ስለ ስም ሲነሳ ደረጀ ኃይሌና አዜብ ወርቁ የደራው ጨዋታ በተሰኘ የሬዲዮ ዝግጅታቸው ሲያቀርቡ የሰማኋቸውን አስገራሚ ስሞች አስታውሳለሁ፡፡ በጎጃም መስመር «ተመስገን አምላኬ ቸር ነውና ነዋይ ሰጠኝ» የምትባል የምግብና መኝታ አገልግሎት የምትሰጥ አንድ ድክም ያለች አነስተኛ ሆቴል ነበረች፡፡ በዘመነ ደርግ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል «እብሪተኛው የዚያድ ባሬ መንግሥት ስንዝር ታህል መሬት ከኢትዮጵያ አያገኝም» የሚባል ሻይ ቤት ተከፍቶ በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ባህር ዳር በተለምዶ በግ ተራ እየተባለ በሚጠራው ብሉ ናይል ሆቴል አጠገብ ያለ አንድ ድርጅት ስም ርዝመት ደግሞ ግር የሚያሰኝ ነው፡፡ «የነአየነ አዳሙ 17 ዓመታት በፍትህ አደባባይ የ26 ዓመት ትንሳኤ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር» ይባላል፡፡
ማሟሟቅ ስለሚያስፈልግ አንድ እጨምራለሁ፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ግሎባል ፖስትን ጠቅሶ ስለ ስም ማውጣት አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ ዘገባው በየአገሩ በልጆቹ ስም ላይ ለመራቀቅ ወይም ለመቀናጣት የሚሞክር ወላጅ እንደማይጠፋ በመግለጽ ይጀምራል፡፡ ለጥቆም በኒውዚላንድ ኗሪ የሆኑ ወላጆች ሊነበብ የማይችል ስምን ለልጃቸው መጠሪያነት እንዳስመዘገቡ ይገልጻል፡፡ታዲያ እንደ ገመድ የረዘመ ስም አላስመዘገቡም፡፡ እጥር ምጥን ያለ እንዲሆን በአንድ ነጥብ ጨረሱት እንጂ፡፡ በቃ አንዲት የነጥብ ምልክት ብቻ ነች የምትታየው፡፡ በድምጽ ምን ተብሎ እንደሚጠራ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ቆይቶ ግን በብዙ ውትወታና ልመና ወላጆቹ ለልጃቸው ሌላ ስም ለማውጣት ተስማምተዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለማስቀረት በጃፓን ሀገር «የልጆች ስም በቀላሉ በጽሑፍ የሚገለጽና የሚነበብ መሆን አለበት» የሚል ህግ አለ፡፡ በጀርመን ሀገር የወንዶችን ስም ለሴት ወይም ደግሞ የሴቶችን ስም ለወንድ መጠቀም አይቻልም፡፡ በተጨማሪም የወንድ ይሁኑ የሴት ተለይተው የማይታወቁ ስሞችን ማውጣት ክልክል ነው፡፡ እዚህ እኛ ሀገር ግን አብነት፣ ብስራት፣ አስራት፣ የትናየት፣ ብርሃን ፣ ፍጹምና ነጻነትን የመሳሰሉ ስሞችን ወንዶችና ሴቶች በጋራ ይጠሩባቸዋል፡፡
እንዲህ ባሉ ስሞች የሚጠሩ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በስማቸው ምክንያት ብዙ ገጠመኞች እንደሚኖሯቸው አልጠራጠርም፡፡ እስኪ የኔን ገጠመኝ ላካፍላችሁ፡፡ ትምህርታችንን አጠናቀን በተመረቅን ማግስት ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አበባ ውስጥ በመምህርነት ሊቀጥረን ጠራን፡፡ ቅጥሩ በሚካሄደበት ወቅት የአዲስ አበባ ዳርቻዎች እንዳሁኑ መሃል አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ሴቶች እንዳይንገላቱ በሚል የከተማዋ እምብረት በሆኑት አራዳ፣ ልደታና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ተመደቡ፡፡ መሃል ከተማ መመደብ ከየትኛውም የከተማው ክፍል በአንድ ትራንስፖርት መምጣት ስለሚያስችል ተመራጭ ነበር፡፡ ወንዶች ደግሞ ዳር ላይ ወዳሉት ክፍለ ከተሞች ተላኩ፡፡ እኔ ግን በስሜ ምክንያት ሴት ነህ ተብዬ ከሴቶች ጋር ልደታ ክፍለ ከተማ ከተምኩ፡፡
የሚፈቀዱና የማይፈቀዱ የስም አይነቶችን ለዜጎቻቸው በዝርዝር ያሳወቁ ሌሎች ሀገራትም አሉ፡፡ በማሌዢያ ልጆችን በእንስሳት፣ በነፍሳት፣ በዕጽዋትና በቀለም አይነቶች መሰየም የሚከለክል ህግ አለ፡፡ እንደ እኛ ሀገር ትርንጎ፣ ሀረግ፣ ወይራውና አንበሴ እያሉ መሰየም አይቻልም፡፡ በሳዑዲ አረቢያም 50 ስሞች ተዘርዝረው ክልከላ ተጥሎባቸዋል፡፡ በዛ ያሉት የተወገዙት የውጭ ሀገር ስሞች በመሆናቸው ነው፡፡ በውጭ ሀገር ስሞች በመጠራት ዘመናዊ ተደርጎ መቆጠር እዚያ ቅዠት ነው፡፡ ‹‹ማሊካ›› በሚል ስም መጠራት ደግሞ የተከለከለው ትርጉሙ ንግሥት ወይም እቴጌ ማለት ስለሆነ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ ክብር መጋፋት ተደርጎ በመቆጠሩ ነው፡፡
በብዙ የአውሮፓ ሀገራት ‹‹ሂትለር›› በሚል ስም መጠራት ክልክል ነው፡፡ ይህ ህግ መኖሩን ጠንቅቀው የሚያውቁ እንግሊዝ ሀገር ውስጥ ኗሪ የሆኑ አዳም የተባለ የ22 ዓመት ወጣትና ክላውዲያ የተባለች የ38 ዓመት ሚስቱ ለአዶልፍ ሂትለር ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ ህጉን ተላልፈው የልጃቸውን ስም ‹‹ሂትለር›› ብለው ሰየሙ፡፡ በዚህ ምግባራቸውም ከወር በፊት በርሚንግሐም ፍርድ ቤት ቀርበው አባትና እናት እያንዳንዳቸው በ6 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ምነው እኛም ሀገር ከሚሰጡት አገልግሎት ጋር ፍጹም የማይገናኝ ስም ለራሳቸው የሚያወጡ ተቋማትን ቆንጠጥ የሚያደርግ ህግ ቢወጣ፡፡ ራሳቸውን የሚያንቆለጳጵሱ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ልብ ብላቹኋል? አንዱ ሬዲዮ ጣቢያ ሥራ በጀመረ ማግስት ነው ራሱን «ተወዳጁ ጣቢያ» እያለ መጥራት የጀመረው፡፡ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብበትና የሚዛናዊነት ጥያቄ የሚነሳበት ሌላ የሬዲዮ ጣቢያ ደግሞ ራሱን «ተመራጭ ተደማጭ» እያለ ያሞካሻል፡፡ በርካታ ዜናዎቹን ምንጭ እየጠቀሰ የሚያቀርብ የቴሌቪዥን ጣቢያ «ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ» እንደሆነ ደጋግሞ ይነግረናል፡፡ ምነው ‹‹የናንተው ሬዲዮ›› እያለ አድማጮቹን ባለቤት ከሚያደርገው የሬዲዮ ጣቢያ ትምህርት ቢወስዱ ፡፡
ሰዎች ስማቸውን ለምን የሚቀይሩ ይመስላችኋል? በቅርብ ጊዜ የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ሰዎች ስማቸውን የሚቀይሩት ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን ስም ሲጠሉት ፣ አካባቢ ሲቀይሩ፣ ሀይማኖት ሲቀይሩ፣ ራሳቸውን መደበቅ ሲፈልጉ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከነአካቴው ማቋረጥ ሲፈልጉና የጾታ ለውጥ ሲያደርጉ ነው፡፡
ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገራት ግን ሥርዓት ሲቀየርም ሰዎች ስማቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ፡፡ እንዴት ካላችሁ አባባሌን ግልጽ የምታደርግ ቆየት ያለች ቀልድ እነሆ፡፡ በደርግ ዘመን ከነበሩ ካድሬዎች አንዱ በለጠ ነው፡፡ በለጠ ሹመት አገኛለሁ ብሎ ሦስት ልጆቹን ደርጉ በለጠ ፣ ትግላችን በለጠ እና አብዮት በለጠ ብሎ ይጠራል፡፡ በኋላ የተመኘውን ሹመት ሳያገኝ መንግሥት ይለወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ስጋት ገብቶት ሦስት ልጆቹን እየመራ ስማቸውን ለማስቀየር ወደ ቀበሌ ሲጓዝ አንድ ወዳጁ ያገኘዋል፡፡ ወዳጁም ጥድፊያውን ተመልክቶ «ወዴት ነው የምትጣደፈው ጓድ በለጠ ?» ይለዋል፡፡ በለጠም «እበላ ብዬ ልጆቼን ላስበላ ነው» ሲል ይመልሳል፡፡ ጉዳዩን አሳምሮ የሚያውቀው ወዳጁም «የሦስት ልጆችህን ስም ከምትቀይር በለጠ የሚለውን ስምህን ቀለጠ ብለህ አስቀይር›› አለው፡፡ ቀልዱ ኤክስፓየርድ የሚያደርጉ ስሞችን ከመስጠት እንድንቆጠብ ይመክራል፡፡ ማንም ቢሆን በዛገ ስም መጠራት አይፈልግም፡፡ ባለንበት ዘመንም ልጆቻቸውን ህዳሴ እያሉ በወቅቱ «ጣፋጭ ቃል» የሰየሙ ወላጆች አሉ፡፡
በ2010 ዓ.ም ሀገራችን ስምን መቀየር የሚያስችል አዲስ ምክንያት ለዓለም አስተዋውቃለች፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ለመኮረጅ ሲሉ ከጎበዝ ተማሪዎች ስም ጋር በሚመሳሰል ስም ስማቸውን በፍርድ ቤት እንደሚቀይሩ አረጋግጧል፡፡ ትምህርት ቢሮው መላ ቢጠፋው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የፈተናው ምዝገባ እስኪጠናቀቅ ስም መቀየር እንዲታገድ የሚጠይቅ ደብዳቤ እስከመጻፍ ደርሷል። ታዲያ በዚህ ብቻ አላበቃም፣ ከደብዳቤው ጋር በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተሰበሰቡና ከጎበዝ ተማሪዎች ስም ጋር የተመሳከሩ የ1 ሺ 550 ተማሪዎችን ስም ዝርዝር የያዘ 37 ገፅ አባሪ ልኳል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ተመልክቶ በክልሉ ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች የ 8ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ እስኪጠናቀቅ በጊዜያዊነት የስም ለውጥን የሚከለክል እግድ ጽፏል።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የመዝገብ ስማቸውን ሳይቀይሩ ከአንዳች ነገር መከለል ሲፈልጉ ምሽግ የሚሆን ሌላ ስም ያበጃሉ፡፡ ለምሳሌ ጋዜጠኞችና ደራሲያን ማንነታቸው እንዳይታወቅ ሲፈልጉ በብዕር ስም ይጽፋሉ፡፡ በ1970ዎቹ አጋማሽ ዝነኛ የሆኑ የብዕር ስሞች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የብዕር ስሞች ከሁለት ቃላት የተመሰረቱ ሆነው “ዘ” በሚል አያያዥ የተጣመሩ ናቸው፡፡ ፊደሉ በግዕዝ ትርጓሜው ቦታ ሳይዝ አይቀርም፡፡ እነዚህ የብዕር ስሞች ቤት የሚመቱና ሳቅ የሚያጭሩ አይነት ናቸው፡፡ ዳንዴው ሰርቤሎ ከስድስት ኪሎ፣ ዘለሌ ዘ ግንፍሌ፣ ዶጮ አንበሴ ከግንፍሌ፣ ጠንክር ዘ ካዛንችስ፣ ፍላስ ዘ ዮሐንስ፣ ቡልቡላ ዘ መርካቶ፣ አሸናፊ ዘ ደቡቡ ከአዲስ አበባ እና ዳግላስ ጴጥሮስ በዘመኑ ታዋቂ ከነበሩት የብዕር ስሞች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎችም የመዝገብ ስማቸውን ትተው የትግል ስም ይወጣላቸዋል፡፡ የትግል ስም እንደ ብዕር ስም ከመደበኛ ስም ጎን ለጎን ሥራ ላይ አይውልም፡፡ በትግል ወቅትም ሆነ ከትግል በኋላ ሙሉ በሙሉ ነባር ስምን የሚተካ ነው፡፡ የትግል ስምን ያስተዋወቁት ኮሚኒስቶች ናቸው ይባላል፡፡ ሆቺ ሚን፣ ሌኒንና ጆሴፍ ስታሊ የተሰኙት ስሞች የትግል ስሞች ናቸው፡፡ እኛም ሀገር በነጻ አውጪነት ሲታገሉ የነበሩ ታጋዮች ቤተሰቦቻቸው ያወጡላቸው ስም በትግል ስማቸው ተቀይሮ እስካሁን ድረስ እየተጠሩበት ይገኛሉ፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹን ብንመለከት ለገሰ ዜናዊ ወደ መለስ ዜናዊ፣ አታክልቲ ጸሐዬ ወደ አባይ ፀሐዬ፣ ወልደ ስላሴ ነጋ ወደ ስብሐት ነጋ፣ ዮሐንስ እቁባይ ወደ አርከበ እቁባይ፣ ዮሐንስ ለታ ወደ ሌንጮ ለታ እንዲሁም ፍሬው ኢብሳ ወደ ዳውድ ኢብሳ ስማቸውን ቀይረዋል፡፡
ኦዴፓና አዴፓን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶችም ስማቸውን ቀይረዋል፡፡ ስም የሚቀይሩት ግለሰቦችና ድርጅቶች ብቻ አይደሉም፡፡ ሀገርም ስም ይቀይራል፡፡ ስዋዚላንድ የተባለችው አፍሪካዊት ሀገር 50ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ስታከብር የሀገሪቱ ንጉሥ መጠሪያ ስሟን ‹‹ኢሰዋቲኒ›› ወደሚለው ቀይረዋል። ቢቢሲ በወቅቱ እንዳስነበበው የስም ለውጡ አንዳንድ የሀገሪቱን ዜጎች አስቆጥቷል፡፡ ንጉሡ የሀገሪቱን ስም ከመቀየር ይልቅ የዜጎቿን ህይወት ለመቀየር ቢታትሩ ይሻላል ያሉም ነበሩ።
ሀገራቸው ከግሪክ ጋር በገባችው እሰጥ አገባ ምክንያት ሜቄዶኒያውያን የሀገራቸውን ስም ትንሽ ፈቀቅ አድርገው ወደ ሰሜን ሜቄዶኒያ ለመቀየር ህዝበ ውሳኔ አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱ የስም ለውጡን ያልደገፉ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ራሳቸውን ከህዝበ ውሳኔው በማግለል ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሜቄዶኒያ አጠቃላይ ህዝብ አንድ ሦስተኛው ብቻ በህዝበ ውሳኔው የተሳተፈ በመሆኑም የሀገሪቱ ስም ባለበት እንዲፀና ግድ ሆነ፡፡
እኛም ሀገር ዶክተር አብይ ወደሥልጣን ከመምጣታቸው ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ኢህአዴግና 16 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ለማድረግ አጀንዳዎች ሲመርጡ አንድ ግር የሚል ነገር ተሰምቷል፡፡ ስንት አንገብጋቢ ችግር ባለበት ሀገር የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ «ኢትዮጵያ የሚለው የሀገሪቱ ስያሜ ወደ ‘ኩሽ ምድር ‘ ይቀየር» የሚል መደራደሪያ አጀንዳ አቅርቦ አገር ጉድ ብሎ ነበር፡፡
ዶክተር በንቲ አጆሉ የተባሉ ሰው ደግሞ ከጀርመኖች ጋር በመተባበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ45 ጊዜያት በላይ ኢትዮጵያ በሚል የተጠቀሰውን ስያሜ ‹‹ኩሽ›› በሚል ቃል ተክተው የራሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አሳትመዋል፡፡ ‹‹ምነው ምን ነካዎት ?›› ሲባሉም ‹‹ግሪኮች መጽሐፍ ቅዱስን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ሲተረጉሙ ኩሽ የሚለውን ቃል ወደ ኢትዮጵያ ለወጡት እንጂ ዕብራይስጡ የሚለው ኩሽ ነው፡፡ ደግሞም ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ማለት ነው፡፡ ግሪኮች መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉሙት ጥቁሮችን ለማዋረድ ብለው ኩሽ የሚለውን ስም በኢትዮጵያ እንደቀየሩት ባደረኩት ጥናት ስለደረስኩበት ነው›› ብለዋል፡፡
እናንተዬ … እንደው ስም በመቀየር መጠመዳችን ግርም አይልም ? ወፍራም ምክንያት ካለ ግን ለምን ይገርማል? በተለይ ከስም ጋር የተቆራኘ ቆሻሻ ታሪክን ለማሽቀንጠር ስምን እንደመቀየር አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ መቼ እንደሚሆን እንጃ እንጂ እኔም ሙሉ ስሜን ሳልቀይር አልቀርም፡፡ ግብር ካልተቀየረ ስምን መቀየር ትርጉም የለውም አትሉኝም ፡፡ እዚህ ጋ የበዕውቀቱ ስዩም ግጥም ቢጠቀስ ሸጋ ነው፡፡
ማጭድ ይሆነን ዘንድ_ ምንሽር ቀለጠ ፣
ዳሩ ብረት እንጂ ልብ አልተለወጠ ፣
ለሣር ያልነው ስለት እልፍ አንገት ቆረጠ ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
የትናየት ፈሩ