ፍሬህይወት አወቀ
ስንዴ በብዛት ከሚመረትበት የሀገሪቱ ክፍሎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አንዱ ነው። በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችም በዋናነት የስንዴ ምርት በማምረት ይታወቃሉ። አርሶ አደሮቹ የሚያመርቱትን የስንዴ ምርት ለቤተሰቦቻቸው ቀለብ በማድረግ ይጠቀማሉ። ከራሳቸው የተረፋቸውን ደግሞ ወደ ገበያ በማውጣት ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ ሌሎች ፍላጎቶቻቸውን ያሟላሉ። በአካባቢው የሚገኙ የአርሶ አደር ልጆችም በግብርና ስራው ተሳትፏቸው የጎላ ለመሆኑ አስረጂ አያስፈልገውም።
አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ በግብርና የሚተዳደር እንደመሆኑ የብዙዎቻችን መነሻ ከአርሶ አደር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አቶ ተድላ ሀይለጊዮርጊስም በአርሲ አካባቢ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል ከአንዱ ቤተሰብ ተገኝተዋል። ትውልድና እድገታቸውም በዚሁ አካባቢ ሲሆን፤ እንደ እኩዮቻቸው ሁሉ ቤተሰባቸውን በግብርና ስራ እያገለገሉ በስንዴ እርሻ ውስጥ አድገዋል።
አብዛኛው አርሶ አደር ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሮ ከሚገፋበት አርሶ አደር የተገኙት አቶ ተድላ ብዙ ልፋትና ድካም የሚጠይቀውን የግብርና ስራ ኖረውበታል። ታዲያ ዛሬ ለደረሱበት ስኬት መብቃታቸው ከሚያደርጉት የበረታ ትጋት በተጨማሪ ከአርሶ አደር ቤተሰብ መገኘታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ይናገራሉ።
በአካባቢው ስንዴ በብዛት የሚመረት ቢሆንም ገብስን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችም ይመረታሉ። በክልሉ ያሉ አርሶ አደሮች በብዛት የሚያመርቱት ግን ስንዴ ነው። ስንዴ በሁሉም ማህበረሰብ ዕለት ዕለት ለምግብነት የሚውል መሆኑን የተረዱት አቶ ተድላም ስንዴን ከማምረት ወደ ንግዱ ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም።
ስንዴ ለዳቦ፣ ለፓስታ፣ ለማኮሮኒ፣ ለብስኩት የሚያገለግል ሁለገብ የምግብ ሰብል መሆኑንም በሚገባ ተረድተዋል። አዋጭነቱን እና ተፈላጊነቱ የገባቸው አቶ ተድላ በ2000 ዓ.ም ጭላሎ እርሻ የተባለው አነስተኛ ፋብሪካ አርሲ ዞን አሰላ ላይ አቋቁመው ስንዴን በጥሬው ከመሸጥ እሴት ጨምረው አንድ ደረጃ ከፍ ያለውን ዱቄት ለገበያ ማቅረብ ጀመሩ።
የስንዴ ዱቄት ገበያውም እየተስፋፋና ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ውጤታማ መሆን ቻሉ። በዚህም ፋብሪካው እሴት ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን የማምረት አቅሙን አጎልብቶ። በመሆኑም በ2003 ዓ.ም እዛው አርሲ አሰላ ላይ ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ የተባለ ትልቅ ፋብሪካ አቋቋሙ።
በአስራ አምስት ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካ ዛሬ ላይ የስንዴ ውጤት የሆኑ የተለያዩ የምግብ ምርቶችን እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ዕውቅናን ያተረፈ ትልቅ ፋብሪካ ሆኗል።
ከአርሶ አደር ቤተሰብ የወጡት አቶ ተድላ ኃይለጊዮርጊስ ትጋታቸው ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ላይ የጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ሆነው በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ተደራሽ መሆን የቻሉ የስንዴ ውጤቶችን በማምረት ላይ ተሰማርተዋል። እኛም እኚህን ታታሪ ሰው ለዛሬ የስኬት እንግዳ አድርገን አቅርበናቸዋል።
ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ከመቋቋሙ በፊት በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት ስንዴ እያመረቱ ለገበያ ያቀርቡ የነበሩት አቶ ተድላ፤ ቀስ በቀስ አነስተኛ የሆነ ዱቄት ፋብሪካ ብሎም ግዙፉን ፋብሪካ ማቋቋም ችለዋል። በመነሻ ካፒታላቸው ሁለት ሚሊዮን ብር የተጀመረው ኢንቨስትመንት ዛሬ ላይ ወደ 25 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፤ አጠቃላይ ካፒታላቸው ደግሞ አንድ ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
ስንዴ አምርተው አዳማና አዲስ አበባ እየወሰዱ ከመሸጥ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ አዋጭ ሆኖ ያገኙት አቶ ተድላ፤ ዱቄቱንም ወደ ተለያዩ ምርቶች በመቀየር ኦኬ ፓስታ፣ ኦኬ ማካሮኒና ኦኬ ብስኩት የተባሉ ምርቶችን እያመረቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለእነዚህ ምርቶች በግብዓትነት የሚውለው ዋናው ምርት የሆነውን ስንዴ ከአካባቢው አርሶ አደር በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ በመሆኑ የጥሬ እቃ እጥረት አይገጥማቸውም።
ፋብሪካው የሚገኘው አርሲ አሰላ ላይ በመሆኑ አርሶ አደሩ በቀላሉ ያመረተውን ስንዴ ለፋብሪካው ማስረከብ ቀላል ሆኖለታል። ይህም አርሶ አደሩ ያለ እንግልትና ውጣ ውረድ ምርቱን መሸጥ አስችሎታል። በተለይም ደላሎች በገዥና ሻጭ መካከል ሳይገቡ አርሶ አደሩ እራሱ ከ20 ኩንታል ጀምሮ ለፋብሪካው መሸጥ ይችላሉ። በአካባቢው ያሉ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ከፋብሪካው ጋር የረዥም ዓመት ግንኙነት ያላቸው በመሆኑም ገበያ ፍለጋ አይወጡም።
የስንዴ ምርቱ በሚደርስበትና መሸጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ስልክ በመደወል ምርቱን እንዲነሳላቸው ያደርጋሉ። ፋብሪካውም በራሱ ተሽከርካሪዎች አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ ገብቶ የስንዴ ምርቱን ያነሳል። ገንዘቡንም ለአርሶ አደሮቹ በባንክ አካውንታቸው ይላካል። ይህም አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት የሚወስድበትን ጊዜና ጉልበት እና ወጪ ቀንሶለታል።
ከአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ባለፈም ፋብሪካው እንዲህ ባለ የግብይት ስርዓት መጠቀሙና በአርሶ አደሩ አቅራቢያ መገኘቱ ተጠቃሚ አድርጎታል። ፋብሪካው ግብዓቱን በቅርበት ማግኘት በመቻሉም ምርቶቹን በስፋትና በጥራት ከፍጥነት ጋር ማምረት እንዲችል አድርጎታል። በመሆኑም ላለፉት 12 ዓመታት የግብዓት እጥረት ሳያጋጥመው ምርቶቹን በመላው የሀገሪቱ ክልሎች ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት የግብዓት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት በመከሰቱ ምክንያት በተወሰነ መጠን የምርት አቅርቦት እጥረት ገጥሟቸዋል። ይሁን እንጂ ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ለአርሶ አደሩ ቅርብ በመሆኑ በአንጻራዊነት በተሻለ አቅም እያመረተ ይገኛል።
ፋብሪካው ለሚያመርታቸው ምርቶች በዋናነት ስንዴን የሚጠቀም ቢሆንም የተለያዩ ኬሚካሎችንም ከውጭ ሀገር ገበያ ያስመጣል። ከኬሚካሎቹ በተጨማሪም ለምርቶቹ ማሸጊያነት የሚያገለግሉ ማሸጊያ ፓኬጆችንም ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባሉ። አስፈላጊው የሆነውን የውጭ ምንዛሪም ከመንግስት በሚደረግለት ድጋፍ ከንግድ ባንክ በቀዳሚነት ያገኛል፤ ግብዓቶቹንም ያሟላል።
በመሆኑም በአሁን ወቅት ፋብሪካው ከዓመታዊ ሽያጭ በአማካኝ (ከ26 መቶ) ሚሊዮን እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል። በፋብሪካው የሚገኙ የተለያዩ ማሽኖችም ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው ናቸው። በቅርቡ የተተከለው አዲስ ፓስታ የሚያመርት ማሽን በአማካኝ በቀን 900 ኩንታል ማምረት የሚችል ሲሆን፤ ማካሮኒ የሚያመርተው ማሽን ደግሞ በቀን 480 ኩንታል ማምረት ይችላል።
እንዲሁም በሰዓት አራት ነጥብ አምስት ቶን ማምረት የሚችሉ አራት የተለያዩ ብስኩት የሚያመርቱ ማሽኖች አሉ። በተጨማሪም በቀን እስከ 2ሺ400 ኩንታል ዱቄት ማምረት የሚችሉ ሁለት የዱቄት ማሽኖችም ይገኛሉ።
ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ አሁን እደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ቀላል የማይባሉ ውጣ ውረዶችን ማሳለፉን ያነሱት አቶ ተድላ፤ በተለይም ፋብሪካው የተገነባበትን ቦታ ከማግኘታቸው በፊት ከፍተኛ የሆነ የቦታ ችግር እንደነበረባቸው አንስተዋል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ኢንቨስትመንት የሚጠይቀውን ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ማለፍና ዓላማን ግብ ማድረስ የግድ መሆኑን ያምናሉ። በዚህም ችግር ሆኖባቸው የነበረውን የመነሻ ካፒታል ጨምሮ ከመንግስት አስፈላጊ የሆኑና በርካታ ድጋፎችን አግኝተዋል።
መንግስት ካደረገላቸው ድጋፎች መካከልም ከውጭ ሀገር የተለያዩ ማሽኖችን እና ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ የተመቻቸላቸው መሆኑ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ከዚህ ውጭም የክልሉ መንግስትና የአርሲ አሰላ ከተማ አስተዳደር ለስራቸው አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን በማድረግ ልዩ ልዩ እገዛዎች ተደርጎላቸዋል። ድጋፉም ጠንክረው እንዲሰሩና ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል።
ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ በአሁን ወቅት ለ1500 ቋሚ እና ለ500 ጊዚያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ፋብሪካው አሁን ከሚያመርታቸው ምርቶች በተጨማሪ በማስፋፊያ አዳዲስ ማሽኖችን በመትከል ኑድልስ ለማምረት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ይህ የማስፋፊያ ስራ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ሲገባ አንድ ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ይችላል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም መላው የፋብሪካው ሰራተኞች ደስተኞች እንደነበሩና እርሳቸውም ባዩት ነገር መደሰታቸውን አጫውተውናል። በጉብኝታቸው ወቅትም ያሉትን ችግሮች በማንሳት የተወያዩ ሲሆን፤ ፋብሪካው ማሟላት የሚገባውን ነገር እንዲያሟላና በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ በተሰጣቸው መሰረት እየሰሩ ይገኛሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከክልሉ መንግስት ሊደረግ ላቸው የሚገቡ ድጋፎችን አስመልክቶም በተለይም የቦታ ችግራቸው እንዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለክልሉ ፕሬዚዳንት በነገሯቸው መሰረት ችግሮቻቸው እየተፈቱላቸው ነው። አጠቃላይ በክልሉ መንግስት በኩል ቀድሞውንም የሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል ያልተቋረጠና አበረታች እንደነበርም አስረድተዋል።
ኢንዱስትሪ የሀገሪቱን ችግር መፍታት የሚችል ዋናው የስራ ዘርፍ እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ተድላ፤ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት በማድረግ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠርና የስንዴ ምርት የሆኑትንና ህብረተሰቡ ዕለት ከዕለት የሚጠቀምባቸውን ምግቦች ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
የጥረታቸው ዓላማም ለበርካታ ወገኖቻቸው የስራ ዕድል መፍጠርና የስንዴ ምርቶችን በስፋትና በጥራት ለዜጎች ማድረስ ነው። በቀጣይም ስራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋፋት ዕቅድ ያላቸው አቶ ተድላ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስራውን በተወሰኑ የክልል ከተሞች ለማስፋት አቅደዋል።
አቶ ተድላ፤ ፋብሪካቸውን ባቋቋሙበት አሰላ አካባቢ ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን በማበርከት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙ ግለሰብ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል፤ አርሲ ውስጥ ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ይማሩበት የነበረን እጅግ አስቸጋሪና ምቹ ያልሆነ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰርተው አስረክበዋል። ትምህርት ቤቱ በግምት ከ500 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ህጻናት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፤ በሚሊዮን የሚገመት ብር ወጪ በማድረግ ከ20 ዓመት በታች የሆኑ የአካባቢው ወጣቶችን በማሰባሰብ የእግር ኳስ ቡድን አደራጅተዋል፤ እነዚህ ወጣቶችም በከተማዋ ካሉ ከሁሉም ክለቦች ከቡና፣ ከጊዮርጊስና ከመከላከያ ጋር መጫወት የቻሉና ይህም ለወጣቶቹ የስራ ዕድል ሆኖ ቀጥሏል።
በአሰላ ከተማ ለሚገኙ አጠቃላይ ተማሪዎችም በጀት መድበው በየዓመቱ ሽልማት ይሰጣሉ። በዚህም በከተማዋ በሚገኙ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለሚወጡ ተማሪዎች እንደየክፍል ደረጃቸው የተለያዩ መጽሐፍቶችን በሽልማት ያበረክታሉ። በተጨማሪም በየዓመቱ ክረምት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማሟላት ያልቻሉ ተማሪዎችን በመለየት እስከ 500 ሺ ብር ወጪ በማድረግ ለተማሪዎቹ የትምህርት ቁሳቁሶችን ያሟላሉ።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገሪቱ መግባቱን ተከትሎም ህብረተሰቡ በወረርሽኙ ምክንያት የሚደርስበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ጫና መቋቋም የሚያስችል አገራዊ ድጋፍ አድርገዋል። በመሆኑም ለኦሮሚያ ክልል መንግስት የአንድ ሚሊዮን ብር ስጦታ በመስጠት አጋርነታቸውን አስመስክረዋል። በአሰላ ከተማ ለሚኖሩ አቅመ ደካሞችም እንዲሁ 570 ሺ ብር ወጪ በማድረግ የምግብ ሸቀጦችን አቅርበዋል።
ከገበታ ለሸገር ወደ ገበታ ለሀገር ከፍ ላለው ፕሮጀክት ከመንግስት በተደረገው ጥሪ መሰረት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል። በቅርቡም በሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት በማውገዝ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን በተለያየ መንገድ ገልጿል። በመሆኑም በአርሲ ዞን ከ600 በላይ ሰንጋዎችን በማሰባሰብ ለመከላከያ ሰራዊቱ በተደረገው ድጋፍ የአቶ ተድላ ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ ነበረው።
በቀጣይም ሀገሪቱ ለምታደርገው ማህበራዊና ኢኮኖሚው ጥሪ ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን የገለጹት አቶ ተድላ፤ አሁን ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ካለበት አስራ አምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በተጨማሪ 35 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በማስፋፊያ ተረክበዋል። በቦታውም የአዳዲስ ማሽኖች ተከላ እየተከናወነ ሲሆን በቅርቡ ወደ ስራ ገብቶ ኑድልስ ማምረት የሚጀምር ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013