ከፓዊ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ በ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ዲጋ ግድብ በፓዊ ከተማ እና በቀጣና 1 መንደር 7 መካከል ይገኛል፡፡ በ1982 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለት ግድቡ 100 ሜትር ወርድና 12 ሜትር ቁመት አለው፡፡ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመስኖ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፤ በውስጡ መንገድ ተሰርቶለት ከግድቡ ማዶና ማዶ ያሉትን ቀበሌዎች ያገናኛል፡፡ የበርካታ ቀበሌዎች ነዋሪዎችም ወደ ፓዊ ከተማ ለተለያዩ አገልግሎቶች ለመምጣት ይህንን መንገድ ይጠቀማሉ፡፡
ግድቡ በመሰንጠቁ ውሃ እያሰረገ ሲሆን በግድቡ ውስጥ ለውስጥ የተሰራው መንገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት የአካበቢው ነዋሪዎች ለአላስፈላጊ ወጪና ድካም እየተዳረጉ ሲሆን፤አንድ ቀን የከፋ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋትም አድሮባቸዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ወርቅዬ ሀምዛ እንደሚናገሩት፤ ለረጅም ጊዜ በግድቡ ውስጥ ባለው መተላለፊያ ሲጠቀሙ ኖረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግድቡ በመሰንጠቁ በእግረኞቹ መንገድ ላይ ውሃ እያሰረገ ነው፡፡ በዚህም ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ ውሃ እያሰረጉ ያሉ ስንጥቆች ከእለት ወደ እለት እየሰፋ ሲሆን በእግረኞች መንገድ ላይ የሚገባው ውሃ መጠን ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ አስቸኳይ ጥገና የማይደረግ ከሆነ ግድቡ በእግረኞች መንገድ ላይ ሊደረመስ ይችላል፡፡ አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች መንገዱን መጠቀም ካቆሙ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን የእግረኞች መንገድ አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኑን ያላወቁ አንዳንድ መንገደኞች ግን አሁንም በዚሁ መንገድ ይሸጋገራሉ፡፡ በአጋጣሚ ግድቡ ቢደረመስ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡
ግድቡ ተደርምሶ ጉዳት እንዳያስከትል መፍትሄ መፈለግ አለበት ያሉት አቶ ወርቅዬ፤ ግድቡ ጥገና የሚደረግለት ከሆነ ጥገና ተደርጎለት ህዝቡ እንዲጠቀምበት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ጥገና የማይደረግ ከሆነም ሰው ወደዚያ አካባቢ እንዳይሄድ መንገዱ መዘጋት አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በፓዊ ወረዳ በቀጣና አንድ መንደር 104 ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳዬ ኢሳ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ለብዙ ዓመታት ከፓዊ ከተማ ወደ ገጠር ቀበሌዎች ለመሄድና ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ወረዳው ለመመለስ በዲጋ ግድብ ውስጥ ባለው መንገድ የአካባቢው ህዝብ ይጠቀም ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት ወዲህ ግን ግድቡ ላይ የደረሰው አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ መተላለፍ አልተቻለም፡፡ የግድቡ ግድግዳ እየፈረሰ ነው፡፡ ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ ውሃው ውስጡን እየሞላው ነው፡፡ ውሃ እያሰረገ ከመሆኑም ባሻገር፤ ወደ መተላለፊያ መንገዱ የሚያስገቡ እና የሚያስወጡ መወጣጫ መሰላሎች አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ በውስጡ ተገጥመው የነበሩ ፓውዛ መብራቶችም ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡
በግድቡ ውስጥ ባለው መተላለፊያ መንገድ ለመሻገር ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ይፈጅ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ካሳዬ፤ በግድቡ ውስጥ ባለው መንገድ ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ ግን ከግድቡ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላኛው አቅጣጫ ለመሻገር እስከ ሦስት ሰዓት የሚፈጅ መንገድ ለመጓዝ እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶች በፓዊ ከተማ እቃ ለመግዛት የያዙትን ገንዘብ ለባጃጅ ከፍለው ለመመላለስም ግድ ሆኖባቸዋል የሚሉት አቶ ካሳዬ ነዋሪው ለአላስፈላጊ ወጪ ብሎም ለጊዜና ጉልበት ብክነት እየተዳረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በቅርብ ርቀት ያለችውን ፓዊ ከተማ ትተው ማንቡክ የሚባል ሩቅ ከተማ ሄደው መገበያየት ግድ አንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡
የፓዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ አሰፋ እንደሚያስረዱት፤ ዲጋ ግድብ ለአካባቢው የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ቢሆንም እንክብካቤ ስላልተደረገለት አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ የአካባቢው ህዝብም ችግሩን በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሲያነሳው ቆይቷል፡፡ 2009 ዓ.ም የህዝቡን ጥያቄዎች በማሰባሰብ ወረዳው ለዞን፣ ለክልልና ለፌዴራል መንግሥት አሳውቋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት መድረክ ላይም ይህ ችግር በህዝቡ ተነስቷል፡፡ ህዝቡ ችግሮች ተቀርፈውለት ግድቡን እንደ አንድ የትራንስፖርት አውታር የመጠቀምና ሌሎች አገልግሎቶችን የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ግድቡ ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ ያላወቁ ሰዎች አሁንም በመንገዱ እየተሸጋገሩ ነው ቢሉም፤ አቶ ብርሃኑ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም፡፡ ሰዎች በውስጡ እንዳያልፉ መከልከሉን ይናገራሉ፡፡
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ታደሰ እንደሚያብራሩት ከሆነ፤ ግድቡ ላይ የተለያዩ ጉዳቶች በመድረሱ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡ የተቋረጡ አገልግሎቶችም አሉ፡፡ የትራንስፖርት አውታርነት አገልግሎት ከተቋረጡት አገልግሎቶች መካከል ለአብነት ተጠቃሽ ነው፡፡ እንክብካቤ አለመደረጉ በግድቡ ላይ ለተፈጠሩ ችግሮች ምክንያቶች ናቸው፡፡ በተለይም የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በአካባቢው ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዲመላለሱ መደረጉ የእግረኞች መተላለፊያ ላይ ጉዳት እንዲደርስ መንስኤ ሆኗል፡፡ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው እንዳይመላለሱ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በግድቡ ላይ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ክልሉ ከአማራ ውሃ ስራዎች ጋር በመሆን የኤክስፐርቶች ቡድን ተዋቅሮ ጥናት እያደረገ ነው፡፡ ጥናቱ ግድቡ ያሉበትን ችግሮች በአጠቃላይ ለማወቅ ብሎም ግድቡ ሙሉ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችልበትን ሁኔታዎችን ለማፈላለግ የሚረዳ ነው፡፡
ጥናቱ ለሦስት ወራት የሚካሄድ ሲሆን፤ ጥናቱ ግድቡ ላይ ያሉ አጠቃላይ ችግሮችን፤ ችግሮቹ የሚፈታበትን አቅጣጫ እንዲሁም ከማን ምን እንደሚጠበቅ ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ግርማ፤ ለጥናቱ የሦስት ሚሊዮን ብር የውል ስምምነት መደረሱን አንስተዋል፡፡ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገራዊ ጨረታ ወጥቶ የጥገና ስራው ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለሙሉ የእድሳት ስራው 250 ሚሊዮን ብር አካባቢ ይፈጃል ተብሎ ይገመታል ብለዋል፡፡
ግድቡ ተደርምሶ በሰውና ንብረት ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ የሚደረግ መሯሯጥ ፋይዳ ስለማይኖረው፤ ግድቡ ተደርምሶ በህዝብና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት የተጀመረው ጥናት በአፋጣኝ ተጠናቆ የግድቡ እድሳት ሥራ እንዲጀመር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
መላኩ ኤሮሴ