ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረው የህወሓት ጁንታ ራሱ በቆሰቆሰው እሳት ነዶ እነሆ ላይመለስ ወደመቃብር ወርዷል። ነገር ግን ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ ሁሉ በሴራ የቆየ በመሆኑ የቡድኑን አስተሳሰብና የጥፋት ፈንጂዎች ለማጽዳት ጊዜ መውሰዱ አይቀሬ ነው።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በየቦታው የለኮሰው ፈንጂም አሁንም እየቆየ እዚህና እዚያ ሲፈነዳ ይስተዋላል። ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በኮንሶ አካባቢ የተፈፀሙ ዘግናኝ የንፁሃን ጭፍጨፋዎችም የዚሁ ሴራ አካላት ናቸው።
ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከ200 በላይ ዜጎች ህይወት መቀጠፉ የሚታወስ ነው። በዚህ አካባቢ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። በተለይ ከለውጡ ወዲህ በተደጋጋሚ ሲከሰት እንደነበር ይታወቃል።
ሰሞኑን ደግሞ በኮንሶ በተከሰተ ጭፍጨፋ ከ65 በላይ ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል። ቀደም ሲልም በጁንታው አማካኝነት በማይካድራ በተፈፀመው ጅምላ ጭፍጨፋ በርካታ ዜጎች መሞታቸው የሚታወስ ነው። በነዚህና መሰል የጥቂት ሴረኞች ደባ የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወት በግፍ አልፏል።
በሃገራችን በዋናነት ብሄርና መልከአምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ባደረገው የክልል አደረጃጀት ክልሎች ቢከፋፈሉም እያንዳንዱ ዜጋ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብት አለው።
ይህ ደግሞ በህገመንግስቱ የተቀመጠ መብት ነው። በመሆኑም በየትኛውም መስፈርት ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩትና የጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ኢ-ህገመንግስታዊ ነው።
ከለውጡ ወዲህ በተደጋጋሚ የሚሰማው ይህ አካባቢ የኔ ነው፤ እከሌ የዚህ ተወላጅ አይደለም የሚሉ በሽታዎች ትልቅ ቀዶ ጥገና የሚፈልጉ የሃገራችን ክፉ በሽታዎች ናቸው። ከነዚህ በሽታዎች በስተጀርባ ያሉት ግን ጥቂት የግል ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ቁማርተኞች ናቸው። በአገራችን ከተከሰቱ ችግሮች ሁሉ በስተጀርባ የነዚህ ሴረኞች ፍላጎትና እጅ አለበት።
የነውጥ እሳቱንም የሚያቀጣጥሉት እነዚሁ ከኋላ ሆነው እሳት የሚለኩሱ ሴረኞች ናቸው። ነገር ግን እሳቱ ሲቀጣጠልና ሲነድ የሚያጠፋው በሰላም ለመኖር የሚጥረውን ደሃ የህብረተሰብ ክፍል ነው። አሁን እያየን ያለነውም ይህንኑ ነው።
ይህ ህዝብና ህዝብን የማጋጨት ሴራ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ያስተዋልነው አዲስ የጥፋትና አገርን የማፍረስ ስትራቴጂ ነው። የለውጡ አካሄድ ያላማረው የህወሃት ጁንታ አባት አገርን ለማፍረስ ይጠቅሙኛል ብሎ ከተከተላቸው መንገዶችም ይህኛው ዋነኛው አካሄድ ነው።
ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሰራበት እንደኖረ ይታወቃል። በተለይ በህዝቦች መካከል አንድነት እንዳይፈጠር በጀት መድቦ ጭምር የተለያዩ ትርክቶችን በማሰራጨት ለዘመናት አብረው የኖሩና እርስ በርስ የተዋለዱ ማህበረሰቦች አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከትና ከዚያም አልፎ ጥላቻ እንዲያሳድር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።
አሁን እዚህም እዚያም የሚከሰቱ በተለይ ብሄርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ዓላማ ኢትዮጵያ ወደብጥብጥና ሁከት እንድታመራና በመጨረሻም እንድትፈርስ ለማድረግ ታስቦ የሚካሄድ ነው።
ይህ ድርጊት ደግሞ በአንድ በኩል በውስጥ የሃገሪቱን ዜጎች በዚህ መልኩ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳና እርስ በርስ ወደመበላላት እንዲያመራ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ሀገሪቱን ከጎረቤት ሃገራት ጋር በማጋጨት አጣብቂኝ ውስጥ የመክተትና የማዳከም ሴራም ጭምር የያዘ ነው።
ሰሞኑን በሃገር ውስጥ ከተከሰቱት ጅምላ ጭፍጨፋዎች በተጨማሪ ለበርካታ ዘመናት በወንድማማችነትና በጥሩ ጉርብትና አብሮ ከኖረው የሱዳን ወንድም ህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሰራው ሴራም የዚሁ አካል ነው። ይህ ሲታይ እነዚህ ግጭቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ ሃይሎች የመጨረሻ አማራጫቸውን እየተጠቀሙ መሆኑን ያሳያል።
በተለይ የህወሓት ጁንታ ቡድን በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጽም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጨረሻው እርምጃ አድርጎ ነበር። ነገር ግን በ15 ቀናት ውስጥ ተንኮታኩቶ ወደቀ።
ይህ ቡድን በዚህ ሁኔታ ቢወድቅም በየቦታው ያደራጃቸውና የቀበራቸው የሴራ ፈንጂዎች ገና በአግባቡ አልተነቀሉምና አሁንም ግጭቶችን መስማታችን አልቀረም። ያም ሆኖ ግን አሁን ትልቁ ሰንኮፍ ተነቅሏል። ቀሪው የቤት ስራ ተንጠባጥበው የቀሩትን ማጽዳት ነው። እነዚህ ሃይሎች ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ጉዳት ማድረሳቸው አይቀሬ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ጁንታውን ለማስወገድ እንደተረባረበው ሁሉ እነዚህን በየቦታው የተጣሉ የጁንታው ፈንጂዎችን በማምከኑ ሂደትም የራሱን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባል። እነዚህ ሃይሎች ጥቂቶች ናቸው። በነሱ የሚመጣው ጦስ ግን ከባድና ሃገርን ለአደጋ የሚዳርግ ነው። ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ሲፈርስ ከሚከሰት ጥፋት ለመዳን ከወዲሁ ቆም ብሎ በማሰብ የጥፋት ሃይሎችን በንቃት ሊጠብቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013