አቶ ተማም ባቲ የተወለዱት ምስራቅ አርሲ ሱዲ ወረዳ ደረባ ከተማ ሲሆን እድገታቸው በአርባ ጉጉ ጀጁ ወረዳ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጀጁ ወረዳ ተምረዋል፡፡ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በአሰላ ኮምፕርሄንሲቭ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቀጥረው ለአስር አመታት አገልግለዋል፡፡ በኋላም በተለያዩ የአገር ውስጥ የእርዳታ ድርጅቶች የሰሩ ሲሆን ውጭ አገር በመሄድ በማስተርስ ኦፍ አርት ትምህርት ተመርቀው በማህበራዊ ስራዎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባትም ናቸው፡፡
አቶ ተማም ወደ ሀገራቸው የገቡት መንግስት ለፖለቲካ ድርጅቶች ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው ሲሆን ዘጠኝ ልኡካን ቡድኖች በመምራት ሰኔ 17 ቀን 2010 ነው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት፡፡ በአሁኑ ሰአት የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ የፖለቲካና የአደረጃጀት ኃላፊ ሁነው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች፤ በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚታየው የሰላም እጦት መደፍረስ፤ ድርጅቱ በአስመራ ስለነበረው ቆይታና በሌሎችም ሰፊ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፤ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ መቼ ተመሰረተ?
አቶ ተማም፡- የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ አዲስ ፓርቲ አይደለም፡፡ ፓርቲው በሦስት ድርጅቶች ውህደት የተመሰረተ ነው፡፡ አንደኛው በጀኔራል ዋቆ ጉቱ ይመራ የነበረው የኦሮሞ አንድነት ግንባር ይባል የነበረው ድርጅት ነው፡፡ በጣም የቆየ ድርጅት ነው፡፡ ሁለተኛው ድርጅት በጃራ አባገዳ ይመራ የነበረው ፍሮንት ፎር ዘ ኢንዲፔደንስ ኦፍ ኦሮሚያ የሚባል ድርጅት ነው፡፡ ሶስተኛው በብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ ይመራ የነበረው ፓርቲ ነው፡፡
ባለፈው ሕዳር ወር መስራች ጉባኤ በአዳማ በአባ ገዳ አዳራሽ አካሂደን የድርጅቱን ፕሮግራም መርምረን አዲስ አመራር ከሀገር ውስጥ አሳትፈን የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ የሚለውን ድርጅት የመሰረትነው እዚሁ ነው፡፡ የስም ለውጥ እንጂ ድርጅቱ ከጥንት ከነበሩት ድርጅቶች ጀምሮ አስቀድሞም የነበረ ነው፡፡ የዚህ ድርጅት አመጣጡ ከኦነግ ነው፡፡ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ ከአገር ወደ ውጪ ወጥተው ትግል ሲገቡ በቀጥታ ኦነግን ነው የተቀላቀሉት፡፡ አገር ቤት እያሉ ከመሄዳቸው በፊትም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በድብቅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአባልነት ባሻገር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ ይባላል፤ እውነት ነው?
አቶ ተማም፡- ለሁለት ዓመት ያህል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡ በቀጥታ ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ከኦነግ ጋር ነው የተቀላቀሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዳማ አባገዳ አዳራሽ ባደረጋችሁት ጉባኤ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር የሚለውን ስም ለምን መለወጥ አስፈለገ?
አቶ ተማም፡- የስም ለውጥ ያደረገውና የወሰነው መስራች ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ ከእንግዲህ ግንባር የሚል ነገር አያስፈልገንም፡፡ ፓርቲ ሆነን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ነው የመጣነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ስታካሂድ ግንባር የሚል አገላለጽ ጥሩ አይመጣም፡፡ ከግንባርነት ወደ ፓርቲነት ተለውጠን ሰላማዊ ትግል አካሂደን ለሕዝብ ምርጫ ለሕዝብ ውሳኔ እንቅረብ በሚል ነው የስም ለውጥ የተደረገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሕጋዊ መንገድ ተመዝግባችኋል?
አቶ ተማም፡- የምዝገባ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በሕጋዊነት እንድንንቀሳቀስ ወረቀት ተሰጥቶናል፡፡ ምዝገባው ተጠናቆ የምዝገባ ሰርተፊኬት አልወሰድንም፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ከኦነግ ጋር የተለያያችሁት በምን ምክንያት ነው?
አቶ ተማም፡- ብርጋዴር ጀነራል ከማል ጦር ይዘው ለአመታት ድንበር ሲጠብቁ የነበሩ ናቸው፡፡ በኋላ በስርአቱ ደስተኛ ስላልነበሩ ጦሩን መርተው ኤርትራ ገቡ፡፡ ከነሙሉ ትጥቁ አሰልፈው ነው ኤርትራ የገቡት፡፡ ኤርትራ ከገቡ በኋላ የኦነግ ጦር አዛዥ አደረጓቸው፡፡ ከዚያም የተጨመሩና የነበሩትን ወታደሮችና አብረዋቸው የሄዱትም መደበኛ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ስለነበሩ በጉሬላ ጦር የውጊያ ስልት (ሽምቅ ውጊያ) ከአንድ ብርጌድ በላይ ጦር አሰልጥነው ሲያበቁ ዘመቻ እንሂድ እኔ የመጣሁት ኤርትራ ውስጥ ልቀመጥ አይደለም ልዋጋ ነው የሚል ሀሳብ ለኦነግ አመራር ያነሳሉ፡፡ የወጣሁት ለሕዝቤ ልታገል ነው፤ ስለዚህ ልዝመት፤ አዝምቱኝ፤ ባሉበት ወቅት በወቅቱ የነበረው የኦነግ አመራር አልተቀበላቸውም፡፡ የጠቡ መነሻ ይሄ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የብርጋዴር ጀነራሉን ሀሳብ ኦነግ ለምን አልተቀበላቸውም?
አቶ ተማም፡- ዋናውን ጉዳይ የሚያውቀው በወቅቱ የነበረው የአቶ ዳውድ ኢብሣ አመራር ነው፡፡ ምን አልባት ጥርጣሬው እነ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ ይሄን ጦር ይዘው ለውጊያ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ አይታዘዙልንም የሚል ሥጋት የነበረ ይመስለኛል፡፡ የሚቀርበው ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ በትክክል ግን ጠቡ የተነሣው ከዚያ ነው፡፡ እንዋጋ፣ እንዝመት፣ በጀት መድቡልን ከሚል የተነሣ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነ አቶ ዳውድ ኢብሣ አስመራ ነበሩ?
አቶ ተማም፡- አዎ፡፡ እዚያው አስመራ ነበሩ፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር እርሳቸው ነበሩ፡፡ እንደውም የጦሩን በጀት መቁረጥ፣ ብርጋዴር ጀኔራል ከማልንም ከጦር አዛዥነት የማንሳት የዚህ አይነት ክስተቶች ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ በድርጅቱ ውስጥ የነበረው አለመግባባት ቀጠለና ሁለት ቦታ ተከፈለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አስመራ ነው ይሄ የሆነው?
አቶ ተማም፡- አዎ፡፡ ይሄ ሲሆን አስመራ የነበረው ጦርና በደቡብ የነበረው ጦር በሙሉ ከነጀነራል ከማል ጋር ነው የወጣው፡፡ ድርጅቱ ሲከፈል ከጀነራል ከማል ገልቹ ጎን ሆነ፡፡ በምስራቅም የነበረው እንዲሁ መቶ በመቶ ከብርጋዴር ጀነራል ከማል ጋር ቆመ፡፡ አስመራ የነበረው አመራር ግማሹ ከጀነራል ከማል ጋር ግማሹ ደግሞ ከአቶ ዳውድ ጋር ተከፍሎ ሁለት ኦነግ ሆነ፡፡ የለውጥ ፈላጊው አነግ የተባለውን ቡድን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ብርጋዴር ጀነራል ከማል ነበሩ፡፡ አቶ ዳውድ የሸኔውን ግሩፕ በሊቀመንበርነት ይመሩ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሸኔ ማለት ምንድን ነው?
አቶ ተማም፡- ሸኔ ማለት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጠሪያ ሥሙ በኦሮሚኛ ሸኔ ጉሜ ነው፡፡ ከዚያ የመጣ ነው፡፡ ክፍፍሉ በዚያ አይነት ነው የነበረው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከተለያዩ በኋላ እኔ የመጣሁት ለመቀመጥ አይደለም ለሕዝቤ ለመዋጋት ነው ያለው የእነ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ ቡድን ምን እንቅስቃሴ አደረገ ?
አቶ ተማም፡- በሽምቅ ውጊያ ለመዋጋት አንድ አገር ላይ ሆነህ ከእዚያ ፈቃድ መገኘት አለበት፡፡ የኤርትራ መንግስት ከአቶ ዳውድ ጋር ነው በግልጽ የወገነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኤርትራ መንግስት ለአቶ ዳውድ ኢብሳ ሙሉ በሙሉ ከወገነ በኋላ የእነ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ መጨረሻ ምን ሆነ ?
አቶ ተማም፡- የብርጋዴር ጀነራል ከማል ጦር በአቶ ዳውድ ኢብሳ ሥር እንዲሰለፍ ከተደረገ በኋላ ከአስር በላይ የሆኑ ኮማንደሮች ታሰሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የት? ኤርትራ ውስጥ?
አቶ ተማም፡- አዎ፤ አስመራ ውስጥ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጀነራል ከማል ገልቹንስ ?
አቶ ተማም፡- ጀነራል ከማል አልታሰሩም፡፡ ኮሎኔል አበበ ግን ታስረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጀነራል ከማል ገልቹ ሰራዊት ተገዶ ነው ወደ ዳውድ ኢብሳ እንዲገባ የተደረገው?
አቶ ተማም፡- አዎ ተገዶ በዳውድ ኢብሳ እዝ ስር እንዲገባ ነው የተደረገው፡፡ ሎጂስቲክሱም፣ ትጥቁም ሥላልነበረ ለመዋጋት አመቺ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በነበረው እንቅስቃሴ ከአገር ውስጥም ከውጭም ብርጋዴር ጀነራል ከማል ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ሰራዊታችሁ ያለው የት ነው፤ በፊት የነበረው ጦር የት ሄደ ?
አቶ ተማም፡- መጀመሪያ የነበረን ሰራዊት በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ በኤርትራ መንግስት አማካኝነት ለአቶ ዳውድ ኢብሳ ነው የተሰጠው፡፡ ዋናው ሠራዊት ጀነራል ከማል ይዘውት የሄዱትንም ሆነ ያሰለጠኑትን ጨምሮ በግድ በጠመንጃ አስገድደው ነው ወደ አቶ ዳውድ ያስገቧቸው፡፡ አሁን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጦር ነኝ ብሎ ወደ መንግስት የገባው ጦር ሙሉ በሙሉ የእኛ ጦር ነው፡፡ በጀነራል ከማል ገልቹ ይመራ የነበረው ነው፡፡ እኛ በአሁኑ ሰአት ሠራዊት የለንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ከመንግስት ጋር እርቀ ሰላም አድርጎአል፡፡ መሳሪያዬን ለአባገዳዎችና ለኦሮሞ ሕዝብ አስረክባለሁ ብሎአል፡፡ ይህንን ሁኔታ እንዴት ነው የምታዩት ?
አቶ ተማም፡- እኛ ለውጡ ፍጹም ሰላማዊ ለውጥ ሆኖ ሀገርም ሕዝብም ተጠቃሚ እንዲሆን ነው የመጣነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠበቅ እንፈልጋለን። የምንሰራውም ለዚህ ነው፡፡ በእኛ በኩል እንደ ድርጅት የዶክተር አብይን መንግስት የሚዋጋ የኦሮሞም ይሁን ሌላ ድርጅት ካለ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ እንዲያውም ከመቃወም አልፈን እንዋጋለን፡፡ የዛን ያህል ውሳኔ ነው ያለን፡፡ ይሄ ለውጥ ሰላማዊ እንዲሆን የዶክተር አብይ መንግስት እስከ ምርጫ እንዲቆይ ነው የምንፈልገው፡፡ ኢትዮጵያን እንደአለፈው ግዜ ለሌላ ሀያ ሰባት አመት እንዲገዛ አይደለም የምንፈልገው፡፡ ይሄን መንግስት ከምርጫው በፊት የሚዋጋ፣ ሊያስወግድ የሚፈልግ፣ ሊጥል የሚያሴር ኃይል ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እኛ እንደ ድርጅት እንዋጋዋለን፡፡
በእኛ በኩል ይሄ ያለው እሰጥ አገባ በእርቅ ቢያልቅ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ እርቅ እንዲሆን ሕዝባችን ሰላማዊ ኑሮ እንዲመራ እንፈልጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የኦሮሞው ሕዝብ በጦርነት ተጎሳቁሎአል፡፡ ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት በቃኝ ብሎአል፡፡ ሰልችቶታል፡፡ ስለዚህ ይሄ ንትርክ በሰላም እንዲፈታ እንፈልጋለን፡፡ ባለፈው እርቅ ላይ ሲባል እንደነበረው ጦሩን ለአባ ገዳዎችና ለኦሮሞ ሕዝብ ሰጥተናል የሚለውን አባባል እኛ ከሩቅ ስናየው አይሰራም፡፡ ጦር በእዝ ነው የሚመራው፡፡ አባገዳዎች መንፈሳዊና ባሕላዊ መሪዎች እንጂ የጦር መሪዎች አይደሉም፡፡ ጦሩን አባገዳ ከጫካ አውጥቶ ምን ሊያደርገው ነው፡፡ እጅ ሊያሰጥ አይችልም፡፡ ይሄ ለእኛ ፖለቲካ ፖለቲካዊ ስልት ነው፡፡ ፖለቲካዊ መገለባበጥ አክሮባት ነው የሚመስለን፡፡ በትክክል አቶ ዳውድ ኢብሳ ጦሩን የሚያዙ ከሆነ በተሰጠው 20 ቀን ውስጥ ወደ መንግስት ማስገባት ነው ያለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አቶ ዳውድ ኢብሳ ይሄን የሸኔ ኦነግ የሚባል ጦር በቀጥታ ያዙታል ይመሩታል ብላችሁ ታምናላችሁ ?
አቶ ተማም፡- ዋናውን ነገር እነሱ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እነሱን ወክዬ አይደለም የምናገረው፡፡ በእኔ ግምት ግን ብዙዎቹ በምእራብ ኦሮሚያ ጦር ይዘው የሚንቀሳቀሱ ልጆች በኢህአዴግ ላይ የተከፉ ልጆች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ያስከፋቸው፤ የታሰሩ፤ የተገረፉ በብሶት ወደ ጫካ የወጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ አቶ ዳውድ አይደለም ወደ ጫካ ያወጣቸው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከተፈለገ እውነቱ ይሄ ነው፡፡ ላያዛቸውም ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ሊቀ መንበር ናቸው፡፡ ወደ መንግስት አመራር ከመጡ ወዲህ የኦሮሚያ የጸጥታና የደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ያላቸው ሚና ምን ይመስላል ?
አቶ ተማም፡- ብርጋዴር ጀነራል ከማል የኦሮሚያ የደህንነት የጸጥታና አስተዳደር ኃላፊ ሁነው ሲሾሙ የመንግስት ስራ ላይ ነው የተመደቡት፡፡ የመንግስት እንጂ የድርጅት ስራ አይደለም፡፡ ኦህዴድም አይደሉም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጀነራል ከማል ኦዴፓ ገብቷል ለምን ሌላ ድርጅት አስፈለገው የሚሉም አሉ፡፡ ይሄ የመንግስትና የፖለቲካ ድርጅትን ስራ አለመለየት ነው፡፡ መንግስት መንግስት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ ጀነራል ከማል እየሰሩ ያሉት ለመንግስትና ለሕዝብ ነው፡፡ ለመንግስት እየሰሩም የራሳቸውን ፓርቲ እየመሩ ነው፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ከማል ይሄን ስልጣን በኃላፊነት የተቀበሉት ሀገርና ሕዝብ ሰላም እንዲረጋጋ በሙያቸው የላቀ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንጂ የስልጣን ጥማትና ፍላጎት ኖሮአቸው አይደለም፡፡ ይህ መንግስት እስከ ምርጫዋ ቀን ድረስ መቀጠል አለበት የሚል እምነት ስላለንም ነው እንደ ድርጅት እሳቸውም እንደ ግለሰብ፡፡ መንግስት እስከ ምርጫው እንዲቀጥል የበኩላችንን እናበርክት ለሰላም መረጋጋቱ የምንችለውን ሁሉ እናድርግ የሚል ውሳኔ ስለተላለፈም ነው፡፡ የበኩላችንን የምናበረክተው በፓርቲው በምንሰራው ስራ ከመንግስትም ጋር ሆነን በሚሰራ የጋራ ስራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች የግዜ ገደቡ መራዘም አለበት ይላሉ፤ እንዴት ያዩታል?
አቶ ተማም፡- እምነታችን ይሄ ምርጫ ሰላማዊና ነጻ ምርጫ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን መንግስት እንዲመሰርት ነው፡፡ ለዚህም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው የመጣነው፡፡ አሁንም እምነታችን ይሀው ነው፡፡ ምርጫው ፍትሀዊና ዴሞክራሲዊ የሚሆነው ለምርጫው የሚያስፈልጉ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ፤ፖሊስ ታዛቢዎች ነጻና ገለልተኛ ሲሆኑ፤የሕግ የበላይነት ሲኖርና ሲከበር፤ ምርጫ የሚያጭበረብር ወይንም የሚሰርቅ ኃይል ካለ በሕግ የምትዳኘው እነዚህ ተቋሞች ሲኖሩ ብቻ ነው ምርጫው ነጻና ዴሞክራሲያዊ የሚሆነው፡፡ ይሄ እንዲሳካ ከአሁኑ ጥረታችንን ቀጥለናል፡፡ ለመንግስት ማስታወስ የሚገባንን እያስታወስን ነው፡፡ ስብሰባዎች በፓርቲዎች መሀል ውይይትም እየተካሄዱ ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ፡፡ ተስፋ በተሞላበት ሁኔታ ይሄ ምርጫ ዲሞክራሲዊና ነጻ ምርጫ ይሆናል ብለን ነው የምናምነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው በተያዘለት የግዜ ገደብ ነው መካሄድ ያለበት ወይንስ መራዘም አለበት ትላላችሁ?
አቶ ተማም፡- እንደ እኛ እምነት በተያዘለት የግዜ ገደብ ቢካሄድ ደስ ይለናል፡፡ ምክንያቱም ይህ የአደራ መንግስት ነው፡፡ ቀደም ሲል አሁን ያለውን መንግስት የሚዋጋን ማንኛውንም ኃይል እንዋጋለን ያልኩበት ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ ሕዝብ አመኔታን ያገኘና አደራ የተሰጠው መንግስት ስለሆነ ነው፡፡ የኦሮሞ ልጆች ሌሎችም የኢትዮጵያ ወጣቶች ደማቸውን አፍሰው ለውጥ አምጥተው ይሄ ያለው መንግስት እነ ዶክተር አብይና ገዱ፣ ፕሬዚዳንት ለማ ከነበረው ጨቋኝ መንግስት ውስጥ ወጥተው የሕዝቡን ትግሉን ሲቀላቀሉ እነዚህ ሰዎች ይሄንን ትግል ሊመሩልኝ ይችላሉ ብሎ ነው ሕዝቡ እስከ ምርጫው ድረስ አደራ የጣለባቸው፡፡ የሕዝብ መንግስት እስከሚመሰረት ድረስ ይሄንን ይዘውት እንዲያካሂዱለት ነው የሰጠው፡፡ ሕዝቡ የሰጣቸውን አደራ ይወጣሉ ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በየፊናቸው ትግሉን በግንባር ቀደምትነት መርተን ለዚህ ድል ያበቃነው እኛ ነን በሚል ሽኩቻና ሽሚያ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በእናንተ እምነት የዚህ ድል ባለቤት ማነው ?
አቶ ተማም፡- ትግሉን ለውጤትና ለድል ያበቃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ እኛ አይደለንም፡፡ ሌሎችም ድርጅቶች አይደሉም፡፡ የድሉ ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን በተመለከተ በብዛት ያሉት ኢህአዴግ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ደመወዝ ሲከፍላቸው የነበሩ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በእውነተኝነት የሕዝብ ድርጅት ነን ብለው በአላማ የተዋቀሩት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገር ደረጃ ከ80 በላይ ፓርቲዎች አሉ፡፡ አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ተማም፡- በመርህ ደረጃም ሆነ እንደ አንድ ግለሰብ እኔም ሳየው የድርጅት መብዛት አይደለም ችግሩ፡፡ እስራኤል 7 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ሀገር ናት፡፤ 31 ፓርቲ አላት፡፡ 31ዱ ፓርቲዎች ለሀገር ጥቅም እንዴት አብረው ይሰራሉ ነው እንጂ ጥያቄው ብዛት አይደለም፡፡ ሕዝቡ የፈለገውን ይመርጣል፡፡ ከ31ዱ ፓርቲዎች ሰው አንዱን ሊመርጥ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ 80 ፓርቲ በጣም ብዙ ነው የሚባል አይደለም፡፡ መንግስት የፈለፈላቸው ፓርቲዎች መሆናቸው ነው ዋናው ችግር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄ ችግር ሊፈታ ወይንም ሊታረም የሚችለው እንዴት ነው?
አቶ ተማም፡- ሕዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ በሚመርጥበት ወቅት ይከስማሉ፡፡ በአላማ አንድ የሆኑት ደግሞ ምንም ሶስትና አራት ቦታ የሚቆሙበት ሁኔታ የለም፡፡ የእኛ አላማ ከሌላው ፓርቲ አላማ ጋር አብሮ የሚሄድ ከሆነ አንድ ላይ መመጣት አለብን፡፡ የኦሮሞ ድርጅቶችን በተመለከተ ኦሮሞ ስለሆንክ ብቻ አንድ አላማ ሊኖርህ አይችልም፡፡ የአንድ አባትና እናት ልጆች የተለያየ አላማ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ በአስተሳሰብ በርእዮተ አለም ደረጃ ከሆነ የኦሮሞ ድርጅት አራት አምስት መሆኑ ችግር የለውም፡፡ አንድ አስተሳሰብ አንድ ርእዮተ አለም ያለው ፓርቲ የተለያየ ቦታ ባይቆም ይመረጣል፡፡ ኦሮሞ ወይም አማራ ስለሆንክ ብቻ አንድ ፓርቲ ልትሆን አትችልም፡፡ ዋናው የምታራምደው አላማ ነው፡፡ መፍትሄው በተቻለ መጠን አንድ ላይ መሰባሰብ ነው፡፡ የተለየ አላማ ያላቸው ደግሞ ያን አላማ ይዘው ለሕዝብ መቅረብ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገውን ይመርጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጉጂ በኦሮሚያ በሶማሌ ድንበሮች አካባቢ የሚካሄዱትን ግጭቶች፣ የዜጎች መፈናቀልና ሞት ዛሬም ድረስ እያገረሸ አልፎ አልፎ ይከሰታል፡፡ መፍትሄው ምንድነው ይላሉ ?
አቶ ተማም፡- የዚህ ችግር ባለቤት ሕዝቡ አይደለም፡፡ የዚህ ችግር ባለቤቶች ጥቅማቸው የቀረባቸው የዚህ መንግስት ባለስልጣናት የነበሩ ናቸው፡፡ ከሕዝብ የወጣ ፓርቲ ሳይሆን የራሳቸውን ፓርቲ በየዞኑ የፈጠሩ ሰዎች ፈጣሪዎቻቸውና የተፈጠሩት ሰዎች ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡
በሶማሌ ክልል ብንወስድ ሕወሓት ነው አብዲ ኢሌን የፈጠረው፡፡ አብዲ ኢሌ ነው ሕዝቡን ያፈናቀለው፡፡ በሌላውም አካባቢ ይኽው ነው፡፡ ኢህአዴግ የፈለፈላቸው አጋር ድርጅቶች የሚሏቸው ናቸው፡፡ለውጡን ስላልተቀበሉት ለውጡ እነሱን የሚጠቅም ሳይሆን የሚጎዳ መስሎ ስለታያቸው ነው ሕዝብን በማፈናቀል የዶክተር አብይን መንግስት መበጥበጥ፤ ሀገሪቷን ማስተዳደር አልቻለም እንዲባል በዚህም የተነሳ ሕዝቡን በማፈናቀል ሕዝቡ ተነስቶ እንዲሰለፍ መንግስትን እንዲያስጨንቅ ነው የሚሰሩት፡፡ ምክንያቱም ለሕዝቡ ቢሆንም ለእነሱ ያልሆነ መንግስት ምናቸውም አይደለም፡፡ ለእነሱ የሚሆን ሌላ መንግስት እንዲመጣ እምነት ያላቸው ሰዎች ናቸው ይሄንን የሚያደርጉት፡፡
መፍትሄው ሕዝቡ ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች ማን እንደሆኑ አውቆ አለመስማት፤ ከዚህ ብጥብጥ ጀርባ ያለው ማነው የሚለውን በደንብ መረዳት፤ ሕዝባችን ጥንትም ሲያደርግ እንደኖረው በሽምግልና በውይይት በቆየው ትልቅ ባሕላችን መሰረት ችግሩን በመፍታት ሀገሩንና ሰላሙን መጠበቅ ነው ያለበት፡፡ ከዚህ ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡ የመንግስት ዋናው ስራ የሕዝብን ሰላም ማስከበር ነው፡፡ ግዴታውም ነው፡፡ የተፈናቀለውን ሕዝብ መልሶ ማስፈር፤ ሌላ እንዳይፈናቀል ሰላም ማስከበር፤ የመንግስትም የሕዝብም ኃላፊነት ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ የየራሱን ኃላፊነትና ግዴታ ከተወጣ ሰላማችን ይከበራል፡፡ ይጠበቃል፡፡ የመንግስት እዳና ኃላፊነት ብቻ አድርጎ መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡ የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡ ራሱን እንዲጠብቅ ሕዝባችንን ማሳወቅ ማስተማርም አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ እንዴት ይገልጹታል ?
አቶ ተማም፡- በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ በሕዝብ የመጣ ለውጥ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የለውጡ ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ጠመንጃ ማንሳት ጦር መሰነቅ አይገባም፡፡ ሕዝቡ ራሱ እኮ ጠመንጃ አልነበረውም፡፡ ኢሕአዴግን ሲዋጋ የነበረው በጦርና በድንጋይ ነው የነበረው፡፡ ሕዝቡ አሁን ጦርና ጠመንጃውን ቁጭ አድርጎአል፡፡ ለሕዝብ እታገላለሁ የሚል ድርጅት በአሁኑ ሰአት ደግሞ ጠመንጃ የሚያነሳበት ምክንያት የለም፡፡ ጠመንጃ አስቀምጦ ሕዝቡ በሰላማዊ ትግል ያመጣውን ለውጥ ወደህዝብ መንግሥትነት መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው የሕዝብ መንግስት አይደለም፡፡ ለውጥን ባመጡት ሰዎች በእነሱ ፍላጎትና ፈቃድ ብቻ ነው ደግ ነገሮች እየተሰሩ ያሉት፡፡ የእነሱ ፍላጎትና መልካም ፈቃድ በማንኛውም ሰአት ሊቀየር ይችላል፡፡ ይሄ መልካምነትና ደግነት ከተቋም የሚመጣ መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያና ለሕዝብዋ ሰላም ሲባል ምን ይጠበቃል ይላሉ ?
አቶ ተማም፡- እንደ ሀገር ለመቀጠል በመጀመሪያ ደረጃ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሕግና ስርአት መኖር አለበት፡፤ ሕግና ስርአት ከሌለ ሰላም ካልሰፈነ እንደ ሀገር መቀጠል ሕልም ነው፡፡ እንደ ሀገር የመቀጠል ኃላፊነት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ነው፡፡ የአንድ ክፍል ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ አንዳንድ ድርጅቶችም ይሁኑ ቡድኖች ወጣቱን ክፍል እንደ ጦር ኃይል ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ፡፡ ወጣቱን ሠራዊት አድርገው የሚያቃጥል፤ የሚገድል፤መንገድ የሚዘጋ፤መንግስትና መዋቅሮቹ በስርአቱ እንዳይሰሩ የሚያደርግ ኃይል አድርገው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡
ወጣቱ ለነዚህ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ የትግሉና የድሉ ባለቤት እሱ ነው፡፡ በተለይም እውነቱን ለመናገር የኦሮሞ ቄሮ ይሄን ለውጥ ለማምጣት ትልቅ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ በደሙና በአጥንቱ ነው ይሄን ለውጥ ያመጣው፡፡ የተቀረውም ሁሉም የኢትዮጵያ ወጣት በየአቅጣጫው በየአካባቢው ያደረገው ትግል ውጤት ነው፡፡ በእብዛኛው ትግሉ በኦሮሚያ አካባቢ ነበር፡፡ በአማራውም በጉራጌውም አካባቢ ወጣቶች ሰፊ ትግል አድርገዋል፡፡ ይሄንን ወጣቱ በደሙ ያመጣውን ለውጥ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል መቆም ያለበት ራሱ ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ ለተለያዩ ቡድኖች ፍላጎት መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ ሕገመንግስቱን እንዴት ይመለከተዋል ?
አቶ ተማም፡- ፓርቲያችን ሕገመንግስቱን ችግር አድርጎ አያየውም፡፡ አፈጻጸሙ ችግር አለው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ለውጦች መደረግ አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ሕገመንገስቱ ጥሩ ዶክመንት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንቀጽ 39ን (የራስን እድል በራስ የመወሰን፤የመገንጠል መብት) እንዴት ታዩታላችሁ ?
አቶ ተማም፡- ከመነሻው የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 39 የተወሰኑ ቡድኖች ለራሳቸው ፍላጎት በሚመች መልኩ የቀረጹት ቢሆንም ለሕዝብ ግን ጥቅም አለው፡፡ አንድ ሕዝብ በእምነቱ፤በዘሩ ከተገፋ ከተጎዳ ከተገለለ ይሄ ሕግ አለኝ ብሎ መከራከር ይችላል፡፡ ተገፍቻለሁ፣ተጎድቻለሁ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌ ጠፍቶአል፤ እንደ ሰው ማንነቴ ተንቋል፤ መብቴ ተደፍሯል፤ ተጥሶአል ይከበርልኝ ብሎ ጥያቄ ማንሳት ይችላል፡፡
አቶ ተማም ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን!
ወንድወሰን መኮንን