በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
መንደርደሪያ፣
በአንድ የራዲዮ ጣቢያ በጎዳና ተዳዳሪዎች ህይወት ዙሪያ መሰናዶ እየቀረበ ነው። ኑሯቸውን ከጎዳና ያደረጉ ከታዳጊ እስከ ሽምግልና እድሜ ክልል ያሉትም ይናገራሉ። ፕሮግራሙ ትኩረትን የሚስብ ያደረጉ ገጠመኞችም አሉት። በትምህርታቸው የዘለቁ የሚባሉ ሰዎችም ኑሯቸውን ከጎዳና ካደረጉ ሰንብተዋል። የአብዛኛዎቹ ወደ ጎዳና መውጣት ምክንያቶች ውስጥ ቤተሰባዊ ምክንያት ሚዛኑ የደፋ ነው።
በቤተሰብ ውስጥ የሚሆኑ አያሌ ነገሮች መካከል አንድ ጉዳይ ብቻውን ህይወትን የማመሰቃቀል አቅም ያለው መሆኑን መሰናዶው ያስገነዝባል። ሁሉም የፈተና ምክንያት የሆኑት ቤተሰባዊ ጉዳዮች በአንድ መልህቅ እጦት መሆኑንም መረዳት ያስችላል። እርሱም ፍቅር! በተግባር መመንዘር ያልቻለ ፍቅር መጥፋት።
ቤተሰብ ማለት፣
ቤተሰብ ምን ማለት ነው የሚለውን ትርጉም ለመስጠት በዘርፉ ላይ የሚያጠኑ አጥኚዎች ቀጥተኛ ትርጉም ለመስጠት ብዙ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ። ተመሳሳይ ግብ ይዘው በመወለድም ሆነ በዝምድና በጋራ መኖር ለእኔ ትርጉሙ ቤተሰብ ነው። ቤተሰብን በአንድ ጀልባ ውስጥ በተሳፈሩ ሰዎችም እመስላለሁ።
ጉዞው ተጀምሮ መዳረሻው ላይ እስኪደርስ ድረስ በጀልባው ውስጥ አብሮ መሆን በብዙ ጥቅም የሚመነዘርበት ህይወት ነው ቤተሰብ። ከጀልባው አላግባብ ለመውጣት ሲሞከር አደጋ የሚከሰትበት ሁኔታን የሚፈጥር ወይንም ተጋላጭነትን የሚጨምርም ማለት ነው።
በቤተሰብ ጀልባ ውስጥ አባት እና እናት የጋራ እንዲሁም የተናጥል ሃላፊነት ይዘው ተሰይመዋል። አንዳንዴ እናት ሳትኖር አባት ብቻ ወይንም አባት ሳይኖር እናት ብቻ የምትቀዝፈው ቤተሰብም ሊሆን ይችላል፤ ጉድለቱ እንዳለ ሆኖ። አባት በአባትነቱ እናትም በእናትነቷ ተፈጥሮዊ ጸጋቸውን ተጠቅመው ውበትን የሚሰጡት ነው ቤተሰብ። ተፈጥሯዊው ጸጋ በተፈጥሯዊ ግዴታነት ሊታይም ይችላል።
እናት በተፈጥሯዊ ጸጋዋ አምጣ ትወልዳለች፤ አባት የቤተሰብ ዋና መጋቢነት ሃላፊነቱን እንዲሁ በተፈጥሯዊ ጸጋው ይወጣል። ሁለቱም ግዴታቸውን ተወጥተው ቤታቸውን ሲያቀኑ ጀልባይቱ መስመሯን ይዛ ወደ መዳረሻው በሰላም ለመድረስ ትፈጥናለች። በእርግጥ ወጀብ ይነሳ ይሆናል፤ ሆኖም ሁሉም ተሳፋሪዎች በአንድነት የቆሙ የጋራ ግብም ያላቸው ናቸውን ወጀቡን እየመከቱ መጓዝ ይቀጥላሉ።
ልጆችም ሆኑ ሌሎች የቤተሰብ አባላትም እንዲሁ የራሳቸውን ሃላፊነት ይወጣሉ። ልጆች አድገው የራሳቸውን ጀልባ መቅዘፍ ሲጀምሩ ከጀልባው ውስጥ ጀልባን ሰርተው ይቀጥላሉ። ጉዞው እንዲህ ይቀጥላል፤ ክቡሩ የሰው ልጅ የሚወለድበትም ሆነ የሚታነጽበት ተቋም ሆኖም ይዘልቃል።
ቤተሰብ ውስጥ እንደ አካልም (በአንድነት) እንዲሁም እንደ ግለሰብ (በተናጥል) ሁሉም የቤተሰብ አባል ሃላፊነት አለባቸው። የቤተሰብ ትርጉም በአካልነትና በተናጥል የሚተረጎም ታላቅ ተቋም መሆኑን መረዳት ይገባል። በፍቅር ውስጥ የሚያብብ ደግሞም የሚጸና ተቋም።
መልህቁ ፍቅር፣
የቤተሰብ መመስረቻ፣ ማደጊያ እንዲሁም መጽኛው ፍቅር ነው። ጠንካራ ፍቅር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ለህይወት ተግዳሮቶች እጅ መስጠት የሚታሰብ አይደለም። የቤተሰብ ጤንነት መታወክ መነሻውም ሆነ መድረሻው ፍቅር መሆኑን መረዳት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ አይጥልም። ፍቅር እንደ አንድ ረቂቅ ሃብትነቱ ረቂቅነቱን ተረድቶ ረቂቅ ሃብቶችን እንዴት መፍጠርም ሆነ ማሳደግ እንደሚገባ ማወቅ ይገባል።
በአንድ ወቅት ከዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ 50 አይሁዶች መካከል ስማቸው የሚገኝበት ራቢ ዴጂድ ዎልፕ በታይምስ መጽሔት ላይ እ.አ.አ በ2016 ፍቅርን በተሳሳተ መንገድ ተርጉመነዋል /We Are Defining Love the Wrong Way የሚል ጽሁፍ አስነብበዋል። በጽሁፋቸውም ፍቅርን ከስሜት ጋር ብቻ አገናኝቶ የመመልከትን ሰንካላ እይታ ተችተዋል።
ሁሉም የቃላት መፍቻዎች እስኪባል ድረስ ፍቅርን በስሜት/feeling/ መግለጻቸው ከተግባር የተፋታ ፍቅርን እውቅና ለመስጠት እድል ፈጥሯል ብለው ሞግተዋል። ሚስቱን እየደበደበ ይህን በፍቅር ስም የሚያቀርብ ሰውን ለመቀበል ምክንያት የሆነው ስሜት ተኮር የሆነው የተሳሳተ የፍቅር ትርጓሜ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ኮንነዋል።
ባለንበት ዘመን በቤተሰባዊ ህይወት ውስጥ ያለው ፍቅር ትርጉሙ እየጠበበ መጥቶ የአልጋ ላይ ጨዋታ አይነት ሆኖ እናገኘዋለን። ግብረስጋ ግንኙነት ከተፈጥሮ የተሰጠ ስጦታ በመሆኑ በጊዜውና በቦታው አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም።
ነገር ግን ወደ ቤተሰብ ጀልባ መወጣጫ የሚሆነው፣ በጀልባው ላይ በጋራ መቅዘፍ የሚያስችለው፣ አውሎ ንፋስ በመጣ ጊዜ አብሮ በጽናት መታገል የሚያስችለው፣ የነገ ተረኛ የጀልባው ቀዛፊዎችን በሚገባ ማስተማር የሚያስችለው ፍቅር ግን አንሶላ ከመጋፈፍ ባሻገር በተግባር የሚገለጠው ፍቅር ነው።
የቤተሰብ ህይወት መልህቁ ፍቅር ሆኖ ሳለ ለፍቅር የሚሰጠው የተንሸዋረረ ትርጉም መሰረት የለሽ ቤተሰብን ለመመስረት ምክንያት እየሆነ ቤተሰብን መመስረትም ሆነ ማፍረስ እቃቃ ጨዋታ እየመሰለው ይገኛል።
መልህቁ በሌለበት መርከቡ እንዴት ይታሰባል? መፍትሄው ቀላል ነው በእውነተኛ የፍቅርን ትርጉም በመተርጎም መነሳት። ቤተሰብ ንቃት በገባው ጊዜ እንደ ምልክት ከሚቀርቡ አታካች የምክንያት ድርደራ ባሻገር መልህቅ የሆነው የፍቅር ባላንስ ስንት ላይ እንደሚቆጥር ማንበብ መቻል አዋጭነት ይኖረዋል።
ያልተዘራ እንደማይታጨድ ከእዚህ ቀደም እንዳነሳነው ለቤተሰብ መጠንከር ምክንያት የሚሆን ፍቅርም እንዲሁ ካልተዘራበት ቦታ ሊበቅል እንደማይችል መረዳት ይገባናል።
ልተዘራ እንደማይታጨድ ከእዚህ ቀደም እንዳነሳነው ለቤተሰብ መጠንከር ምክንያት የሚሆን ፍቅርም እንዲሁ ካልተዘራበት ቦታ ሊበቅል እንደማይችል መረዳት ይገባናል።
ቤተሰብ ሲታመም፣
በማንኛውም ግለሰብም ይሁን ቤተሰብ በማንኛውም ጊዜም ሆነ ቦታ ፈተና ሊገጥም ይችላል። ሁልጊዜ በፈተና የተሞላች ምድር ውስጥ እንደምንኖር መረዳት ተገቢነት አለው። ቤተሰብም አንዱ ህመም የሚገጥመው ተቋም ነው። ይህ ታላቅ ተቋም ሲታመም ህመሙ እንዳይሰፋ ደግሞም ደጋግሞ እንዳያመረቅዝ መፍቻ ቁልፉን በሚገባ ማሰብ ይገባል።
የቤተሰብ ህመም መላ ቤተሰቡን የሚረብሽ የቤተሰብ አባላትም ስሜታዊ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ሊያደርግም የሚችል ነው። ስሜታዊ ውሳኔዎችም የህይወትን አቅጣጫ ፍጹም ቀይረው ባልታሰበ መንገድ ውስጥ መጓዝንም ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህ ሲሆን መፍትሄ ፍለጋው የሁሉም ሲሆን ባልና ሚስት ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።
መፍትሄ ፍለጋውም ለተፈጠረው ችግር እውቅና በመስጠት መጀመር የተሻለው ይሆናል። ቤተሰቡን ጤንነት እያወከ ያለ ጉዳይ በተፈጠረ ጊዜ አለባብሶ ለማለፍና ጉዳዩን ለማድበስበስ መሞከር ቤተሰቡን ያልተረጋጋ ቤተሰብ አድርጎ አለመረጋጋቱም ዘወትር ሆኖ ለልጆች የሥነ-ልቦና ቀውስ ምክንያት ይሆናል። ችግር ሲከሰት ችግሩን እንደ ችግር መቀበል ወደ መፍትሄ ለመድረስ በብዙ ያግዛል። ችግሩን መፍቻው ጉዞም በፍቅር ውስጥ መሆኑ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
በፍቅር ውስጥ መፍትሄ የማይገኝለት ችግር የለም ብሎ ማመን ለፍቅር ትልቅ ቦታን ወደ መስጠት ይጋብዛል። ፍቅር ውስጥ መፍትሄው አለ። ነገር ግን ፍቅር እንደ ረቂቅ-ሃብትነቱ ድንገት የሚገነባ አይደለም። ድንገትም የሚፈርስ አይደለም። የፍቅር አቅምን ይዞ የሚሄድ ቤተሰብ በፈተና ወቅት አውጥቶ የሚመነዝረው ሃብት አለው። የበደል ብዛት ሆኖ ቤተሰቡን ሊያጠፋው ሲል ፍቅር መልህቅ ሆኖ ሊያጸናው ይችላል።
ዶ/ር ብርያን ዝትዝማን የተሰኙ ተመራማሪ የቤተሰብ ችግሮችን እንዴት መፍታት ተገቢ እንደሆነ በጻፉት ጽሁፋቸው የሚከተሉትን ምክሮችን አስቀምጠዋል።
1. ለመነጋገር አመቺ የሆነን ከባቢ ሁኔታን መፍጠር፣
በጀልባዋ ውስጥ አብረው እየኖሩ ከመነጋገር መቆጠብ የብዙ ቤተሰቦች መገለጫ ነው። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እየኖሩ እርስ በርስ አለመተዋወቅ። በተለይም በቴክኖሎጂ ዘመን ሁሉም ሰው ከራሱ ጋርና ከሞባይሉ ጋር በሚሆንበት ሁኔታ ለመነጋገር አመቺ ሁኔታን የመፍጠር አቅም እየተዳከመ ያለ ይመስላል። ባልና ሚስት እንዲሁም መላው ቤተሰብ በተረጋጋና ቀልብን በሰበሰበ ሁኔታ መነጋገር የሚያስችል ድባብን መፍጠር ተገቢነት አለው።
በመደበኛነት ቤተሰብ የሚወያይበት ከባቢን የመፍጠር ባህል ጤናማ ቤተሰብ ለመገንባት ያግዛል። በተለይም በቤተሰብ ውስጥ ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ በተረበሸ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሳይሆን ለመነጋገር አመቺ የሆነ ድባብን በቅድሚያ በመፍጠር ለመነጋገር መሞከር ፍሬያማ ያደርጋል።
2. ችግሩን መቀበል መቻል፣
የቤተሰቡን ጤንነት የረበሸው ጉዳይ ላይ ጥፋተኛ የሚሆነው አካል ሃላፊነት መውሰድ መቻል ሌላው የመፍቻው ነጥብ ነው። የቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው ያለው የፍቅር አቅም ጠንካራ ከሆነ ጥፋተኝነቱን የሚቀበል የቤተሰብ አባልን ሌሎች የቤተሰብ አባላት የመቀበል እድላቸው ሰፊ ነው።
በማንኛውም ቦታ ላይ አንድ ሰው ጥፋተኛ ሆኖ እያለ፣ ጥፋተኝነቱንም እያወቀው እንዲሁ በዝምታ ከሚያልፍ ጥፋተኝነቱን ቢቀበል ወደ መፍትሄው እጅጉን እየቀረበ ነው።
3. የችግሩን ምንጭ ማግኘት፣
ዛሬ የቤተሰቡን ጤንነት የረበሸው ጉዳይ ነገም መደገም እንዳይችል ከምንጩ ማድረቅ መቻል ተገቢነት አለው። በመሆኑም የችግሩን ምንጭ በማግኘት የጀልባይቱ አባላት በሙሉ ችግሩን ከምንጩ በማድረቅ ውስጥ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ችግሩ ከምንጩ ማድረቅ ካልተቻለ እያመረቀዘ ቤተሰቡን የመረበሽ እድሉ ሰፊ ነው። ቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ሚና ያላቸው ባልና ሚስት ያደጉበት ባህል የተለያየ መሆኑ ወይንም ከተለያየ ቤተሰብ የመጡ በመሆናቸው ችግሩን ከምንጩ የማድረቅ ሂደት ቀላል ላይሆን ይችላል።
4. ቁጣንና ትዕቢትን አስወግዶ በግንኙነት ላይ ማተኮር፣
እውነትን ለመነጋገር ደግሞም ለመኖር ከሚያከብዱት ነገሮች መካከል ቁጣና ትዕቢት ናቸው። አዎንታዊ የሆነን ተግባቦት ለማድረግ አዳጋች ከሚያደርግ ቁጣ መታቀብ ያስፈልጋል። ቁጣ ተገቢነት ቢኖረውም ጸሃይ የገባው ቁጣ ከሆነ ግን ነገሮችን ባልተገባ አቅጣጫ እንድሄዱ ስለሚያደርግ ሊገራ ይገባዋል። ትዕቢትም እንዲሁ ነው። የቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው በደንብ የሚተዋወቁ እንደመሆናቸው ትዕቢት ቤተሰብ ውስጥ አደገኛ ዋጋን የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል።
5. ራስን ከጉዳት መጠበቅ
በቤተሰብ ውስጥ ስለ ቤተሰብ ጤንነት ሲባል ጉዳትን መቀበል በስፋት ይታያል፤ በተወሰነ ደረጃም ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፤ ምክንያቱም ዋጋ ሊከፍሉለት ስለተገባ ጉዳይ ሲባል ዋጋ መክፈል ለነገሩ የሰጠነውን ዋጋ የሚያሳይ ስለሆነ። እናቶች ስለ ልጆች ብለው ዋጋን በመክፈል በብዙም ይነሳሉ።
ይህ በሰፊው በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ የሚታይ እውነት ነው። በተቻለው መጠን የቤተሰብ ጤንነትን መጠበቅ አንድ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ራስን ከጉዳት መጠበቅ ደግሞ እንዲሁ ተገቢነት ይኖረዋል። ቤተሰብ ችግር ውስጥ ሲገባ የሚፈጠረው ወጀብ ስሜትን የመረበሽ ሰላምን የመንሳት ነገሮችን በፍጥነትና በአደገኛ አቅጣጫዎች እንዲሄዱ የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል። በእዚህ ውስጥ ራስን መጠበቅ መቻል በብርቱ ይመከራል።
ከእዚህ በላይ ከተጠቀሱት በቤተሰብ ውስጥ ችግር ሲፈጠር እንዴት ሊያዝ እንደሚገባው ምክሮች በላይ ከመነሻው መድረሻውን መተለም ዋና ሊሆን እንደሚገባ እንመክራለን።
ከመነሻው መድረሻውን፣
የቤተሰብ ጀልባን ወደ መመስረት የሚሄዱት ባልና ሚስት ከመነሻው መድረሻቸውን ማስመር አለባቸው። ጀልባውን አስነስቶ ደስ ወዳለው አቅጣጫ ሁሉ መሄድ ትርጉም የለውም፤ ለአደጋም ያጋልጣል። ቤተሰብ በሩቅ ምልከታ ውስጥ መመስረት አለበት። ይህ ራዕይ ነው። ራዕይ የሌለው ቤተሰብ አጥሩ ፈራርሶ መረን የመውጣት እድሉም ሰፊ ነው። አንሶላ ለመጋፈፍ ብቻ ወደ ቤተሰብ ጀልባ የወጣ ሃላፊነቱም ሆነ ስራው ከስሜት ውጭ ሆኖ አይታየም። በቤተሰብ ውስጥ የሚሰሩ የበረከቱ ሃላፊነቶች አሉ።
በቤተሰብ ውስጥ ሰውን የመሰለ ፍጡር ይወለዳል፣ ያድጋል ደግሞም ለቁምነገር ይበቃል። በቤተሰብ ውስጥ የቤተሰብ አባላት በህይወት ጉዟቸው ሁሉ ለሌሎች ትምህርት ይወሰዳል። በቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በልቡ ያለው ሠርቶት ሊያልፍ የሚፈልገውን ሰርቶ እንዲያልፍ ሁኔታዎች ይመቻቹለታል። በቤተሰብ አማካኝነት አንድ ሰው ከማህበረሰቡ ጋር ይገናኛል። በቤተሰብ ውስጥ ሌሎችም ብዙ ነገሮች።
ከመነሻው የቤተሰብ ቁልፍ ሃላፊነት ያለባቸው ባልና ሚስት መድረሻቸውን መተለም መቻል አለባቸው። የግል ግባቸው በቤተሰባዊ ግብ ውስጥ በሚገባ ተቀናጅቶ መፍሰስ እንዲችል ከጅማሬው መነጋገር አንዱ በሌላው ውስጥ ሃሳቡን ማስቀመጥ በውይይት መካከል የጋራ ትልምን መተለም ተገቢ ነው። ይህን ሳያደርጉ ቤተሰባዊ ህይወትን እንደ እስርቤት መቁጠር የራስን ስንፍና ያጋልጥ ይሆን እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም።
ቤተሰብ በፍቅር ላይ ተመስረቶ በፍቅር ውስጥ አብቦ በፍቅር ውስጥ የሚባዛ ታላቅ ተቋም ነው። ይህ ታላቅ ተቋም ጤናማ በሆነ ቁጥር አካባቢ፣ ከተማ፣ ሀገር እንዲሁም አለም ጤናማ ትሆናለች። የቤተሰብ ጤንነት የተናጋ በሆነ ጊዜ ግን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ገፈቱ ለሁሉም ሊደርስ ይችላል። ከመነሻው መድረሻውን መተለም ጤናማ ቤተሰብ ለመመስረትና ለመምራት ፍቱን መድሃኒት ነው። ከመነሻው መድረሻውን መተለሚያ መልህቅ ደግሞ – ፍቅር!
ማጠቃለያ
ቤተሰብን በቤተሰብ ህግ ለማቆም ከመሞከር በፍቅር መመስረት ተገቢነቱን እምነት በማድረግ፤ ከፍቅር በሚወጣ ሃላፊነትን በመሸከም ጀልባውን የሚቀዝፉቱ እንዲበረቱ እንመክራለን። በቤተሰብ ውስጥ ያለው ታላቅ ሃላፊነት ተመንዝሮ እንዲባዛ ፍቅር ቦታውን ይያዝ። በፍቅር ውስጥ ስሜት ብቻም ሳይሆን ሃላፊነትም አለና የቤተሰብ አባላት ሃላፊነታቸውን በመወጣት ፍቅርን በተገቢው ትርጉም በመተርጎም ለመልህቅነት እንጠቀምበት። ፍሬ ያለው ቤተሰብ ፍሬውን እንዲያበዛ፤ ፍሬ የጠፋበትም ወደ ፍሬ እንዲመጣ ፍቅር በመልህቅነቱ ስፍራውን ይያዝ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013