አዲስ አበባ፦ የአዋሽ ወልድያ ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ ያለው 270 ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ግንባታ 97 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተፈራ በተለይ አዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በምዕራፍ አንድ 97 በመቶ የተጠናቀቀው የባቡር መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለማግኘቱ ምክንያት ብቻ ወደ ሙከራ ለመግባት አልቻለም፡፡
ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ ያለው ይህ የባቡር መንገድ በ2012 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ግንባታው ሙሉ በሙሉ አልቋል ማለት በሚያስችል ደረጃ ተከናውኗል።
አቶ ደረጄ ባቡሩ የሚሰራው በኤሌክትሪክ ኃይል እንደመሆኑ ለኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የኃይል ጥያቄ ቀርቦ፤ የኃይል መስመሩን አቅርቦቱን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል። የኃይል አቅርቦት ጥያቄው እንደተመለሰም ሙከራ ተደርጎ አገልግሎት የመስጠት ስራውን ይጀምራልም ብለዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የሚገነባው ከኮምቦልቻ ወልድያ ሃራ ገበያ ያለው የባቡር ፕሮጀክትም 122 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት ግንባታው ከ65 በመቶ በላይ አፈፃጸም አለው። የሁለቱም ምዕራፍ የባቡር መንገድ ግንባታ በድምሩ 87 በመቶ ደርሷል። ሆኖም፤ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ስራውን የሚሰራው ከኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጋር በመተባበር እንደመሆኑ ግንባታው ቢጠናቀቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ካልቀረበ የባቡር መስመሩ አገልግሎት መስጠት እንደማይችል አቶ ደረጄ ተናገረዋል።
ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት በተጨማሪም መስመሩ በሚዘረጋባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ የፀጥታ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ምንም እንኳን የፀጥታ ችግሩ ፕሮጀክቱን በሚያስቆም ደረጃ የተፈጠረ ባይሆንም፤ አገሪቷ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት መንገድ እየዘጋ ስራውን አስተጓጉሏል። በመሆኑም እነዚህንና መሰል ችግሮችን ከመስተዳድሮቹ ጋር በመሆን ምክክር ተደርጎ መፍታት መቻሉን አቶ ደረጄ ተናግረዋል።
በሁለት ምዕራፍ የሚገነባውና 392 ኪሎ ሜትር የአዋሽ ወልድያ፤ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት የቅድመ ዝግጅት ስራው ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም ተጀምሮ፤ የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም በቀድሞው የኢፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋዩ በይፋ መቀመጡ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ፍሬህይወት አወቀ