
– ብሥራት አክሊሉ (ዶ/ር) የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማሕበር በሰሜን አሜሪካ ፕሬዚዳንት
ከተቋቋመ አንድ መቶ (100) ዓመት ሊሆነው የአንድ ወር ጊዜ ነው የቀረው። በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ስሙ ከፍ ብሎ ይነሳል። በያኔው የቀለም (አካዳሚክ) ትምህርት፤ በአየርና በየብስ፣ በምህንድስና፣ በሳይንስ፣ በሂሣብ እና በሌሎችም ዘርፎች ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸውን ምሁራን ያፈራ ስለመሆኑ አብዝቶ ይነገርለታል። የዚህ ትምህርት ቤት ፍሬ የሆኑ አንዳንዶችም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ይገኛሉ።
በተለያየ የትውልድ ዘመን ውስጥ ዘመንን የተሻገረው ይህ ትምህርትቤት አሁን ላይ ደግሞ ፖሊ ቴክኒክ ሆኖ በሥነጥበብ፣ በእደጥበብና በሙዚቃ ዘርፎች በማስተማር ላይ ነው። ትምህርትቤቱን ያቋቋሙት ኢትዮጵያን ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ እንዳስተዳደሯት የሚነገርላቸው አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው። ትምህርትቤቱንም ተፈሪ መኮንን ብለው ነበር የሰየሙት።
የአፄው አስተዳደራዊ ሥርዓት ከተለወጠ በኋላ ግን ትምህርትቤቱ ስሙ ተቀይሮ እንጦጦ በሚል ስያሜ ነው ሲጠራ የቆየው። ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል ወሮ በነበረበት ጊዜም ቪክቶር አማኑኤል ተብሎ ተሰይሞ ነበር። ለአራት ዓመታትም ጣሊያናውያን ብቻ የሚማሩበት ትምህርትቤት ነው የነበረው። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ከአንድ ወር በፊት በቀደመው ስሙ ተፈሪ መኮንን ተብሎ እንዲጠራ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ አግኝቷል፡
ትምህርትቤቱ በቀድሞ ስሙ እንዲጠራ የቀደሙት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ብዙ ደክመዋል። የቀድሞ ተማሪዎች ተቆርቋሪነታቸውን ያሳዩት ወደቀደመ መጠሪያ ስሙ እንዲመለስ ብቻ አይደለም። ትምህርትቤቱ ቀድሞ ያፈራቸው ተማሪዎቹ እንደኮሩበት ሁሉ የአሁኖቹም በተመሳሳይ የሚኮሩበትና ለሀገር የሚያኮሩ ሙያተኞችም እንዲወጡ የቀድሞ ተማሪዎች በሀሳብ፣ በገንዘብና በቻሉት ሁሉ እያገዙት ይገኛሉ።
ቀደምቶቹ የጀመሩትን መልካም ሥራ የሚያስቀጥሉ ተተኪ ማፍራትም ሌላው የእንቅስቃሴያቸው አካል ነው። የቀድሞ ተማሪዎች፤ ትምህርት ቤቱ የተመሠረተበትን አንድ መቶ ዓመት ለማክበርም ከትምህርት ቤቱ እና ከአዲስ አበባ ከተማ እተዳደር ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር የቅድመዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
የተማሩበት ትምህርት ቤት ሲመሰረት ይጠራበት በነበረው ስም እንዲጠራ ፈቃድ ለማግኘት የቀድሞ የትምህርት ቤቱን ተማሪዎች በመወከል የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች በመመላለስ፣ ለትምህርትቤቱ በሀሳብ፣ በገንዘብና በተለያየ መንገድ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በማስተባበር፣ ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ ያሉት ብሥራት አክሊሉ (ዶ/ር) የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማህበር በሰሜን አሜሪካ ፕሬዚደንት ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።
ብሥራት (ዶ/ር) ኑሮአቸው በአሜሪካን ሀገር ነው። ‹‹ከሀገር እስከ ውጭ ሀገር የመማርና ከፍ ላለ ሥራም ለመታጨት የደረስኩት በሀገሬ ውስጥ ጥሩ በሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ መማር በመቻሌ ነው›› ይላሉ፡፡
ውለታ አለብኝ ብለው በማመን ከሚኖሩበት አሜሪካን ሀገር እየተመላለሱ ነው የቀድሞ ትምህርት ቤታቸው ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ በኃላፊነት እየሰሩ የሚገኙት። አሁንም የመቶኛ ዓመት ክብረበዓል እስኪጠናቀቅ በኢትዮጵያ ለመቆየት ወስነው በሥራ ላይ ይገኛሉ። ብሥራት (ዶ/ር) ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ቀድሞ መስፍን ሐረር መንገድ ተብሎ ይጠራ በነበረው ሾላ ሰፈር ነው። የትናንት ትውስታቸውን፣ ዛሬ ደግሞ በተቆርቋሪነት ለቀድሞ ትምህርት ቤታቸው ምን እየሰሩ እንደሆነ እንደሚከተለው አጫውተውናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስኪ በቅድሚያ ስለ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አንዳንድ ነገሮችን፣ የመማር እድሉን እንዴት እንዳገኙና የነበርዎትን ትውስታ እናንሳ?
ብሥራት (ዶ/ር)፡- ከተማርኩበት ተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት የወጣሁት የዛሬ 58 ዓመት ነው። በቀለም ትምህርት ጠንካራ የሆንኩበት፣ በሥነምግባር የታነጽኩበት፣ ዛሬ ለምገኝበት ጥሩ ደረጃ ያበቃኝ እና መሠረት የሆነኝ ተፈሪ መኮንን ነው። የትምህርት ቤቴ ትውስታው ከዐይነህሊናዬ አይጠፋም።
እኔ ከመግባቴ በፊት ትምህርት ቤቱ በ1917 ዓ.ም ሲከፈት አባቴ ነው የገባው። አባቴ ስድስት ዓመት እንደተማረ ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችን ኢትዮጵያን በኃይል ሲወር ቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል ተብሎ በዚያን ጊዜ ተማሪዎች ሆለታ ወደሚገኘው የጦር አካዳሚ እንዲሄዱ ተደረገ። በወቅቱም በትምህርት ቤቱ ተምረው ጀነራል ደረጃ የደረሱ እነ ጀነራል ከበደ ገብሬ፣ ጀኔራል እያሱ መንገሻ፣ ዋቅጅራ ሰበዳ እና ሌሎችም ተማሪዎች ናቸው የነበሩት።
ተማሪዎቹ ወደ ሆለታ እንደተዘዋወሩ ብዙም ሳይቆይ ጦርነቱ ተጀመረ። በወቅቱም ግማሾቹ ተማሪዎች ወደአርበኞቹ ተቀላቀሉ። ገሚሶቹ ደግሞ ከሀገር ወጡ።
በጦርነቱ ወቅት የተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት እጣ ፈንታም በጣሊያን እጅ ላይ ነው የነበረው። ተፈሪ መኮንን መሆኑ ቀርቶ ቪክቶር አማኑኤል ትምህርትቤት ተብሎ ተሰየመ። በወቅቱም ኢትዮጵያውያን በትምህርትቤቱ መማር እንደማይችሉ ተከልክለው ጣሊያኖች ብቻ ነበሩ ለአራት ዓመታት የተማሩበት። ፋሽስት ጣሊያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ እና አፄ ኃይለሥላሴም በስደት ከቆዩበት ከእንግሊዝ ሀገር ተመልሰው ሀገራቸው ሲገቡ ትምህርትቤቱን መልሰው አደራጁት።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሀኪም ተብለው የሚታወቁት ሀኪም ወርቅነህ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን አስተዳዳሪ ሆነው ሲሰሩ ነበር። በኋላ ላይ ግን አፄ ኃይለሥላሴ አሜሪካንንም እንግሊዝንም ወደ ጎን ብለው ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የወጡ የትምህርት ዓላማ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ በትምህርት የላቁ ናቸው ያሏቸውን ከውጭ ሰው ፈለጉ። ምርጫቸው ያደረጉት ካናዳን ነበር።
ካናዳዊያኑ ጀስዊቶች እንዲመጡ አደረጉ። በወቅቱ አፄ ኃይለሥላሴ ያስጠነቀቁት ኃይማኖታቸውን የሚያንፀባርቅ አለባበስ እንዳይለብሱ፣ ኃይማኖታዊ ትምህርትም እንዳይሰጡ፤ ፋዘርና ብራዘር የሚለውን አጠራርም እንዳይጠቀሙ፣ ሚስተር መባል እንዳለባቸው ነበር። አነርሱም ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው በኮሌጅ ደረጃ ኃላፊነት ላይ የሰራ ዶክተር ማት የሚባል ሰው አንድ አምስት ሰው ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ትምህርትቤቱንም ማስተዳደር ጀመረ።
በዚህ ወቅት ነበር እኔም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የገባሁት። እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ የተማርኩት በሰፈሬ ራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው አርበኞች ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ሶስተኛ ክፍል ስደርስ ከሰፈር በእግር ተመላልሼ መማር እንደምችል ቤተሰቤ በማመኑ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እንድገባ ተጠየቀ። የነበረኝ የትምህርት ማስረጃ የተሟላና የትምህርት ውጤቴም ጥሩ ስለነበር ትምህርት ቤቱ ተቀበለኝ። ትምህርት ቤቱ የቤተሰብ ነው ማለት ይቻላል። አባቴ፤ ሁለት ታላቅ ወንድሞቼ ቀድመው ተምረዋል። እኔም በመቀጠል ነው የተማርኩት፡፡
ወንድሞቼ እዛው እያደሩ ነበር የሚማሩት። እኔ በገባሁበት ጊዜ ግን የተማሪ ቁጥር ብዙ በመሆኑ ከሶስተኛ እስከ 11ኛ ክፍል እየተመላለስኩ ነበር የተማርኩት። በወቅቱም ኢትዮጵያውያን፣ አሜሪካውያን፣ ሕንዳውያን መምህራን ናቸው ያስተማሩን። በነበረኝ የትምህርት ቆይታ ትምህርት ቤቱ የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሀገሩን የሚወድ፣ ጥሩ ሥነምግባር ያለው ዜጋ ለማፍራትም ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። አንድ ሰው ሙሉ ሰው መሆን የሚችለው በሥነምግባሩም የታነፀ ሲሆን እንደሆነ በወቅቱ ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳድሩት ካናዳዊ ይከተሉት የነበረ መርህ ነው። ምግብ ስንመገብ እንኳን በልተን እስክንጨርስ ወሬ አናወራም። ተማሪውን በሥነምግባር ማነጽ የካናዳዊያን መርህ ነው ማለት ይቻላል።
ከትምህርት ሰዓት ውጭ በተለያዩ ጉዳዮች ተማሪዎች ክርክር (ዲቤት) የሚያደርጉባቸው፣ የስካውት፣ የስፖርት እና ሌሎችም ተማሪዎች የሚሳተፉባቸው ክበባት ነበሩ። ተማሪዎች ማኅበራዊ ተሳትፎ እንዲለማመዱም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የግንባታ ሥራዎችን በመሥራት ጭምር እንዲሰሩ ይደረጋል። ሌላው የትምህርት ቤቱ ጥንካሬ የነበረው የጥናት አዳራሽ (ሆል) አለ።
የቀኑ ትምህርት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሲያበቃ ሁሉም ተማሪ ወደ ጥናት አዳራሽ ገብቶ የተሰጠውን የቤት ሥራ ይሰራል። የተማረውን ይከልሳል። ተቆጣጣሪ መምህርም ስላለ የጥምህርት ጥያቄ ያለው ተማሪ ጠይቆ መልስ ያገኛል። ተማሪ ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣ ተገቢው ክትትል ይደረግ ነበር። የነበረው የትምህርት ሥርአት በራሱ የሚተማመን ጎበዝ ተማሪ እንድሆን ብቻ ሳይሆን በሥራ ዓለምም ከፍ ያለ ቦታ እንዲደርስ መሠረት ሆኖኛል፡፡
የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትውስታዎቼ ሰፊ ናቸው። በመጽሐፍ መልክ ለማዘጋጀት እያሰብኩ ነው። ከመምህራኖቻችን ጋር የነበረን ቀረቤታም የቤተሰብ ያህል ነው የነበረው። ያኔ የተፈጠረው ቀረቤታ አሁንም አለ። የጂኦግራፊና የስፖርት መምህራችን የነበረው ሚስተር ቱሬን የሚባል ካናዳዊ አስተማሪያችንን በየዓመቱ ካናዳ ቤቱ ሄደን እንጠይቀው ነበር። ለሌሎች ሲያስተዋውቀንም ይኮራብን ነበር። ተፈሪ መኮንን የተመሰረተበት አንድ መቶ ዓመት ሲከበር የማየት እድሉ ይገጥመዋል ብለን ተመኝተን ነበር። ግን አልሆነም 99 ዓመት ከአስር ወር ሲሆነው አረፈ። ከተማሪዎች ጋርም መፈላለጉና መጠያየቁ አለ። ሁላችንንም አንድ ያደረገን ትምህርት ቤታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ሲቀርዎት የወጡበት ምክንያቱ ምን ነበር?
ብሥራት (ዶ/ር) ፡– እስከ 12ኛ ክፍል ያልተማርኩት በዚያን ጊዜ የአሜሪካን ፊልድ ሰርቪስ የሚባል ፕሮግራም ነበር። ከየትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እንዲወዳደሩ እድል ይሰጣል። ውድድሩን ላለፈ ተማሪ የአንድ ዓመት የትምህርት ዕድል ይሰጣል። እኔም በውድድሩ አልፌ ተመረጥኩ። በወቅቱ ከየትምህርት ቤቱ የተመረጥነው 52 ነበርን ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አሜሪካን ሀገር ሚኒሶታ ውስጥ በሚገኝ ሚኒታንጋሀ በሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር የተማርኩት። ጊዜው እኤአ 1966 ነው።
በትምህርት ቤቱ ከነበሩት ተማሪዎች ጥቁር እኔ ብቻ ነበር የነበርኩት። በትምህርት ችሎታዬ መምህራኖቹ ሲደነቁብኝ ነበር። የተማርኩበትን ትምህርት ቤትም እንዲሁ ሲያደንቁ ነበር። የግል ትምህርት ቤት ነበር የመሰላቸው። መንግሥት ያቋቋመው መሆኑን ስነግራቸው አላመኑም። ይሄ በትምህርት ቤቴ እንድኮራ አድርጎኛል። የአንድ ዓመት ትምህርቴን በጥሩ ውጤት አጠናቅቄ ወደ ሀገሬ ተመለስኩ። ማንም ሰው በዚያው መቅረት አንደማይችል በቅድሚያ ተነግሮናል። ወደ ሀገሬ ተመልሼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) የትምህርት ክፍል ገብቼ ለሁለት ዓመት ትምህርቴን እንደተከታተልኩ የተማሪዎች ንቅናቄ ተጀመረ። ዩኒቨርሲቲም መማር ማስተማሩ ተስተጓጎለ። አማራጭ መፈለግ ስለነበረብኝ በወቅቱ የአሜሪካን ኢንፎርሜሽን ሰርቪስ የሚባል ተቋም ነበር። በተቋሙ ውስጥ የትምህርት ዕድል የሚገኝባቸው መረጃዎች ስለነበሩት አድራሻ እየፈለኩ የትምህርት ማስረጃዬን እያያዝኩ በአሜሪካን ሀገር ለሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ላኩ። ተሳክቶልኝ ለትምህርት አሜሪካን ሀገር ሄድኩ። አሜሪካን ሀገር የሄድኩበት አጋጣሚ ይሄ ነው፡፡
በአሜሪካም የመጀመሪያ ዲግሪ ካልተር ከሚባል ኮሌጅ አገኘሁ። ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ማሳቹሴትስ ሰራሁ፡። ከቦስተን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በኢኮኖሚክስ ሶስተኛ ዲግሪ (PHD) አገኘሁ። ትምህርቴን እንደጨረስኩ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ መሥራት ፈልጌ ነበር። በወቅቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ስለነበር የተረጋጋ ነገር ስላልነበር ወደ ሀገር መመለስ አልቻልኩም። በአሜሪካን ሀገር በተማርኩበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር የመሆን እድል አገኘሁ። ለአራት ዓመት በመምህርነት ሰራሁ። እያስተማርኩ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የሥራ ማመልከቻ አስገብቼ ሥራ አገኘሁ። በተቋሙ ውስጥ ባገኘሁት የሥራ እድል ጣሊያን ሀገር 10 ዓመት፣ ኒዮርክ ውስጥ ወደ 20 ዓመት በሥራ ቆየሁ። አሁን ጡረታ ላይ ነው የምገኘው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናንተ በተማራችሁበት ዘመን ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የሚማሩ ሴት ተማሪዎች አልነበሩም?
ብሥራት (ዶ/ር) ፡- መጀመሪያ ላይ ሴት ተማሪዎች አልነበሩም። በኋላ ላይ ግን ኮሜርስና ሆሚኢኮኖሚክስ የሚባሉ የትምህርት አይነቶች መሰጠት ሲጀምሩ ሴቶችም መማር ጀመሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከስም ስያሜ ጀምሮ የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዷል። በሂደት የነበሩትን ለውጦች ቢያስረዱን?
ብሥራት (ዶ/ር)፡- ተፈሪ መኮንንን ትምህርት ቤት በብዙ ለውጦች ውስጥ አልፏል። እኛ ስንማር የቀለም (አካዳሚክ) ትምህርት ነበር የሚሰጠው። አሁን ደግሞ የተለያየ የሙያ ትምህርት እየተሰጠ ነው። የትምህርት ሥርዓት ለውጥ አለ ማለት ነው። ከተማሪ ቁጥር አኳያም በርካታ ለውጦች አሉ። አሁን ሰፊ ቁጥር ያለው ተማሪ ነው እየተማረ ያለው። የትምህርት ይዘቱም እንደቀድሞው አይመስለኝም። መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው የሚሰማኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማሕበር መስርታችሁ እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ እንደሆነ ይታወቃል። ማሕበር ያቋቋማችሁበት ምክንያት ምንድን ነው ?
ብሥራት (ዶ/ር)፡- ማህበራችን የተመሠረተው የዛሬ 14 ዓመት ነው። መነሻውም ጴጥሮስ አክሊሉ የሚባለው ወንድሜ ነው። ትምህርት ቤቱን ለመጎብኘት ሄዶ ጎዶሎ የሆነ ነገር ታየው። ወደቤት ገብቶም ለእናታችን አዝኖ ይነግራታል። እናታችንም አባትህም እናንተ ወንድማማቾችም የተማራችሁበት ትምህርት ቤት ነው። ለምን ድጋፍ አድርጋችሁ ወደቀደመ ዝናው እንዲመለስ አታደርጉም አለችው። ወንድሜም የትምህርት ቤቱን አስተዳደርና የቀድሞ ተማሪዎችን በማነጋገር፣ በእርሱ በኩል በአሜሪካን ሀገር የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች በሰሜን አሜሪካ ብሎ ማሕበር አቋቁሞ ትምህርት ቤቱን ለማገዝ እንደሚሰራ አስታወቀ። አዲስ አበባ ከተማ ያሉት የቀድሞ ተማሪዎች ደግሞ የራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ሁኔታዎችን አመቻቸ።
የአሜሪካውም የአዲስ አበባውም ለአንድ ዓላማ ነው የቆሙት። የትምህርት ቤቱን የቀድሞ ስም ማስመለስ፣ ትምህርት ቤቱን በተለያየ መንገድ መደገፍን ዓላማ አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት። በአሜሪካን የተቋቋመው የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማሕበር በሰሜን አሜሪካን የሚል ነው። አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚገኘው ደግሞ የተፈሪ መኮንን የቀድሞ ተማሪዎች የእርዳታ ድርጅት የሚል ስያሜ ነው ያለው። በአሜሪካም በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሆን የተፈለገው አብዛኛው ተማሪ ያለው አዲስ አበባ ከተማ ስለሆነና ሥራውም የሚሰራው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኘው ትምህርት ቤት በመሆኑ ነው።
ወንድሜ እኤአ በ2011 በአሜሪካን ሀገር ማሕበሩን አቋቁሞ የመሪነቱን ድርሻ ወስዶ መንቀሳቀስ ጀመረ። ለሶስት ዓመት አገልግሎ በምርጫ መሪነቱ ወደኔ መጣ። ማሕበሩ በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ፣ የኒዮርክ፣ ካሊፎርኒያ፣ ሳውዝ አፍሪካ፣ ሚድልኢስት እያለ ወደ 11 ቻፕተር (ክፍሎች) የተከፋፈለ ነው። ይህ የሆነው እያንዳንዱ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለመለየትና ለአሰራርም እንዲመች ነው። ለምሳሌ ኒዮርክ አካባቢ ያሉ አባላት ለብቻቸው በትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ሥራ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡
መሪነቱን ተቀብዬ ባደረኳቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ስም እንደሚመለስ ጥያቄ ለማቅረብ ጥሩ አጋጣሚ ያገኘነው በኢሕአዴግ የመንግሥት ሥርዓት አፈጉባኤ የነበሩት አቶ ዳዊት ዮሐንስ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ ስለነበሩ እንዲረዱን ተደረገ። በአጋጣሚም ነቀፌታ አልነበረም። ሆኖም አዲስ አበባ ላይ ትንሽ ችግር አጋጠመን። የሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ስለነበር ብዙ ተመላለስኩ። ጉዳዩን ለማስረዳት ወደ አራት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባዎችን ነበር ያነጋገርኩት። ፈቃደኛ ናቸው ግን አልፈፀሙልንም፡፡
በዚህ የተነሳም አንዳንድ የቀድሞ ተማሪዎች የማሕበሩ አባል መሆን እየፈለጉ ግን የተማሩበትን የትምህርት ቤት ስያሜ በጣም ይፈልጉት ስለነበር ወደኋላ ማለት ጀመሩ። ሆኖም ከብዙ ጥረት በኋላ ከአንድ ወር በፊት ውሳኔ ማግኘት ችለናል። ብዙ አባላቶችም ደስተኞች ሆነዋል። የማሕበሩ አባል ለመሆንም ብዙዎች ፍላጎት እያሳዩ ነው። በዚህ አጋጣሚ የብዙ ጊዜ ጥያቁያችን መልስ በማግኘቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በማሕበሩ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ደግሞ ስለማሕበሩ ሕጋዊነትና ማሕበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት ይንገሩን?
ብሥራት (ዶ/ር) ፡- ማሕበራችን ሕጋዊ እውቅና አለው። በማሕበራት ማደራጃ (በሲቪል ሶሳይቲ ኦርጋናይዜሽን) ተመዝግቦ እውቅና አግኝቷል። በኢትዮጵያም ተወካይ አለን። ሕጋዊ ሆነን ነው የምንቀሳቀሰው። ዓመታዊ ስብሰባም እናደርጋለን። የሰራናቸውን ሥራዎች እንገመግማለን። ማሕበራችን ትልቁ ሥራው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየው ከትምህርት ቤቱ አመራሮች ጋር በመነጋገር ተማሪዎች የሚያስፍልጋቸውን ነገሮች ለይቶ እገዛ ማድረግ ነው።
በተለይ ሴት ተማሪዎች አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ የገንዘብ አቅም ውስንነት አለባቸው። በዚህም ለግል ንጽህና መጠበቂያ የሚያስፈልጋቸውን እንኳን ለማሟላት ይቸገራሉ። አንዱ ተግባር እንዲህ ያለውን ችግር መፍታት ነው።
ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች ወደ ስድሰት መቶ ይሆናሉ። የተሻለ የትምህርት ውጤት ለሚያስመዘግቡ የተወሰኑ ወንዶችም ማሕበሩ ድጋፍ እያደረገ ነው። በትምህርታቸው ጠንካራ ሆነው በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ነው የምናግዛቸው። በዋና ዋና በዓላት ወቅት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች በተለይ አነስተኛ ደመወዝ ያላቸውን የበዓል መዋያ ማሕበሩ ያበረክታል።
ትምህርት ቤቱ የኮምፒውተር ጥያቄም አቅርቦ ማሕበሩ አሟልቷል። ለትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ክፍልም ማሕበሩ የእማሆይ ጽጌ ፋውንዴሽንን ድጋፍ ጠይቆ የሙዚቃ መሣሪያ ለማሕበሩ አበርክተው ለትምህርት ቤቱ ተሰጥቷል። ፋውንዴሽኑ እማሆይ ጽጌ ይጠቀሙበት የነበረውንም ፒያኖ ጭምር ነው ያበረከተው። ትምህርት ቤቱም የሙዚቃ ክፍሉን በእማሆይ ጽጌ ስም ሰይሟል። ይህንንም እማይሆይ ጽጌ ትምህርት ቤቱ የተመሰረተበትን አንድ መቶ ዓመት ሲያከብር በሕይወት እንዲያዩ ፍላጎት ነበረው። ግን ሳይሆን ቀርቶ እማሆይ ጽጌ አንድ መቶ ዓመት ሊሞላቸው ጥቂት ወራት ሲቀራቸው አረፉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የማሕበሩ እንቅስቃሴ ትምህርት ቤቱን እስከ ምን ደረጃ ማድረስ ነው? አያይዘው የማሕበሩ እንቅስቃሴዎች አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚልበት ሁኔታ ይስተዋላልና ይህን ችግር ለመቅረፍ ማሕበሩ የዘረጋው የአሰራር ሥርዓት ካለ ይግለጹልን
ብሥራት (ዶ/ር)፡- በምኖርበት አሜሪካን ሀገር የቀድሞ ተማሪዎች ማሕበር መመስረት እንደ ባሕል ሆኖ የሚሰራበት ነው። ትምህርት ቤቶችን የሚረዱት ቀድሞ በትምህርት ቤቱ የተማሩ ተማሪዎች ናቸው። አንዳንዶች በሕይወት እያሉ ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ሲሞቱ ለተማሩበት ትምህርት ቤት እንዲውል ያደርጋሉ። ያወርሳሉ፡፡
እኔን ትልቅ ደረጃ ያደረሰኝ ትምህርትቤቴ ነው። ሌላውም ዕድሉ ይድረሰው ብለው ነው የተማሩበትን ትምህርት ቤት ለመርዳት የሚነሳሱት። አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ይልቅ ከቀድሞ ተማሪዎች ነው ብዙ ነገር የሚያገኙት። የእኛም ማሕበር ይሄ አይነት ባሕል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር ነው ፍላጎቱ። ብዙ ሰው ለቤተክርስቲያን ብዙ ነገር ያደርጋል። ለተማረበት ትምህርት ቤት ድጋፍ ማድረግ ግን የተለመደ አይደለም። ትምህርት ቤትን ማገዝ የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማሕበር በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶችን የማገዝ ባሕል እንዲጎለብት ነው ፍላጎቱ፡፡
ማህበሩ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ድጋፍ ሲጠይቅ የማሟላት ፍላጎት አለው። ለምሳሌ ትምህርት ቤቱ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የመድረስ እቅድ አለው። ይህንኑ ለማሳከትም ማሕበሩ ከጎኑ ሆኖ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ማሕበሩ ተተኪዎች እንዲኖሩት ይፈልጋል። እኛ ላለፉት 14 ዓመታት ሰርተን እዚህ አድርሰናል። በግሌ የትምህርት ቤቱ አንድ መቶ ዓመት እስኪከበር ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ እየሰራሁ ነው። ከበዓሉ በኋላ ግን መሪነቱን ለሌላ አሸጋግራለሁ ብያለሁ። ሁሉም ሰው መሳተፍ አለበት፡፡
የቀድሞ ተማሪ እኛ ብቻ አይደለንም። ከእኛ በኋላ የተማሩትም፣ አሁን እየተማሩ ያሉትም ‹‹የቀድሞ ስለሚባሉ›› የማሕበሩ አባል መሆን አለባቸው። ተተክተውም መሥራት ይኖርባቸዋል። እንዲህ ከሆነ ማሕበሩ ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል። የማሕበሩ አባላት ይሄ እንዲሆን ነው ፍላጎታችን። አሁን ማሕበሩ በአጠቃላይ ወደ አምስት መቶ የሚሆኑ አባላት አሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የተለያዩ የግንባታ ሥራዎችን አይተናል። ስለግንባታውና ትምህርት ቤቱ የተመሠረተበትን አንድ መቶ ዓመት ሚያዚያ ወር ለማክበር እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ደግሞ ይንገሩን
ብሥራት (ዶ/ር) ፡- ትምህርት ቤቱ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ግንባታ፤ የትምህርት ቤቱን አንድ መቶ ዓመት የምሥረታ በዓል ማክበር ብቻ ሳይሆን አንድ ነገር ለማበርከት ታስቦ እየተሰራ ነው። ማሕበሩ በተለያዩ ደረጃዎች ሊያከናውናቸው የሚፈልጋቸው ሥራዎች አሉት። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ የሆነው ኒዮርክ ቴትራ ብለው የሰየሙት አራት ከተሞች አካባቢ ይዞ የሚንቀሳቀሱት የማሕበሩ አባላት በትምህርት ቤቱ ውስጥ እንደመናፈሻ የሚያገለግል በስማቸው የሚሰራ ሥራ እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህም ተጀምሯል፡፡
ከዚያ ባሻገር ግን በማሕበሩ ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ባለ አራት ወለል (ጂ ፕላስ ፎር) ሕንፃ ለመገንባት ነው ያቀደው። የሕንፃ ግንባታው የመሠረት ድንጋይ የበዓሉ ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የሚከናወን ይሆናል። የሕንፃውን ግንባታ ለመከታተል ኃላፊነት የወሰደው የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ነው። ተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ትምህርት ቤትን የሚመጥን የበር መግቢያ ግንባታ ሥራም ተጀምሯል፡፡
ማሕበራችን የሚመራበት የአደራ ቃል አለ። አፄ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤቱን ሲያቋቁሙ ‹‹ይህችን የእውቀት ምግብ ሰጥታ የምታሳድጋችሁ ትምህር ቤት በጥበብ አድጋችሁ በአእምሮ በምትጎለብቱበት ጊዜ እግዚአብሄር እንደየእድላችሁ በሚሰጣችሁ እውቀት የሀገራችን መሳሪያ ናትና እንዳትጠብ እንድትሰፋ፤ እንዳትወድቅ እንድትበረታ እንድትረዷት እለምናችኋለሁ›› ነበር ያሉት። እኛም የቀድሞ ተማሪዎች ማሕበር ኃላፊነት፣ አደራ አለብን ብለን መመሪያችን አድርገናት ነው የምንቀሳቀሰው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ እናመሰግናለን። መልእክት ካለዎት እድሉን ይውሰዱ
ብሥራት (ዶ/ር)፡- በበዓሉ ለመታደም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ብዙዎቹ የቀድሞ ተማሪዎች እንደሚመጡ ተስፋ አለን። ሆኖም ግን ማሳሰብ የምፈልገው ያለብንን ኃላፊነትና አደራ ለመወጣት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ነው። በቀጣይ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብርም ስለሚዘጋጅ ሁሉም ለትምህርትቤቱ እጁን እንዲዘረጋ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም