መርድ ክፍሉ
ከአገራችን የሕዝብ ብዛት አኳያ ከግማሽ የማያንሰው ቁጥር በወጣት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው። ወጣቶች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል።
ወጣቶች በአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እምቅ የሥራ ኃይልና ጉልህ ድርሻ አላቸው። በዚህም በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ ካላቸው ሚና አንፃር ተጠቃሚነታቸውም ማደግ አለበት።
እንደ ዩኒሴፍ ሪፖርት በአፍሪካ አህጉር ከሚኖረው አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 65 በመቶ የሚሆነው ዕድሜው ከ35 ዓመት በታች ነው። በሀገራችንም የወጣቱ ብዛት ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከግማሽ በላይ እንደሚደርስ ይገመታል።
በመሆኑም ከሕዝብ ብዛት መጨመር ጋር ተያይዞ አገራት ከራሳቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ጋር ሊጣጣም የሚችልና የወጣቶችን ችግር የሚፈታ ፖሊሲ ቀርፀው ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፤ እስካሁንም ከ120 በላይ የሚሆኑ አገራት የወጣቶች ፖሊሲን ተግብረዋል።
ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን በ1996 ዓ.ም ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ በአገር አቀፍ ደረጃ በማዘጋጀት ወጣቶች እየተገነባ ባለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና በሚካሄደው ፈጣንና ዘላቂ ልማት በላቀ ደረጃ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከየአኗኗር ዘይቤያቸው ጋር የሚጣጣም ፕሮግራም ማዕቀፍ በማዘጋጀት የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጣቶች የልማት ፓኬጆች ተቀርጸው ተግባራዊ ተደርገዋል።
መንግሥት በቀጣይ አስር ዓመት አገሪቱ ትመራበታለች ያለውን እቅድ አዘጋጅቷል። በእቅዱ ውስጥ የወጣት ተጠቃሚነትና ውክልና እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጧል። በእቅዱ ዙሪያ በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ ወጣቱን በምን ዓይነት መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧል?
አቶ ማቲያስ፡- በአስር ዓመት እቅድ ውስጥ ወጣቱን በተመለከተ ሦስት ዋና ዋና መስኮች ተዘጋጅተዋል። የመጀመሪያ የወጣቱን መብት ማስከበር ነው። ሁለተኛው የወጣቱ ተሳትፎና ውክልና ማስጠበቅ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ የወጣቱ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። በመስኮቹም ውስጥ ብዙ ዝርዝር ተግባራት ይገኛሉ።
የወጣቱን መብት ማስከበር ሲባል ወጣቶች ተፈጥሯዊ መብቶቻቸውና ተፈጥሯዊ ያልሆኑ መብቶቻቸው እንዲጠበቁና እንዲከበሩ የማድረግ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የማስከበር፣ ከአደጋና ከስጋት ነፃ የመሆን እና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ሥራን ያካትታል።
የወጣቱ ተሳትፎና ውክልና ማስጠበቅ ሲባል በሁሉም መስኮች ያልተገደበ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። የወጣቱን ተሳትፎ ስንመለከት በዋናነት ውክልና ሲባል በሦስቱ ምክር ቤቶች ማለትም በሕግ አውጪ፣ በሕግ ተርጓሚና በሕግ አስፈፃሚ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የማሳደግ እንዲሁም ወደ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ የማድረግ ነው።
በችግር አፈታት እንዲሁም በሕይወት ክህሎት ስልጠና ማዳበር ውስጥ ተሳትፏቸውን የሚያሳድጉበት እና የበጎ ፈቃደኝነት ተሳትፏቸውን የሚያጎለብቱበት ነው። በተጨማሪም በወጣት ማዕከላት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ፣ የትምህርትና የጤና ተሳትፎ የማሳደግ ሥራዎች ለመስራት እቅድ ተይዟል።
በወጣቱ ተጠቃሚነት ላይ ደግሞ ወጣቱ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ታስቧል። በአሁኑ ወቅት የወጣቱ ቁጥር እየጨመረ ስለሚገኝ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እንዲሁም ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በስፋት ለመስራት እቅድ ተይዟል።
በሥራ ፈጠራና ከሥራ አጥነት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመቅረፍ የሥራ ክህሎትን ለማሳደግና ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሥራዎችን ለመስራት ታቅዷል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በልዩ ሁኔታ የሚከናወኑ ተግባራት የሚኖሩ ሲሆን የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አገር አቀፍ የወጣቶች ፖሊሲን ለመከለስ ታስቧል። ፖሊሲው ለአስራ ስድስት ዓመታት እያገለገለ የሚገኝ የሕግ ማዕቀፍ ነው። ፖሊሲውን ለማሻሻል ሥራዎች ተጀምረዋል።
ፖሊሲው ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለማስተካከል ይሰራል። ከዚህ ውጪ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ነፃ አደረጃጀት ለመፍጠር የታሰበ ሲሆን አደረጃጀቱ ከፖለቲካም ሆነ ከመንግሥት ጋር ንክኪ የሌለው ነው። አደረጃጀቱ በወጣቶች የሚመራና የሚተዳደር ሲሆን ነፃ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች የሚያቅፍ ነው። አደረጃጀቱ እንዲመሰረት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን አደረጃጀቱ ወደ ተግባር ሲገባ ወጣቶች የልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋል።
የወጣት ማዕከላትን የማደስና ዘመናዊ የማድረግ እንዲሁም የማህበራዊ ሥራ ፈጠራ ዕድሎች የማመቻቸት ሥራዎች ታስበዋል። ሞዴል የአፍሪካ ወጣት ማዕከላትን በአገሪቱ የመገንባትና ወጣቶች ርስበርስ የሚገናኙበት መድረክ በማጠናከር የኢትዮጵያ ወጣቶች ከአፍሪካ አገራት ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ይደረጋል።
ከትምህርት ጥራትና ከወጣቶች የሥራ ልምምድ ጋር በተያያዘ ኢንተርን ሽፕ እና አፓረንት ሽፕ መርሃ ግብሮችን ለማስጀመር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከሌሎች አጋራት ጋር በመተባበር የወጣቶችን የሥራና ሙያዊ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉ ሥራዎችን እንዲከናውኑ ይደረጋል።
እንዲሁም የማማከር ሥራዎችና የሕይወት ክህሎት ስልጠና የሚያገኙበት ማዕከል ለመገንት በተጨማሪም የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት እንዲገነቡ የማድረግ ሥራ ይሰራል። የበጎ ፈቃድ ባህልን የማሳደግ ሥራ በልዩ ሁኔታ እቅድ ተይዞ እየተሰራም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአስር ዓመቱ እቅድ ሲዘጋጅ መነሻ ሁኔታዎቹ ምን ነበሩ?
አቶ ማቲያስ፡- እቅዱ ሲዘጋጅ መነሻዎቹ ብዙ ነበሩ። የመጀመሪያው ያለፉት ዓመታት እቅዶች ውስጥ የነበሩ ክፍተቶች፣ ጥንካሬዎችና መሰራት የነበረባቸው ሥራዎች ናቸው። ሁለተኛው የየዓመቱ የልማት ግቦች ናቸው።
የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተርና የተለያዩ ፕሮግሞችና አጀንዳዎች አሉ። በአህጉር ደረጃና በአገር ደረጃ የተቀመጡት ግቦች ሌላው መነሻ ነበሩ። ከዚህ ውጪ እየጨመረ የመጣው የወጣቶች ቁጥርና የወጣቶች ፍላጎት ለእቅዱ እንደመነሻ ጥቅም ላይ ውሏል። በሌላ በኩል የወጣቱ አቅምና ብቃትም እንደመነሻ ጥቅም ላይ ውለው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የወጣቱ የፖለቲካ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ በቀጣይ አስር ዓመት እቅዱ ምን ለመስራት ታስቧል?
አቶ ማቲያስ፡– ወጣቱ በፖለቲካ መስኮች ላይ ተሳታፊና አመራር ቦታዎች ላይ እንዲቀመጥ ግብ ተጥሎ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። በሕግ አውጪ፣ በሕግ ተርጓሚና በሕግ አስፈፃሚ ቦታዎች ላይ የሚኖርን ድርሻ ለማሳደግ ታስቧል። ነገር ግን ይህ ሥራ ለብቻ የሚከናወን አይደለም። ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ በመሆን የወጣቱን ተሳታፊነት ለማሳደግ ይሰራል።
በአገሪቱ አሁን ካለው የወጣቱ የፖለቲካ ተሳትፎ በጣም አነስተኛ ነው። በተለይ በመንግሥት የአስተዳደር እርከኖች ላይ በሕግ አውጪና ተርጓሚ ላይ ያለውን የወጣቶች ተሳትፎ ለማሳደግና ብዙ ወጣቶች ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ይሰራል። የወጣቶች የአመራር ክህሎት የሚያሳድጉ ስልጠናዎች በስፋት ይሰጣሉ። የአፍሪካ ወጣቶች ማዕከል ሲገነባ የወጣት አመራሮች መፍለቂያ እንደሚሆን ይታሰባል።
አዲስ ዘመን፡- በየጊዜው እየተከናወነ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ ሥራ ወጣቱን ምን ያክል ተሳታፊ እያደረገ ይገኛል?
አቶ ማቲያስ፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ አለ። ብዙ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር እየተሳተፉ ሲሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ እንዲመጣ አድርገዋል። በዚህ ዓመት የነበረውን ብንመለከት አስራ ስድስት ሚሊዮን ወጣቶች በአስራ ሦስት የአገልግሎት መስኮች ላይ በመሳተፍ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳን ችለዋል። ይህ ሰፊ ማህበራዊ አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል በእቅድ ውስጥ ተካቶ እየተሰራ ይገኛል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ትልቁ ነገር ይህ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት አገር አቀፍ የበጎ ፈቃደኝነት ፖሊሲ ተቀርፆ ይጠናቀቃል ተብሎ ታስቧል። በፖሊሲው በጎፈቃደኞችን የሚያበረታቱና ዋስትና የሚሰጡ ተግባራት ይካተትበታል።
አዲስ ዘመን፡- የወጣት ማዕከላት እድሳት ምን የተለየ ነገር ይዟል? ቀድሞ የነበረውስ ምን ችግሮች ነበሩበት?
አቶ ማቲያስ፡– ወጣት ማዕከላት የወጣት ሥነ ምግባር መገንቢያ ማዕከላት ናቸው። ወጣቶች አካልና አዕምሮ ለመገንባት በነዚህ ማዕከላት እንዲያሳልፉና ካልባሌ ቦታዎች እንዲርቁ ለማድረግ ታስቦ ነበር የተገነቡት። ነገር ግን በተግባር የታየው ወጣት ማዕከላት ለወጣቱ ምቹ ያሆኑበት ሁኔታ አለ።
በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ወጣቶች፣ ለሴቶችና ለታዳጊ ወጣቶች ምቹ አልነበረም። አብዛኛዎቹ የሚገኙት በቀበሌ ግቢ ውስጥ ሲሆኑ የተቀሩት ራቅ ያሉ ቦታዎች ላይ ነው። ማዕከላቱ በበቂ ቁሳቁሶች ያልተሟሉበት ሁኔታም አለ። ይዞታቸውም ምቹና ሥርዓት የያዘ አይደለም።
ስለዚህ በአስር ዓመቱ እቅድ ከተካተቱት ውስጥ አንዱ በመሆኑ ማዕከላቱን ምቹ እንዲሆኑ አድርጎ ማደስና ለወጣቶች ምቹና ተስማሚ የማድረግ ሥራ ይሰራል። ማዕከላቱ ወጣቶች አዕምሯቸውን ብቻ የሚያዝናኑበትና ጊዜ የሚያሳልፉበት ብቻ ሳይሆን የሥራ ፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትና የሚማሩበት በተለይ ደግሞ የማህበራዊ ሥራ ፈጠራ ማለትም ለማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ በዚያውም የሥራ ፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ሁኔታም ይፈጠራል።
በነዚህ ሥራዎች ላይ ጥናቶች የተጠኑ ሲሆን የሌሎች አገራት ተሞክሮ ተወስዶ ሰፋ ያለና ለሁሉም ወጣቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል። ሁሉም ወጣቶች በፍላጎት በማዕከላቱ የሥራ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ሁኔታም ይመቻቻል።
አዲስ ዘመን፡- የወጣቱ ወደ ውጭ መሰደድ ጋር በተያያዘ በአስር ዓመቱ እቅድ ውስጥ በዚህ ዙሪያ ምን ለመስራት ታስቧል?
አቶ ማቲያስ፡– ከወጣቶችን ስደት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት በአስር ዓመቱ እቅድ ተይዞ ለመስራት ታስቧል። የመጀመሪያው ለመስራት የታሰበው በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የሥራ አማራጮች ወጣቶች እንዲያውቁትና ወደ ሥራ መስኩ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው።
ወጣቶች በስደት ካሉበት አገር ከሚያገኙት ያልተናነሰ አንዳንዴም የተሻለ የሥራ ዕድሎችና አማራጮች መፍጠር ታስቧል። በአገር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ መሰናክሎችን በማስወገድ ወጣቱ በማንኛውም የሥራ መስክ እንዲሰማራ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በእቅድ ውስጥ ተካተዋል።
ሌላው የችግሩ መንስኤ ተብሎ በተቀመጡ የመውጫና የመግቢያ በሮች አካባቢ በመሄድ ከወጣቱ፣ ከማህበረሰቡና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመቀናጀት የስደት አስከፊነትና በአገር ሰርቶ መለወጥ ክብር መሆኑን የማስተማር እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሥራቸው ውስጥ ስለ ስደት አስከፊነት መልዕክት እንዲያስተላልፉ የማድረግ ሥራዎችም ታስበዋል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች አሻፈረኝ ብለው ወደ ስደት የሄዱ ወጣቶች በስደት ካሉበት ቦታ የሚመለሱበት ሁኔታ ተመቻችቶ የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና ከስደት ተመልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታዎች ለመስራት በዋናነት በእቅድ ውስጥ ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን፡- የወጣት ፖሊሲው ላይ የሚደረገው ማሻሻያ ምን ምን ጉዳዮች ላይ ነው? ማሻሻያው ለምን አስፈለገ?
አቶ ማትያስ፡– የወጣቶች ፖሊሲው ምን ለውጥ አመጣ ከሚለው አንፃር ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። ፖሊሲው ተግባር ላይ ከዋለ አስራ ስድስት ዓመት ሆኖታል። በአስራ ስድስት ዓመት ቆይታው ምን ውጤት አመጣ እና ያለው ጠንካራና ደካማ ጎኑ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው። የፖሊሲው መሻሻሎች በጥናት ከተለየ በኋላ የጥናቱ ግኝት ፖሊሲው ይከለስ ወይስ ባለበት ይቆይ የሚለው የሚወሰን ይሆናል። ጥናቱ በአማካሪ ድርጅቶች እገዛ እየተሰራ ነው።
ፖሊሲው ምን ውጤት አመጣ፣ ያሉት ደካማ ጎኖችና የነበሩ ክፍተቶች ምንድናቸው የሚለውን በሦስቱ መስኮች ማለትም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስክ ፖሊሲው ተግባራዊ ሲሆን በወጣቶች ሕይወት ላይ ምን ለውጥ አመጣ የሚለውን እየተጠና ይገኛል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013