ከገብረክርስቶስ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ሙት ወቃሽ ለመሆን አይደለም – ነገር ግን ያለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ በአምሳለ-የትህነግ ቡድን የተቀረጸ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም።
ቀድሞ ነገር ከምን ዓይነት ጭቆና እንደሆነ ባይታወቅም የትግራይን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ በሚል እኩይ ዓላማ ሕዝብን በማደናገር ሺዎችን በእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያልቁ አስደርጓል።ሚሊዮኖችን እስከዛሬም ባልተላቀቁት የችጋር ቀንበር ደቁሷል።
ነጻ አወጣዋለሁ ያለውን ሕዝብ በውሸትና በማታለል የራሱንና በዙሪያው የተሰለፉትን ዘራፊዎች ኪስ ሲያደልብና ሆዳቸውን ሲያጠረቃ ኖሯል። አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብቶ የዘረኝነት መርዝ እየበጠበጠ ለኢትዮጵያ ግቷል።
በፍጻሜው ታዲያ ይኸው አሁን ከሞተም በኋላ እንኳ በትህነግ የተጋቱት የዘረኝነት መርዝ እንደ አብሾ አናታቸው ላይ ወጥቶ መግደል፣ ማፈናቀልና መጨፍጨፍ የዕለት ሥራቸው ያደረጉ ኃይሎች ዛሬም በየስርቻው እየተመለከትን ነው።
አሁን ተረኛው የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ነው። እርግጥ ነው በዚህ ክልል የትህነግ ቡድን የቆሰቆሰው ረመጥ ዜጎችን ማቃጠል ከጀመረ ሰነባብቷል። የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው ጉዳቱ እጅግ ተባብሶ ወደ አስከፊ ደረጃ መሸጋገሩ እንጂ።
በዚህ ጽሁፍ ታዲያ በክልሉ እንዲህ ለጎመራው የዘር ፖለቲካ እኩይ ፍሬ የእርሻውን፣ የዘሩን፣ የአበባውን እና የገበሬዎቹን ነገር ለመቃኘት እንሞክራለን።
ወዲያውም የፌደራል መንግስቱ የትህነግን ቡድን ታሪክ እንዳደረገ ሁሉ በነካ እጁ ያን አካባቢም እንዲታደገው የሚያስችሉትን የሕግ ማዕቀፎች እንዳስሳለን።
ቤኒሻንጉል/ጉሙዝ – የእጅ አዙር አሃዳውያን መፈንጫ
በትህነግ መራሹ የዘር ፌደራሊዝም የበይ ተመልካች ሆነው ከማዕከላዊው መንግስት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ከተገለሉት አካባቢዎች ውስጥ የቤኒሻንጉል ክልል አንዱ ነው።
ልክ እንደሌሎቹ አጋር ተብለው በዳር ከሰነባበቱት ክልሎች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ቤኒሻንጉልን ሲዘውሩ የኖሩት የትህነግ ቅጥረኞች ነበሩ።
በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቴክኒክ አማካሪ እየተባሉ በመሾም አሶሳን በመዳፋቸው እንዳለች የጤፍ ቅንጣት እንዳሻቸው ሲያገላብጧት ኖረዋል።
ሪቫን ሲቆርጡ፣ ስብሰባ ሲከፍቱና መግለጫ ሲሰጡ በቴሌቭዥን መስኮት የምናያቸው የአገሬው ሰዎች ቢሆኑም ቅሉ ነፍስና እስትንፋስ ሆነው ሲዘውሯቸው የነበሩት ስውር ፊቶች ግን ትህነጎች ነበሩ።
ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ያልነበረው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚባል ተቋም በማቋቋም የትህነጉ መሰሪ አባይ ጸሀዬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠገብ ተቀምጦ በሪሞት ኮንትሮል ቤኒሻንጉልን እንዳሻው ፈንጭቶበታል።
የትህነግ ባለስልጣናት በዚህ መልኩ ያን ክልል የግል ርስታቸው ሲያደርጉ የትህነግ ባለሃብቶች ደግሞ መሬቱን ወርረው የባንክ ብድር ለመውሰድ መያዣ አድርገውታል።ምድሩ ያፈራውን ወርቅ፣ ማሩን፣ እጣንና ቀርከሃውን ደግሞ የኮንትሮባንዳቸው ምንጭ አድርገው ክልሉን ዘርፈዋል።
የትህነግ ባለሥልጣኖችና ባለሃብቶቹ ያንን ክልል ሲዘውሩ ታዲያ የተጠቀሙበት ቁልፍ መሳሪያ ዘረኝነትን መዝራት ነበር። በክልሉ ከሁሉ ቀድመው የነበሩትን አምስት ብሔረሰቦችን የክልሉ ብቸኛ እና ሉዓላዊ ባለቤቶች አድርገው በሕገ-መንግስታቸው ሳይቀር በደማቁ እንዲሰፍር አደረጉ።
ዘረኝነት በምቹ የጥላቻ እርሻ ላይ ዘርተው ቡቃያው በመላ ክልሉ እንዲያቆጠቁጥ አደረጉ። ነባር የተባሉት የክልሉ ብቸኛ ባለቤቶች በቁጥር ጥቂቶች ሲሆኑ በሌላ በኩል ቤኒሻንጉልም የኢትዮጵያ አገራቸው አካል ነውና ከረዥም ዓመታት አስቀድሞ በስፍራው የሚኖሩ የአማራ፣ የኦሮሞና የአገው ሕዝቦችን ግን በጠላትነት እና በወራሪነት እንዲፈርጇቸው ተደርጓል።
ይህ እኩይ ዘር በፍጻሜው ለፍሬ በቅቶ በርካቶችን ለሞትና ለመፈናቀል ዳርጓል። በተለይም ከ2010 ለውጥ በኋላ በክልሉ ሁሉም አካባባዎች ዘርን መሰረት ያደረጉ አሰቃቂ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። የዛሬን አያድርገውና የትህነግ ቡድን መሪዎች በዚህ እልቂት የድል ጽዋቸውን ከፍ አድርገው ውስኪ ሲራጩ ኖረዋል።
በክልሉ ከተፈጸሙት ግፎች የመተከሉ ወደር የሌለው ሆኗል። ያም ሆኖ “የዛሬውን ሲያወጉ የትላንቱን ይዘነጉ” ሆኖብን ነው እንጂ በካማሽና በአሶሳ አካባቢ የተፈጸሙት ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች ሊዘነጉ አይገባም።
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለተፈጸሙት የዘር ጥቃቶች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ሰዎች ላይ መንግስት በተለያዩ መዛግብት የወንጀል ክስ በመክፈት ሕግ ለማስከበር ጥረት አድርጓል። ይሁንና ከክስ መዛግብቱ ለመረዳት እንደሚቻለው ከተከሳሾች ውስጥ አብዛኞቹ በቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ ይገኛል።
በችሎት ነገራቸው በሌሉበት እየተሰማ ያሉት ተከሳሾች ደግሞ አብዛኞቹ በክልሉ የዘረኝነትና የእጅ አዙር አሃዳዊነት ተልዕኮን ሲያስፈጽሙ የኖሩ የትህነግ የመጋረጃ ጀርባ ተዋንያንና ዘራፊ ባለሃብቶች ናቸው።
እነዚህም ከለውጡ በኋላ መቀሌ ከትመው ለመጨረሻው የወያኔ ሴራ ሲሰናዱ የኖሩና የማይነካውን ነካክተው ከትህነግ ጋር ታሪክ ሆነዋል፤ እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳይታወቅም ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ሌሎቹ ተከሳሾች ደግሞ በተለያየ የመንግስት ኃላፊነት ላይ የነበሩና ዜጎችን በብሔራቸው እያስለዩ ጨፍጭፈውና አስጨፍጭፈው በመሰወር ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ የአገሬው ባለቤት ነን ባዮች ናቸው።
የወንጀል ምርመራ ሳይደረግባቸውና ሳይከሰሱ እስካሁንም ድረስ በመንግስት ቢሮ ተቀምጠው የዘረኝነት ንግዳቸውን እያጧጧፉ ያሉትን ባለሥልጣናት ደግሞ ብልጽግና ይቁጠራቸው።
የሆነው ሆኖ አሁን በመተከል እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ የሚያረጋግጠው ክልሉ የዘረኝነትን መርዛማ ፍሬ በልተው ወደለየለት እብደት የተሸጋገሩ ጽንፈኞች መፈንጫ መሆኑን ነው።
ይህ ሁኔታም ብዙም ሳይቆይ ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ሊቆጣጠረው ከሚችለው ውጭ ወደመሆን እንዳይሸጋገር ያሰጋል።
እናም እስካሁን የሆነውን መመለስ ባይቻልም ቅሉ ወደፊት በአካባቢው የተዘራውን እኩይ የዘረኝነት ፍሬ ለማርከስ ፍቱን መድሃኒት ሊበጅለት ይገባል።በውጤቱም በሌሎቹም የአገሪቱ አካባቢዎች የተዘራውን የጽንፈኝነት መርዝ ከስሩ ለመንቀል ተምሳሌታዊ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል።
የዚህ መሰረቱ ደግሞ የማዕከላዊው መንግስት በትግራይ ክልል እንዳደረገው ሥር ነቀል ሕጋዊ ዘመቻ ማድረግ ነው።
ሥር–ነቀል ዓላማን ያነገበ ጣልቃ ገብነት የግድ ነው
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት መሰረት የፌደራል መንግስቱ ሕገ-መንግስቱን የመጠበቅና የመከላከል ሥልጣንና ኃላፊነት አለው።በተለይም በየትኛውም ክልል ከክልሉ ዓቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ ጥያቄ መሰረት የፌደራል መንግስቱ የመከላከያ ኃይል እንደሚያሰማራ ተደንግጓል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በማንኛውም የኢትዮጵያ ጥግ ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማስቆም ሳይችል ሲቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ አነሳሽነትና ያለክልሉ ፈቃድ ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያደርግም በሕገ-መንግስቱ ሰፍሯል።
ይህ ብቻም ሳይሆን ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነም የፌደሬሽን ምክር ቤት ፌደራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
እነዚህን ለፌደራል መንግስቱ የተሰጡትን በመላ አገሪቱ ሕግን የማስከበር እና የዜጎችን ደህንነትና የአገርን ሕልውና የማስጠበቅ ኃላፊነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ታዲያ በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ በ1995 ዓ.ም. ወጥቷል።
በዚሁ ዓዋጅ መነሻም ኢትዮጵያን ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ሰቅዞ ይዟት ከኖረው ሾተላይ የማላቀቅ ጣልቃ ገብነት በትግራይ ክልል ተካሂዷል። በውጤቱም ትህነግን ከትግራይ ሕዝብ ትከሻ ላይ ማላቀቅ ተችሏል። አሁን ደግሞ በዚሁ የሕግ ማዕቀፍ መሰረት የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ተረኛ ታካሚ መሆን አለበት።በዚያ ክልል ከአካባቢው አስተዳደር አቅም በላይ የሆነ ከፍተኛ የሰላምና ደህንነት አደጋ ተፈጥሯል።
ከሁሉም በላይ በሕገ-መንግስቱ ከተደነገጉት የሰዎች መብቶችና ነጻነቶች ያልተጨፈለቁትንና ያልተጣሱትን መጥቀሱ ይቀላል።ዜጎች ዘራቸው እየተለየ ተጨፍጭፈዋል፤ ተሰደዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ በሰላም እንዳይኖሩ በሥጋት ቆፈን ተከበዋል።
በአዋጁ መሰረት ደግሞ እንዲህ ያለ ከክልሉ ዓቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መንግስት ጠያቂነት የፌደራል መንግስቱ የመከላከያ ሰራዊት ያሰማራል። እርግጥ ነው በቤኒሻንጉል በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩትን ችግሮች ተከትሎ ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቶች እየተቋቋሙ ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል።
ይሁንና የጥፋቶቹ ዋነኛ ጠንሳሽና አስፈጻሚዎች ላይ ላዩን የማልያ ለውጥ አድርገው ለብልጽግና የተሰለፉ የመንግስት ሹማምንት በመሆናቸውና የአካባቢው በደንና በረዣዥም ሳሮች የተሞላ መሆን ወታደራዊ ሥኬቶችን ማምጣት እንዳልተቻለ ተደጋግሞ ይገለጻል።
የሆነው ሆኖ አሁን በመተከል እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ከዚህ ቀደም ተግባራዊ የተደረጉት ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቶች የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በቂ አለመሆናቸውን ያረጋግጣል።
በመሆኑም ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጉዳዩን በአስቸኳይ በጥልቀት በማየት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱን በስፋትና በተጠናከረ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ለአፈጻጸሙም የክልሉ አስተዳደር ቁልፍ የፈቃደኝነት ሚና እንዲወጣ ማድረግ ይኖርበታል።
በሌላኛው የጣልቃ-ገብነት አማራጭም በተመሳሳይ በክልሉ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች በጣም አሰቃቂ በሆነ መልኩ እየተጨፈለቁ በመሆናቸውና የክልሉ አስተዳደርም ይህንን መቆጣጠር ባለመቻሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ አነሳሽነትና ያለክልሉ ፈቃድ ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አለበት።
እርግጥ ነው ምክር ቤቱ ርምጃ ለመውሰድ የጀመራቸው ሕጋዊ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው እየተደመጠ ነው። በዚሁ አግባብም ምክር ቤቱ ርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲወሰዱ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ አለበት።
በዚሁ መሰረት በቅድሚያ በክልሉ የሚኖሩ የማንኛውም ብሔር ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቤኒሻንጉልም አገራቸው በመሆኑ በሰላምና በደህንነት የመኖር መብታቸውን ማረጋገጥ የግድ ነው።
“የክልሉ ባለቤት ብሔር ብሔረሰቦች– በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሺናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ”
ክልሉ ወደሰላምና መረጋጋት በሚመጣበት ወቅትም ትህነግ የተከላቸውን የዘረኝነት አሜኬላዎች አንድ በአንድ ነቅሎ ማቃጠል ያስፈልጋል።ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው የክልሉን ሕገ-መንግስት ማሻሻል ነው።
“በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም የክልሉ ባለቤት ብሔር ብሔረሰቦች በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሺናሻ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው” ይላል በ1995 ዓ.ም. የወጣው የክልሉ ሕገ-መንግስት።
የቤኒሻንጉል ክልል ሕገ-መንግስት የትህነግ የዘረኝነት ሕጋዊ ልባስ ቋሚ መዘክር ነው። በሕገ-መንግስቱ መሰረት አምስቱ ብሔረሰቦች የክልሉ ባለቤቶች ናቸው።ሌሎቹ ግን ኢትዮጵያዊነታቸው ተደምስሶ ሁለተኛ ዜጎች መሆናቸው በሕግ ተደንግጓል።
እንዲህ ያለ አሳፋሪ ሕገ-መንግስት ያለበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ባለቤቶች ከተባሉት ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ ቢጨፈጨፉና ቢፈናቀሉ ምን ይደንቃል?!
ዘረኝነትን እና ከፋፋይነትን በሕገ-መንግስት ደረጃ እንዲህ በይፋ ደንግገን ካስቀመጥን እና በሕዝቡም ዘንድ “ነባርና መጤ፤ ባለቤትና ባይተዋር” የሚል እኩይ አስተሳሰብ ካሰረጽን በኋላ ዜጎች በዘራቸው ምክንያት እየተለዩ ቢጨፈጨፉ ለምን ይደንቀናል!?
ኢትዮጵያውያንን ባይተዋር የሚያደርጉ እንዲህ ያሉ የዘር ፖለቲካ ነጸብራቅ የሆኑ ሕግጋተ-መንግስት በቤኒሻንጉል ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ክልሎች አሉ።
በአንድ በኩል እንዲህ ዓይነት ከፋፋይና ዘረኛ ክልላዊ ሕገ-መንግስት፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት የሚል ስላቅ በፌደራል ህግ-መንግስት ውስጥ ያስቀመጠ ሥርዓተ-መንግስት በምድር ላይ የኢትዮጵያው ብቻ ነው።
እናም በቤኒሻንጉል ክልል በሚደረገው ጣልቃ ገብነት ሕገ-መንግስቱን በማሻሻል ጭምር ለሌሎቹም ዘረኛ ክልላዊ ሕገ-መንግስታት ሞዴል የሚሆን እውነተኛ የለውጥ መንገድ መከፈት ይኖርበታል።
ይህንን አሳፋሪ ገጽ ማጥፋት ካልተቻለ ሌላው ሁሉ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ “አሻግራችኋለሁ” የሚለው የብልጽግና አመራር በቅጡ ሊገነዘበው ያስፈልጋል።
ሌላው የጣልቃ-ገብነቱ መሰረታዊ አቅጣጫ ከክልል አስተዳደር ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ የገዥውን የብልጽግና ፓርቲ አመራር በጥልቀት በመገምገም የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ነው።
ሶስተኛውና መሰረታዊው ደግሞ ከዚህ ቀደም በክልሉ በተፈጸሙት ዘግናኝ ወንጀሎችና በአሁኑ የመተከል ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበትን ሁሉ ለሕግ ማቅረብ የግድ ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2013