ፎቶ ጋዜጠኛ እዮብ ተፈሪ ሜቴክ ካቋቋማቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ በሆነው በኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስምንት ዓመት ከዘጠኝ ወር ገደማ ሰርቷል። ከግማሽ በላይ የሆነው ስራው በኦዲዮቪዥዋል ላይ ያተኮረ ነው።
ቀጥሎም በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የሰራ ሲሆን፣ በገባ በስድስተኛው ወር መስሪያ ቤቱ ሲፈርስ ደግሞ ወደ ብሮድካስት ባለስልጣን ተመድቦ ከዛም ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዝውውር በመምጣት እየሰራ ያለ ነው። ወደ 12 ዓመት ገደማ በሙያው መስራቱን ይናገራል።
በኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ሲሰራ በነበረበት ወቅት በፎቶ ባለሙያነትም ጭምር ቢሰራም ለአምስት ተከታታይ ጊዜ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ቦንድን የገዛ ሆኖ ሳለ አንዴም እንኳ ግድቡን የማየት እድል ሳይመቻችለት መቅረቱን በቁጭት ይናገራል።
ምክንያቱም አለቆቹ ለሙያው ግንዛቤ ስለሌላቸው እነርሱ ወደስፍራው በሚያቀኑበት ወቅት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ነበር ፎቶ አንስተው ከሱ ተጠቀም ሲሉት የነበረው። አሁን ግን ወደትክክለኛው ቦታ መጥቻለሁ ማለት እችላለሁ ይላል።
መንግስት በቅርቡ የጁንታው ታጣቂ ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ያለውን ሁነት እንዲዘግቡ ወደስፍራው ከላካቸው የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል እዮብ ተፈሪ አንዱ ነውና በግንባር ያጋጠሙትን ሁነቶች እንዲያጋራን ጠየቅነው።
አዲስ ዘመን፡- የጁንታው ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ወደ ህግ ማስከበሩ እንደሚገባ በተነገረህ ወቅት እንደ አንድ ዜጋ ምን ተሰማህ?
እዮብ፡– እውነት ለመናገር ቀደም ሲል መንግስት ሲሄድ የነበረበት መንገድ ህዝቡን ትዕግስት አሳጥቶት ነበር። የሰሜን እዝ በመጠቃቱና የአገር መከላከያ ሰራዊት ህልውና ጥያቄ ውስጥ ከገባ በኋላ መንግስት ወደ ህግ ማስከበሩ በመግባቱ ተደስቻለሁ። በተገቢው ሰዓት የተወሰደ ትክክለኛ ርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ። እንዲህም ስል በተፈጠረው ነገር በጣም ማዘኔን እየገለጽኩ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሚዲያ ባለሙያ ደግሞ በወቅቱ ወደ ስፍራው ሄደህ ትዘግባለህ ስትባል ምን አይነት ስሜት አደረብህ?
እዮብ፡– ሁለት አይነት ስሜት ነው የተሰማኝ። የቤተሰብ ኃላፊ እንደመሆኔ ጉዳዩ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አሳስቦኝ ነበር። ምክንያቱም ወደጦርነት ነው የምሄደው፤ ጦርነት ደግሞ ድምጹ የአድናቆት ጭብጨባ አይደለም። የመሳሪያ ጩኸት ነው የሚደመጠው። ጠንከር ካለ ደግሞ ጉዳዩ ከዛም የሚያልፍ ነው። በቅጽበታዊ ነገር ምን ሊፈጥር እንደሚችል ሳስብ ስጋት ብጤ ውስጤን ጫር ማድረጉን መሸሸግ አልፈልግም።
ሌላው ስሜቴ ደግሞ በጉዳዩ መሳተፍ እንድችል መደረጌ ደስተኛ አድርጎኛል። እንደነገርኩሽ ኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ለዘጠኝ ዓመት ነው ስሰራ የነበረውና በኢንዱስትሪውም ውስጥ የነበረውን የጁንታውን ቡድን ሴራ ጠንቅቄ የማውቅ ነኝ። የጁንታውን አካሄድን በኢንዱስትሪው ቆይታዬ ስለማውቅ የእነርሱን ምዕራፍ ለመዝጋት በሚያስችለው ሂደት ላይ በመሳተፌ ደስተኛ ነበርኩ።
የጁንታው ቡድን የሚታወቀው አንዱን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር አጋጭተው እገዛና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በማለት ገንዘብ በመሰብሰብ ወደኪሱ ለማስገባት ተወዳዳሪ የሌለው በመሆንም ጭምር ነው። በሶማሌ እና በኦሮሚያ መካከል ግጭት ተፈጠረ ድጋፍ ያሻቸዋል ይባልና ገንዘብ ይሰበሰባል፤ የት እንደሚገባ ግን አይታወቅም።
እንዲሁም ቆሼ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ በዚህ በዚህ ምክንያት ጉዳት ደረሰበት ይባልና ገንዘብ ይሰበሰባል፤ ግን ተጎጂው ሲጠቀም አይታይም፤ ገንዘቡ የት እንደሚደርስም አይታወቅም።
ከዚህ ሌላ ለህዝብ ያላቸው ንቀት ወደር የለውም። አንዴ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ቀደም ሲል እሰራ ወደነበረው ኢንዱስትሪ መጥተው ሲያወያዩ ተወያዩን ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ሲጋራቸውን እያጨሱ ነበር። ሲጋራ እያጤሱ ቀረጻ ማካሄዱ ስለከበደኝ በቅርብ ላሉ ኮሎኔል አለቃዬ ብንግራቸው ዝም ብለህ ስራህን ስራ ነበር ያሉኝ። ከዚያም ሚሞሪውን ነበር አለቃዬ የተቀበለኝ። እነዚህ ነገሮች ያበሳጩኝ ስለነበር የእነርሱን የውድቀት መጨረሻ ማየትን እጅግ እናፍቅ ስለነበር ወደስፍራ በማቅናቴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ።
አዲስ ዘመን፡- በቆይታህ ያስተዋልከው ጉዳይና ስሜትህን የተጫነ እንዲሁም ያስደሰትህ ነገር ካለ ብትገልጽልን?
እዮብ፡– ብዙ የሚያሳዝን ነገር እንዳለ መደበቅ አልፈልግም። ጽንፈኛው ቡድን መውደቃቸው እየታወቀ ምነው ወደህሊናቸው ተሰብስበው ከዚህ ውርደትና ሞት ራሳቸውን ቢያድኑ ስል መቆጨቴ አይቀርም። በዚህ ህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ የህይወት መጥፋት፣ የጊዜ እንዲሁም የንብረት ውድመት ሁሉ አለ። ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ባልተከፈለና ለልማት ቢውል ስልም አስባለሁ።
እብሪታቸውና ትምክህታቸው ምን ቦታ ላይ እንደጣላቸው ባየሁ ጊዜ ብዙ መልካም ነገር እንዲያደርጉ ተለምነው አሻፈረኝ በማለት የደረሰባቸው ስለሆነ ስለነሱ አዝናለሁ። በእነሱ ወገን የተጎዳውንና የሞተውን ሁሉ ሳይ መቋቋም አቅቶኝ ነበር። ሰው ከመቅስፈት ከህይወት ወደሞት ሲለወጥ ማየቱ ለእኔ ከባድ ነበር። እንደ አልባሌ ነገር የሰውን ልጅ ክንብል ብሎ በማየቴ ከባድ ነበር።
ካስደሰተኝ መካከል ለምሳሌ ጩቤ በር፣ ዋጃ፣ አላማጣ የሚባል ቦታ እስኪደረስ ድረስ ሰው ደስተኛ ነበር፤ እኔ የነበርኩበት ራያ ግንባር መነሻው ጩቤ በር ነው። የህግ ማስከበር ሂደቱ በዋናነት የተጀመረው ተክላይ በር በሚባል አካባቢ ነው።
ከጩቤ በር በኋላ ዋጃ፣ አላማጣ እየተለቀቀ ወደ ተክላይ በር ተገባ። በየቦታው ሲደረስ የሰው ደስታ በጣም ከፍ ያለ ነበር። ምክንያቱም ጁንታው የሰው መልክ ያለው ቢሆንም ሰው ሳይሆን አረመኔ ነበር ሲሉ ነበርና ደስታቸውን በማየቴ ደስ ሲለኝ ነበር።
ሞሆኒ ላይ እኛ ከሞት ተረፍን የሚያስብለንን አጋጣሚ አሳልፈናል። እኛ ካለንበት 25 ያህል ሜትር ርቅት ላይ ከአንድም ሁለት ሶስቴ መድፍ ወደቀ። እኛን ባይነካንም ንጹኃን ዜጎች ላይ ግን ጉዳት አደረሰ። እኛ የነበርንበት ተሽከርካሪ ውስጥ አቅጣጫውን የሚያመላክት ባለሙያ ስለነበር ከዚህ በኋላ መኪናዋ በእይታ ውስጥ ስለሆነች በፍጥነት እንውጣ አለ፤ ይህን እያለ ባለበት ወቅት መድፍ በመጣሉ የተወሰነ ፍንጣሪ ያገኘው ወታደር ነበር። እኔ መኪና በ200 የፍጥነት ወሰን ሲነዳ አይቼ አላውቅም፤ ያኔ ግን ፍጥነቱን በአግባቡ አጣጣምኩት። ያኔ በትክክል የጦር ሜዳ ላይ መሰለፌን አረጋገጥኩ።
ይህን ሁሉ ካሳለፍን በኋላ አበርገሌ የሚባል ቦታ ተከዜ አካባቢ ያለው የጁንታው ታጣቂ ሰራዊታችንን እዛ ቦታ አይሄዱም ብሎ አስቧል። አካባቢው ድንጋያማ ከመሆኑም በላይ እጅግ አስቸጋሪ ነው። የሚገርመው የከባድ መሳሪያ ጥይቶች ያሉት እዛ አካባቢ ነው። ለመከላከያ ሰራዊታችን ምስጋና ይግባውና እዛ አካባቢ ሱር ኮንስትራክሽን የቆፈረላቸው ረጅሙ ዋሻ የጁንታው መቀበሪያቸው መሆን ቻለ። መከላከያችን ምንም ችግር ሳይደርስበት መሳሪያዎቹን ሁሉ ድል አደረገ።
በአካባቢው የነበሩት ተሽከርካሪዎች ሳር ሁሉ በቅሎባቸው የአካባቢው በቀል ዛፍ መስለዋል። በወቅቱ የነበሩት ሻለቃ እንዳሉትም የበቀሉ አትክልት ነው የሚመሱለት። እነዚያ ተሽከርካሪዎች ሁሉ መሳሪያዎችን እንደጫኑ ነበር የቆሙትና እነዚህ ገቢ በመደረጋቸው ደስተኛ ነኝ።
ጁንታው ካለው የመሳሪያ ብዛትና አካባቢውን ቀድሞ እንደሚመቸው አድርጎ ከመያዙ የተነሳ መከላከያ ሰራዊት ምንም ሊያመጣ አይችልም ሲል አስቦ የነበረ ቢሆንም ባልጠበቀው ቅጽበት ውጊያው ራሱኑ መልሶ አጥቅቶት ድል በመደረጉ በጣም ደስተኛ ነኝ። መከላከያ ሰራዊቱ አገሩን ለማስከበር ያደረገው እንቅስቃሴ የሚያኮራ ነው። ድል በማድረግም መቀሌን መቆጣጠር በመቻላችን በጣም አስደስቶኛል።
መነሻችን ቆቦ ነበር፤ መቀሌ ስንደርስ ብዙ ውጣ ውረድ አልፈን ነው። ብዙ ጊዜም ስንንቀሳቀስ የነበረው ያለአጃቢ ነው። በወቅቱ በግንባር የቆየሁት ለ40 ያህል ቀናት ሲሆን፣ ያለውን ነገር በመዘገብ ሽፋን ለመስጠት ሞክረናል ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ በግንባሩ የተገኘነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽ ነን።
ሌሎች ከቀናት በኋላ ተቀላቅለውናል። እንዲያም ሆኖ የመተባበር መንፈሱ ነበር። ከዚህ ውጭ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም ነበሩ። ለምሳሌ አልጀዚራ ከዘገበው ነገር የታዘብኩት ነገር ቢኖር በአሉታዊ ጎኑ ያነሳው ጉዳይ ተጠቃሽ ነው። ከዚህ ባሻገር ያነሳሁትን ምስል ስጠን የሚል ልመናም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በግንባር ባለህበት ወቅት የተለያዩ ፎቶዎችን በማንሳት ለህትመት መብቃቱ ይታወቃልና የትኛው ምስል ነበር ቀልብህን የገዛው?
እዮብ፡- የዚያን ያህል አስደሳች ነው የምለው ነገር የለም፤ ምክንያት ብትይኝ ደግሞ ብዙዎቹ እንባቸውን ሲያዘሩ ነው የሚስተዋለውና ነው። በሰራዊቱም ዘንድ ቢሆን በጁንታው ቡድን በደረሰው ጥቃት ውስጡ የተጎዳ በመሆኑ ፊቱ ላይ የሚነበበው ቁጭትና ወኔ ነው።
በእርግጥ ከቀን ወደቀን እውነት ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆኗና ድል እየተቀዳጀ ወደፊት መገስገሱን በካሜራዬ እያሰቀረሁ ወደመገባደጃው በመድረሴና በድል መጠናቀቅ መቻሉ ሁሌም የሚያኮራኝና የሚያስደስተኝ ጉዳይ ነው። የዚህንም ሂደት ምስል በካሜራዬ ማስቀረት በመቻሌ እድለኛ ነኝ ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ ነው።
የሰራዊቱን እውነተኛ ውሎና ስሜት በማንሳት ከየዕለቱ ዜና ጋር ለህትመት እንዲበቃ መደረጉን ሳይም ደስ እሰኝበታለሁ። በተለይ ካነሳኋቸው ፎቶዎች መካከል የወታደሮች ሚስቶች ከሆኑት የትግራይ ተወላጆች መካከል አንዷ በጁንታው በደረሰባት ግፍ ለስደት ከቤቷ ወጥታ ልጇን እያጠባች ባለችበት ወቅት በካሜራዬ ያስቀረሁትን ፎቶ ብቻ በማየት ትክክለኛውን ስሜት ማንበብ የሚያስችል ነው ብዬ የማስበው ምስል ነው።
ለሰዎች የስቃይ ምንጭ የሆነው የጁንታው ቡድን ሲሆን፣ ለዚህም ትምክህተኝነቱና እብሪቱ ብሎም ትክክለኛ የሆነ የአሰራር ስርዓት ማጣቱ ነው ለብዙዎች ሰቀቀን ሆኖ ያለፈው። አሁንም ያ ነገር ዳግም እንዳይመጣ ማረጋገጫ ሊሆን የሚችለው የትኛውም በስልጣን ላይ ያለ አካል ከዚህ አይነት እብሪትና ሞገደኝነት ሊጸዳ የሚችለው ካልተገባ አስተሳሰብ መላቀቅ ሲችል ነው።
ህግ ማስከበሩ ምንም እንኳ በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል መጠናቀቅ ቢችልም በሂደቱ ኪሳራ አለ። ይህ ኪሳራ እንዳይኖር ክፉውን ሐሳብ ከወዲሁ እየገደሉ መሄድ መልካምም ተመራጭም ነው እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጠኸን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ
እዮብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013