አስቴር ኤልያስ
የፎቶ ጋዜጠኛ ዳኜ አበራ በፎቶግራፍ ሙያ ወደ 38 ዓመት ያህል አገልግሏል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከደርግ ሥርዓት ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ የቻለ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜም ከሞት ጋር እንደተጋፈጠም ይናገራል። የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ረጅሙን ጊዜ በግንባር ከቆዩት ፎቶ ጋዜጠኞች መሃል አንዱ ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባድሜ ላይ ደርሶ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልብ ከሰራዊት እኩል በቦታው ተገኝቶ በካሜራው ያስቀረው የሰንደቅ ዓላማውን የመስቀል ሥነ ሥርዓት ፈጽሞ የማይረሳው ነገር እንደሆነም ይናገራል።
አልሸባብ ሲደመሰስ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሶማሊያ ሞቃዲሾ ሲገባ እርሱም አብሮ ገብቶ በካሜራው ያስቀረውን ምስል መቼም የማይዘነጋው እንደሆነ ይገልጻል።
ከእነዚህ ውጭ ደግሞ በልማቱ ዘርፍ ትልልቅ አገራዊ የሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተለይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በስፍራው በመገኘት ምስላቸውን ማስቀረት የቻለም ነው። በቅርቡ ደግሞ ስግብግቡ ጁንታ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ህግ ማስከበሩ ሂደት ሲገባ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተው እንዲዘግቡ ሲደረግ ፎቶ ጋዜጠኛ ዳኜም አንዱ ሆኖ ስራውን የከወነ ሲሆን፣ የነበረውን ቆይታ ያካፍለን ዘንድ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከዳኜ አበራ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የጁንታው ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ወደ ህግ ማስከበሩ እንደሚገባ በተነገረ ወቅት እንደ አንድ ዜጋ ምን ተሰማህ? እንደ ሚዲያ ባለሙያ ደግሞ በወቅቱ ወደስፍራው ሄደህ ትዘግባለህ ስትባልስ ምን አይነት ስሜት አደረብህ?
ዳኜ፡– መከላከያ መጠቃቱ ይሆናል ብዬ ያልጠበቅኩት ነገር ነው፤ ምክንያቱም ሰራዊቱ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ የተውጣጣ ነው። ሸር ተጠንስሶ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ይፈጸማል የሚል ግምት በጭራሽ አልነበረኝም። ይበልጥ በስፍራው ደርሼ ጉዳዩን ሳይ ደግሞ የበለጠ ነው ያዘንኩት። የትግል አጋር ሆኖ ዱር ገደሉን አብሮ የወጣና የወረደ ወገን ቀርቶ ለአንድ ቀን እንኳ አብሮ የዋለ ወዳጅ ሲጎዳ ያሳዝናል፤ የጁንታው ቡድን ግን በሰራዊቱ ላይ ያደረገው ያንን ነው። ከሰብዓዊነት ውጭ በመሆኑ በወቅቱ የተሰማኝ ነገር በጣም ከባድ ነበር።
ይህን ተከትሎ በወቅቱ ወደስፍራው እንድሄድ ሲነገረኝ ምንም አላቅማማሁም። በእርግጥ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በውግያ አውደ ግንባሮች ያላት ታሪክ የድል ነው። በአሁኑ ግን ወደስፍራው ለመሄድ ስዘጋጅ ያሳዘነኝና ያስደነገጠኝ ነገር ቢኖር የራሳችን ወገኖች ባደረሱት ጥቃት በመሆኑ በውስጤ የነበረው ሃሳብ የተምታታ ነው። ምክንያቱም የራሴ ከምትይው ወገን ጋር ጎራ ለይቶ መጣላት የሚከብድ ነገር በመሆኑ ነው። የጁንታው ቡድን በጣም ጥቂት ሆኖ ሳለ እሱ ባመጣው መዘዝ ብዙ ነገር ሊጎዳ መሆኑ ነበር ሲታሰበኝ የነበረው።
የመጀመሪያው ዕለት ጎንደር ገብተን ብዙም ሳንቆይ ደግሞ ወደ ዳንሻ አቀናን። የሁመራ አየር ማረፊያ በሰራዊቱ ጀግንነት በመለቀቁ ደግሞ ከዳንሻ ወደ ሁመራ የሄድኩት ከሰራዊት ጋር ነበር። በወቅቱ በጣም ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ቀደም ሲል ሰራዊቱ በብሄር ተከፋፍሏል በማለት በብዙ ሲወራ የነበረው ነገር ሐሰት መሆኑን ነው ማረጋገጥ የቻልኩት።
እንዲያውም ማስተዋል የቻልኩት ይበልጥ አንድነቱ የጎለበተ መሆኑን ነው። ጁንታው ሰራዊቱን የመከፋፈል ዓላማ አንግቦ ቢንቀሳቀስም ከበፊቱ ይልቅ አንድ እንዲሆኑ አድርጓል ማለት ይቻላል። ቆስለው እንኳ ከግንባሩ አንውጣም እያሉ ሲታገሉ የነበሩትን አይቻለሁ። ይህን ስታዪ ኢትዮጵያውያን ከተነካን ወደኋላ የማየት ሃሳብ እንደሌለን ነው መታዘብ የምትችዪው።
አዲስ ዘመን፡- በቆይታህ ያስተዋልከው ጉዳይና ስሜትህን የረበሸህ ነገር ካለ ብትገልጽልን?
ዳኜ፡– በመጀመሪያ ወደስፍራው ያቀናሁት ጥቅምት 28 ቀን ነበር። በመጀመሪያ ዙር የሄድኩት በዳንሻ በኩል እስከ ሁመራ ድረስ ሲሆን፣ የነበረው ነገር ከባድ ነው፤ የአካባቢው ህብረተሰብ በጁንታው ቡድን ተበድሏል። ሰላማዊ ሰው እጅግ በጣም ተጎድቷል። ከአካባቢው መፈናቀሉ በራሱ ስቃይ ሆኖበታል።
ከጁንታው ሰራዊት መካከል ተማርከው ያገኘኋቸው ብዙ ናቸው። በተለይ “የአብረኸት እንባ” በሚል ርዕስ በወጣው ዜና የአብረኸትን ፎቶ ሳነሳ አብሬ እያነባሁ ነበር። በወቅቱ ስትናገር የነበረው በተሰበረ ልብ ነው። ከንግግሯ ይልቅ እንባዋ ጮክ ብሎ የልቧን ስብራት ይናገር ነበር። ከመከላከያ ጋር ትዋጊያለሽ ተብላ መሳሪያ ብትታጠቅም አንድም ጥይት ሳትተኩስ ነው የተማረከችው።
ለምሳሌ አንድ ያገኘኋቸው ኮሎኔል ሻምበል በየነ የሚባሉ ሰው (በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለከዘራው ኮሎኔል ተብሎ የተገለጸው) የከዷቸው በሰሜን እዝ ውስጥ አብረው የነበሩ አለቆቻቸው ናቸው። ይሁንና በሰራዊቱ መካከል ከነበሩት ከጁንታው ቡድን ውጭ የነበሩትን የመከላከያ ሰራዊት አስተባብረው የፈመጸሙት ጀብዱ መቼም የማይረሳ ነው።
ምንም እንኳ እግራቸው ላይ ሁለት ቦታ በጥይት የተመቱ ቢሆንም አንዷ ጥይት ወጥታ አንዷ ቀርታ እንኳ ጀግንነታቸው የሚገርም ነበር። እየተዋጉም ኤርትራ ድረስ ሄደዋል። ከባድ የተባለው የተንቤን ውጊያ ላይ ከዘራውን እንደያዙ ሰራዊቱን እያዋጉ አግኝተናቸዋል። ህመም ሲሰማቸው በከዘራው እየተመረኮዙ እያዋጉ ስለነበርም ባለከዘራው ኮሎኔል እየተባሉ ነበር የሚጠሩት።
በእርግጥ ሁሉም የትግራይ ሰራዊት በግንባሩ ሲሳተፍ አምኖበት እንዳልሆነም ብዙ ማሳያዎች ሊሆኑ የሚችሉትን በወቅቱ አይተናል። አዲ አገራይ የሚባል ከተማ ባልና ሚስት ወታደሮች እሷ ነፍሰጡር በመሆኗ ፈቃድ ወስደው ተያይዘው ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። እሷ ቀድማ በመውጣቷ ለጊዜው በዛው ከተማ ቤት ተከራይተው ይኖራሉ።
በዚህ መሃል መንግስት የህግ ማስከበሩን ተግባር በመጀመሩ በአካባቢው ሽብር ሆነ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንዲት የትግራይ ብሄር ተወላጅ የሆኑ እናት ነፍሰጡሯን አስር አለቃ፣ በዚህ ቀውጢ ጊዜ መሄድ የለብሽም እኔ እንከባከብሻለሁ በማለት ምንም የሚበላ በሌለበት የራሳቸውን የዕለት ጉርስ በማካፈል አቆይተዋት እዛው እንድትወልድ አድርገዋል።
እኚህ እናት አካባቢው ሲረጋጋ ደግሞ ሽሬ ከተማ ድረስ መኪና ለምነው ይዘው በመምጣት ለወታደር አስረክበዋታል። እንዲህ አይነትም በጎነትም ያየሁበት ነው።
እጅግ በጣም ከተደሰትኩባቸው ጉዳዮች አንዱ ደግሞ ታግተው የነበሩ መኮንኖችን ሳስታውስ ነው። በወቅቱ መኮንኖቹ በጁንታው ቡድን ታግተው ስለነበር ሰራዊቱ መሪ አልነበረውም።
የጁንታው ቡድን የመኮንኖቹ መታገት ለሰራዊቱ መበታተን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብሎ አስቦ የነበረ ቢሆንም የበለጠ አንድነቱን ያሳየበትን አጋጣሚ ማስተዋል ችያለሁ። እንዲያውም በውጊያው ስፍራ የሰራዊቱን ትብብር ሳስተውል ትንሷዋን ኢትዮጵያ እንዳይ አድርጎኛል።
ቀደም ሲል እንደተባለውም በመከላከያ ውስጥ የአንድ ብሄር የበላይነት ነው የነበረው። በአሁኑ ወቅት ግን ይህ የአንድ ወገን የበላይነትን ሰራዊቱ ራሱ መስማት አይፈልግም። አንድነታቸው ይበልጥ ጎልቷል። መኮንኖቹ ከታገቱበት ተለቀው ሲመጡ የነበረው ስሜት በጣም ከፍ ያለ ነው። ከአስለቃቂዎቹ አንዱ ኮሎኔል ሻምበል አንዱ ናቸው። አለቆቹ ሲመጡ የሰራዊቱ ደስታ በጣም ከፍ ያለ ነበር።
መንግስት በህግ ማስከበሩ ተግባር አፋጣኝ ድል ማስመዝገብ መቻሉ እውነትን በመያዙ ነው ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም ያሸነፈው እውነት ነው። ምክንያቱም ሰራዊቱ ግፍ ተፈጽሞበታል። በዳይና ተበዳይ አለ፤ በዳይ ግን የተገባውን ውርደት ተከናንቧል። ጄነራሎቹን የምስጋና እና የግብዣ ፕሮግራም አለ ብለው ጋብዘው ሰራዊቱን ማጥቃት የክፋቱ ጥግ ማሳያ ነውና በቃላት የሚገለጽ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አንተ ቀደም ሲልም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ልምዱ አለህና እንደ ሚዲያ ባለሙያ አንድ ጋዜጠኛ በግንባር ተገኝቶ ለመዘገብ ምን ምን ነገሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት ትላለህ?
ዳኜ፡– የሚዲያ ባለሙያ ወደስፍራው ሲንቀሳቀስ ልምድ ያለውም የሌለውም ሊኖር ይችላል። የጦርነት አዘጋገብ ልምዱ ብዙዎቻችን የለንም። ምክንያቱም መዘገብ ያለበትና የሌለበት ነገር አለ፤ እንዲያው ለዜና ሽፋን ተብሎ ብቻ መረጃ ጠቃሚና ጎጂነቱን ሳናረጋግጥ ለህትመት ማብቃቱ አሊያም አየር ላይ ማዋሉ የከፋ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ በተለይ የጦርነት አዘጋገብን ስልት መከተሉ የግድ ይላል።
የትኛውንስ ፎቶ አሊያ ምስል መጠቀም አለብን የሚለው ነገር ማስተዋልን ይጠይቃል። በጦር ግንባር የሚያስከፋ ነገር ጋዜጠኛውን ሊያጋጥመው ይችላል። በዚያ ጊዜ ስሜታዊ ሆኖ መዘገብየለብንም። ማልቀስም መፍራትም ሳያስፈልግ በቆራጥነት ስሜት መስራትን የግድ ይላል።
ያጋጠመኝን ነገር ባነሳልሽ ስራችንን እየሰራን ባለንበት ወቅት ወደቆላ ተምቤን ሄድን። ከዚያኛውም ሆነ ከእኛ በኩል መሳሪያ እንዳለቀ ሰማን። ኮሎኔሉ ግቡ ብለው አዘዙን። በተራራው ዙሪያ ስድስት ዙር ምሽግ ተቆፍሮበታል።
እሱን ምሽግ በፎቶም በተንቀሳቃሽ ምስልም እንድንወስድ ተብሎ ወደስፍራው ለመሄድ መኪና ውስጥ ገባን። ስንገባ ግን መግባት የነበረብን ፎቶና ቪዲዮ ካሜራ ባለሙያዎች ብንሆንም አንደኛው ሪፖርተር ገብቶ ውስጥ አገኘሁት።
ከእኔ ጋር ያለውም ሪፖርተር ጌትነት ተስፋማሪያም ሊገባ ሲመጣ ፎቶ ነው የተባለው ስለዚህ አንተ መግባት የለብህም፤ ከሞትኩም እኔ ልሙት ብዬ እሱን አስቀረሁት። እሱ እኔን ስለሰማ ቀረ፤ ሌሎቹ ደግሞ ገና የመጀመሪያቸው በመሆኑ ወደቦታው ለመሄድ ፈለጉ። ግን ከከባድ ፈተና ነው የወጣነው።
እኛን አጅቦ የሄደው ወታደር ራሱ እንሂድ ሲባል እኔ ጥሩ ቦታ ይዤያለሁና እባካችሁ ልዋጋበት ሲል ነበር። መያዝ የሚገባንን ምስል ይዘን ስንሄድ ከሞት ጋር እየተጋፈጥን መሳሪያ ከየአቅጣጫው እየተተኮሰ ነበርና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሳስታውስ መቼም የሚረሳ አይደለም። ይህ ምን ማለት ነው ብትይኝ የጦር ውሎ ዘገባን አዘጋገብ ልምዱ እንደሌለን ነው የሚያሳየን።
አንድ በጣም የተደመምኩበት ነገር ቢኖር ካሜራ ይዘው መሳሪያም ጎን ለጎን አንግበው እየተዋጉ ምስል የሚያስቀሩ ወታደሮችን ማየቴ ነው። ምንም ታሪክ ሳይቀራቸው በአንድ እጃቸው ካሜራቸውን በአንዱ ደግሞ መሳሪያቸውን አንግተው ነው ታሪክ ሲያስቀሩ የነበረውና መከላከያን በዚህም ስራ ሳላደንቅ ማለፍ አልችልም።
አዲስ ዘመን፡- በግንባር ባለህበት ወቅት የተለያዩ ፎቶዎችን በማንሳት ለህትመት መብቃቱ ይታወቃልና የትኛው ምስል ነበር ቀልብህን ገዝቶት የነበረው?
ዳኜ፡- በእርግጥ ብዙ ፎቶዎች ከዜናዎቹ ጋር ተዋህደው ለህትመት በቅተዋል። መድፍ ከጁንታው ቡድን እኛን ለማጥቃት እየተተኮሰም ፎቶ አንስቻለሁ። ሌላው እኛ የነበርንበት ሽሬ ላይ ከሁመራ የተፈናቀሉ ስደተኞች ነበሩ። ህጻናቱ እናትና አባቶቻቸው የት እንደሄዱ አያውቁም።
ሌሎቹ የዘጠኝ እና የአራት ዓመት ህጻናት ደግሞ ብቻቸውን ከሰው ጋር ተፈናቅለው መጥተው ሽሬ ነበሩ። እነዛን ህጻናት ሲንከባከቡ የነበሩ የሰራዊቱ አባላት ወደቤተሰቦቻቸው በመኪና ሊሸኟቸው ሲሉ መኪና ውስጥ ካስገቧቸው በኋላ መኪናው ሊንቀሳቀስ ሲል አንደኛው ህጻን አንደኛውን የሰራዊት አባል ቻው ካለው በኋላ እንደገና ሊሰናበተው ፈልጎ ይጠራው ጀመር። ወታደሩም ሮጦ ሄዶ አቅፎት ሲሳሳሙ ያነሳሁት ፎቶ ልቤን ያርደዋል። ምንም እንኳ የስጋ ዝምድና በመካከላቸው ባይኖርም በህጻኑና በወታደሩ መካከል ግን ፍጹም የሆነ የአባትነትና የልጅነት ስሜትን ነው ማስተዋል የቻልኩት።
ሌላው ሰራዊቱ ውጊያ ላይ ውሎ አረፍ ባለበት ወቅት እኔ ዞር ዞር እያልኩ አንዳንድ ነገር እመለከት ነበርና አንድ ነገር ቀልቤን ገታ ያደርገዋል፤ ይኸውም ሁለት ወንድና ሴት ወታደሮች ሲሆኑ፣ ወንዱ የሴቷን ጸጉር እየፈታ አየሁ። ፎቶ ላንሳችሁ ስል ጠይቄ ካነሳኋቸው በኋላ ስለራሳቸው ይነግሩኝ ጀመር።
እሷ ታንክ ተኳሽ፣ እርሱ ደግሞ አለቃዋ እንደሆነ ነገረችኝ። በወቅቱ ደግሞ በውጊያው የእርሱ ጓደኛ የሆነው የእርሷ ባል የት እንዳለ አለማወቃቸውንም ነገሩኝ። እነርሱ መትረፋቸውን እርሱ ግን የት እንደሆነ አለማወቃቸውን አወጉኝ። የእነሱን ምስል በካሜራዬ ማስቀረቴ ራሱን የቻለ ታሪክ ሆኖ ነው የሚሰማኝ።
ከህትመት ሚዲያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነበር በቦታው ተገኝቶ ሁነቱን ሲዘግብ የነበረው። ይህ ታሪክ በመሆኑ ፕሬስ ስራዎቹን ሁሉ በአግባቡ ነው ዘግቦ ያስነበበው የሚል አተያይ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጠኸን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ
ዳኜ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013