‹‹እንደ ሀገር በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለውን የሚቲዎሮሎጂ ክስተት መመዝገብ የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው›› – አቶ ፈጠነ ተሾመ

– አቶ ፈጠነ ተሾመ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አኅጉር ፕሬዚዳንት

አንድ ምዕተ ዓመት ከደፈነ እነሆ ሶስት አስርት ዓመታት አልፈውታል። ለ130 ዓመታት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ እየሰበሰበ፣ እየተነተነ እና መረጃውን ለሚመለከተው ባለድርሻ አካል እያጋራ ዛሬ ላይ ደርሷል – የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት። ኢንስቲትዩቱ በተቋም ደረጃ ከመቋቋሙ በፊት በ1954 የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል የሆነና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የራሱን ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ነው።

ይህ ተቋም ዛሬ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለሚመለከተው አካል በማቅረቡ በኩል እየተሰጠው ያለ ግብረ መልስ እንዴት ይገለጻል? የሚቲዎሮሎጂ መረጃ አሰባሰቡን በምን ያህል ደረጃ አዘምኗል? በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አኅጉር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ጊዜ ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ፈጠነ፡- ተቋሙ የተለያዩ ስያሜዎችን ይዞ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ተጨማሪ አገልግሎቶችን በማካተት ራሱን ወደ ኢንስቲትዩት ከፍ አድርጓል። ለምሳሌ ወደ ኢንስትቲዩት ከፍ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የአየር ጸባይ ለውጥ መቋቋሚያ ተግባርና ኃላፊነት መጨመሩ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ክስልጠና እና ምርምር አኳያ በተሰጠው ትኩረት ምክንያት ነው።

ኢንስቲትዩቱ በዚህ ውስጥ ሆኖ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችንም እየተወጣ የሚገኝ ነው፤ በሀገሪቱም ያለውን ከአየር ጸባይ እና ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችል ሰፋፊ ሥራዎችን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ያለ ተቋም ነው። እነዚህን ተግባራት ለማከናወን በአዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት በተጨማሪ የክልል ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላትን በማደራጀት ሰፋ ላሉ እንደ ኦሮሚያ እና አማራ ክልልና ለሌሎች ክልሎችም በስፋት እየሰራ ይገኛል። ለምሳሌ በአማራ ክልል የምስራቅ አማራ እና የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በሚል ዞኖችን እና ወረዳዎችን በስሩ ይዞ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለመሆን በመስራት ላይ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በሶስት ማዕከላት ባሌ ሮቤ፣ አዳማ እና ጅማ ላይ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው። በቀሩት ክልሎች የሀገሪቱም መልክዓምድራዊ አቀማመጧን መሰረት በማድረግ በዚያም አካባቢ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የአየር ጸባይ ሁኔታ ወሰን የማይገድበው በመሆኑ በአንድና በሁለት ክልል ሳይወሰን ለአጎራባችም ጭምር የሚሰራ ነው።

ሥራውን ውጤታማ እና ተደራሽ ለማድረግ ሌላኛው መታሰብ ያለበት በርካታ የሚቲዎሮሎጂ ምልከታ አውታር ዝርጋታ በጣም አስፈላጊ መሆኑ ነው። ስለዚህ ኢንስቲትዩቱ ካለው የአንድ ሺ 372 በሰው መረጃ ከሚሰበሰብባቸው ጣቢያዎች በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ የሆኑ አውቶማቲክ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ወደ 300 የሚደርሱ በመላ ሀገሪቱ ተተክለዋል። ስለዚህ መረጃዎች በ15 ደቂቃ ልዩነት በብሔራዊ መረጃ ቋት ማየት ተችሏል። በዚህ ደረጃ ተቋሙ ዘምኗል።

ሁለተኛው ከአውቶማቲክ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ በተጨማሪ ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ተከላ ተከናውኗል። ቀደም ሲል ሻውራ በሚባል ቦታ በጎንደርና በባሕዳር አካባቢ የተተከለ ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ መካከለኛውን ኢትዮጵያ ለማየት ያስችለን ዘንድ በደብረብርሃን አካባቢ እነዋሪ በሚባል አካባቢ ተከላው ተከናውኖ ሥራ እየሰራ ነው። ሶስተኛ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኢሉ አባቦር ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ተከላው እየተከናወነ ይገኛል። የደቡብ ኢትዮጵያን በተመለከተ ደግሞ ሀድያ ዞን አካባቢ በአንዱ አካባቢ ተተክሎ መረጃ ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

እነዋሪ ላይ የተተከለው በአጠቃላይ ግቡ በሰሜኑ ምዕራብ የሀገራችን ክፍል በተለይ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ያለውን የአየር ሁኔታ ለማየት የሚያስችል የመከታተያ ራዳር ተክለናል። ከዚያ ቀጥሎ መካከለኛ ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ በላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ውስጥ ያሉትን ተፋሰሶች አካባቢ የሚከሰቱ የቅጽበታዊ ጎርፍ አደጋ፣ የወንዞች ውሃ ሙላት፣ የሚመጣውን ከባድ ዝናብ መከታተል የሚያስችል የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ነው።

ሶስተኛው በምዕራብ ኢትዮጵያ የተተከለው ደግሞ በጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጋምቤላና አሶሳ ዙሪያ ማየት የሚችል የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ነው። ሌላኛው አስቀድሜ እንደጠቀስኩት በደቡብ ኢትዮጵያ የተተከለ ነው። እነዚህን መሳሪዎች በመጠቀም በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለውን የሚቲዎሮሎጂ ክስተት መመዝገብ የሚያስችል አቅም እንደ ሀገር እየተገነባ ነው። እየተገነባ ባለው አቅምም ለቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የአደጋ ስጋት ከመከላከል አንጻር፣ ለአቪዬሽን ለአውሮፕላን በረራ አገልግሎት ለመስጠት አንዲያስችል ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው። ይህ በሚቲዎሮሎጂው መስክ የተዘረጋው መሰረተ ልማት ተቋማዊ እድገቱን እያፋጠነ ያለ ነው፤ በተለይ ለውጡን ተከትሎ ራዳሮች ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፊንላንድ መንግሥት ጋር በሚቲዎሮሎጂ ስም ገንዘብ በብድርም ሆነ በድጋፍ መልክ በመጠየቅ በፓርላማ ደረጃ ተወስኖ መሳሪያዎቹ በመግባታቸው ተቋሙን ከጠናከር አኳያ ሰፊ ሥራ እንዲሰራ ያስቻሉ ናቸው

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያሉት ምን ያህሉ ራዳሮች ናቸው? የአንድ ራዳር ዋጋስ ምን ያህል ነው?

አቶ ፈጠነ፡- በአሁኑ ጊዜ እየሰሩ የሚገኙት ሁለት ራዳር ናቸው። በተከላ ላይ ያሉት ደግሞ ሁለት ናቸው። በተከላ ላይ ያሉት ከሁለት ወር በኋላ ወደተግባር ስለሚገቡ በጥቅሉ አራት ራዳሮች በሥራ ላይ ይሆናሉ። የአንዱ ራዳር ዋጋ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዩሮ ነው። ይህ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲቀየር ወደ 330 ሚሊዮን ብር አካባቢ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ራዳሮች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ኢትዮጵያ ከአየር ጸባይ ትንበያ ጋር ተያይዞ በእስካሁኑ ሂደት ምን ያጣችው ነገር አለ? መተከላቸውስ ምን ያስገኘለት ፋይዳ አለ?

አቶ ፈጠነ፡- ዋናው ነገር እኛ የምንሰጠው ትንበያ ነው። የሚሰጠው ትንበያ ደግሞ ትንሽ ወደ ትክክለኛነት ያደላ ይሁን እንጂ መቶ በመቶ ነው ማለት አያስደፍርም። ስለዚህ የተሟላ መሳሪያና ቴክኖሎጂ በታጠቅን ቁጥር የትክክለኛነት መጠኑም የዚያን ያህል እየቀረበ ይመጣል።

በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት መከታተያ መሳሪያዎች እየተተከሉ ነው። የከፍታ አየር መመዝገቢያ ጣቢያዎች እየተተከሉ ነው። እነዚህ መሰረተ ልማቶች መኖራቸው ብቻ በራሱ ግብ አይደለም፤ እነዚህን መሳሪያዎች በአንድ ቦታ ላይ በመያዝ የተቀናጀ የመረጃ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳላጥ እንዲቻል ሰፊ የሆነ መሰረተ ልማት ወሳኝ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሁሉ በቦሌ እየገነባን ያለው ዘርፈ ብዙው ሕንጻ ምቹ የሚያደርግልን ይሆናል። እኛ ብቻ ሳንሆን ባለጉዳዩም መጥቶ ማየት የሚያስችለውን ነው። ለምሳሌ በአንደኛው አካባቢ በተተከለው ራዳር አማካይነት እዛ አካባቢ ያለውን የአየር ሁኔታ መረጃ አንድ የሚመለከተው አካል ቢፈልግ ማየት ይችላል። ስለዚህ እየተገነባ ያለው ህንጻ ለዚያ ሁሉ መሰረተ ልማት ሊሆን የሚችል ነው።

በሌላ በኩል ከዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ከአፍሪካ አኅጉር ጽህፈት ቤትነት በተጨማሪ በቅርቡ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የቀጠናዊ ስልጠና ማዕከል ሆነን ተመርጠናል። ይህ ለእኛ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አኅጉር ለሚኖሩ ለሌሎች ሀገራትም ስልጠና እንድንሰጥ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አንዱ ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን አለበት በሚል ሀገራችን ልትመረጥ ችላለች። በመሆኑም የተቋሙ እድገት ከጊዜ ወደጊዜ ከፍ እያለ የመጣ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት መስጠት ተልዕኳችን ነው ብለን በእቅድ ያየዝነውን ግብ እያሳካ ያለ ተቋም ነው።

አዲስ ዘመን፡- አዲሱ ሕንጻ የሚጠናቀቀው መቼ ነው?

አቶ ፈጠነ፡- ሕንጻው የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት በ2012 ዓ.ም የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ከጄኔቫ ወደ ኢትዮጵያ በሚዛወርበት ወቅት በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አማካይነት ነው። ሕንጻው ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋናው መስሪያ ቤትና የዓለም ሚቲዎሮሎጂ የአፍሪካ አኅጉር ጽህፈት ቤቱ በጋራ ወደ ሕንጻው ለመግባት በመታሰቡ ነው። የሕንጻው ግንባታ በአሁኑ ጊዜ ወደማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በቀጣዩ አዲስ ዓመት ብዙ ነገሩ ይጠናቀቃል ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያ በሰው አማካይነት መረጃ ይሰበሰብ ነበር ብለዋል፤ አሁን ግን 300 መሳሪያ እንዳለ ገልጸዋል። ከዚህስ በኋላ ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለማድረስ በተጠቀሰው ቁጥር ብቻ ይቻላል ወይስ የታቀደ ሌላ ነገር አለ?

አቶ ፈጠነ፡- ተቋሙን ይበልጥ እያዘመንን እንገኛለን። በሰው ይሰበሰብ የነበረው መረጃ ወደ አውቶማቲክ መሳሪያ እየተተካ ይገኛል። እስካሁን የተከናወነው በ300 መሳሪያ ይሁን እንጂ ወደፊት የሚቀጥል ይሆናል። በእርግጥ መሳሪያው በውጭ ምንዛሪ የሚመጣ እንደመሆኑ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፤ ቢሆንም በተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይ ነን። በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወነው የጎርፍ  መከላከል ፕሮጀክት መሰረት ወደ አንድ መቶ ተጨማሪ አውቶማቲክ መሳሪያ ግዥ ለማከናወን በሒደት ላይ ነው። በዚህም ጨረታ ወጥቶ ተጠናቋል። በቀጣዩ ዓመት ወደሀገር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ ፕሮጀክት ደግሞ ከመስኖ እና ቆላማ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወደ አርብቶ አደር አካባቢ 107 ተጨማሪያ መሳሪያዎችን ለመትከል ታቅዷል። በመሆኑም በቅርቡ ከ300 ወደ 507 ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ተገልጋዮች ግብረመልስ የሚሰጧችሁ በምን መልክ ነው? ትክክል ነው ወይም ትክክል አይደለም ይላሉ?

አቶ ፈጠነ፡- ከተተከሉት ጣቢያዎች መረጃዎች ይሰበሰባሉ፤ የመረጃ የጥራት ቁጥጥር የሚባል አለ። እሱ መረጃ ይከማቻል። የተከማቸው መረጃ የሚሰጠው ተተንትኖ ነው እንጂ ጥሬ መረጃ አይሰጥም። በእርግጥ ጥሬ መረጃ የሚፈልጉ ተመራማሪዎች አሉ። የሚሰጠው ለእነርሱ ነው።

ለውሳኔ ሰጪ አካላት፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤና፣ ለአደጋ ስጋት፣ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ደግሞ የምንሰጠው ትንበያ አለ። ይህ ትንበያ ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸውን ሶስት ወቅቶችን በልግ፣ ክረምትና በጋን መሰረት በማድረግ ነው። እነዚህ የበልግ፣ የክረምት እና የበጋ ወቅቶች ከመግባታቸው በፊት ትንበያ የምንሰጥበት ሁኔታ አለ። እነዚህን ትንበያ ስንሰጥ ከውሳኔ ሰጪ አካላት ጀምሮ ባለድርሻ አካላት ባሉበት ነው። መድረኩ “የሰጣችሁን ትንበያ በትክክል ተጠቅመንበታል፤ ወይም ደግሞ አልተጠቀምንበትም፤ የሰጣችሁን ትንበያ ትክክል አይደለም” በሚል በስፋት የሚተችበት ነው። ከዚያም እሱን መሰረት በማድረግ ቀጣዩ ትንበያ ይህ ነው ተብሎ ይፋ ይደረጋል። ይህ ደግሞ በግብርና፣ በውሃ፣ በጤና፣ በአደጋ ስጋት ሴክተሮች ምን አይነት ዝግጅት ማድረግ አለባቸው የሚል ምክረ ሐሳብ የምናቀርብብት መድረክ አለን። ስለዚህ የባለድርሻ አካላትና የመረጃ ሰጪ እና የመረጃ ተጠቃሚዎች የጋራ መድረክ አለን ማለት ነው።

ነገር ግን ለአቪዬሽን ሚቲዎሮሎጂ ማለትም ለአየር በረራ አገልግሎት ወቅት ተጠብቆ የማይሰጥ ስለሆነ በየ24 ሰዓቱ በፈረቃ ጭምር ሰዎች እዚያው ውለው እያደሩ መረጃ ይሰጣሉ። ይህ ደግሞ የእነርሱን ባህሪ መሰረት በማድረግ ለብቻቸው ከሲቪል አቬዬሽን፣ ከአየር መንገድ የግል አውሮፕላን ያላቸው ግለሰቦች ጭምር ያሉ ሲሆን፣ የእነርሱ መድረክ ደግሞ ለብቻ የሚካሔድ ነው። በዚህ መልኩ የድርሻችንን ሁኔታ እንገመግማለን ማለት ነው። እኛም ቅሬታ ካለንና እነርሱም ያላረኩበት መረጃ ካለ ቅሬታቸውን የሚገልጹበት መድረክ አለን። የእነርሱ የእርካታ ደረጃ መጠይቅ ተበትኖም ጭምር የሚገመገምበት ሁኔታ አለ። በጥቅሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጣም የተቀናጀ የምክር አገልግሎት አለን። የኢንስቲትዩቱ ትንበያ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።

አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ እራሱ የሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜን የአየር ትንበያን ለግብርና እና ለመሰል ሴክተር ምክረ ሐሳብ ይሰጣልና የዘንድሮ የአየር ትንበያ እንዴት ይገለጻል? የአየር ሁኔታው የሚያመላክተው ምንን ነው?

አቶ ፈጠነ፡- የዘንድሮን በተመለከተ እንደሚታወቀው አሁን የበልግ ወቅት ሲሆን፣ ይህም ከየካቲት እስከ ግንቦት ድረስ ያሉ ወራትን የያዘ ነው። የበጋ ወቅት ደግሞ ከጥቅምት እስከ ጥር ድረስ ሲሆን፣ የክረምት ወቅት፣ ከሰኔ ጀምሮ እስከ መስከረም ያሉትን ወራት የሚያካትት ነው። እነዚህ ወቅቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተለያየ እንድምታ አላቸው። ለምሳሌ በማዕከላዊ አካባቢ ክረምት ሁልጊዜ ዝናብ ነው። በልግ ዋንኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነባቸው አካባቢዎች ግን ክረምት ደረቃማ ነው። ይህ ማለት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ደቡብ ኦሮሚያ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ የባሌ ቆላማ ዞኖች በልግ ዋንኛ የዝናብ ወቅታቸው፤ በጋ ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። ስለዚህ በክረምት ወቅት እነርሱ ዘንድ ዝናብ የሚጠበቅ አይደለም። ቢዘንብ እንኳ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተብሎ የሚፈረጅ ነው።

የሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍል፣ ከመካከለኛ አጋማሽ ጀምሮ ያሉ አካባቢዎች ደግሞ ክረምት ዋንኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። አሁን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚዘንበው ዝናብ እና የበልግ ዝናብ በልግ ለእኛ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታችን ነው። ይህ የሚጠበቅ ነው። ለእርሻውም ለእንስሳቱም አስፈላጊ ነው። ይሁንና ዋንኛ የዝናብ ወቅታችን አይደለም። ለምሳሌ የምስራቅ አማራ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የምስራቅ ትግራይ አካባቢዎች በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። በክረምቱም ወቅት ዝናብ ያገኛሉ። ደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግን በልግ ዋንኛ የዝናብ ወቅታቸው ሲሆን፣ በጋ ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው።

አሁን ባለንበት ወቅት ለምሳሌ ቦረና፣ ሱማሌ ዝናብ ማግኘት ያለባቸው ክልሎች ናቸው፤ አሁን ባለንበት ጊዜ ዝናብ የማያገኙ ከሆኑ በቀጣይ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የሚጠብቁ ይሆናሉ። አሁን ዝናብ አላገኙም ማለት በቀጣዩ ዓመት የድርቅ ችግር ሊያደርስ ይችላል። ከብቶቻቸውም ጉዳት ይደርስባቸዋል። ባለፈው እኤአ በ2020 እና 2022 አካባቢ የተከሰተው ድርቅ በዚህ አሁን ባለንበት አይነት ተከታታይ ወቅቶች መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ ነው።

አሁን ያለንበት የበልግ ወቅት ከመግባቱ በፊት ጥር ላይ ትንበያ ተሰጥቷል። በመሆኑም ከውሳኔ ሰጪ አካላት እስከ ተጠቃሚ ሴክተሮች ድረስ የተሳተፉበት መድረክ በልግ ሊኖረን የሚችል ወይም የአየር ንብረት ጥናት (Climatology) አጠቃላይ በመደበኛ ሁኔታ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ ሲሆኑ፣ እነዚህ አካባቢዎች ዓመቱን ሙሉ ማለትም እስከ ስምንት ወራት ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ናቸው። የተተነበየውም ጥሩ የዝናብ ወቅት እንደሚኖር ነው።

በልግ እንደ ወቅት ለትንበያ የሚያስችግር አይነት ሁኔታ አለው። ምክንያቱም ካሉት ወቅቶች ውስጥ የሚዋዥቅ ሁኔታ የሚታይበት ወቅት በመሆኑ ነው።

እኛ የምንሰጠው የአራት ወር ትንበያ ነው። ይህን አይነት ትንበያ የሚሰጡ ሀገራት ብዙ አይደሉም። ትንበያ የሚሰጡት የአጭር የአጭር ጊዜውን ነው፤ ማለትም ቀረብ ቀረብ እያሉ ነው። ምክንያቱም ለአራት ወር መተንበያ አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ኢ-ተገማች የሆኑ ክስተቶች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ የተተነበየውን ትንበያ የመለወጥ አቅም ይኖራቸዋል፡

ዋናው ነገር የኢትዮጵዮያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ ከሰጠ በኋላ በየመሃሉ በአስር ቀን፣ በየወር የሰጠውን ትንበያ እያሻሻለ ይሄዳል። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የተተነበየው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ነው። ሌሎቹ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ደግሞ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያ ተሰጥቷል። የተወሰኑት የደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ተተንብየዋል። በጥቅሉ በበልግ ወቅት የሚጠበቀው ዝናብ እየተገኘ ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፋዊ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶችን በመተንተን ኢትዮጵያን ምን ያህል ታድጓታል? ለአብነት ቢጠቅሱልን?

አቶ ፈጠነ፡- የዓለም አቀፍ ትንበያ ማዕከል የምንለው የሕንድ ውቅያኖስ ላይ፣ ሜዲትራንያን ባሕር ላይ የኢሊኖ ወይም የላሊና ክስተት አለ ብሎ የሚተነብይ ተቋም አለ። በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል የሆኑት የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ትንበያ ማዕከላት ተብለው የሚጠሩ ናቸው። በተለይ የወቅት ትንበያ በምንሰጥበት ወቅት እሱን እንደግብዓት እንጠቀማለን። ትንበያውን ይፋ ከማድረጋችን በፊት በትንበያው ዙሪያ ወደ አንድ ሳምንት ያህል ክርክር እናደርጋለን። ከዚህ የተነሳ ዓለም አቀፍ የትንበያ ማዕከል የተነበዩትን ነገር በአግባቡ እናያለን ማለት ነው።

በአሜሪካን ሀገር የአሜሪካ ብሔራዊ የከባቢያዊ እና ውቅያኖስ አስተዳደር ተብሎ የሚጠራው የአፍሪካ ዴስክ አለው። ስለዚህ እሱም ከትንበያ አንጻር ያለው ምንድን ነው? ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ምንድን ነው ያሉት? የሚለውን በማጤን በሀገራችን ያለው እንድምታ ምንድን ነው? የሚለውን የሀገራችንን መረጃ አክለንበት የረጅም ጊዜ ትንበያ የአየር ጸባይ ለውጡ ምን ይመስላል? የሚለውን ከግንዛቤ አስገብተን ከራሳችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ደግሞ እናያለን።

ስለዚህ በዚህ ደረጃ የዓለም አቀፉ ትንበያ እንደ ግብዓት ይወሰዳል። የዓለም አቀፉ ሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እንደ ግብዓትነት ይወሰዳል። የሳተላይት መረጃዎቻችንን እናያለን። እኛ የሰበሰብናቸውን የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ከግምት እናስገባለን። ኢትዮጵያ ደግሞ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል ናት። የሚጠበቅባትንም መዋጮ ታዋጣለች። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆናም እየሰራች ነው። እኔ ደግሞ የቀጣናው ፕሬዚዳንት ነኝ። የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ አባል ሆነንም እየሰራን ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ያላት ሀገር ነች ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ጥንቃቄና ርምጃ መውሰድ እንዲችል የምትሰጡትን መረጃ ወይም ምክረ ሐሳብ ያልተጠቀመበት ወይም የማይጠቀምበት አለ? የገመገማችሁት ነገር ካለ ቢገልጹልን?

አቶ ፈጠን፡- በአሁኑ ጊዜ በጣም ተሻሽሏል፤ እኤአ ወደ 2003 እና 2004 አካባቢ የተሳታፊው ቁጥር ዝቅተኛ ነው፤ ሲጋበዙም ብዙ ሰው መጥቶ አይሳተፍም። መረጃውን ለመስጠት የምንጽፈው ደብዳቤ ነው። በዚህ ውስጥ ግን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አይቀሩም። ምክንያቱም የእኛን ትንበያ መሰረት አድርጎ ድርቅ ወቅት ከሆነ መረጃ ከወዲሁ ለማሰባሰብ ያመቸው ዘንድ የሚሰጠውን መረጃ በትጋት ይከታተላል።

ነገር ግን ባለፉት አስር ዓመታት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ የማወቅ ጉጉቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነወ። በተጨማሪም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው መድረክ አቅጣጫ ይሰጣል፤ ስለዚህ የሚቲዎሮሎጂን መረጃ ሰምቶ የማይተገብር አካል የለም። በሚዘጋጁ መድረኮች ላይም በተገቢው መልኩ ይገኛሉ። ግብርና ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የእነዚህ መስሪያ ቤቶች ሚኒስትሮችና ኃላፊዎች በመድረኩ ይገኛሉ ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በመረጃ አሰባሰቡ፣ አደረጃጀቱና አተናተኑን በተመለከተ የዘመነ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ፈጠነ፡- ሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰብ ከጀመረ ወደ 130 ዓመታት ያህል አስቆጥሯል ማለት ይቻላል፤ ምንም እንኳ በዚያን ጊዜ እንደ ዛሬው ተቋም ሆኖ ባይመሰረትም፤ በወቅቱ መረጃ መሰብሰብ ተችሏል። በመሆኑም ለ130 ዓመታት የተሰበሰበ መረጃ አለ። ከዚህ የተነሳ ተቋሙ ትልቅ የሚቲዎሮሎጂ ሀብት አለው። እንደ ሀገር የመጀመሪያው ጣቢያ አዳሚቱሉ ሲሆን፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ጋምቤላ ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዚያ ጣቢያዎች እየተስፋፉ ሔደው አንድ ሺ 372 መድረስ ችለዋል። ከእነርሱ የተሰበሰቡት የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች በተደራጀ ሁኔታ ‹‹በሃርድ ኮፒ›› ተሰንደዋል። ‹‹በሃርድ ኮፒ›› መሰነድ ብቻ ሳይሆን መረጃዎቹን ከውድመት ለመታደግ ዲጂታይዝድ መደረግ አለበት በሚል ዳታን ከአደጋ መከላከል የሚል ፕሮጀክት ተነድፎ አጠቃላይ ያለውን መረጃ ከ85 በመቶ በላዩን ስካን በማድረግ ወደ ዲጂታይዝ መቀየር ተችሏል። ስለዚህም ተቋሙ ዘምኗል የሚያስብለው አንዱ፤ ነባሩን መረጃ ወደ ዲጂታላይዝ መቀየርና ማስተካከል መቻሉ ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አዳዲስ መሳሪያዎችን በመትከል የሚቲዎሮሎጂ አሰባሰብ ሒደታችንን እያዘመንን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- የዓለም ሚቲዎሮሎጂ የአፍሪካ ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ መሆኑ ከበፊቱ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው?

አቶ ፈጠነ፡- የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ማለት ልዩ ባህሪ ያለው ተቋም ነው። ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው ከተባለ፤ በጤና፣ በአየር ሁኔታ፣ በአየር ንብረት፣ በአየር ጸባይ ለውጥ፣ በውሃ ላይ እና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ቴክኒካል ተቋም በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህ ድርጅት በስትራክቸሩ መሰረት ወደ ስድስት ቀጣናዎች አሉት። አንዱ ቀጣና አፍሪካ ነው። ስለዚህ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ከስድስቶቹ አንዱ ነው።

ከዚህ ቀደም ጽህፈት ቤቱ የነበረው ቡሩንዲ ነው። ቡሩንዲ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት አካባቢው ምቹ አይደለም በሚል ወደ ጄኔቫ ተዛውሮም ነበር። በኋላ ላይ ግን ወደ አህጉሩ መመለስ አለበት በሚል የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ኮንግረንሱ ወሰነ። ጽህፈት ቤቱን ወደ አህጉራቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ተብሎ ሲጠይቅ ፍላጎታቸውን ካሳዩ አስር ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። አስሩም በየደረጃው ተገምግመውም ነበር፤ በወቅቱ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ክቡር ታዬ አጽቀስላሴ በዚያን ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩና ጽህፈት ቤቱ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ መሆን የሚያስችለው አንድ ሺ አንድ ምክንያት አለ ሲሉ ተናግረው፤ ይህንኑ አብራርተዋል። አንደኛው ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙዎችን የአፍሪካ ሀገራት የሚያስተሳስር ነው። ሁለተኛው የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ነው። ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ብትመረጥ ሁሉንም በእኩልነት ማስተናገድ ትችላለች ብለዋል። ሌላው ምክንያት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትም ይህን ሁኔታ ለማስተናገድ አቅም አለው። ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ጋርም ስንነጻጸር በጣም ትልቅ ሕዝብ ያለን ትልቅ አቅምም ያለን ስንሆን፤ ብዙ ሀገራትንም የምናገለግል ነን።

አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ሚቲዎሮሎጂ ስንመለከት የኢትዮጵያን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን አያክሉም። እኛ ከዚህ አንጻር የመንግሥት ትኩረት ያለንን ነን። በቅርቡ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ለመትከል እያደረግን ባለው እንቅስቃሴ መንግሥት ለሌሎቹ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሰጠውን ያህል እኩል ትኩረት ሰጥቶናል። ቦሌ ላይ እየተጠናቀቀ ያለው ሕንጻም ቢሆን ያስፈልጋል ብሎ አምኖ በቁርጠኝነት ያደረገው ተግባር ነውና በዚህ እና መሰል ምክንያቶች በብዙ ውድድር ታምኖበት ጽህፈት ቤቱ እዚህ መሆን ችሏል።

ከአንድ ወር በፊት የተወሰነው ነገር ቢኖር የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ቀጣናዊ የስልጠና ማዕከል መሆኑም ጭምር ነው። ቦሌ ላይ እየገነባነው ያለው ሕንጻ አንደኛ የአስተዳደር ሕንጻ ነው። ሁለተኛ የቴክኒክ ሕንጻ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የስልጠና እና የምርምር ማዕከል ነው። ይህ ማዕከል ከዩኒቨርስቲዎች ጋር የሚሰራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው እየሰራ ያለው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ነው። የስልጠና ማዕከላቱ አንደኛ የራሳችንን ባለሙያዎች የምናበቃበት ነው። ከዚያ ቀጥሎ ለሌሎች ለአፍሪካ ቀጣና ሀገራትም ስልጠናዎች የሚሰጡበት ነው። ማዕከሉ እዚህ በመሆኑ እኛ እንደ አንድ ተቋም ተጠቃሚ ነን። የአፍሪካ ሀገራትም ብዙ ጊዜ ወደሀገራችን ስለሚመጡ እግረ መንገዱንም የቱሪዝም ዘርፉ እያደገ ይሄዳል። ሀገራችን የኮንፈረንስና የስልጠና ማዕከል እየሆነች ትሔዳለች።

ስለዚህ ሚቲዎሮሎጂ በአንድ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርንም ሥራ እየሰራ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ትልልቅ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንፈልጋለን። የውጭ ተቋማት ወደሀገራችን መምጣተታቸውና በዚህ ሀገር መስራታቸው ተከፋይነታቸው በዶላር ነውና ለሀገራችን አንድ ግብዓት ነው። ሴክተሩ እዚህ በመሆኑ የሚከናወኑ መድረኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ይበዛሉ። የሰው ኃይል ለማብቃትም ማሰልጠኛው እዚህ በመሆኑ ውጭ ልከን ልናሰለጥን የምንችለው አንድ፤ ቢበዛ ሁለት ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል። እዚህ በመሆኑ ግን እስከ አስር ሰውም ማሰልጠን እንችላለን። ከሌሎች ሀገራትም በስኮላርሽፕ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። ማሰልጠኛውን እያዘመንን እንሔዳለን።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ፈጠነ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You