ከገብረክርስቶስ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
በዚሁ የሕግ ዓምዳችን ላይ “ጋብቻ የሚፈርስባቸው ምክንያቶች” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ከረዥም ጊዜ በፊት አንድ ጽሁፍ አቅርበንላችሁ ነበር።
በዚያ ጽሁፍ በአገራችን በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሰረት ጋብቻ የሚፈርስባቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር መዳሰሳችን አይዘነጋም።
አያይዘን ታዲያ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 20938 ሚያዝያ 11 ቀን 1999 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ተጋቢዎች ተለያይተው ለረዥም ጊዜ የሚኖሩ ከሆነ ፍቺ እንደፈጸሙ እንደሚቆጠር በሰጠው ውሳኔ ዙሪያም ማብራሪያ አቅርበን ነበር።
ይሁንና ይህ ውሳኔ ሕገ-መንግሥታዊነቱ አጠያያቂ በመሆኑ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ ላለፉት 14 ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ሲያከራክር ከቆየ በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰበር ውሳኔው ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ነው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።
እኛም ይህንኑ መሰረት በማድረግ የግንዛቤ ስንቅ ቋጥረንላችኋል።
ጋብቻ የሚፈርስባቸውን መንገዶች በወፍ በረር
ጠቅለል ባለ አነጋገር ጋብቻ በሁለት መልኩ ነው የሚፈርሰው – ሕግ በሚያስቀምጣቸው ምክንያቶች እና በባልና ሚስቱ ምክንያት።
ከተጋቢዎቹ የአንዱ መሞት ወይም በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ መሰጠቱ ጋብቻ የሚፈርስበት አንዱ ሕጋዊ ምክንያት ነው። ባል ወይም ሚስት በህይወት ከሌለ/ች አብሮ መኖር የሚባለው ጉዳይ በመሰረቱ ስለማይኖር ጋብቻ በህግ ይፈርሳል ማለት ነው።
በሌላ በኩል ባል ወይም ሚስት ጠፍቶ/ታ ወሬው/ዋ ለሁለት ዓመታት ያልተሰማ እንደሆነ ማንኛውም ሰው ቢሆን የመጥፋት ውሳኔ በፍርድ ቤት እንዲሰጥበትያስደርጋል።
በዚሁ መነሻ ፍርድ ቤቱ የመጥፋት ውሳኔውን በሰጠበት ቀን ጋብቻው እንደሚፈርስ ስለ ሰዎች የተመለከተው የፍትሐብሔር ሕጋችን ይደንግጋል።
የመጥፋት ውሳኔ የተሰጠበት ተጋቢ ተመልሶ ቢመጣ እንኳን ቀደም ሲል የነበረውና በመጥፋቱ ምክንያት የፈረሰው ጋብቻ ተመልሶ በመምጣቱ ምክንያት ዳግም ነፍስ አይዘራም።
ለጋብቻ መፍረስ ሕጉ ራሱ ከሚያስቀምጣቸው ከሞትና ከመጥፋት ምክንያቶች በተጨማሪ ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ከተጣሰም ለጋብቻ መፍረስ ምክንያት ይሆናል።
ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነጻና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሳይሰጡ ወደ ትዳር ውስጥ ገብተው ከሆነ፤ 18 ዓመት ሳይሞላቸው የተጋቡ ከሆነ፤ ተጋቢዎቹ ወላጆችና ተወላጆች አልያም እህትና ወንድም ወይም አክስት አጎት ከሆኑ ጋብቻውን ህጉ ራሱ ፈራሽ ነው ይለዋል።
ከእነዚህ የህግ ምክንያቶች ሌላ ራሳቸው ተጋቢዎቹ በሚወስዱት እርምጃ ጋብቻ ሊፈርስ ይችላል። ይኸውም ፍቺ መፈጸም ነው።
አንድም ባልና ሚስት ጋብቻቸውን ለማፍረስ ሊስማሙ ይችላሉ፤ አልያም በተናጠል ጋብቻቸውን በፍቺ ማፍረስ ይችላሉ። ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑ ይህንኑ ለፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔያቸው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ እንዲሁም ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ካመለከቱ ጋብቻ ይፈርሳል።
በባልና ሚስት የጋራ ስምምነት ከሚቀርብ የፍቺ ጥያቄ በተጨማሪ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት በመሆን ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ካመለከቱ ጋብቻ ይፈርሳል።
አወዛጋቢው የሰበር ውሳኔ
በ1999 ዓ.ም. በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ሰበር ሰሚ ችሎት በተቋጨው የክርክር ዶሴ ወይዘሮ ሣራ ልንጋነ ከአቶ ይልማ ወልደ ሐና ጋር በ1966 ዓ.ም. ይጋባሉ። ይሁንና በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ባልና ሚስት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ ሚስት በ1977 ዓ.ም. ሌላ ትዳር ይመሰርታሉ።
አቶ ይልማም በበኩላቸው በ1987 ዓ.ም. ከወይዘሮ ሸዋዬ ተሰማ ጋር ጋብቻ ይፈጽማሉ። የኋላ ኋላ አቶ ይልማ ይሞታሉ። በመጨረሻም ሁለቱ ወይዛዝርት እኔ ነኝ ሚስት እኔ ነኝ ሚስት በመባባል ሙግት ገጥመው ጉዳያቸው እስከ ፌደራሉ ሰበር ችሎት ይደርሳል።
ሰበር ችሎቱም በቀደመው ትዳር ወይዘሮ ሣራ እና አቶ ይልማ ምንም እንኳ የቀደመ ጋብቻ ቢኖራቸውም ባለመግባባታቸው ከተለያዩ በኋላ በየፊናቸው የየራሳቸውን ሕይወት መጀመራቸውን በማውሳት ጋብቻቸው እንደፈረሰ ይቆጠራል የሚል አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል።
እርግጥ ነው ጋብቻው በሞት፣ በመጥፋት ወይም በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ ፈርሷል ባይባልም ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የመተጋገዝ፣ የመደጋገፍና የመከባበር እንዲሁም አብሮ የመኖር ግዴታን የሚጥል ሆኖ ሳለ ባልና ሚስቱ በተለያየ ምክንያት ተለያይተው ለረዥም ጊዜ መኖራቸው ጋብቻውን እንደሚያፈርሰው ተደርጎ መወሰዱ ተገቢ ሊመስል ይችላል።
ይሁንና ይህ ውሳኔ ገዥ ሆኖ በአገሪቱ መላው ፍርድ ቤቶች አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሆኖ በቆየባቸው ባለፉት በርካታ ዓመታት አንድም በሕጉ ከተመለከቱት የጋብቻ መፍረስ ሁኔታዎች ውጭ በችሎቱ የተጨመረ ምክንያት በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሴቶች በጋብቻ ውስጥ ሊያገኙ የሚገባቸውን የንብረት መብት በእጅጉ የሚጎዳ ነው በሚል የውዝግብ ምክንያት ሆኖ ኖሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ታሪካዊ ውሳኔ
ይህንን የሰበር ውሳኔ ተከትሎ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በርካታ አቤቱታዎች ሲቀርቡለት ነበር።
በዚሁ መነሻም ከቀረቡት አቤቱታዎች ውስጥ አንዱን በመውሰድ የሰበር ውሳኔው ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው የሚል ውሳኔ እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ምክር ቤቱም ውሳኔውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ሲል ወስኗል።
በሕገ-መንግስቱ መሰረት የፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሕግን መተርጎም ሲሆን፤ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠ ነው።
በፓርላማው በወጣው የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ መሰረት ጋብቻ የሚፈርሰው በሕጉ በተቀመጡት ምክንያቶች (በሞት፣ በመጥፋት እና ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ አለመሟላት) እንዲሁም በተጋቢዎቹ በራሳቸው (በስምምነት ወይም በተናጠል ፍቺ) ብቻ ነው።
ይሁንና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት ጋብቻን ለማፍረስ ከተቀመጡት ከእነዚህ ምክንያቶች ውጭ ተጨማሪ ምክንያት (የተጋቢዎቹን ለረዥም ጊዜ ተለያይቶ መኖር) በማስቀመጥ ነው ፍቺን የፈቀደው።
ይህ ደግሞ ተገቢነት ያለው የሕግ አተረጓጎም ማስቀመጥ ሳይሆን በሕጉ ከተቀመጡት ምክንያቶች ውጭ የሆነ ሌላ ምክንያት ማስቀመጥ በመሆኑ ሕግ እንደማውጣት ይቆጠራል ማለት ነው። ሕግ ማውጣት ደግሞ የፓርላማ ሥልጣን እንጂ የፍርድ ቤት ሥልጣን አይደለም።
በዚሁ መነሻ ነው እንግዲህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እጅግ ዘግይቶም ቢሆን የሰበር ውሳኔው በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 55 ሥር ለሕግ አውጭው አካል የተሰጠውን ሕግ የማውጣት ሥልጣን በሚጋፋ መልኩ የተወሰነ ነው በማለት ከእንግዲህ በኋላ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተደርጎ በመላ አገሪቱ ፍርድ ቤቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ውሳኔን ያሳለፈው ማለት ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013