አስመረት ብስራት
ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒቶች ወይም የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በሰውነት ውስጥ እንዳይባዛ የሚከላከል መድኃኒት ነው። አንድ ሰው ኤች.አይ.ቪ እንዳለበት ካረጋገጠ መድሀኒቱን መጀመር ይኖርበታል። ይህን መድሀኒት የሲዲፎር ሴል ቁጥር እንዳይወርድ የሚያግዝ ሲሆን ይህ ችግር እንዳይከሰት በጊዜ መጀመር ይገባል።
የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያሳየው የሲዲ ፎራቸው መጠን ሳይወርድ በፊት ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒት የጀመሩና ለአምስት ዓመታት መድሀኒቱን በአግባቡ የወሰዱ የ67 ዓመት አዛውንት በመጨረሻ መድሀኒቱን እንዲያቆሙ ተደርጓል።
እንዲያቆሙ የተደረገው ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒቱ በሚገባ በመወሰዱ በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ መጠን አውርዶት በምርመራ እንኳ መታየት የማይችልበት ደረጃ ላይ ስላደረሰው ነበር።
በቀጣይ አዛውንቱ ካለ ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ለዘጠኝ ዓመታት ቫይረሱን ተቆጣጥረው መኖር ችለዋል። እኚህ ሰው በተደረገላቸው የተለያየ ምርመራም የሰውነታቸው በሽታን የመከላከል አቅም ኤች.አይ.ቪ ኔጌቲቭ ከሆነ ሰው ጋር መመሳሰሉ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የጤናን ሁኔታ ለማሻሻል እንዲሁም የቫይረሱን ሥርጭት በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ሲዲ ፎራቸው ከአምስትመቶ ሳይወርድ በፊት ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት መውሰድ ይኖርባቸዋል የሚል ስምምነት ላይ እየተደረሰ ነው።
እንዲህም ሆኖ ግን በርካታ ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ግን ሀይማኖታዊ ስርአት አይፈቅድልንም በሚል ምክንያት መድሀኒቶችን እያቋረጡ ላልተገባ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን በፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒት አወሳሰድ ላይ በተከናወነው የቅስቀሳ መድረክ ላይ ለመስማት ችለናል።
በመድረኩ ላይ የተለያዩ ታላላቅ መንፈሳዊ አባቶች፤ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተሰፋዬ፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ሰዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተው የነበረ ሲሆን በወቅቱ ምስክርነታቸውን የሰጡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ የኦርቶዶክስ፣ የአስልምና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ከአስራ አምስት አመታት በላይ ቫይረሱ በደማችን ውስጥ እንኳን ቢኖር ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒት በመውሰድ ህይወታችን ሊቀጥል ችሏል ብለዋል።
አግብቶ የእናትነት ፀጋ እስከማየት የደረሱት እነዚህ እንስቶች በህይወታቸው መንፈሳዊ ስርአቶችን በመከወን መድሀኒታቸውን በአግባቡ በመውሰድ ህይወታቸውን በአግባቡ ለመምራት እንደቻሉ ነው ያስረዱት።
የጉባኤውን መጀመር በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያበሰሩት የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሀገራችን የቫይረሱን ስርጭት ለማቆም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች የህክምና ክትትላቸውን በአግባቡ ማከናውን እንዲችሉ ሲደረግ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አዲስ እያንሰረራ ያለው የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ስርጭትን ለማቆም በሀይማኖት ሰበብ መድሀኒታቸውን የሚያቋርጡ ህሙማን ከዚህ ተግባር መቆጠብ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
በመቀጠል ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉት አቶ መኮንን አለሙ ከፀበል፣ ከዱአና ከፀሎት ጎን ለጎን መድሀኒቱን መውሰድ ያለምክንያት የሚጠፋውን የቫይረሱ ተጠቂዎችን ህይወት ሊታደግ የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ ከሀይማኖት አባቶች ጋር የሚደረግ ግንኙነት የመንፈስ ጥንካሬን እንደሚያጎናፅፍ አስረድተው መንፈሳዊውንም ሆነ ህክምናውን ጎን ለጎን ማስኬድ አዲስ ከቫይረሱ ጋር የሚወለዱ ልጆች እንዳይኖሩ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ቀደም ሲል የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሀይማኖት አባቶች አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን በመቀዛቀዝ ላይ ያለው ኤች.አይ.ቪ ቫይረስን የተመለከተ ንቅናቄ አሁንም በሀይማኖት አባቶች አስተምህሮት ሊደገፍ የሚገባ መሆኑን ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከስድስት መቶ ስድሳ ሰባት ሺ በላይ ሰዎች በደማቸው ውስጥ መኖሩን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ፤በሁሉም ህብረተሰብ የጋራ ርብርብ መጥቶ የነበረው የአመለካከት ለውጥ ወደኋላ እንዳይመለስ የሀይማኖት አባቶች አስተምሯቸውን አጠናከረው መቀጠል የሚገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ምክረ ሀሳባቸውን ያስቀመጡት አባቶች የሰው ልጅ በምድር ኖሮ ለማለፍ እስከተፈጠረ ድረስ በህይወቱ መቀለድ የማይኖርበት መሆኑን አስረድተው ፀበሉንም፣ እምነቱነም፣ ፀሎቱንም ሳያቆሙ መድሀኒት በመውሰድ እራሳቸውን ከከፋ ህመም መጠበቅ የሚገባቸው መሆኑን አስተምረዋል።
በእምነት እያሳበቡ መድሀኒት ማቆም ራስን ከመግደል የማይተናነስ ሲሆን ፈጣሪ ከፈጠራቸው ተክሎች የተፈጠሩ መድሀኒቶችን አልጠቀምም ማለት በፍፁም ከመንፈሳዊ አስተምህሮት ውጪ ነው ብለዋል።
በሽታው የመጣው ከፈጣሪ፣ ማርከሻ መድሀኒቱም የሚገኘው በፈጣሪ ፍቃድ በመሆኑ የሀይማኖታዊ ስርአቶችን ከማከናወን ጎን ለጎን መድሀኒቶችን በአግባቡ መውሰድ ተገቢ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
̋አላህ መድሀኒት የሌለው በሽታ አልፈጠረም። ካለእርጅና ሞት” ያሉት ሀጂ ኡመር ጥበቡን ሰጥቷቸው በቅንነት ሊረዱን የመጡ የህክምና ባለሙያዎችን አለመተባበር ግን ተገቢ አይደለም ብለዋል።
በተለያዩ የመፃህፍ ቅዱስ ክፍሎች የተለያዩ መድሀኒቶችን መጠቀም መፈቀዱን አስታውሰው ከሀይማኖት አባቶች ጋር የሚከናወኑ መንፈሳዊ ተግባራት ለስነልቦና እጅግ በጣም ጠቃሚ በመሆኑ ከመድሀኒቱ ጎን ለጎን እምነታዊ ተግባራትን መፈፀም ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል።
በጉባኤው ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሰባት የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች መድሀኒት ማቋረጥ ሀይማኖታዊ አስተምህሮ አለመሆኑን አስገንዝበዋል። በጉባኤው ማጠናቀቂያ ተሳታፊዎቹ ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
የተለያዩ የመረጃ መዛግብት እንደሚያመለክቱት በዓለም ዙሪያ ዛሬ ኤች.አይ.ቪ በደሙ ውስጥ የሚገኝ ሰው ቁጥር 36.7 ሚሊየን ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነው የፀረ-ኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) መድሀኒት ይወስዳል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013