ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) – የመጋቢት 24 ንግግሮች በጥቂቱ

በቅርብ ባሳለፍናቸው ዓመታት ውስጥ በሀገራችን ብዙ የለውጥ መንገዶችና ወጣገባ ጉዞዎችን አድርገናል። በነዚህ ጥቂት ዓመታት በሀገራችን የሆኑና የምናስታውሳቸው ዓበይት ጉዳዮች ብዙ ቢሆኑም፣ በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን የመጡበት ጊዜ ትልቁ ክስተት ነበር። መጋቢት 24 ቀን በታሪክ ልዩ ቀን ሆና እንድትታወስ ያደረጋት አንደኛው ምክንያትም ይህ ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም እንዳለፉት ከሰማንያ በላይ ዓመታት ሁሉ እያንዳንዱ የሀገራችን እርምጃ እልፍ ጉዳዮችን እየሰነደ አኑሮታል። ከዚሁ ማኅደር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ዓመታት መጋቢት 24 ላይ ካደረጓቸው ንግግሮች መካከል አዲስ ዘመን ለንባብ ያበቃቸውን ጥቂቱን እንደሚከተለው ቀንጨብ አድርገን እናስታውስ።

“ከሁሉ አስቀድሜ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ለተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሔ አካል ለመሆን፤ የሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፤ ለአሕጉራችን ምሣሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ። ”

“ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቷ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ። ከሁሉ አስቀድሜ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍትሔ አካል ለመሆን፣ የሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፣ ለአኅጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ። በተመሳሳይ የመንግሥታዊ ሥልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫወቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ሕዝባችን ስም ከልብ አመሠግናለሁ። ”

“ዕለቱ ለሀገራችን ታሪካዊ ቀን ነው። …አሁንም ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ ዕድል ነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል። ”

ትናንት አባቶቻችን በመተማ፣ በዓድዋና በማይጨውና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩዋት ሀገር አለችን። እኛ ዕድለኞች ነን። ውብ ሀገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ሕዝብ ነን። ኅብረታችንን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ፣ ለሌሎች ሕዝቦችም የነፃነት ትግል አርዓያ ሆኗል።

“ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር ስሜት ዘወትር የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀደመው ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትሕ እንዲጠበቅ፣ ብልፅግና ያለ አድልዖ ለመላው ዜጎች ይዳረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ፤ ይደክማሉ። በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው ስለ ሀገር አንድነትና ሰላም፣ ስለ ፍትሕና እኩልነት እንዲሁም ስለ ብልፅግና ይጮኻሉ…”

“ዴሞክራሲ ለእኛ ባዕድ ሀሳብ አይደለም። … ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ዴሞክራሲ መደማመጥን ይጠይቃል። ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፣ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው። ”

“በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆን ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚሁ ነው። ”

“ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋሓደ ነው። አማራው በካራማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤኒሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሀዲያውና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋሕደዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን። ”

(አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም)

—-

“ኢትዮጵያውያን ሰይፍ ያስፈልገናል። …እኔ ያለ እናንተ ምንምና የማልረባ ነኝ። …የጎደለና ያልተሟላ ነገር ካለ በከፍተኛ ትሕትና ኢትዮጵያውያንን ቆሜ ሳይሆን ዝቅ ብዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ቁጣና ተግሳጻችሁ ለእኔ ሽልማቴ ነው፤ ተስፋ ጥላችሁብኝ በዳተኝነት ሳይሆን ከዕውቀት ማነስ የተነሳ ያልሠራሁት ከሌለ በስተቀር ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ እንዳገለገልኩ እረዳለሁ። …ዓላማዬ በነፃነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን መፍጠርና ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ነው እንጂ፤ ምንም የሸፍጥ ሀሳብ የለኝም።

“ቱሪዝምን በሚመለከትም በመጪው መስከረም ወር ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በሙዚየምነት ከአዳዲስ ሥራዎች ጋር ለሕዝብ ክፍት ይደረጋል። በቀጣይ ዓመትም አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክትም ቢያንስ አንድ አራተኛው ይጠናቀቃል። ”

“ኢትዮጵያ ምትክ የሌላት ብቸኛ ሀገራችን ናት። ለውጡ ብዙዎች የሞቱለት፤ የተገረፉለት፤ የታሰሩለት፣ የተሰደዱበት፣ ያለቀሱበት፣ የጸለዩበት የሁላችን ድምር እንጂ፤ የጥቂት ግለሰቦች አልነበረም። በብዙዎች የመጣን ለውጥ በተባበረ ክንድና በመደመር ሃሳብ መጠበቅና ማስቀጠል ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚጠበቅ አደራ ነው።

“አንድም ቦታ ጠይቀን ድጋፍ ሳናገኝ የተመለስንበት ዓለም የለም። …በዓመት ውስጥ ከአውሮፓም፣ ከአሜሪካም፣ ከቻይና እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ድጋፍ ተገኝቷል። ”

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት ሥርዓቱን ለማሳደግ ዋነኛው ምሰሶ መንግሥት ስለሆነ መንግሥት አርቆ አሳቢና ሆደ ሠፊ መሆን ካልቻለ ዴሞክራሲን መገንባት ያስቸግራል። ”

(አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም)

“ውድ የሀገሬ ሕዝቦች፤ የሕዳሴው ግድባችንን ግንባታ የጀመርንበትን ዘጠነኛ ዓመት በምናከብርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ሁለት ጉልህ ፈተናዎች ገጥመውናል።

አንደኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ራሱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን የተመለከተ ጉዳይ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው ለእኛ ለሰው ልጆች ትልቁ ፀጋችን ሕይወት ሲሆን ይሄን ድንቅ ፀጋ ሊነጥቀን የኮሮና ወረርሽኝ የእያንዳንዳችንን በር እያንኳኳ ከደጃችን ቆሟል። …በአሁኑ ሰዓት ወረርሽኙ 201 ሀገራትን አዳርሷል። ከፍተኛ ስርጭት የተመዘገበባቸው 10 ግንባር ቀደምት ሀገራት ከጠቅላላ የኮሮና ተጠቂ 80 በመቶውን ይሸፍናሉ። 90 በመቶ የሚሆነው የኮሮና ሞት የተመዘገበው በእነዚህ ሀገራት ነው።

በሀገራችን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ዛሬ 26 ቢሆንም በሚቀጥሉት ሳምንታት ቁጥሩ ሊያሻቅብ ይችል ይሆናል። ምናልባትም ሞት ያጋጥመንም ይሆናል። አሁን በሽታው ከአዲስ አበባ አልፎ በክልል ከተሞችም እየታየ ነው። ለቁጥጥር እንዳያስቸግር አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው መንደሮች እንዳይገባ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናል። በመንግሥት በኩል የጥንቃቄ ሕጎችን በጥብቅ ለማስፈጸም፣ የመከላከያና የሕክምና ቁሳቁሶችን በየቦታው ለማዳረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

ውድ የሀገሬ ሕዝቦች፤ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከምትጠነቀቅላቸውና በስስት ከምታያቸው ፀጋዎቿ ሁለተኛው የሕዳሴ ግድባችን ነው። የሕዳሴ ግድባችን ከዕለት ጉርሳችን ቀንሰን በተባበረ ክንድ እየገነባን እዚህ ያደረስነው ብቻ ሳይሆን የማድረግ አቅማችንን ያሳየንበት ትልቁ ፀጋችን ነው። ለግድባችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጠው አንድም የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ ሁለትም የትስስራችን ገመድ በመሆኑ ጭምር ነው። የፊታችን ክረምት ግንባታው ተገባዶ የውሃ ሙሌ ት እንጀምራለን።

የኮሮና ወረርሽኝ በዚህ ወቅት መከሠቱ ትኩረታችንን ቀንሶ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን በማጓተት ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው። በወረርሽኙ ምክንያት ተዘናግተን የግድብ ባለቤት የመሆን ጉዟችን ማዝገም የለበትም። እስከዛሬ አሳድገን አሳድገን ፍሬውን ለማየት የጓጓንለት ልጃችን አሁን በተጋረጠብን አደጋ ምክንያት ፍሬውን ከማየት መገታት የለብንም።

ቤት በመቀመጥና ቶሎ ቶሎ ንጽሕናችንን በመጠበቅ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል በአንድ በኩል፤ የሕዳሴ ግድባችን ግንባታው ተጠናቆ በቶሎ የውሃ ሙሌቱ እንዲጀምር በአቅማችን መዋጯችንን መላክ በሌላ በኩል ከሁላችንም ይጠበቃል። በእርግጥ ጊዜያችንን በሥራ ስናሳልፍ የነበረን ሰዎች ለኮሮና ሲባል ቤት ውስጥ መቀመጥ አስቸጋሪ ነው። ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራዎችን ሊያደርስብንም ይችላል። ሆኖም ግን በሌላ መልኩ ካየነው ይሄንን አጋጣሚ ለመልካም ተግባራት ልናውለው እንችላለን።

ኮሮናን ለመከላከልም ሆነ ግድቡን ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ በማሸነፍ ወኔ መነሣት አለበት። …የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት እንዲረዳ በሚል በተዘጋጁ የመልዕክት መላኪያ ቁጥሮች አማካኝነት ጥቆማና ድጋፍ ስናደርግ በተመሳሳይ ለሕዳሴው ግድብ በ8100 ላይ A ብለን በመላክ የድጋፍ ቤተሰብነታችንን ማረጋገጣችንን እንቀጥላለን። በዚህ መልኩ በመጪው ወራት ውስጥ በዝቅተኛ የጉዳት ሰለባ ኮሮናን ከሀገራችን አጥፍተን፤ በአፋጣኝ ሕዳሴ ግድባችንን የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት አጠናቀን ሁላችንም ስኬታችንን ለማየት እንደምንበቃ አልጠራጠርም። በእርግጥ በተባበረ ክንድ ከሠራን ኮሮናንም እንከላከላለን፤ ግድቡንም እንጨርሳለን።” ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

(አዲስ ዘመን መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም)

——

“ምሑራንና ኮሚሽኑ አስተያየትና ምክረ ሐሳባችሁን የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የታሪካዊ ጉዟችን የላቀ እንዲሆን እማጸናለሁ። የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሀገር ስምምነትን በምትፈልግበት በዚህ ወቅት አማካይ ሆናችሁ ሁሉን የማስማማት አደራ አለባችሁና የማቀራረቢያውን መድረክ በማገዝ ሀገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ከልብ በመነጨ ትሕትና እጠይቃለሁ። … ሕዝብ ያላከበረው እና ሕዝብ ያልደገፈው እንቅስቃሴ ውጤቱ መና ነውና መላ ኢትዮጵያውያን ድጋፋችሁ፣ ተሳትፏችሁ፣ ክብራችሁና ጸሎታችሁ ከኮሚሽኑ እንዳይለይ ከታላቅ አክብሮት ጋር እጠይቃለሁ። ”

“በለውጥ ሂደት ወቅት ግባችንን ለማሳካት ከመተባበር ይልቅ በጥቃቅን ጉዳዮች እርስ በርስ መጓተቱን ስለምናስቀድም በመጀመሪያ ተጨናግፎ ይቀራሉ። መጨናገፋቸውን ልብ የምንለው ዘግይተን በመሆኑ ዕድሎቹ ካለፉ በኋላ እንደ ሀገር መልሰን እንቆጭባቸዋለን።”

“የቀደመውን ትውልድ ይሄንን ያንን ቢያደርግ ኖሮ፤ እያልን እንደምንወቅሰው ሁሉ፣ የቀደመው ትውልድም ከእሱ በፊት የነበረውን ትውልድ ሲኮንን ነበር። ከዚህ የታሪክ አዙሪት ለመውጣት እስካልወሰንን ድረስ ነገ የእኛም ዕጣ ካለፈው የተለየ አይሆንም።

(አዲስ ዘመን መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You