ያቃተን ወደሚበልጠው መመልከት ነው

ከምንምነት ለመውጣት ሀገር ያስፈልገናል። የነበሩንን ለማስቀጠል፣ ለሚኖሩን ዋጋ ለመስጠት የትቅቅፍና የትስስብ ፖለቲካ ያስፈልጋል። የኃይል ርምጃ የሚያሳጣው ሀገር ነው ። በዓለም ላይ ታሪክ እንዳይረሳቸው ሆነው የተመዘገቡ መጥፎ ታሪኮች በእልህ፣ በቁጣ፣ በጥላቻ፣ በዘረኝነት የተከሰቱ ናቸው። አንድ ነገር ከመከሰቱ በፊት መጠንቀቅ እንጂ ከተከሰተ በኋላ ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡

‹ቤት በጥበብ ይሰራል በማስተዋልም ይጸናል› የሚል ቅዱስ ቃል በቅዱስ መጽሀፍ ላይ አውቃለው። በእውነትም ቤት ለመስራት፣ ጎጆ ለመቀለስና ትዳር ለማቆም የበረታ እውነትነት አለው። በዚህ ሀሳብ ውስጥ ቤት የሚለውን ቃል እንደሀገር፣ እንደሕዝብ፣ እንትውልድ ልንተረጉመው እንችላለን። ኢትዮጵያን እንደቤት ብንወስዳት ጥበብና ማስተዋል የታከለበት አብሮነታችን፣ ትስስራችን፣ ወግ ባህላችን፣ ታሪክ እሴቶቻችን ደግሞ የሕልውናችን ማሰሪያ ሆነው የሚነሱ ናቸው፡፡

በሰላም ለሰላም እና በጦርነት ለሰላም የተለያዩ እሳቤዎች ናቸው። በነዚህ ሁለት የተለያዩ ምርጫዎች ዓለም ጥንድ ጎራዎችን ፈጥራለች። እንደእኛ ሀገር የፖለቲካና የኃይል ልምምድ ብንነሳ ሁለተኛው እሳቤ ላይ እናርፋለን። ሰላምን በኃይል ለመውለድ የምናደርገው የእልህ ትንቅንቅ ስልሳ ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም አልበረደም። እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄ አካሄዳችን ትርፋችንን ከማጉደልና ኋላ ቀርነታችንን ከማጉላት ባለፈ የሰጠን የክብር ስም የለም፡፡

በስልሳ ዓመታት የፖለቲካ ትርክት ውስጥ እንደሀገር ብዙ ጎሎብናል። ዛሬ ላይ ለእርስ በርስ ጥላቻ መንገድ የከፈቱ የዘረኝነትና መሰል አክሳሪ የጥፋት ምንጮች በዛ ማህጸን የተጸነሱ ስለመሆናቸው መስካሪው ብዙ ነው። ስልሳ ዓመታትን በጦርነትና በመሰል የፖለቲካ ትንቅንቅ መቧደን ለድሀ ሀገርና ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ያን ከመሰለው የእርስበርስ ትንቅንቅ ወጥተን ስለሀገር መመካከሩ የበለጠ ዋጋ እንዳለው በመረዳት የሚከብድ አይደለም፡፡

በጦርነት አቅሏን ላጣችው ሀገራችን ሰላም እና የሰላም ጉባኤ ምን ማለት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ላሳለፍንውና ለምናሳልፈው ብዙሀን መሻት እጅግ ዋጋ ካላቸው ቁምነገሮች መሀል የመጀመሪያው የሰላምን ዋጋ የተረዳ ፖለቲከኛ መፍጠር ነው። ፖለቲካው በሰላማዊ ሀሳብ ከዳበረ በኃይል የሚፈታ ግለሰባዊና ማኅበረሰባዊ ችግር አይኖርም። እንደሀገር የሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች በሕገመንግስቱ እንዲፈቱ አስገዳጅ ስርዐት ይሰጣል።

በብዙ ነገር ላይ ፈር ስተናል። ፖለቲካው ፈር ስቷል፣ ፖለቲከኛው ፈር ስቷል። የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ጦርነት ሆኖ በተለያየ ዘመን ላይ አስተውለናል። ደፋቸውም በመከራና ስቃይ፣ ሞትና ጉስቁልና ሆኖ ተመልክተናል። የዚህ ሁሉ ሰለባ ደግሞ ሕዝብ ነው። የሕዝብ እዬዬ ከፖለቲከኞች አሸሸ ገዳሜ እንደሚወጣ የታወቀ ነው። የሀገር ዋይ ዋይ እንደዚሁ ፈር በሳቱ ሀሳብ የለሽ ስሜታዊነት በኩል የሚታዩ የድርጊት ውጤቶች ናቸው።

ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ፖለቲካ መፍጠር ከሰነበቱብን የጦርነት እና መሰል ልምምዶች ለመራቅ እንደ መፍትሄ የሚወሰድ ቀዳሚ አማራጭ ነው። በብዙ ችግር ውስጥ ተዘፍቀን የምንገኘው ቅደም ተከተሉን ባልጠበቀ አካሄድ ነው። በጦርነትና በመሰል የእርስ በርስ ፍትጊያ ስልሳ ዓመታት የዘላለምን ያክል ነው። በተለይ ደግሞ እንደእኛ ላሉ ራሳቸውን በምግብ ላልቻሉ፣ በውጪ ሀገራት ርዳታ ለሚኖሩ ትርጉሙ ከዚህም በላይ ነው፡፡

ቅደም ተከተላችን ከሰላም ወደሰላም ነው። ከጦርነት ወደሰላም የነበረውን ፖለቲካዊ መርህ ሽረን ከሰላም ወደሰላም ሽግግር ያስፈልገናል። ሀገር ሰላምን እና ሕዝባዊነትን ባስቀደመ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቅደም ተከተል ውስጥ ካልሆነች በጦርነትና በመሰል የጥላቻ ትርክቶች ዋጋ ለመክፈል ቅርብ ናት። የውሀውን ምንጭ አድርቆ ውሀ ፍለጋ የሚሄድና የውሀውን ምንጭ ጠብቆ በውሀ የሚረካን ሁለት ግለሰቦች እንዴት ትገልጽዋቸዋላችሁ? ምንጩን ያደረቀው የመጀመሪያው ግለሰብ በተፋለሰ ቅደም ተከተል ውስጥ ነው ይሄ ያሳለፍነውን ስድስት አስርት ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ ሲያመላክት ምንጩን ጠብቆ በውሀ የረካው ግለሰብ ደግሞ በተዋበ ቅደም ተከተል ውስጥ ያለ የምንመኘውን ነገ የሚወክል ነው፡፡

የሰላም ምንጮች ያስፈልጉናል። ምንጮቻችን ባህሎቻችን እና እሴቶቻችን ናቸው። ምንጮቻችን የመከባበርና የመቻቻል ጥንተ ወጎቻችን ናቸው። ምንጮቻችን በጋራ ተቀድተው በጋራ የሚፈሱ የትስስር ልማዶቻችን ናቸው። እነዚህን አፍርሰን የምንገነባው ሀገር የለም። እነዚህን ንደን የምንማግረው ትውልድ የለም። እንደሀገር ለመፍጠር እንደግለሰብ መበርታት አለብን። እንደማኅበረሰብ ለመበርታት እንደፖለቲካ መዘመን አለብን። እንዲህ ያለው አካሄድ ነው በጸና ቅደም ተከተል ውስጥ አኑሮ የሰላም ጀምበር የሚፈነጥቅልን፡፡

ዝማኔ የሀሳብ ሙላት ነው። በሀሳቡ ያልዘመነ ጭንቅላት በምንም ቢበረታ ዋጋ አያወጣም። በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ልቀው በመታየት ፊተኛ የሆኑት ሀሳባውያን ናቸው። ሀሳባውያን ጦርነትን ከነመንስኤው ቆፍረው የቀበሩ ናቸው። ማንም ሰው በየትኛውም ልዩነቱ ላይ በመነጋገር መግባባት ይችላል ባይግባባ እንኳን በልዩነት ውስጥ ወደሚበልጠው ማስተዋል ይችላል በሚል ምልከታቸው ይታወቃሉ። ወደሚበልጠው ካስተዋልን በትናንሽ ነገሮች ጦር መሳበቃችን ይቀራል፡፡

ሀገር፣ ሕዝብ፣ ትውልድ ለየትኛውም ፖለቲከኛ ፊተኛ ጉዳዮቹ ናቸው። ታሪክ፣ ባሕል፣ እሴት በየትኛውም የፖለቲካ ሜዳ ላይ የአንድነት ቀለሞች ናቸው። እነዚህን መመልከት ሲያቅተን በሞራልና በሀሳብ ዝለን እንደጦርነት ላሉ ትናንሽ ነገሮች እንረታለን። በትናንሽ ነገር መረታት ደግሞ ዋጋ ያለውን ውድ እውነት በማሳጣት ዋጋ ለሌለው ርካሽ ሀሰት ይዳርጋል። በእውነቱ ያቃተን ወደሚበልጠው መመልከት ነው። የሚበልጠው ደግሞ በሚበልጥ ሀሳብ የሚደረስ እንጂ በኃይል የሚደርስ አይደለም።

ሀሳብ ሀገር የምትድንበት፣ ትውልድ የሚሽርበት የመፍትሄና የበጎ እይታ መገኛ ነው። በዓለም ላይ ጦርነትን ከሚሽሩ አዋጪ የሰላም መንገዶች መሀል ዋነኛው የመነጋገር ባህል ነው። የመነጋገር ባህል ደግሞ ከታች ጀምሮ ወደላይኛው የስልጣን ከፍታ እያደገ የሚመጣ ከሁሉ ለሁሉ የሆነ ነጻ አውጪ የድል ፍኖት ሊባል ይችላል። ይሄን የድል መንገድ ብዙ ሀገራትን ከመከራ የታደገ ለእኛም የጦርነት ትንቅንቅ መፍትሄ የሚሰጥ ነው፡፡

ድል ያለው ሰላም ውስጥ ነው። ሌላው የድል መንገድ ሁሉ አክሳሪ እና አውዳሚ ነው። በተለይ ሰላምን በጦርነት ለማምጣት መሞከር የተሳሳቱ ከሚባሉ የሰላም አካሄዶች ሁሉ የባሰው እና የከፋው ነው። በዚህ እውነታ በኩል ብንመለከታቸው የስልሳ ዓመት የጦርነት ታሪኮቻችን ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈሉንና እንዳሳጡን ለመረዳት አይከብድም። የነጻነት መዳረሻቸውን በሰላም በኩል ያደረጉ ከሌላው በተሻለ አሸናፊዎች ናቸው። እኚህ ልምምዶች እኛም ሀገር ተለምደው የጦርነት የአቅጣጫዎቻችንን ቢቀይሩልን መልካም ነው፡፡

ስለሰላም የሚያወጋ የምክክር መድረክ ለእርቅና ለአንድነታችን ወሳኝ ነው። ሀገራዊ ምክክርን የመሰሉ ስለሰላም በሰላም የቆሙ፣ አስታራቂና አግባቢ የአንድ ዓላማ ጉባኤዎች ወሳኝነታቸው እሙን ነው። አንድ ዓላማን ያነገቡ የወንድማማቾች የሰላም ሕብረት እንደሚያሰፈልገን ሀቅ አለው። እነዚህ ሰላም ተኮር የእርቅና የተግባቦት ልምምዶች እንደመጣንበት ስልሳ ዘመን የጦርነት ታሪክ ሁሉ ስለሰላም ልማድ በመሆን ነጋችንን የሚወስኑልን ናቸው፡፡

ለአንድ ዓላማ በአንድነት መቆምን የመሰለ የሉአላዊነት ተገን የለም። በጦርነት የወየቡ የታሪክ እና የክብር መልኮቻችን ወደቀድሞ ይዞታቸው ተመልሰው በኢትዮጵያዊነት የሚሞሸሩት ስለሰላም ስናብር ነው። በጦርነት ምን እንዳጣንና ምን እየጎደለብን እንዳለ ማወቅ አለብን። በዚህ ስልጡን ዘመን ላይ በሀሳብ ማሸነፍ ካልቻልን ሌላ የማሸነፊያ አማራጭ አይኖረንም ቢኖረን እንኳን እንደጦርነት ከብዙ ዋጋ መክፈል በኋላ ባለ መጨባበጥ በኩል ነው፡፡

የአንድ ነገር ዋጋው ምን ያክል እንደሆነ ለማወቅ በግለሰብ ሳይሆን በሕዝብና ሀገር መሰላት አለበት። ጦርነት ከፋች የሆኑ ምክንያቶቻችን በግለሰብ የተሰሉ ሀገርና ሕዝብን ያላካተቱ ናቸው። ሀገርና ሕዝብ ያልተሰላበት የትኛውም ነገር ዋጋ አስከፋይ ነው። ከአንድና ሁለት ወገን ወጥተን ወደሰፊውና ወደብዙሀኑ እንመልከት። ሀገር እያሳጣ፣ ትውልድ እያቀነጨረ ባለነገር ውስጥ ዋጋ የለም።

“ከድጡ ወደማጡ “ የሚለው አባባል ከባሰ ወደባሰን ለመግለጽ የተሰጠ አባባል ነው። መጥፎ ታሪኮቻችን ካላስተማሩን፣ ከትላንት ጠፋቶቻችን ካላሰላሰልን ከባሰ ወደባሰ ጉዞ ላይ እንደሆንን አመላካች ነው። ጦርነት ተደጋግሞ አይደለም ለአንድ ጊዜ ቢሆን እንኳን ዋጋ አስከፋይ ነው። የእኛ የጦርነት ታሪክ ደግሞ የረጅም ጊዜ ታሪክ ነው። ከድጥ መውጣት አልቻልንም። ነጋ ጠባ ወደባሰ ንትርክ እያቀናን ነው፡፡

ሰላምን በኃይል የማምጣት የቆየ ልምምዳችን ተቀይሮ ኢትዮጵያን እንደ አዲስ መፍጠር አለብን። ያለን ትንሽ ነገር ነው እሱኑ ለጦርነትና ለእርስ በርስ ግፊያ ሰጥተን እጣ ፈንታችን ምን ሊሆን ነው? አይደለም ለድሀ ሀገርና ሕዝብ ቀርቶ ላላቸውም ቢሆን ጦርነትና ሰላም አብረው የሚቆሙ አይደሉም። በሰላም ለሰላም አብሮ መቆምን፣ ኢትዮጵያ መባልን፣ በወንድማማች መጠራትን ልንለማመድ ግድ ይለናል።

ፖለቲካ ወለድ የሆኑ ቅየቶች ቢያጨቀዩትም ሰላም የሁሉም ፍጥረቶች የመኖር ዋስትና ሆኖ በተፈጥሮ የተሰጠ ስጦታ ነው። አንዳንድ ነገሮች ከእጅ እንዳይወጡ አጥብቆ መያዝ እንጂ ከወጡ በኋላ ለመመለስ ብዙ ዋጋ ነው የሚጠይቁት። ሀገር ተረት ተረት የላትም። በተረት ሁሉም ተረት ማብቂያ አለው። ሁሉም አፈታሪክ ተረት ተረት ብሎ ጀምሮ አፌን በዳቦ አብሱ ብሎ የሚያበቃ ነው፡፡

የእኛ የጦርነት መከራ የት ጋ..መቼ ይሆን ማብቂያው? ለሁልጊዜ ጦርነት ይቻላል? ለሁልጊዜ ገሎ መሞት ይሆናል? ከማጥ የሚያወጡ፣ ከድጥ የሚታደጉ የሰላም መንፈሶች ለዚህ ትውልድ እና ለዚህ ፖለቲካ ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው። ሀገር የሚሰጡ፣ ትውልድ የሚያቆዩ የትርክት ውርሶች ያስፈልጉናል።

ነውር ወለድ የትርክት እዳችን እንደበጎ ውርስ ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ የመጣንበትን አዘንግቶ የምንሄድበትን እንዳያሳጣን ቆም ብለን ልናስብ ይገባል። ትውልድ ሀገር ይፈልጋል፣ ራዕይ ሀገር ይፈልጋል፣ ታሪክ፣ እሴት፣ ባሕል ወግ በሀገር በኩል የተዋቡ ናቸው። ክብር ሀገር ይፈልጋል፣ ማንነትና ሉአላዊነት በሀገር የነቁ ናቸው። ሀገር የሌለው ለእኚህ ሁሉ ባዕድ ነው። እነዚህ ሁሉ የሌሉት ደግሞ ምንም ነው። አበቃሁ፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You