ኢትዮጵያ እንድትፈርስ፣ ህዝቦቿም እንዲበታተኑ አጥብቀው የሚሰሩ ሀይሎች እንዳሉ ይታወቃል። የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና እድገት የማይፈልጉት እነዚህ ሀይሎች ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ሊኖሩ ይችላሉ።
እነዚህ የጠላት ሀይሎች በተለያየ ቦታ ልዩ ልዩ አጀንዳ በመቅረጽ ጭምር የሀገሪቱን ሰላምና ልማት፤ የህዝቦችንም ደህንነትና አንድነት በሚያናጋ መልኩ እየሰሩ ነው። ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሆነው የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስና የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ከውጪ ሀይሎች ጋር ጭምር ተልዕኮ ተቀብለው የሚሰሩ አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት ለሴራቸው ማካሄጃ፣ ለተልዕኮዋቸው ግብ መምቻ በዋናነት የሚጠቀሙት ጥቅመኛ የሀገር ውስጥ ተላላኪዎችን ነው።
ባለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው መንግስት በዋነኛነት ሲሰብክ የኖረው አንድነት ላይ ሳይሆን ልዩነት ላይ ነው። አንዱ ብሄር በሌላው ላይ እንዲነሳ፤ አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥላቻን እንዲያሳድር የሆነ ያልሆነ ትርክት በመፍጠር ዜጎች በጠላትነት እንዲተያዩና ጣት እንዲቀሳሰሩ ጭምር አስቦ ሲሰራ ቆይቷል። ይሄን በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ የተዳፈነን እሳተ ገሞራ ደግሞ ዛሬ በመቆስቆስ አሁን ለሴራው ማሳለጫ እየተጠቀመበት ይገኛል።
የሀገራችንን ሰላምና ልማት የማይፈልጉ፤ ሁልጊዜም ተረጂ ሆና እንድትኖር፣ የተፈጥሮ ሀብቷንም እንዳትጠቀም እና ያሰበችበት የዕድገት ደረጃ እንዳትደርስ በተለያየ ጊዜ ውጥኗን የሚያደናቅፉ፣ ብድርም ሆነ እርዳታ እንዳታገኝ ጥረት የሚያደርጉ የውጭ ሀይሎችም መኖራቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።
ህዝቧ በስደት፣ ሌላውም በሀገር ውስጥ በድህነት እንዲማቅቅ እና እንደትናንቱ የለጋሾችን እጅ እንዲያይ የሚሹ ሀይሎች ዛሬም በሀገር ውስጥ ሰላም ኖሯት አንድነቷ ተጠብቆ ልማቷን ወደፊት እንዳታስኬድ አቅደው እየሰሩ ናቸው። በሀገር ውስጥ ትንሽ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር በእሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ጭምር ይደግፋሉ፤ በየአቅጣጫው ያቀጣጥላሉ።
ሆኖም ግን ጀግናው መከላከያ ሰራዊት በግንባር፣ መላው ህዝብ ደግሞ የተለያየ የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ጦርነትን መክቶ የጠላትን ሴራ ሲያከሽፍ ቆይቷል። አሁንም የሚያጋጥመውን ለመመከት ብቁና ዝግጁ ነው።
ኢትዮጵያውያንን ሰላም ሊያሳጡና በከብቶች በረት እንደገባ አመለኛ በሬ ሊያምሱ የሚፈልጉ ጠላቶች በራሳቸው አልሳካ ሲላቸውና የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ሲያስታውሱ እርስ በራስ ለማጫረስ ተግተው ይሰራሉ። ይሄ ሴራቸው የነበረ ነው። አሁንም አለ፤ ወደፊትም አይኖርም ብሎ ማሰብ አይቻልም። ይሁን እንጂ ለእንዲህ አይነቱ አገር አፍራሽ ሴረኛ መድሀኒቱ አንድነትን ማጠናከር ብቻ ነው።
አንድነቱን ያጠናከረ ህዝብ ሶስት ዓመት የታቀደውን ጦርነት በሶስት ሳምንት ድል ማድረግ እንደሚቻል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረውን ህግ የማስከበር ጦርነት ማረጋገጥ ተችሏል። አሁንም በመተከል የተከሰተው የህዝብ ሞትና መፈናቀል ማቆም የሚቻለው አንድ መሆን ሲቻል፤ የሴረኛውን ሰንኮፍ በጋራ ከመሰረቱ መንቀልና ለውጪው ጠላትና ለሀገር ውስጡ ተላላኪ እጅ ባለመስጠት ብቻ ነው።
ለውጪው ሀይሉም ዋናው መድሀኒቱ ኢትዮጵያውያን እስከመጨረሻው የሰላም በሮችን ከፍተን ሁሉንም ነገር ለመፍታት መትጋት ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ አንድ ሆኖ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ብለው ተንኮል የሚሰሩ ሴረኞችን ነቅቶ መጠበቅና ሴራውን ማምከን ያስፈልጋል።
በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን ማጠናከር፤ በችግር ላይ ያሉትን መደገፍና የተፈናቀሉትን ማቋቋም ያስፈልጋል። ሀገርን የማፍረስ የውስጣዊና የውጪ ሀይል ፍላጎትን ማምከንና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ የምንችለው እኛው ነን። ለዚህ ደግሞ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል። የታቀደልንን ሴራ ማምከን የምንችለው በተፈጠረልን አጀንዳ ላይ እየፈሰስን ሳይሆን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ጠንክረን በአንድነት ስንከላከል ነው!።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013