ፋንታነሽ ክንዴ
አባት ልጁን በጠዋት ከእንቅልፉ ይቀሰቅስና ራቅ ወዳለ ቦታ ይልከዋል።መልዕክቱን አድርሶ ሲመለስ ጓደኞቹ ሜዳ ላይ ጨዋታውን አድርተውት ሲመለከት ያለምንም ማቅማማት ይቀላቀላቸዋል።በጨዋታ መሀል አቀበቱን ሲወጣ ቁልቁለቱን ሲወርድ ድካም ይሰማውና ወደቤቱ ጉዞ ይጀምራል፡፡
ከቤታቸው አቅራቢያ ሰብል ሲሰበስብ የነበረው አባት የልጁን መዛል ተመልክቶ ያበረታው ዘንድ ባቄላ እሸት ቆርጦ ይሰጠዋል።የወፎችን ጫጫታ ተከትሎ ከቤት የወጣው ልጅ ረሃብ ጸንቶበት ኖሮ ባቄላውን ተቀብሎ በፍጥነት ከነሽፋኑ መመገብ ይጀምራል።ረሃቡ ፋታ ሲሰጠው ረጋ ብሎ ሽፋኑን እየፈለፈለ ይበላል።በሂደት የጥጋብ ስሜት ሲሰማው ደግሞ የባቄላውን ፍሬ እየጠረጠረ መብላት ጀመረ። ሁነቱን በአንክሮ ሲከታተል የነበረው አባት ለልጁ አንድ መልዕክት ያስተላልፋል። እንደመጀመሪያውም እንደመጨረሻውም አትብላ እንደመሀከለኛው ብላ እንጂ የሚል፡፡
ይህን አፈ-ታሪክ እንዳነሳ ያስገደደኝ ህዝቡ ለኮቪድ 19 እየሰጠ ያለው ምላሽ ነው።መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ‹‹አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ ጃፓናዊ ኮሮና ቫይረስ ተገኝቶበታል።ጥንቃቄ እናድርግ›› የሚል መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረው ነበር።ከተሾሙ ከቀናት በኋላ በቀጥታ ስርጭት ወደ ሚዲያ ብቅ ያሉት የዶክተር ሊያ ታደሰ መግለጫም የምክትል ከንቲባውን መልዕክት አጠናከረ።
እነዚህ ዜናዎች ብዙዎቻችንን ጭንቀት ውስጥ የከተቱና ምን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ እስኪቸግረን ድረስ ግራ ያገቡን ነበሩ። አውቶብስ ውስጥ በተከፈተ ሬዲዮ ዜናውን የሰሙ ተሳፋሪዎች በድንጋጤ አውቶብሱን አስቁመው ስለመውረዳቸው በቦታው ላይ ከነበሩ ሰዎች ሰምተናል።በከተማዋ ውስጥ ያሉ መድሃኒት ቤቶች ሳኒታይዘርና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በሚፈልጉ ሰዎች ሲጨናነቁም ሰዓታት አልፈጀባቸውም።
ይህን ተከትሎ በነበሩት ጊዜያት ብዙዎች ርቀታቸውን ለመጠበቅና ለእጅ ንጽህና የሰጡት ትኩረት ከፍ ያለ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ሰርግ፣ ክርስትናና ሌሎች የሰዎችን መሰባሰብ የሚጠይቁ ዝግጅቶች ተሰርዘዋል፤ አልያም በጣት በሚቆጠሩ ሰዎች ለዛውም በከፍተኛ ጥንቃቄ ተከናውነዋል።ይህ ብቻ
አይደለም፤ በዓይን የሚያውቁትን ሰው ለቅሶ ካልደረስኩ እንዴት ዓይኑን አየዋለሁ የሚል ማህበረሰብ ባለበት አገር ላይ የቅርብ ቤተሰብ በሞት የተለያቸው ሳይቀሩ ቀብር እና ለቅሶ ለመድረስ እስከማመንታትም ደርሷል፡፡
ጥንቃቄው በግለሰቦችና ቤተሰቦች ብቻ የተወሰነ አልነበረም።በመንግስትና የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር እንጂ።ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለወራት በሮቻቸውን ከርችመው ማንም ድርሽ እንዳይል አድርገዋል።መንግስትም ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ከመዝጋት እስከ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የደረሰ ጠንካራ የመከላከል እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡
በወቅቱ መንግስት በወሰዳቸው ጠንከር ያሉ የመከላከል እርምጃዎች እና ህብረተሰቡ ባደረገው ከፍተኛ ጥንቃቄ ኮቪድ 19 የተፈራውን ያህል ጉዳት እንዳያደርስ ማድረጉን የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።ሰሞኑን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዞት በወጣ ዘገባ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተናገሩትም የባለሙያዎችን ሀሳብ የሚያረጋግጥ ነው።‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ትልቅ ሥራ ባይሰራ ኖሮ አሁን ላይ የሚኖረው ሁኔታ ከዚህ የከፋ ይሆን ነበር፡፡›› ብለዋል።
እዚህ ላይ ግን ብዙዎች በቴክኖሎጂ የተራቀቁትን ቻይናን፣ አሜሪካንና አውሮፓን በዚህ ደረጃ ያሸበረውና የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈው ኮሮና ቫይረስ አፍሪካን ብሎም ኢትዮጵያን ምን ያደርጋቸው ይሆን? በየቀኑስ ስንት ይቀብሩ ይሆን? ብለው መጨረሻችንን ለማየት ጓጉተው የነበሩ ወዳጅ ጠላቶቻችንን አፍ ያዘጋልንን የፈጣሪን ቸርነት አለማንሳትና ምስጋናም አለማቅረብ ንፉግነት ይመስለኛል። እናም ሰዎች እንደተመኙልን ሳይሆን አንተ እንዳሰብክልን ሆኖ እስካሁን ስለጠበከን እናመሰግንሃለን ማለት ወድጃለሁ።
ነገርን ነገር እያነሳው የትናንቱን ሁነት አጋራኋችሁ እንጂ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ እንኳን ያለፈውን ለማስታወስ ሳይሆን የዛሬ እንቅስቃሴያችንን ለመፈተሽ ነው፡፡
ዛሬ ግን ነገሮች የተቀየሩ ይመስላሉ።ኮቪድ ዛሬም ስጋትነቱ እንደጨመረ እየተነገረ ባለበት ሁኔታ ሰዎች ደስታንም ሆነ ሀዘንን ለመጋራት በርከት ብለው ይሰበሰባሉ። መሰብሰባቸው ባልከፋ ያለ በቂ አለፍ ሲልም ያለምንም ጥንቃቄ መሆኑ እንጂ።በሃይማኖት ተቋማት፣ በገበያ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት ላይና በሌሎችም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ኮቪድን ከግምት ያስገባ አይደለም።
ብዙ ሰዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግን ችላ ብለዋል።ርቀታቸውን ለመጠበቅና ለንጽህና የተሰጠው ትኩረትም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለይ በትራንስፖርት ላይ ለምን ጭንብል አታረጉም በሚል ጥያቄ በሚያነሱ ሰዎች የሚሰጠው ምላሽ ግልምጫ ከፍ ሲልም ስድብ የታከለበት እየሆነ ይገኛል።ይህ ደግሞ የሁላችንንም ቤት ሊያንኳኳ የሚችል አደጋ እንዲያንዣብብ አድርጓል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ እንዳስታወቀው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ 19 ስርጭት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በየዕለቱ ከሚደረጉ ምርመራዎች ውስጥ ከአስር በመቶ በላይ የሚሆኑት ቫይረሱ እየተገኘባቸው ነው። ከዚህ ውስጥ በርከት ያሉት ጽኑ ህክምና የሚፈልጉ ሆነዋል።ይህንም ተከትሎ ሆስፒታሎች ሁሉንም ጽኑ ህክምና ፈላጊዎች ተቀብለው ለማስተናገድ እየተቸገሩ ይገኛሉ። ብዙዎች ህይወታቸውን እያጡም ናቸው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በቅርቡ እንደገለጹት፤ አንዳንዴ ሰው ፖዘቲቭ ሆኖ አልጋ ይዞ መታከም ሲኖርበት አልጋ የሚያጣበትና የመተንፈሻ መሳሪያዎች የሚያዙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በየመንደሩና በየሰፈሩ ሰው ሃላፊነት ተሰምቶት ጥንቃቄ የሚያደርግ ከሆነ በመከላከሉ ላይ በአገር ደረጃ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
በተለይ የፊት ጭንብል ማድረግ ቀላል እና በሽታውን ለመከላከል ግን ትልቅ ውጤት ያለው ስለሆነ መተግበር ይገባል።የእጅ ንጽህናና የፊት ጭንብል ከ90 በመቶ በላይ በሽታውን እንደሚከላከል በሳይንሱ የተረጋገጠ ስለሆነ ሁላችንም ሃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡
ስለሆነም በመግቢያው ላይ በአፈ-ታሪኩ እንደተገለጸው ልጅ መጀመሪያ ላይ መኪና አስቁሞ እስከመውረድ የደረሰው ፍርሃታችን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዳናደርግ የሚያደርገን ሊሆን ስለሚችል አስፈላጊ አይደለም። አሁን እያሳየነው ያለው መዘናጋትም ራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና አገራችንን ከፍ ላለ ጉዳት ሊዳርግ ስለሚችል መታረም ይኖርበታል።
ሁላችንም የየራሳችንን ሃላፊነት ከተወጣን ከራሳችን አልፎ ሌሎችም በጤና እንዲኖሩ ማድረግ እንችላለንና በጤና ባለሙያዎች የሚመከሩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2013