አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህግን ተከትለው የሚሰሩ የሪል ስቴት አልሚዎችን እንደሚደግፍ ነገር ግን ህገወጥ የሆኑት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትናንት ከሪል ስቴት አልሚዎች በመከሩበት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ የሪልስቴት ዘርፉ የከተማውን የቤት ችግር ለመቅረፍ እንደ አጋዥ ፕሮጀክት የሚጠቅም መሆኑን ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ህግን ተከትለው የሚሰሩ የሪል እስቴት አልሚዎችን እንደሚደግፍ ነገር ግን ህገወጥ የሆኑት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድም አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም የሪልስቴት ባለቤቶች የሚጠበቅባቸውን የሊዝ እና ተያያዥ ክፍያዎች እንዲያጠናቅቁ፤ በተጨማሪም በአስቸኳይ በየክፍለ ከተማቸው በመገኘት የድርጅታቸውን ፋይል በህጋዊ መልኩ እንዲያደራጁ አሳስበው፤ ይህ ካልሆነ ግን በየቦታው ያሉ የሪልስቴት ቤቶች ባለቤት አልባ እንደሆኑ በመቁጠር የከተማ አስተዳደሩ እንደሚወርሳቸው አሳውቀዋል፡፡
በመጨረሻም ከዚህ ቀድም ከዘርፉ ጋር ተያይዞ ጉዳዮችን እንዲያጠና የተቋቋመው ግብረሃይል በጥቂት ጊዜ ውስጥ የቀሩ ሪልስቴቶችን እና በራሳቸው መሬት ገዝተው የሚያለሙ አልሚዎች ያሉበትን ህጋዊ አካሄድ ፣ የግንባታዎቹ ደረጃ እና ያለባቸውን ችግር እንዲፈትሽም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ከሪልስቴት አልሚ ኩባንያዎች በተደረገው ምክክር በዘርፉ የሚነሳውን የሊዝ ፣ የይዞታ እና መሬትን በህገወጥ መንገድ አጥረው ያስቀመጡትን ህጋዊነት እንዲፈትሽ ከዚህ ቀደም የተቋቋመው ከሁሉም የባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረሃይል ባቀረበው ሪፖርት እንደተመለከተው፤ በቦሌ፣ በየካ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፍተሻ ተደርጓል፡፡ ግብረ ሃይሉ ውጤቱን ትናንት ለባለድርሻ አካላት ሲያቀርብ ከተፈቀደለት ይዞታ በላይ አስፋፍቶ መያዝ፣ የሊዝ እና የቤት ግብር አለመክፈል፣ ግንባታ ጀምሮ ማቆም፣ ከተፈቀደለት አገልግሎት ውጪ መሬቱን መጠቀም፣ መሬትን ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ/መሸጥ እና የመሳሰሉት በሪልስቴት ዘርፉ የተስተዋለ ችግር መሆኑን አንስቷል፡፡
ግብረ ሃይሉ ባገኘው ውጤት ከ130 ሪል ስቴቶች ስድስት የሪል ስቴት ባለቤቶች የቤት ግብር እየከፈሉ ያሉ፣ ሃያ አንድ የሪል ስቴት ባለቤቶች መክፈል ጀምረው ያቋረጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ የ103 ሪል ስቴት ባለቤቶች ደግሞ ምንም አይነት ክፍያ ያልጀመሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የቤት ግብር የተረጋጋና አስተማማኝ በመሆኑ ከሌሎች የታክስ አይነቶች በተለየ መልኩ የማይለዋወጥና የማይሰወር ፣ ለቁጥጥር አመቺና ከታክስ ለመሸሽ የማይመች ሆኖ ሳለ በመረጃው እንደተረጋገጠው ከ4,433,468 ካ.ሜ ከተሰጠ ቦታ ላይ መሰብሰብ የሚገባው የቤት ግብር ገቢ ያልተሰበሰበ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ምንም እንኳን በአልሚዎቹ የተስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ቢሆኑም በከተማ አስተዳደሩም በኩል ምላሽ ሊያገኙ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ምላሽ ባለማግኘታቸው ችግሩ የአንድ ወገን ብቻ ያለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ለአብነትም የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አለሟሟላት፣ ከማስተር ፕላን ጋር የተያያዙ አዳዲስ ማሻሻያዎች መኖር፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ መጉላላት መኖሩ፣ የወሰን ማስከበር ችግሮችና የመረጃ አያያዝ ችግሮች ዋና ዋና ዎቹ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ኢያሱ መሰለ