ከተፈጠረብን፣ የማቃጠልና የመደንዘዝ ስሜት በሆዳችን የላይኛው ክፍል ሊሰማን ይችላል፤ ይህ ስሜት ሄድ መጣ የሚል ሊሆን ይችላል፤ በተለይ ሆዳችን ባዶ በሚሆንበት ሰዓት ማለትም በመደበኛ የምንመገብባቸው ሰዓታት መሃል እና በሌሊት ጊዜ ሕመሙ በደንብ ሊሰማን ይችላል።
የሕመሙ ቆይታም ከደቂቃዎች እስከ ሰዓታት የሚቆይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምግብ እንደበላን፣ በተለይ ወተት እንደጠጣን እና ፀረ አሲድ መድኃኒቶችን እንደወሰድን ሕመሙ ጋብ ይላል።
በአጠቃላይ ቀደም ብለው በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡- የሆድ መነፋት፣ ግሳት፣ የረሃብ ስሜት አለመሰማት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ያለምክንያት ክብደት መቀነስ ሊታዩ ይችላሉ። በጨጓራ ውስጥ የሚያጋጥም ቁስለት ደም ወደ ላይ እና አንጀታችን ውስጥ እንዲፈስ ሊያደርግ ይችላል፤ ከባድ የሚባል የጤና ችግርም ሊፈጥርብን ይችላል።
በመሆኑም የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩን ወደ ሕክምና በመሆድ የምንገኝበትን ሁኔታ መመርመር አለብን።
የሰገራ መጥቆርና ደም መቀላቀል ካለ፣ ለመተንፈስ መቸገር ካጋጠመን፣ ያለስራ የመልፈስፈስና የድካም ስሜት ከተጫነን፣ የቆዳ መገርጣትና ራስን የመሳት ሁኔታ ከታየብን፣ የተፈጨ ቡና የመሰለ ነገር የሚያስመልሰን ከሆነ፣ በቀላል በመድኃኒት የማይጠፋ ከባድ የሆድ ህመም ካለን የጨጓራ ባክቴሪያ ሊሆን ስለሚችል መታየት አለብን።
አልፎ አልፎ ደግሞ የጨጓራ ባክቴሪያ የጨጓራ ካንሰር ሊያስከትል ይችላል፤ እንዲያ ሲሆን በመጀመሪያ አንዳንድ ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፤ ለምሳሌ ማቃር ሊበዛን ይችላል።
በመቀጠል ግን የሆድ ሕመምና ማበጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ያለመራብ ስሜት፣ ትንሽ ከተመገብን በኋላ በጣም የጠገብን የሚመስለን ስሜት መሰማት፣ ማስመለስና ምክንያቱ ያልታወቀ የክብደት መቀነስ ሊታይብን ይችላል። ነገር ግን ይህ ነገር የሚከሰተው እድሜ እየገፋ ሲሄድ ነው።
በሕክምና ተቋም ለምርመራ ስንሄድ የጠቀስናቸው ምልክቶች ካልታዩብን የጨጓራ ባክቴሪያ ምርመራ ላይታዘዝልን ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት ባክቴሪያው ለክፎን የሚውቅ ከነበረ፣ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከጨጓራ ባክቴሪያ ውጪ ለሕመም ማስታገሻ የሚወሰዱ እንደ አስፕሪን ያሉ መድኃኒቶች በጨጓራ ንብርብር ላይ ተመሳሳይ ጉዳት ሊያደርሱብን ይችላሉ፤ በመሆኑም ትክክለኛው የጨጓራ ሕመም የፈጠረብንን ነገር ለመለየት ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በአጠቃላይ በጊዜውና በአግባቡ ያልታከሙ ህሙማን ዘንድ በሽታው ሊወሳሰብና ወደ ከባድ የጤና ችግር ሊያመራ ይችላል። ከእነዚህ መሃከል፡-
ሀ. የጨጓራ መድማት (ቡና አተላ የመሰለ ትውከት ወይም ሬንጅ የመሰለ ሰገራ ማየት)
ለ. የጨጓራ ወይም አንጀት መበሳት
ሐ. የጨጓራ መጥበብ
መ. የቁስሉ ወደ ሌላ አካባቢ መዝለቅ
ሠ. ካንሰር
እንዴት ይታከማል?
በጨጓራ ባክቴሪያው አማካኝነት ያጋጠመን ቁስለት ካለ ባክቴሪያዎቹን የሚገድል ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት ወይም ከዛም በላይ የሚቆይ የመድኃኒት ሕክምና ሊሰጠን ይችላል፤ ቁስለቱ እንዲድንም ሌሎች መድኃኒቶች አብረው ይታዘዙልናል።
በዚህም መሰረት የተለያዩ መድኃኒቶችን በመቀላቀል ሊታዘዝልን ይችላል። ይኸውም፡- አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ባክቴሪያዎቹን ለመግደል ከተጠቀሱት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ ይታዘዝልናል።
በጨጓራ ውስጥ አሲድ የሚረጩትን ጥቃቅን ቧንቧዎች በመዝጋት አሲድ የሚቀንሱ መድኃኒቶች አብረው ይታዘዛሉ። ጨጓራችን ብዙ አሲድ እንዲያመነጭ የሚያደርገውን ሂስታሚን የተባለውን ውሁድ መመረት የሚቀንሱ መድኃኒቶች ጨምረው ሊያዙልን ይችላሉ።
በዚህ ሕክምና በቀን እስከ 14 የሚደርሱ መድኃኒቶችን ለሳምንታት እንድንውጥ ሊታዘዝልን ይችላል፤ 14 ኪኒኖችን በቀን መዋጥ ብዙ ይመስላል፤ ነገር ግን ይህንን ሕክምና ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ለምሳሌ የታዘዘልንን የአንቲባዮቲክ መድኃኒት በስርዓቱ በታዘዘው መንገድ ካልወሰድን፣ ባክቴሪያው ሳይጠፋም ቀርቶ መድኃኒቱን ልናለማምደው እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ቀጣይ የባክቴሪያ ልክፍቶች ሲያጋጥሙን ለማከም አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የመድኃኒት ሕክምናውን ካደረግን በኋላ ባክቴሪያው ለመጥፋቱ ድጋሚ የሰገራና የትንፋሽ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
የጨጓራ ባክቴሪያን ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ ሌሎች ጀርሞችን ለመከላከል ከምንወስደው የጥንቃቄ እርምጃ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይኸውም እጅን በሳሙና ከምግብ በፊትና ከመፀዳጃ ቤት መልስ በደንብ መታጠብ፣ በፅዱ ሁኔታ ያልተዘጋጀ ወይም የቀረበ ምግብና መጠጥ አለመጠቀም፣ ያልበሰሉ ምግቦችን አለመጠቀም ናቸው።
እንዲሁም ጭንቀትና ውጥረት፣ ቅመም የበዛባቸው ምግቦችና ሲጋራ ማጨስ ለጨጓራ ቁስለት የማይዳርጉን ቢሆንም ሁኔታውን ግን ሊያባብሱ ስለሚችሉ ቢያንስ ከቁስለት እስከምንድን ድረስ መጠቀም ወይም ማድረግ የለብንም።
ምንጭ – ከሐኪም ቤት.ኮም
አዲስ ዘመን ታሕሣሥ 22/2013