‹‹እንደራሴ ማለት በድሮ ጊዜ ወይንም ስልጣኔ የሚባለውን እሳቤ ከመቀበላችን በፊት ሀገሩን ወክሎ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚዘዋወር ሰው እንደራሴ ይባል ነበር። አሁን ላይ አምባሳደር በመባል በተለያዩ ሀገራት እንደሚሾሙት ማለት ነው።›› በማለት ስያሜውን ያብራራል። ወጣት ኒቆዲሞስ የሺጥላ፡፡
ወጣት ኒቆዲሞስ የእንደራሴ የወጣቶች ማኅበር ጠቅላይ ጸሀፊ ነው። ማኅበሩም በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች እና በሚሳተፍባቸው መድረኮች የወጣቶች እንደራሴ ወይንም አምባሳደር መሆንን ዓላማው አድርጎ እየሰራ ይገኛል። ይህ የወጣቶች ማኅበር ዓላማው ለወጣቶች የተለያዩ እድሎችን በመስጠት ማብቃት ዓላማው ያደረገ መሆኑን ወጣት ኒቆዲሞስ ይገልጻል ።
እንደራሴ የወጣቶች ማኅበር ከተመሰረተ ሶስት ዓመት ያክል ጊዜን አስቆጥሯል። የሲቪል ማኅበረሰብ ምዝገባ ፍቃድ ያገኘው ይህ የወጣቶች ማኅበር የተመሰረተው በአንድ ወጣት አማካኝነት ነው። የማኅበሩ መስራች ወጣት ብሩክ አስቻለው ዓላማ እና ሀሳብ የሚጋሩ በርካታ ወጣቶች በአባልነት እና በበጎፍቃደኝነት ማኅበሩን በመቀላቀል ማኅበሩ በሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት ላይ በማሳተፍ ላይ ይገኛል።
ወጣቶችን በተለያየ መንገድ ለማብቃት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ያላቸውን እውቀት በልምድ እንዲያዳብሩ የስራ እድሎችን በመስጠት ወጣቶች ላይ ይሰራል። ‹‹ ሲመሰረት በአንድ ሰው የተመሰረተ ቢሆንም ዓላማው ጠንካራ ስለነበር ሌሎች በዚህ ዓላማ የምናምን ወጣቶችን ስቦን በጋራ እየሰራን እንገናኛለን። ›› ሲል ወጣት ኒቆዲሞስ ማኅበሩ ለወጣቶች የሚሰጣቸውን ጥቅሞች ያስረዳል ።
‹‹ እንደራሴ በዋናነት ሶስት ዓላማ አለው። አንደኛው ለወጣቱ ዓላማ መስጠት ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው። ሁለተኛው ዓላማቸውን ግባቸውን እንዲያሳኩ የተለያዩ እድሎችን መስጠት ስልጠናዎችን ማዘጋጀት፣ ሶስተኛው ከራሳቸው አልፈው ማኅበረሰባቸውን እና ሀገራቸውን የሚረዱ ወጣቶች ማድረግ ነው። ››
ወጣቶችን በማብቃት እና እድል በመስጠት ወጣቶች ባላቸው እውቀት የተሻለ እንዲሆኑ የሚሰራው ይህ ማኅበር አፍሪካ ወጣቶች ፎረም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲካሄድ አስችሏል። ‹‹ የአፍሪካ የወጣቶች ፎረም አኅጉር አቀፍ ነው። እንደአኅጉርም በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።›› የሚለው ጠቅላይ ጸሀፊው በቀጣይም በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀሳቦች እና መድረኮች እንደሚቀጥል ጠቁሟል ።
የአፍሪካ ወጣቶች ፎረም በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ ‹‹ በአፍሪካ ሰለብሬትስ›› ወይንም አፍሪካ ታከብራለች በተሰኘው የባሕል፤ የፋሽን እና የቢዝነስ ሳምንት ውስጥ ነው። በዚህ ሁነት ውስጥ የአፍሪካ ወጣቶች ፎረም ራሱን ችሎ ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው ነበር። የእንደራሴ ወጣቶች ማኅበር ይህንን እድል ለማግኘት እና ፎረሙን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ትልቅ ጥረት ማድረጉን ጠቅሷል።
‹‹ እንደራሴ በወጣቶች የሚመራ እና ወጣቶች ላይ የሚሰራ ድርጅት ነው። ›› በማለት የሚገልጸው የማኅበሩ ጠቅላይ ጸሀፊ እንደራሴ በዙሪያው ያሉ የተለያዩ ወጣቶችን ለማብቃት በሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ ከተለያዩ ሀገር ውስጥ ከሚገኙ የወጣት ማኅበራት እና ቡድኖች ጋር እንዲሁም በአኅጉረ አፍሪካ የሚገኙ ትልልቅ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚጠቀሙበትን እድል ለመፍጠር የሚሰራቸው ስራዎች ለዚህ ፎረም አዘጋጅነት እንዲመረጥ አድርገውታል ።
‹‹ ወጣቶች ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ መፍትሄ ናቸው ብለን ነው የምናምነው። አኅጉራችን ባሏት የወጣቶች ቁጥር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። ተፈጥሯዊ ሀብት፣ የሰው ኃይል ኖሮን ነገር ግን እድገት ማምጣት ያልቻልነው ወጣቱን መጠቀም ስላልቻልን ነው። ›› ይህንን የወጣት ቁጥር ወደ ሀብት በመቀየር ለአፍሪካ ወደፊት መራመድ ምክንያት መሆን የማኅበሩ ዓላማ ነው ።
የዘንድሮው ዓመት ‹‹አፍሪካ ታከብራለች ›› ክንውን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥ ተካሂዷል። ክንውኑ ለሶስት ቀናት የቆየ ሲሆን ለሶስት ቀን የቆየ የፋሽን ኤግዚቢሽን፣ የባሕል ምሽት እንዲሁም በአፍሪካ ወጣቶች ፎረም አልፏል። እ.አ.አ 2024 ከሕዳር ስድስት እስከ ስምንት ለሶስት ቀናት በቆየው የአፍሪካ ታከብራለች ክንውን ውስጥ በመካተት የአፍሪካ ወጣቶች ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ችሏል ፡፡
‹‹ አፍሪካን ሰለብሬትስ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ይዘጋጃል። የወጣቶች ፎረምን አካቶ ሲዘጋጅ ግን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው። ›› በማለት የሚያብራራው ጸሀፊው ይህንን ለማሳካት ማኅበሩ በሀገር ውስጥ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ ከሚገኙ ወጣት ማኅበራት ጋር የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች፣ የልምድ ልውውጦች ፎረሙን ለማዘጋጀት እንዲመረጥ ምክንያት እንደሆነው አስታውሷል።
የአፍሪካ ታከብራለች ክንውን ዋና ዓላማውም የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ በአፍሪካ የበለጸገ የጥበብ፣ የባህል፣ የቅርስ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስተዋወቅ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ውህደት በማበረታታት የአፍሪካን በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ማክበር ነው።
በአፍሪካ ወጣቶች ፎረም ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች ተሳትፈዋል። በስራ ላይ የሚገኙ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወጣቶች በፎረሙ ላይ ተሳትፈዋል። በፎረሙ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ቋሚ መቀመጫ እንደሚገባት ተነስቷል።
በፎረሙ ላይ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ልምዳቸውን አጋርተዋል። ተሳታፊ ከነበሩ ወጣቶች ጋር እንዲሁ የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴን እና ትምህርት በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ምን ይመስላል በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተዘጋጅቷል። ስለ ስራ ፈጠራ፣ ወጣቶች በቢዝነስ ዙሪያ ሊኖራቸው ስለሚገባ እውቀት፣ በቢዝነስ ዓለም ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች እና መፍትሄዎች በውይይት ላይ የተነሱ ሀሳቦች ናቸው።
ወጣቶች አሁን ዓለም እያስተናገደች ባለችው ፈጣን ለውጥ ውስጥ አብረው መጓዝ የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸው በመድረኩ ላይ ተገልፇል። ራሳቸውን በእውቀት ማብቃት፣ ከቀለም እውቀት ባሻገር ባህሪያቸው፣ ከሌሎች ጋር በጥምረት የመስራት፣ የስራ – ስነምግር፣ ከሰዎች ጋር የመግባባት፣ ያላቸውን አቅም የመግለጽ የስነ-ተግባቦት ክህሎቶቻቸው ላይ መስራት እንደሚገባቸው በፓናል ውይይቱ ላይ ተነስቷል።
በአፍሪካ ያሉ ሀገራት ምንም እንኳን የተለያዩ ቢሆኑም ተመሳሳይ የሆነ ችግርን እንደሚያስተናግዱ በመድረኩ ላይ ተነስቷል። የፓን አፍሪካን እሳቤን በማምጣት በአፍሪካ የሚገኙ ወጣቶች በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ የራሳቸው የሆነ ራዕይ ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ። የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚችሉ ተጠቁሟል። ወደ ስራ ፈጠራ የሚገቡ ወጣቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ምቹ ስነ-ምሕዳር መፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ መሆኑም በፓናሉ ላይ ከተነሱ የመፍትሄ ሀሳቦች ውስጥ ነው።
በዚህ ክንውን ውስጥ የተካሄደው በፓናል ውይይት ላይ ልምዱን ለማጋራት የተገኘው የሀሁ ጆብስ የስራፈጣሪ ኦፕሬሽናል ዳይሬክተር ናትናኤል ታምራት የአፍሪካ ወጣቶች ፎረም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጊቢ ውስጥ በትልቁ የአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ መካሄዱ ለየት እንደሚያደርገውም ገልፇል። ወጣቶችን ያሳተፈው የአፍሪካ ወጣቶች ፎረም እንደ አኅጉርም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም በሚሰጠው እና ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጥር 29 ቀን 1953 ዓ.ም ለአፍሪካውያን ሕዝብ የወደፊት እድገት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መርቀው በከፈቱት የአፍሪካ አዳራሽ መካሄዱ ለየት ያደርገዋል። ‹‹ ወጣቶች ስራ ፈጠራ ላይ እና ቢዝነስ ተኮር የሆኑ እንደዚህ አይነት መድረኮችን ማግኘታቸው በጣም ጥሩ እድል ነው። ›› ሲልም ናትናኤል አክሏል።
የእንደራሴ የወጣቶች ማኅበር የተመሰረተው በአዲስ አበባ ውስጥ ቢሆንም ሌሎች በየሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በማሳተፍ ምን ስራዎችን እየሰራ ነው ብለን ጥያቄ አቅርበንለታል። ‹‹ በማኅበራችን ውስጥ በርካታ በጎፍቃደኞችን እናሳትፋለን በዚህም በአካልም ባንሄድ በሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ የሚገኙ ወጣቶች የተለያዩ ወጣቶች የሚገናኙባቸውን መድረኮች ፈጥረው ይሰራሉ። ››
ማኅበሩ ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ ለወጣቶች በተለያዩ ርዕሶች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ይሰጣል። ከዩኔስኮ ጋር በነበረው የሁለት ዓመት ስምምነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብ ስልጠና እንዲሰጥ አድርጓል። ‹‹ እርግጥ ነው አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ወጣቶችን ማግኘት ችለናል። የዚህ ዓመት እቅዳችንም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች ጋር መድረስ እንፈልጋለን። ›› የኒቆዲሞስ ሀሳብ ነው።
ወጣት ኒቆዲሞስ ያጠናው Global studies and International Relations) የእንደራሴ ወጣት ማኅበር ለመቀላቀል አስቀድሞ ስለማኅበሩ ይሰማው የነበረ መረጃ ቀርቦ አባል እንዲሆን አድርጎታል። ‹‹መጀመሪያ እንደራሴን ስቀላቀል የኮሙኒኬሽን ባለሙያ በመሆን ማኅበሩን ለማገልገል ነበር ። ›› በማለት ጊዜውን የሚያስታውሰው ወጣት ኒቆዲሞስ ማኅበሩ የሚሰራበት ዓላማ እና በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ሚና አድጎ በቋሚነት ማኅበሩን በመቀላቀል አሁን እየሰራበት ወደሚገኘው የጠቅላይ ጸሀፊ ስራ ላይ ይገኛል ። በማኅበሩ ውስጥ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ገደብ የሌለው ሲሆን በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በፖለቲካ ሳይንስ እና የኮምፒውተር ሳይንስ እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ወጣቶች ይገኙበታል።
ወጣቶች በተለያየ መንገድ ማኅበሩን በበጎፍቃደኛነት የሚቀላቀሉ ሲሆን፤ በበጎፍቃደኝነት ለተሳተፉ አባላት የተለያዩ በማኅበሩ በኩል የሚመጡ እድሎችን ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እድል ይሰጣል። ‹‹ በእንደራሴ በኩል ከበርካታ ተቋማት ጋር የመስራት እድል አለን። እነዚህ ተቋማት ሰራተኞችን አሰልጥነው መቅጠር ፈልገው ወደ እኛ ሲመጡ በማኅበራችን የበጎፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎችን ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡››
ከተመሰረተ ሶስት ዓመት የሆነው የእንደራሴ የወጣቶች ማኅበር ወደፊት በሀገር ውስጥ የተመሰረተ ዓለምአቀፍ ተቋም በማድረግ ከአፍሪካ ውጪ በመስራት ወጣቶችን ማገናኘት በእቅዶቹ ውስጥ የተያዘ ነው።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም