አንድ ነዶ አንድ ፈርዶ ይላሉ አባቶች፡፡ ሀገራዊ ጉዳዮች የሁሉም ዜጋ የወል ጉዳዮች ናቸው፡፡ በሀገር መሪ ጫንቃ ላይ ብቻ የሚጣሉ፤ ከአንድ ሰው ብቻ መፍትሄው የሚጠበ ቅባቸውም አይደለም፡፡ ሀገር ሀገር የምትሆነው የምትከበረው የምታድገው ሁሉም ዜጋ በየተሰለፈበት መስክ የየበኩሉን ድርሻ በትጋት ሲወጣ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ዳር እስከዳር እየነፈሰ ያለው ፖለቲካዊ ማእበል ሀገራዊ ኢኮኖሚያችንን እንዳይጎዳው መጠንቀቅ ግድ ይላል፡፡
ሀገር በፖለቲካ ብቻ አትቆምም፡፡ ሀገርን አጽንቶ የሚያቆማት ዋናው መሰረት ኢኮኖሚው ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ አብዛኛው ሕዝብ ትኩረቱን በፖለቲካው ላይ በማድረጉ ሀገራዊ ኢኮኖሚው ከፍተኛ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቶአል፡፡ በመንግስት ሰራተኛውም ሆነ በግሉ የተለያዩ ዘርፎች ኢኮኖሚያችን መዳከም አሳይቶአል፡፡ የሁሉም ሰው የእለት ተእለት ስራ ፖለቲካዊ ወግና ስላቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የፋብሪካው ወዛደር ካላመረተ፤ ገበሬው በአግባቡ ካላረሰ፤ የግንባታ ሰራተኛው በመንገዱም ሆነ በቤት ግንባታው የሚፈለገውን ስራ ካልሰራ፤ ነጋዴው በተገቢውና ስርአት ባለው መንገድ የሸቀጥ አቅርቦቶችን ካላከፋፈለ ኢኮኖሚያችን ታሞአል ማለት ነው፡፡
የምርት አቅርቦትና የሸቀጥ ክፍፍሉ በአግባቡ ካልተመራ፤ በሕዝቡ ፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ከተፈጠረ፤ የገበያ ልቅነትና ስርአተ አልበኝነት ከሰፈነና ሆን ተብሎ በሕብረተሰቡ ላይ ከአቅሙ በላይ የሆነ የገበያ ዋጋ በመጫን ሕብረተሰቡ እንዲማረር ከተሰራ ኢኮኖሚውን በማዳከም የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ታስቦበት የሚሰራ ሴራ መሆኑ ለክርክር አይቀርብም፡፡
የሀገር ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የገበያ ስርአተ አልበኝነት እንዲፈጠር ሆን ተብሎ የሸቀጥ እጥረት በሌለበት እንዳለ እንደተፈጠረ ተደርጎ የሚሰራው ስራ በሕግና በስርአት የማይመራ የገበያ ዋጋ መናር ሕብረተሰቡን ለአመጽ ለብጥብጥና አለመረጋጋት ቀስ በቀስ እየገፉት ያሉ ጉዳዮች ስለሆኑ በግዜው ሊቀረፉ ይገባል፡፡ ይህ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚኬድበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ቆሞ ሊከላከለው ይገባል፡፡ ፖለቲካው ቆሞ የሚሄደው ጠንካራ ኢኮኖሚ መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ ለአንድና ለተወሰኑ ሰዎች የሚተውና ተላልፎ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ ለመውቀስ፣ ለመተቸት፣ ለመንቀፍና አቃቂር ለማውጣት ግንባር ቀደም የመሆኑን ያህል እኔስ ሁላችንስ የበኩላችንን ሀገራዊ ድርሻ በኢኮኖሚ ግንባታው፤በሰላምና መረጋጋቱ፤በተለያዩ ዘርፎች ተወጥተናል ወይ ብሎ መጠየቅ ይገባዋል፡፡ ሁሉንም ነገር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ መጠበቅ አይቻልም፡፡
መሪ አቅጣጫ የሚያሳይ ኮምፓስ ነው፡፡ የተሰጠን አቅጣጫና መንገድ ተከትሎ መስራት፤መትጋት፤ ሀገሬን መለወጥ ሰላሟን ማስከበር አለብኝ ብሎ ተግቶ መስራት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በወሬ፣ በአሉባልታና በስም ማጥፋት ያደገ ሀገርና ሕዝብ በዓለም አልታየም፡፡ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ሀገር የሚያድገው ስራን ኃይማኖታቸው ባደረጉ እልፍ ዜጎች ትጋትና ብርታት ነው፡፡ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በመሰረቱ መለወጥን ይጠይቃል፡፡
የአስተሳሰብ ለውጥ፤የአመለካከት ለውጥ፤የአተያይ ለውጥ፤ ሲፈጠር የትኛውም ለውጥ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው የተሻለ ሀገራዊ ስኬት ያስገኛል፡፡ ወደፊት ሊተም ይችላል፡፡ የተጠናወተን አንዱ ክፉ ደዌ ከሰማይ በታች ያለውን ነገር ሁሉ መቃወም ነው፡፡ የሚታዩ ለውጦችን መካድ፡፡ ተቃውሞን ስልጣኔ አድርጎ የመውሰድ ልክፍት፡፡
እኔ የፈለኩት ካልሆነ ለውጥ የለም አልመጣም ብሎ መሸምጠጥ፡፡ ሀገርን ያህል ታላቅ ጉዳይ በግለሰብ (ቦች) ጉዳይ ማኮስመን ነውር ነው፡፡ ይህን የጨለመ አስተሳሰብ ቆርጠን መጣል አለብን፡፡ ሰፊ ለውጦች አሉ፡፡ ተስፋ በተሞላበት ጉዞ ላይ ነን፡፡ ሰላማችንን ነቅተን እንጠብቃለን፡፡ ኢኮኖሚያችንን ቀን ከለሊት ሰርተን እናሳድጋለን፡፡ ሀገራችንን ከተዘፈቀችበት ብድር እናወጣለን የሚል ቁርጠኛ ውሳኔ መወሰን ስንችል ብቻ ኢኮኖሚውን በአጭር ጊዜ ማሳደግ የምንችለው፡፡
ዶክተር አብይን መውደድና ማክበር ማለት አንገቱን አቅፎ መሳምና ማልቀስ ብቻ አይደለም፡፡ሀገርን ለመለወጥ መጀገን፤ ለሰላሟ መቆም፤አዋኪዎችን መግታትና ማንበርከክ፤ ለኢኮኖሚያችን ማደግ በብርታት መስራት ስንችል ያኔ ነው ለመሪያችን ያለን እውነተኛ ፍቅር የሚገለጸው፡፡ በወሬ ሳይሆን በስራና በስራ ብቻ፡፡
ኢኮኖሚያችንን ሊያሳድግ፤ እኛንም ከችግር ሊያወጣን፤ ድህነታችንንም ለመክላት የሚያስችለን ለሊት ከቀን በየመስኩ ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው፡፡ ገበያው ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያችንም ተቀዛቅዟል፤ በሁሉም መስክ ማለት በሚቻል መልኩ፡፡
ዛሬ ሞልቶ የተረፈው ስራ አይደለም፡፡ ስራ ኖሮት የማይሰራው ከሚሰራው በእጥፍ ይበልጣል፡፡በፖለቲካ ወሬና ሱስ ተጠምዶ ሲያውካኩ ሲያመነዥጉ መዋልን የመሰለ ሀገር ገዳይ በሽታ የለም፡፡ መስራት የሚገባንን እለታዊ ስራ ትተን ሀገርን በኢኮኖሚ ማሳደግ አይቻልም፡፡
እንደ ሀገር እስከ አንገታችን ድረስ በውጭ ብድርና እዳ ተዘፍቀናል፡፡ የተቻለውን ያህል ቢሰራም ከፊሉ ወይም የበለጠው የብድር ገንዘብ መመዝበሩ ለውይይት አይቀርብም፡፡ የኢትዮጵያ ሙሰኞች ከድሀው ሕዝብ ጉሮሮ የሚነጥቁ የለየላቸው ረሀብተኞች ናቸው፡፡
ሀገራዊ እዳዎቻችንን ለመክፈል ተግቶና ጠንክሮ ከመስራት ውጪ በወሬና በስላቅ የምናሳልፈው ግዜ ሊኖር አይገባም፡፡ አንድም መላው ሕዝብ ተግቶና ጠንክሮ ሰርቶ ሀገሩን በኢኮኖሚ በማሳደግ ከድሕነት ወጥታ ከብድር እንድትላቀቅ ማድረግ ወይም ተከፍሎ በማያልቅ ብድር ሀገርን ማስያዝ ነው ምርጫው፡፡ ይህ እንዲሆን የሚፈቅድ የለም፡፡
በየመስኩ ኢኮኖሚውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስራዎች ተቀዛቅዘዋል፡፡ በተለይ በኮንስትራክሽንና በመሳሰሉት፡፡ በኢኮኖሚስቶች ሀቲት መሰረት በቀዘቀዘ ገበያ ውስጥ ዋጋ ይወርዳል፡፡ በእኛ ሀገር ግን ገበያውም ቀዝቅዞ ዋጋው ተሰቅሏል፡፡ አይደለም በእለታዊ ገቢ ለሚተዳደርና ወር ጠብቆ ለሚኖር የመንግስት ሰራተኛ ሀብት አለን ለሚሉትም ፈታኝ ሁኖ ቀርቧል፡፡ ሀብታቸውን እንዲጠራጠሩ ያደርጋል፡፡የኢኮኖሚያችን መገለጫ ይሄ ነው፡፡
ገበያው ጤናማ አይደለም፡፡ ጤናማ የገበያ ፉክክር ከሌለ ሀገር አይዘመንም፡፡ በነበረው ነው የሚያዘግመው፡፡ በመዳህ ጉዞ የትም አይደረስም፡፡ እድገት የሚመጣው ሰርቶ በመስፈንጠር ነው፡፡
ብዙዎችን የሚያነታርከው የምዕራባውያን አቀንቃኞች ታላቅ ስጋት መንግስት የሚከተለውን የኢኮኖሚ ስርአት በጥርጣሬ የሚያዩበት መነጽር ነው፡፡ እነሱ ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ኢኮኖሚዋን በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንድታውል ነው ጩሀታቸውን የሚያሰሙት፡፡ እንዲህ አይነት ማፈሪያ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ሁለመናችን ለውጭ ባለሀብት ከተሸጠ ሀገርና ነጻነት አለን፤ ኢኮኖሚያችን ነጻ ነው ማለት ስለዚህ ኢኮኖሚውን ጠቅልሎ ለውጭና ለውስጥ ባለሀብቶች መሸጥ አይመከርም፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን በተመቸ መልኩ እድገቱን ይቀጥላል፡፡ አንድ ኢኮኖሚስት እንዳሉት የወደቁት ልማታዊ መንግስት የሚለውን አስተሳሰብ የመሩት ግለሰቦች እንጂ ስርአቱ አልወደቀም፡፡ ሌብነትንና ዘረኛነትን እንጂ አምርረን የጠላነው የተገኘውንና የተመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ አይደለም፡፡
ከድህነት እንድንወጣ ከአለም አቀፍ አጋሮች ስናገኝ የነበረውን የእርዳታና የብድር ገንዘብ ዘርፈው ከብረው ልማታዊ ባለሀብት ነን ከሚሉ አላጋጮች ነው ጠባችን፡፡ ከተገኘው የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ ጸብ የለንም፡፡ እንዲቀጥል እንሻለን፡፡ እንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮት ስታመጣ ምጣኔዋን በሁለት እጥፍ ለማሳደግ ወደ ስድሳ አመት ነው የወሰደባት፡፡ አሜሪካ በቴክኒዮሎጂ ተደግፋ ምጣኔዋን ለማሳደግ ሀምሳ አመት ተጉዛለች፡፡ ልማታዊ መንግስታት የነበሯቸው እንደ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮርያ፣ ኢንዶኒዢያና ማሌዥያ ያሉ ሀገራት ምጣኔያቸውን እጥፍ ለማድረግ 10 አመት ብቻ ነው የወሰደባቸው፡፡
መንግስት በልማት ስራው ውስጥ ተሳትፎ ማድረጉ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ የግድ ለበለጸጉ ሀገራት የኢኮኖሚ ባርነት ማጎብደድ የለብንም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የልማታዊ መንግስትን ፍልስፍና ጥቂት ግለሰቦች የራሳቸው ሀብት ማግኚያና መክበሪያ አድርገው ሲሰሩበትና ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ ለውጥ ያላመጣው ለዚህ ነው፡፡ የኢኮሚ ተወዳዳሪነት ከሌለ ማደግ አይቻልም፡፡ እንደ ሀገር ተበድረን ተበድረን ጣሪያው ላይ ደርሰናል፡፡
ብድርም ገደብ አለው፡፡ አንገታችን ድረስ በውጭ ብድር ተሰንገን ተይዘናል፡፡ ከእዳችን ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ ኢኮኖሚያችንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ብቻ ነው፡፡ ፖለቲካውን ለቀቅ ኢኮኖሚውን ጠበቅ እናድርግ ! እንስራ- እንበርታ- እንለወጥ !
መሐመድ አማን