ለምለም መንግሥቱ
ጭስ አልባው በመባል የሚታወቀው የቱሪዝም ኢንደሥትሪ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ብዙ ሀገራት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። የገቢ ምንጫቸው በቱሪዝም ላይ የተመሰረቱ ሀገሮች ደግሞ ጥቅሙን የተረዱ በመሆናቸው ሰው ሰራሽ፣ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶቻቸውን ጨምሮ ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ሀብታቸውን በማደራጀት፣ የቱሪዝም መዳረሻ መሠረተ ልማት በመገንባት፣ ቱሪዝምን ለመሳብ የሚያስችሉ የማስታወቂያና የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ቱሪሥቶችን ወይንም ጎብኝዎችን ይስባሉ። የቱሪዝም ሀብት መኖሩ ብቻ በቂ ባለመሆኑ በማስተዋወቅና አስፈላጊ ነገሮችን በማድረግ ሳይታክቱ የሚያከናውኑት ተግባር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል።
ቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ትስስር በመፍጠር ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። በሰዎች መካከል የሚፈጠረው ማህበራዊ ግንኙነትና የባህል ልውውጡ ዓለምን አንድ መንደር ለማድረግ ያስችላል። ከዚህ አንጻር ለቱሪዝም የሚሰጠው ትኩረት አንዱ ከሌላው እንደሚለይ ቢታወቅም ዘርፉ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ግንዛቤ ሊያዝ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችው ትኩረት ምን ይመሥላል የሚለውን እንደሚከተለው ዳሰናል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ትኩረት ያገኘው ከጣሊያን ወረራ ወዲህ ከ1950ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፣ተጠሪነቱ ለማሥታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሆነ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በ1954ዓ.ም ተቋቋመ። በወቅቱም ከ1955 እስከ 1959፣ከ1960 እስከ 1965 ባሉት ጊዜያቶች የሚከናወኑ የቱሪዝም ዕቅዶች ተነድፈው ሲተገበሩ ነበር። በተለይ ከ1955 እስከ 1959 በነበሩት አመታት ለቱሪዝም መዳረሻ በሆኑት አካባቢዎች የሆቴል ቤቶች ግንባታ ለማከናወን ‹‹ማስተናገድና ቱሪዝም››በሚለው ላይ ነበር ዕቅዱ ትኩረቱን ያደረገው።
ዕቅዱን ለመተግበርም የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ሆቴል ቤቶችንና የትራንስፖርት አውታሮችን በማደራጀት ጎብኝዎችን ለመሳብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት መግለጫ የሚሰጡ ቢሮዎች በውጭ ሀገር ጭምር መክፈት ከተግባራቶቹ መካከል ይጠቀሳል። በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን 118ሺ690 ቱሪስቶች ከአውሮፓ፣አሜሪካን፣ከአፍሪካና ከተለያዩ ሀገሮች በመሳብ ተጠቃሚ መሆን ተችሏል። በወቅቱም የአንድ ቱሪሥት የቆይታ ጊዜ አራት ቀናት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንደመረጃው በሶስተኛው የዕቅድ ዘመን ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍ ያለ ጥቅም የሚያስገኝ ኢንደስትሪ መሆኑ ታምኖበት ፖሊሲና መመሪያ በማዘጋጀት ዘርፉ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጓል። በመመሪያው የቱሪስት መዳረሻዎችን መሠረተ ልማት ማሟላት፣የቱሪስት ቁጥርን መጨመር፣ በዘርፉ ላይ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ማጎልበት ይጠቀሳሉ።
ይሁን እንጂ የቱሪዝም ዘርፉ የመዳከም ችግርም ገጥሞትም ነበር። በተለይ ከ1966 እስከ 1970 ሰነዶችን እንኳን ማግኘት ከባድ እንደነበር መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። ዘርፉ አንዴም እየጠነከረ፣ሌላ ጊዜም እየተዳከመ አሁን ላይ ደርሷል። በአሁኑ ወቅትም ከ2013ዓ.ም ጀምሮ የአስር አመት የቱሪዝም መሪ ዕቅድ ተነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በዕቅዱ ዙሪያ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ አማካሪ አቶ አህመድ መሐመድ ጋር ቆይታ አድርገናል።
እንደ አቶ አህመድ፤ዕቅዱ አራት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ያለው ሲሆን፣ለቱሪዝም ዕድገት ማነቆ የነበሩት ተለይተው ዘርፉን በሚያሳድጉት ላይ ቢሰራ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው። ከዕቅዱ አንዱ ተወዳዳሪነትን መፍጠር ነው፣በዚህ ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራትን ማሳደግ፣ በአገልግሎት እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ፣ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማጎልበት፣የቱሪሥቱን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥራ ሌሎችንም ተግባራት በማከናወን ተወዳዳሪነትን መፍጠር ነው።
ሁለተኛው የመረጃ ልዕቀትን ይመለከታል። በንግድ፣በባህል፣በማህበራዊና በሌሎችም ተሳስሮ በአንድ መንደር ውስጥ የሚገኘውን ዓለም የበለጠ ማስተሳሰር ላይ ያተኩራል። ትውልድ የሚፈልጋቸውን ለማቅረብና በቴክኖሎጂም ለመጠቀም ሥራዎች መስራት አለባቸው የማስተዋወቅ ሥራ ውስጥ ለመግባት ደግሞ ቴክኖሎጂዎቹ አስፈላጊ ናቸው።
በአጠቃላይ ጎብኚው ባለበት ሆኖ መረጃውን እንዲያገኝና ወደዚህ ሲመጣም ቀድሞ በማስመዝገብ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ የሚያስችል አሰራር ነው የተዘረጋው። በተጨማሪም ዘርፉ በፈጠራ እንዲከናወን የዕውቀት አስተዳደር የሚዘረጋበት፣የቱሪዝም መረጃ ሥርዓት የሚገነባበት በአጠቃላይ ትልቅ የመረጃ አብዮት የሚፈጠርበት ቁልፍ ተግባር በዕቅዱ ተካትቷል።
ሶስተኛው አቅም ግንባታ ላይ ያተኩራል። የቱሪዝም ዕቅዱን ለማሳካት የአደረጃጀት፣የሰው ኃይል ልማት፣ደረጃውን የጠበቀ መሠረተልማት ማሟላት የሚሉት ይጠቀሳሉ። የግሉን ዘርፍ፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና ሌሎችንም ለማሳተፍ አደረጃጀት ወሳኝ ስለሆነ በዚህ ረገድ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን፣አደረጃጀት እንደዘርፍም እንደተቋም የሚወሰድ አሰራር ነው።
የቱሪዝም አገልግሎት ሰውን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ የበቃ የሰው ኃይል ልማት ያስፈልጋል። ጥናትና ምርምር የተግባቦት ደረጃን በተሻለ ደረጃ በማሳደግ ዘርፉን ማገዝ ይገባል። በሀገሪቷ እየተገነባ ካለው ዕውቀት መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር ቱሪዝምን ለማሥተሳሰር ጥራት ያለው ጥናትና ምርምር እንዲሁም ዕውቀት በማጎልበት ላይ ሥራዎች ይሰራሉ። እንዚህ ሥራዎች በትኩረት ከተሰሩ ቱሪዝምን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ይቻላል ።
ስትራቴጂ ሲነደፍ በጀትና የተለያዩ የድጋፍ ማስተግበሪያዎች አብረው ይያያዛል። እያንዳንዳቸው ግምታዊ በጀት ተይዞላቸዋል። አዳዲስ 59 መዳረሻዎች ለማልማት ሲታሰብ ወጭው ቅድመጥናት ተደርጎ ነው።
በጀቱም ከመንግሥት፣ከባለሀብቶች፣በጉልበት ተሳትፎና በተለያየ መንገድ ከማህበረሰብ የሚገኝ ሲሆን፣የመንግሥት ወጭ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ አጠቃላይ የተያዘው በጀት ወደ 39ቢሊየን ብር ይደርሳል።
የ2013ዓ.ም የቱሪዝም መሪ ዕቅድ የአስር አመት ነው። ‹‹አንደኛ የመንግሥት የፕላን ኮሚሽን አቅጣጫ ነው። ሌላው የቱሪዝም ዕቅዱ በአምስት አመት ብቻ የማይካተቱ ሰፊ ዝርዝር ነገሮች ይዟል። ወደ አሥራ አምስት አመትም ሊሸጋገር ስለሚችልና እንደሀገር ከሚታቀዱ ሌሎች እቅዶች ጋርም ተመጋጋቢ እንዲሆን ሰፋ አድርጎ ማቀዱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ሥራዎቹ ግን በጊዜ ተከፋፍለው የሚሰሩ ይሆናል። እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ሥራዎች ተከፋፍለውና ተቆጥረው ይከናወናሉ››በማለት የቱሪዝም ፖሊሲ ሰነድ ዝግጅት መጀመሩን አመልክተዋል።
አቶ አህመድ እንዳሉት፤ የአቅም ግንባታን ለመገንባት የህግ ማዕቀፍ አያስፈልግም። እንደውም አቅም ግንባታ የተሻለ ሕግ ለማውጣት የሚረዳ በመሆኑ ቀድሞ መጀመሩ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። የቱሪዝም አስተዳደር ከዚህ ቀደም የህግ ማዕቀፍ አልነበረውም። አሁን ግን የህግ ማዕቀፍ የግድ ነው።
እንደሀገር የቱሪዝም ዘርፉ በመመሪያ፣ በደንብ ሲመራ እንደነበር ይታወቃል። የአሁኑ የቱሪዝም መሪ ዕቅድ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ የሚያደርገውስ ምንድ ነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። አቶ አህመድ ለዚህም ምላሽ አላቸው። እርሳቸው እንዳሉት ከዚህ በፊት መመሪያና ፖሊሲ ነበር። ነገር ግን የዘርፋ አስተዳደር አዋጅ አልነበረም። ፖሊሲውም 12 አመት አልፎታል።
የአሁኑን የተለየ የሚያደርገው ከለውጥ በኋላ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሥርዓትን መሠረት ያደረገ ዕቅድ መሆኑ፣ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን ጥንካሬና ድክመት ለይቶ ለሥራ መዘጋጀቱ፣ የሀገር ሀብትን አሟጦ ለመጠቀምና ሀብቱን ለይቶ በመረጃ አደራጅቶ ለማቅረብ፣ ለውጡን ማዕከል ያደረገና ህብረተሰቡን የሚጠቅም መሆኑ እንዲሁም የቱሪዝም ገበያ ሥርዓት ማስፈን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው።
ስትራቴጂው ከዝግጅት ባለፈም ወደ ትግበራ ገብቷል። ይሁን እንጂ ዓለምአቀፍ ሥጋት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ባልተወገደበትና ሀገራዊ መረጋጋቱም ገና በመስፈን ላይ ባለበት ወቅት መሆኑ ሥጋት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። አቶ አህመድ ግን በዚህ ወቅት ስትራቴጂው ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋል መጀመሩን እንደ መልካም ዕድል ያነሳሉ።
እርሳቸው እንዳሉት እንደኮቪድ19 ያሉ ችግሮች ሲከሰቱ ምን አይነት እርምጃ መወሰድ አለበት የሚለውን ለማየት ዕድል ሰጥቷል። በዚሁ መሠረትም የቱሪዝም ዘርፍ ቀውስ አስተዳደር ሥርዓት እንዲካተት ምክንያት ሆኗል። ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ በጣም የተለጠጠ ዕቅድ ለማዘጋጀት ነበር የታሰበው። ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሞሮኮ ወደ አስር ሚሊየን ቱሪስት ታስተናግዳለች።
ኮቪድ ደግሞ 30 በመቶ ነው ጉዳት ያስከተለው። ይሄ ግምት ውስጥ ገብቶ ነው ስትራቴጂው የተዘጋጀው። ሀገሪቱ ከገጠማት ቀውስ ጋር ተያይዞ የተነሳው ደግሞ ችግሩ ኢትዮጵያን ብቻ የሚያጋጥማት ባለመሆኑ ለዚህም መፍትሄ ተቀምጧል። ኢትዮጵያ ተገዳ ወደ አላስፈላጊ ጦርነት እንድትገባ ያደረጋት ነገር አዲስ ክስተት ነው። በአሁኑ ጊዜ ወደተረጋጋ ሥርዓት እየገባች በመሆኑ ዘርፉ መልሶ እንዲያንሰራራ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ሳይቀር በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራው ይጠናከራል።
በመንግሥት ህግን ለማስከበር የተወሰደው እርምጃ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ለመጨመር እንደ አንድ የፖለቲካ አቅም ተወስዷል። የጁንታው ቡድን ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ሳይቀር በመጠቀም ያደረገው እንቅስቃሴ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያደርስ ይችል ነበር። ነገር ግን ፖለቲካል ካፒታል የሚባለው የዲፕሎማሲ እና ሌሎችም ጥረቶች ግጭቱን በፍጥነት ለመቀልበስ አስችሏል።
ለአብነትም እንደ አይስላንድ ያሉ ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው ሀገሮች ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ ማህበራዊ ድረገጾችና ሌሎች አማራጮችን ተጠቅመው የቅስቀሳ ሥራ በመሥራት ነው። ቱሪዝሙን ወደነበረበት መመለሥ የቻሉት። በኢትዮጵያም ይህን ታሳቢ ያደረገ ስትራቴጂ ነው የተዘጋጀው።
ቱሪዝም አካታች የቱሪዝም ገበያ በመሆኑ፤ለህግ የሚገዛ፣በእውቀት የሚመራ፣በቀጣሪና በተቀጣሪ መካከል ግንኙነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ሥርዓት በመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው፣ በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ የተደራጁ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ፣ ሆቴልችም እንዲስፋፉ ስትራቴጂው የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዘርፈብዙ የሆኑ ሥራዎችን ባካተተው የአስር አመቱ የቱሪዝም መሪ ዕቅድ ላይ በዘርፉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ አካላት፣ በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ የተቋሙ ሰራተኞች፣ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ እውቀት ያላቸው የተካተቱበት አካላት ያዘጋጁትና ተተችቶ የዳበረ ሰነድና ለትግበራ የበቃ መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል።
ብዙ የተደከመበት ስትራቴጂ እንዲተገበር የተቀመጠውን የክትትልና ቁጥጥር ስልት አስመልክተው ሲናገሩም፤‹‹ እንዲህ ያሉ ችግሮች ዓለምአቀፋዊ ናቸው። መንግሥታት ቃል የሚገቡትን አስፈጻሚ ተቋማት ወደ ተግባር የማይቀይሩት ደካማ በመሆናቸው ነው። ስለዚህ እኛም ይህን ዕቅድ ለማስተግበር ምን አይነት አመለካከት፣ አሰራር፣የሰው ኃይል መኖር አለበት የሚል ብሄራዊ የሆነ የብቃት ቁጥጥርና ክትትል ወይንም ኢንቬንተሪ የተባለ የአሰራር ሥርዓት ዘርግተናል።
በዚህ ውስጥ አዳዲስ ነገሮች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቱሪዝም አንጻር ከዚህ ቀደም ዲዛይን ማርኬቲንግ የሚባል ሥራ ላይ አልዋለም። ስትራቴጂው እንዲህ ያሉ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦች አሉት። ››ሲሉ አስረድተዋል።
የክትትል፣ ቁጥጥር፣ እንዲሁም ሥራውን በመገምገም ከማጠናከር ጎን ለጎን ባለድርሻ አካላትና የተዋቀረ ኮሚቴ ተሳትፎ እንዲጎለብት በማድረግ ዕቅዱን የመተግበር ሥራ ይሰራል ብለዋል።
ግንዛቤ የመፍጠሩም ሥራ እንዲሁ አልተዘነጋም። በተለይም መገናኛ ብዙኃን ዕቅዱ መሬት ላይ መውረዱን ተከታትለው በመተቸትም ሆነ የተሰራውን ሥራ በማሳየት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ምቹ በማድረግ ዕቅዱ የሁሉም አካል እንዲሆን ተደርገጓል።
ከትራንስፖርት፣ ከሆቴሎችና ከአስጎብኝዎች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የሚነሱ ምቹ ያልሆኑ አገልግሎቶች አሁንም እንዳይቀጥሉ በስትራቴጂው ስለተቀመጠው ነጥብም አቶ አህመድ እንዳስረዱት፤ በጣም ከታዩት ውስጥ ይጠቀሳሉ። ዘርፎቹ የሚደገፉበትና የሚበቁበት ጠንካራ የሆነ የአስተዳደር መዋቅሮች ተደራጅተዋል።
ለአብነትም ከሆቴል ቤቶች ጋር በተያያዘ ምደባ ላይ ትኩረት ያደረገ የደረጃ አሰጣጥ አሰራር ይቀየራል። ቱሪዝም ናሽናል ኦዲት የተባለውን አሰራር በመተግበር እንዲሁም ሥራውን የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በመተግበር የተሻለ አገልግሎት ለመሥጠት ጥረት ይደረጋል።
በቱሪዝም መዳረሻ በኩልም በስትራቴጂው በተቀመጠው አቅጣጫ ቀደም ሲል የነበረውን አሰራር መነሻ ያደረገ ሲሆን፣ በፊት የነበረው የትኩረት አቅጣጫ ለዓለም ገበያና ለማስተዋወቅ በሚቀርቡት ላይ ነበር። በዓለም የቱሪዝም ገበያ ውስጥ እነ ቻይና፣ ጃፓን፣ መካከለኛ ምሥራቅ፣ ሩሲያ እየገቡ ስለሆነ እነርሱን ማዕከል ያደረገ የቱሪዝም መዳረሻና አቅርቦት መኖር አለበት በሚል ተቃኝቷል። ተመልካች ብቻ ሳይሆን በሚጎበኘው አካባቢም ተሳትፎ ያለው ቱሪስት ነው የሚፈለገው።
ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ዕምቅ ሀብቶች ባለቤት ናት። ይሁን እንጂ በአግባቡ እንዳልተጠቀመች ይታወቃል። አሁን ግን በስትራቴጂው በደንብ መታየቱን አቶ አህመድ ይናገራሉ። ማስተርካርድ ከተባለ ዓለምአቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር እየተሰራ በመሆኑ እንደ ሥጋት የተነሱት ክፍተቶች መፍትሄ ያገኛሉ።
በተጨማሪም 59 መዳረሻዎችን ለማልማት የተያዘው ዕቅድም በቀላሉ አይታይም። ከነዚህ መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተነሳሽነት ወንጪ፣ ኮይሻና ጎርጎራን ጨምሮ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ጥሩ ማነቃቂያዎች ናቸው።
‹‹ከጭስ አልባው ኢንደስትሪ ለመጠቀም ላለፉት አመታት ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ለስትራቴጂውም ያለፉት ሥራዎች መነሻ ናቸው። የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር፣ ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
ከነ ክፍተቱም ቢሆን መንግሥት ባመቻቸው ዕድልና በሀገር ሀብት ዘርፉን እንዲያግዙ የሆቴል ቤቶች ግንባታ መከናወናቸው የቱሪስት ፍሰቱን ከ250ሺ ወደ 910ሺ አድርሶታል። ሶስት ነጥብ አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል። በመንገድና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች እንደአንድ አቅም ተወስዶ ነው ስትራቴጂው የተነደፈው››ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ አቶ አህመድ ማብራሪያ የአስርአመቱ የቱሪዝም መሪ ዕቅድ ያጓጓል። ውጤቱ ይጠበቃል። ‹‹በዕቅዱ የመጨረሻ አመት በ2022 ዓ.ም ሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊየን አካባቢ የሚሆን ቱሪስት በመሳብ 23 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት ነው በስትራቴጂው ሰነድ ላይ የተቀመጠው። ከስራ ዕድል አንጻር ደግሞ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ቱሪዝም እንደ አንድ ኤክስፖርት ወይንም የወጭ ንግድ የሚወሰድ ዘርፍ በመሆኑ በዚህ ረገድም የሚሰራው ሥራ ወደ 26 በመቶ ድርሻ አለው። ቱሪዝም ኤክስፖርት በኢትዮጵያ የተለመደ አይደለም። አሁን ግን ለመጀመር ታቅዷል። አሰራሩ አገልግሎትን ኤክስፖርት ማድረግ ነው››በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን ባለው መረጃ ኢትዮጵያ በቱሪዝም እንቅስቃሴ ከአፍሪካ 17ኛ፣ ከ140 ሀገራት ደግሞ 19ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይህን ደረጃ ለማሻሻል ስትራቴጂው ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013