ክለቦች ለእግር ኳስ እድገት ዋልታና ማገር እንደሆኑ ይታመናል። በሊግ ውስጥ የሚሳተፉት ክለቦች መጠናከር ለእግር ኳሱ እድገት ብቻም ሳይሆን ጥራት ያለው ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች በማፍራት ረገድ ሰፊ ሚና አለው። በተጨማሪም ከፍተኛ ገቢ በመሰብሰብ ለማህበረሰቡ ተደራሽ በመሆን አማራጭ የመዝናኛ እድል መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸው በዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በተጠቀሱት ማንጸሪያዎች የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ጥንካሬና ውጤታማነት ከተመለከትናቸው እድለኛ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። የሊጉ ጥንካሬ ከክለቦች ጥንካሬ የሚቀዳ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መልክ አልባ መሆን ከክለቦች አቅምና ጥንካሬ ማጣት የመነጨ እንደሆነ ስፖርቱን በሚገባ የተረዱት ሙያተኞች የሚሰጡት አስተያየት ነው። በዚህ ደረጃ የሚገኘው ፕሪሚየር ሊጉ አሁን ባለው ድካሙ፣በቁልቁለት ጉዞው ላይ እንዲሄድ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ችግሮች የአሰልጣኞች ፍልሰት ተጠቃሽ ይሆናል።
የክለቦች የውጤታማነት ፣ፍሬያማነት መሰረት የሆኑት አሰልጣኞች ከክለብ ክለብ የሚያደርጉት መዘዋወር ፤ስምምነት አልባ የክለቦችና የአሰልጣኞች ውዝግብ የፕሪሚየር ሊጉ የውድቀትም የቅዥትም ምክንያት ተደርጎ ቢወሰድ አላዋቂ አያስብለም። የክለቦችና አሰልጣኞችን የተረጋጋ የሥራ ግንኙነት መጥፋት በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ በሞቀ ሁኔታ እንደቀጠለ መሆኑ ከሰሞኑ የተሰሙ የስንበት ዜናዎችን መጥቀስ በቂ ማስረጃ ይሆናል።
በአሰልጣኝ ስነብት የሚናጠው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጉዳይን ከደደቢቱ ስንብት ብንጀምር ክለቡ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ቡድኑን በአሰልጣኝነት ሲመሩ የቆዩት ኤልያስ ኢብራሂም እና ጌቱ ተሾመን አሰናበተ። በውድድር ዓመቱ የውጤት ቀውስ ውስጥ የገባው ክለቡ ሁለቱን አሰልጣኞቹን ከማሰናበቱ አስቀድሞ በውጤት ማጣት ምክንያት ሁለቱም አሰልጣኞቹን አሰናብቶ ነበር። ደደቢት በተሰናበቱት አሰልጣኞች ምትክም በጊዜያዊነት የመቐለ 70 እንደርታ እና አማራ ውሃ ሥራ አሰልጣኝ የነበረው፤ በዚህ ዓመት ደግሞ በደደቢት የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ ሲሰራ የቆየው ይድነቃቸው ዓለሙን በዋና አሰልጣኝ ቦታ ላይ ተክቷል። ይህ የአሰልጣኞች ስንብት ጉዳይ በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ የአሰልጣኞች ተረጋግቶ አለመቀመጥ በሰፊው አንዳለ እንደ አንድ ማሳያ ይጠቀሳል።
የፕሪሚየር ሊጉን ሌላኛውን ገመና የሚያሳየውን ነጥብ ከደደቢት ብዙም ሳንርቅ አዲግራት ወልዋሎ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ ላይ ያሳርፈናል። ባለፈው ዓመት በሁለተኛው ዙር ወልዋሎን በመያዝ ከቡድኑ ጋር የአንድ ዓመት ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ዛሬ ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመመያየት የይልቀቁኝ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል። ከወልዋሎ ቤት የተሰማው የአሰልጣኝ የመልቀቂያ ደብዳቤ እዚህ ጋር ደግሞ ሌላ ትኩሳት መኖሩን አመላካች አድርጎታል።
በእርግጥም በ2010 የውድድር ዓመት የካቲት ወር ላይ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን በመረከብ በሊጉ እንዲቆይ ያስቻሉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ዘንድሮም ከክለቡ ጋር አብረው ቀጥለዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ቡድኑ መጥፎ አጀማመር ካደረገ በኋላም በተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፎ ወደ ውጤት መንገድ በመመለስ ደረጃውን ቢያሻሽልም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ዳግም ወደ ሽንፈት ተመልሷል። ከዚህ በተጨማሪም አሰልጣኙ ከሜዳ ውጪ ያሉት በርካታ ያልተፈቱ ጉዳዮች በቡድኑ ውጤት፣ ተነሳሽነት እና አጠቃላይ የቡድን መንፈስ ላይ ከባድ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን በመግለፅ ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
የክለቡ ምላሹ እስካሁን ያልታወቀ ቢሆንም ይህ ጉዳይ የአሰልጣኞችን በአንድ ክለብ ተረጋግቶ ያለመቆየት ችግርን እንደማሳያ መጥቀስ ያስችላል። ከወልዋሎ ወደ ደቡብ ፖሊስ ስንሸጋገር አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ደቡብ ፖሊስ መለያየታቸው እውን መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ እየተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የተጠናቀቀው የውድድር ዓመትን በቻምፒዮንነት በማስጨረስ ለመጨረሻ ጊዜ ከስምንት ዓመታት በፊት ወደተሳተፈበት ውድድር የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ የቀድሞው አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራውን ዳግም በዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በሊጉ እስካሁን ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ደደቢትን ከረታበት ውጪ 10 ሽንፈት የገጠመው ሲሆን፤ ሁለት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቦ በ10 የግብ ዕዳ እና 5 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የክለቡ የውጤት ቀውስ ውስጥ መግባትም አሰልጣኙን ለማሰናበት ምክንያት እንደሆነው ለመገመት አይከብድም። በአሰልጣኝ ስንብት የሚናጠው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጠቀሱት ክለቦች እንደማሳያ ይነሱ እንጂ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ብቻ አንጋፋውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ በርካታ ክለቦች የአሰልጣኝ ስንበትና ቅጥር ዜና ተሰምቶባቸዋል። ይህ ጉዳይም የፕሪሚየር ሊጉ መኮሰስ መውደቅ መቆርቆዝ እንደ ትልቅ ምክንያት ተወስዶ መፍትሄ ቢበጅለት መልካም ይሆናል ባይ ነን።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ዳንኤል ዘነበ