
-አቶ አዝመራ እንደሞ ከሎ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በፓርላማ ብቅ ብለው ዛሬ ድረስ ከብዙዎቻችን ሕሊና የማይጠፋ ንግግር አደረጉ። ከእዛ እለት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ገቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2010 ዓ.ም እንዴት ወደ ሥልጣን መጡ?፤ የሥልጣን ሂደቱን እና የብልፅግና ፓርቲ አፈጣጠርስ ምን ይመስላል?፤ በተለይም በምርጫ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ምን ተጨባጭ ውጤቶች ተገኙ?፤ ለምርጫ 2018 ምን ዝግጅት እየተደረገ ነው? በሚሉና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ እንደሞ ከሎ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ መሪነት የመጡበትን ሁኔታ ቢያስታውሱን?
አቶ አዝመራ ፦ ዐቢይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን የመጡት ከብልፅግና በፊት በኢሕአዴግ ውስጥ እያሉ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተካሂዷል። ሆኖም ሽግግሩ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለ የግለሰቦች ሽግግር ነው የነበረው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የደኢሕዴን እንዲሁም የኢሕአዴግ አባል የነበሩ ሲሆን የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኦሕዴድ አባል ነበሩ፤ ኋላ ላይ ብልፅግናን የፈጠሩ የመሠረቱ ናቸው። ወደ ሥልጣን የመጡበት ሂደትም ከዚሁ ጋር የተሰናሰለ ነው። ሂደቱ ሽግግር ነው።
ሆኖም ሽግግሩ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለ እና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መካከል የተደረገ የግለሰቦች ሽግግር ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተካሂዷል ማለት ቢቻልም ሰላማዊነቱ አሁንም በግለሰብ ደረጃ ነው። ወደ ብልፅግና ስመጣ ዶሮ እንቁላል እንደምትጥል ብልፅግና ከኢሕአዴግ ውስጥ ነው የተወለደው። ዶሮ እንቁላል ትጥላለች፤ ከእንቁላል ውስጥ ጫጩት እንደሚወጣው ነው የብልፅግና ውልደት።
አዲስ ዘመን፦ እንደሀገር ከለውጥ በኋላ ዴሞክራሲ በመገንባት ረገድ ምን ተጨባጭ ለውጥ መጣ?
አቶ አዝመራ ፦ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2006 እስከ 2009 አካባቢ ጀምሮ የሕዝብ ጥያቄዎች እየሰፉ የመጡበት ጊዜ ነበር። ይሄ የሕዝብ ጥያቄ በጣም ጎልቶ የወጣው ደግሞ 2009 እና 2010 ዓ.ም ላይ ነው። የመልማት፤ የዴሞክራሲ፤ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነበሩ። በወቅቱ የነበረው መሪ የአራቱ ክልል ብሔራዊ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ፓርቲ ኢሕ አዴግ ነው።
ሕዝቡ የሚፈልገውን ካለመመለስ ጋር ተያይዞ የሕዝብን ገፊነት እና በኢሕአዴግም ውስጥ ያሉ አካላት በተለይ አሁን ከደረስንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን አኳያ ለውጡን መምራት ፤ ሕዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ ማስተናገድ፤ የአሠራር ሥርዓት መቀየር መለወጥን የሚጠይቁ ስለነበሩ እንዳልኩት ብልፅግና ከዚህ ውስጥ ለመወለድ ቻለ። ከነዚህ አካላት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው። በመሆኑም ለውጡን በፊት አውራሪነት በመምራት እንዲሁም የሕዝቡን ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ በ2010 ዐቢይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጡ። ይሄ ታሪክ ዛሬ ሰባተኛ ዓመቱን ይይዛል። በነዚህ ሰባት ዓመታት የመጡ ለውጦችን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ቢሆንም አንዱ ተጨባጭ ለውጥ ዴሞክራሲን ከመገንባት አኳያ የመጣው ለውጥ ነው።
አንደኛ አንዱ የዴሞክራሲ መለኪያ መብትና ግዴታን በቅጡ ማወቅ ነው። ሁለተኛ ሕግና ሥርዓትን ማክበር ለዚህ ሕግና ሥርዓት ተገዢ መሆን ነው። ሦስተኛ የሚወጡ አዋጆች፤ ሕጎች ለሕዝብ ጥቅም ናቸው ወይ ብሎ ማሰብ ነው። ከሕጉ ስንነሳ በለውጡ ዓመታት ሁሉም ሕጎች ለሕዝብ ጥቅም በመውጣታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ ታሪክ ተቀይሯል። ለሕዝብ ጥቅም በወጡ አዋጆችና ሕጎች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ ቡድን በዚህ አግባብ ውስጥ በተገቢው መንገድ እየተጠቀመ ነው አይደለም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨባጭ ግን ዜጎች በአደባባይ የመሰላቸውን ሀሳብ ያለ ገደብ የመግለጽ ዕድል በኢትዮጵያ ምድር ተረጋግጧል።
ሃይማኖቶች ነፃነታቸው በመረጋገጡ በአደባባይ ለመሰበክ በቅተዋል። በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በሌሎች መንገዶች ሃሳቡን በአደባባይ የሚገልጽ ዜጋ ሰዶ ማሳደድ፤ ማሰር፤ ማሰቃየት አይደርስበትም። እንደሀገርም የምንከተለው ሥርዓት፤ ብሔረሰቦችን፤ ቋንቋዎችን፤ ታሪኮችን ግለሰቦችን የሚያከብር እንዲሆን ሥርዓት ተዘርግቷል።
እዚህ ጋር በቅድሚያ ከ2010 በፊት የነበረው የሕዝብ ጥያቄ ምንድነው ብሎ ማየቱ ጠቃሚ ነው። ወጣቱ ምን ይጠይቃል?፤ አርሶ አደሩ ምን ይጠይቃል?፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረ ጥያቄ ምንድን ነበር?፤ ዳርም መሐልም ያሉ ክልሎች፤ ሕዝቦች ምን ፍላጎት ነበራቸው?፤ የተመለሱት ጥያቄዎች ምን ነበሩ? የሚሉትን ለመመልከት ተሞክሯል።
ከለውጡ በፊት ወደ ሀገር ለመግባት ምሕረት ይደረግልኝ ጥያቄ ነበር፤ የብሔር የማንነት ጥያቄ ነበር፤ እነዚህ ከሞላ ጎደል የምሕረት ጥያቄ በተሟላ ተመልሷል ተብሎ እንኳን ባይወሰድ ለመመለስ ጥረት ተደርጓል። የማንነት፤ የብሔር፤ የቡድን መብቶች የተመለከቱ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድም የተሻሉ ነገሮች ነበሩ።
ሆኖም ዴሞክራሲ ጥያቄ አንድ ቦታ ተጀምሮ ሌላ ቦታ የሚያበቃ አይደለም። ቀጣይነት አለው። በዚሁ ሁኔታም የዴሞክራሲ ጥያቄ እስከ ለውጥ ቀጥሎ ነበር። ይሄን የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ የመጀመሪያው ጉዳይ የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንከባለሉ የመጡ ጥያቄዎች፤ በእውነት አሉ ወይስ የሉም ብሎ መፈተሽ ነው።
የለውጡ ሥርዓት እንደገባ በኋላ 2010/መጋቢት 24 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገቡ ፓርላማ ውስጥ ያደረጉት ንግግር ነበር።
በነገራችን ላይ ይሄ ንግግር እስከዛሬም ይሠራል። ሁሉንም ነገሮች በሚገባ አጢኖ ወደ ኋላ ተመልሶ ያንን ንግግር ለሚያዳምጥ ሰው መደመርን፤ የመደመር መንገድን፤ የመደመር ትውልድን፤ የኢኮኖሚ፤ የዲፕሎማሲ፤ የፖለቲካ፤ የዴሞክራሲ ሪፎርም ሁሉ እዛ ንግግር ውስጥ ነበሩ።
ፓርላማ ላይ ያደረጉት ንግግር ዜጎች፤ እንደ ግለሰብ የመረዳት እና አረዳድ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ያቋም ለውጥም የለም፤ የሀሳብ ለውጥም የለም እስካሁን ቀጥሏል። በመጣንበት ዓውድ ውስጥ የነበሩ ጥፋቶችን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ እንዲኬድባቸው ሆኗል። ችግሩን ከሥር መሠረቱ ተረድቶ መነሳት አንዱ በራሱ ለውጥ ነው።
በሌላ በኩል ችግሮቹን የሚፈቱ የአሠራር ሥርዓቶች፤ የሕግ ማሻሻያዎች፤ የአዋጅ ማሻሻያዎች፤ ተደርገዋል። ሕዝብን ማዳመጥ፤ የፖለቲካ ምሕዳርን ክፍት ማድረግ፤ የግል እና የሕዝብ መገናኛ ብዙኃንን፤ የዴሞክራሲ ተቋማትን እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ ዕንባ ጠባቂን እና ሌሎች ተቋማት በአዲስ መልክ መፍጠር አስፈላጊ ነው ተብሎ እንዲፈጠሩ ተደርጓል።
ከዴሞክራሲ አኳያ ዋነኛ ለውጥ ብለን የምንወስደው የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ይሄም የተደረገው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ ተመስርቶ እና ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጋር የሚጣጣሙ የዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት በማድረግ ነው።
እነዚህ ተቋማት የሚመሩበት፤ የሚቋቋሙበት አዋጅ እና ሕግ እንዲወጡም ተደርጓል። የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ የዕንባ ጠባቂ ማቋቋሚያ ማሻሻያ የተደረገበትን አዋጅ መውሰድ ይቻላል። ኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ በሚመስል መልኩ እንደገና ተሻሽሎ የወጣበትም ሌላው ማሳያ ነው።
እነዚህንም ተቋማት የሚመሩ ግለሰቦች ከማንኛውም ፖለቲካ ነፃ የሆኑ መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት በሕገ መንግሥቱ እና በተቋቋሙበት አዋጅ እና ሕግ ላይ መሠረት አድርገው የሚያገለግሉ የተቋማት መሪዎች ተሾመዋል፤ ተመርጠዋል።
በዋነኝነት ደግሞ በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከመጣንበት ጋር ሲነፃፀር እጅግ በተሻለ ሁኔታ ቅቡልነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ችለናል። ይሄ የተቋም ውጤትና የአሠራር ሥርዓት ነው።
በሌላ በኩል መሐልም ዳር ላይም ያለው በቡድንም፤ በአደረጃጀትም፤ በአስተዳደርም፤ በግለሰብም፤ ያለ ሁሉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሳተፍበት ሥነምሕዳር ተፈጥሯል። የዴሞክራሲ ምሕዳርን እያሰፋ የሚሄደው አንዱ ይሄ በመሆኑ ቀላል ለውጥ አይደለም። ሌላኛው ከዴሞክራሲ አኳያ ለውጥ ብለን የምንወስደው መንግሥትም ሆነ ፓርቲ የሚሠራቸው ሥራዎች እንደቀድሞው በምስጢር የሚያዙና ከስብሰባ በኋላ በተደረገ አጭር መግለጫ ተለባብሰው የሚቀሩ ሳይሆኑ አደባባይ ላይ ያሉ መሆናቸው ነው። ይሄ አንዱ ባልተለመደ ሁኔታ አትዮጵያ ውስጥ በብልፅግና ዘመን መጣ ተብሎ የሚወሰድ ለውጥ ሲሆን ራሱ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና እንኳን ሳይቀር ለካድሬዎቹ፤ ለፓርቲ አመራሮቹ፤ የሚያሠለጥናቸው ሥልጠናዎች፤ ውሳኔዎች፤ እያንዳንዱ መንግሥት እየሄደበት ያለው እና ሊሄድበት ያሰባቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች፤ የብልፅግና ጉዞዎች፤ የልማት ጉዞዎች ዶክመንተሪ ሆኖ ለሕዝብ ይቀርባል።
ይሄ ግልፀኝነት አሁን ላይ እንደ ኢትዮጵያ ሰፍቶ እኛ ያለንበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያደርጋቸው መደበኛ ስብሰባዎች ከ99 በመቶ በላይ በቀጥታ ስርጭት ለሕዝቡ እንዲተላለፉ አስችሏል። ይሄ የዴሞክራሲ መገለጫ ግልፀኝነት፤ ተጠያቂነት ማስፈን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ ማድረግ ነው።
በነገራችን ላይ በለውጡ ዘመን የሃይማኖት፤ የንግድ የመሳሰሉ በአጠቃላይ ከ280 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥረዋል። ይሄ ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለው አስተዋፅዖ የጎላ እንደመሆኑ ከዴሞክራሲ አኳያ የመጣ የለውጥ ውጤት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ከለውጡ በኋላ የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት ምን ጥረት ተደርጓል?
አቶ አዝመራ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ከለውጡ በኋላ የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ይሄ በመንግሥት ወይም በሆነ አካል የሆነ ብቻ ሳይሆን ከእድገታችን ደረጃ ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ አንፃር የሕዝባችን እድገት ደረጃ፤ የተቋማት መደራጀት አቅም ደረጃ የመገናኛ ብዙኃኖቻችን የግንዛቤ ደረጃችን፤ የመሠረተ ልማት መሟላት፤ ተደራሽነት፤ ለመረጃ ያለን ቅርበት፤ እነዚህ ተደምረው ወደፊት የምንሄድባቸው ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው እንደ መንግሥት የሚታዩ ሁለት ነገሮች አሉ።
አንዱ ራሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የገዥ ፓርቲ (ኢሕአዴግ) አካታች አልነበረም። ብሔራዊ ድርጅቱን ኢሕአዴግን የወከሉት አራት ክልሎች ነበሩ። በለውጡ አጋር የሚባለው ጠፍቶ በኢትዮጵያ ጉዳይ በአንድ ላይ የሚመክሩና የሚወስኑ ሁሉም ዋና ሆነዋል። እነዚህን ያካተተው ብልፅግና ፓርቲ ተብሎ መፈጠሩ በራሱ የአካታችነት ዋናው መለኪያ ሲሆን አንዱ በመሠረታዊነት ተጨባጭ ለውጥ የመጣበትም ማሳያ ነው።
ሌላኛው በመሠረታዊነት መጣ ብለን የምናየው ለውጥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ ሀገራዊና ክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመኖራቸውን ጉዳይ ነው። መኖራቸው እና፤ በምርጫ ውስጥ ገብተው መሳተፋቸው ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ በእያንዳንዱ ጉዳዮች ላይ አብረው እየመከሩ እየተወያዩ፤ ህጸጾችን እያወጡ መስተካከል ያለባቸው እየተስተካከሉ እንዲሄዱ የሚደረግበት ሂደት ቀላል አይደለም።
ከዚህ በዘለለ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም፤ በፖለቲካ ፓርቲ ሕገ ደንብም በየትኛውም ዓለም ላይ አሸናፊ ፓርቲ ሕግ አውጭውንም፤ ሕግ አስፈፃሚውም ቦታ ይይዛል። በለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል ብለን የምንወስደው አንዱ ይሄ አካሄድ ነው። ለምሳሌ፦በየደረጃው ክልሎችን ጨምሮ እስከታችኛውመዋቅር፤ እስከ ዞኖች ወረዳዎች ድረስ ተፎካካሪዎች ፓርቲዎች ምርጫ ባያሸንፉም ብልፅግና ባሸነፈበት አስፈፃሚ ሆነው እንዲመሩ ተደርጓል። በሀገር ደረጃ የትምህርት ሚኒስትሩን ጨምሮ በዚህ መልኩ የሚመሩ ሚኒስትሮችን መቁጠር ይቻላል።
በእርግጥ ይሄ እየሰፋ መሄድ አለበት ብለን እናምናለን። በመሆኑም ይሄ በራሱ ምን ያህል የፖለቲካ ምሕዳሩ እየሰፋ እንደሄደ ማሳያ ነው ።
ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተያይዞ ስናስበው ከፋም ለማም በየዞኑ፤ በክልሉ፤ በፌዴራል የሚገቡትም በምርጫ ወንበር ለማግኘት በቂ መንግሥት የሚያስብል ቁጥር እንኳን ባያገኙ የመረጣቸው ሕዝብ አለ። ስለዚህ ለሕዝብ ክብር ሲባል እና በራሳቸውም ልምምድ እንዲያደርጉ ዕድል ስለሚሰጥ ባያሸንፉም በየደረጃው ውክልና እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይሄ ደግሞ ለሥልጣን ብሎ መሟሟት እየቀነሰ የሚሄድበት አጋጣሚም ይፈጠራል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሃሳብ በኢትዮጵያ ላይ ገዥና አሸናፊ እንኳን ባይሆንም የተወሰነ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ይኖሩታል። ለምሳሌ፦ባለፉት ዓመታት የትምህርቱን ዘርፍ ሥብራት ለመጠገን በቂ ነው ተብሎ ባይገመትም በእጅጉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ተሄዷል። ነገር ግን ዛሬ ላይ በምንፈልገው መፍጠር የሚችል፤ በሚፈለገው ኢትዮጵያን ማሻገር የሚያስችል ጥራት ደረጃ ላይ አልደረስንም። በጥራት ጉድለት ያለበትን ለማረም ተብሎ ብልፅግና የፖሊሲ ለውጦች አድርጓል። እነዚህም ፍሬ ማፍራት ጀም ረዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ብቻ ሳይሆን ተሸንፈውም ቢሆን አብረውን ይሥሩ የሚለውን እሳቤ የዛሬ 20 ዓመት ብንጀምረው ኖሮ አሁን የምናየው ግርግር አይኖርም ነበር። ፓርላማ ውስጥ የሚኖረው የተፎካካሪ ወንበር በ10እና 20 ሳይወሰን 40 በመቶ ይሆን ነበር። እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን የምንፈልገው ይሄ ነው።
ዛሬ እንደ ኢትዮጵያ እነዚህን የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በማስገባት የፖለቲካ ምሕዳሩን አስፍተን የአጭር እና የረጅም መሠረታዊ ግቦችን እያሳካን እንገኛለን። ይሄ ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ፤ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት፤ የወል ትርክት መገንባት አለብን በሚለው ጉዞ ውስጥ የራሱ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን ፦በለውጡ ዓመታት ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በመደረጉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እየታየ ያለው ለውጥ ምንድነው?
አቶ አዝመራው፦ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት እዛም እዚህም ግጭቶች ቢኖሩ እንኳን ዜጎች እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ አላሉም። በግጭት ውስጥ ሆነውም ይለፋሉ፤ ይሠራሉ፤ ያመርታሉ፤ በዚህም የተትረፈረፈ ምርት እና ምርታማነት ያስገኘ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል። ይሄ ተጨባጭ ለውጥ የመጣው ደግሞ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በመደረጉ ነው።
ለምሳሌ፦ ድሮ ስንዴ ማምረት ለተወሰኑ አካባቢዎች የተሰጠ ፀጋ መስሎ ነበር የሚታየው። ሩዝ የሆነ አካባቢ መብቀል የሚችል ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ቡና፤ ፍራፍሬ፤ አኩሪ አተር የሚበቅለው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው የሚበቅለው ተብለን ነው የኖርነው። እኔ ተወልጄ ያደኩበት ቦታ ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል። የፖለቲካ ሥነምሕዳሩ ሀገር በቀል እይታችን ስላሰፋው ዓይናችንን ስለገለጠልን በአካባቢ ፀጋ ላይ ተንተርሰን መሥራት፤ መልማት አለብን ወደሚለው እሳቤ ገባን። ከዛሬ ስድስትና ሰባት ዓመት በፊት የሚደረገው ቡና መትከል ከሆነ ሁሉም ቡና መትከል፤ ውሃ ማቆር ከሆነ ሁሉም ውሃ ማቆር ነበር።
ዛሬ ይሄ ታሪክ ተቀልብሷል። በየአካባቢው ላይ ያሉ አመራሮች ነፃነት ተፈጥሮላቸዋል። ከግብርና አኳያ የመጣው ለውጥ ቀላል አይደለም። ፍራፍሬ፤ ቡና የማያበቅሉ አካባቢዎች የሚባሉ ወይም ሰዎች አያበቅልባቸውም ያሏቸው ዛሬ በቡና ምርታማነታቸውን አረጋግጠው የቡና ሽፋናችንን እንዲጨምር አድርገዋል። የዛሬ ስምንት ዓመት በዓመት ቡና ልከን ከምናገኘው በላይ ባለፉት ስድስት ወራት ብዙ ቢሊዮን ገቢ አግኝተናል። ይሄ ባለፉት ስድስት እና ሰባት ወራት ውስጥ የቡና ሽፋን መጨመር በስድስት ዓመት ውስጥ የተሠራው የለውጥ ፍሬ ነው። ፍራፍሬም ሆነ ስንዴ ከውጭ ማስገባት አቁመናል። ድሮ ሩዝ ምን እንደሆነ በማያውቀው አካባቢ ዛሬ ሩዝ እየበቀለ ነው። ወርቅ ማዕድኖቻችንም በዚሁ መልኩ በእጃችን ማውጣት ችለናል።
እንደ ሀገር የተፈጥሮ ደን አጠባበቅ ተፋሰስ ልማት ብለን በተወሰኑ ክልሎች በ1999 ዓ.ም ሚሊኒየምን ታሳቢ በማድረግ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላመጣም ነበር። አረንጓዴ ዐሻራ መተግበር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ግን ኢኮኖሚው ዕሴት በሚጨምር መልኩ በመላው ሀገሪቱ ላይ ተቋማዊ አድርገን በመሥራታችን የደን ሽፋናችን ጨምሯል፤ የውሃ እርጥበትን መቆጣጠር ተችሏል፤ የምንተክላቸውን ምርቶች እና የግብርና ውጤቶች፤ ፍራፍሬ እና የኢኮኖሚ እሴት የሚጨምሩ ቡናን ጨምሮ በመሆኑ እንደ ግለሰ ብም ሆነ እንደ ሀገር ገቢያችን ጨም ሯል።
አሁን እየገደብን ያለውን የሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ወደፊት የምንገድባቸውን ጨምሮ የውሃ አቅማችንን የሚጨምር ውጤት አግኝተናል። አልፎ ተርፎ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሻምፒዮን እየሆነች የምትሄድበት ዕድል ተፈጥሯል።
ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ በፋይናንስ ነፃነትም ላይ ተጨባጭ ለውጦችን አምጥቷል። ከለውጡ በፊት የነበረው የፋይናንስ ክምችት ዛሬ ላይ ስናነፃፅረው በብዙ እጥፎች ተቀይሯል። የባንክ ኢንዱስትሪ ሰፍቷል፤ የባንክ አገልግሎት እና የስልክ ተጠቃሚ ቁጥር ጨምሯል። አሁን ላይ በከተሞች አካባቢ ገንዘብ ይዞ መዞር ነውር እየሆነ መጥቷል።
ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ባለፉት ሰባት ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ፤ በግብርና፤ በማዕድን ዘርፍ ከሰሀራ በታች ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ፤ በምሥራቅ አፍሪካ ሻምፒዮን እንድንሆን ያስቻለ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል። ዓለም ከግሎባላዜሽን ውጭ መኖር አትችልም የሚለውን መርሕ በመከተል የኢኮኖሚ ሪፎርም (ሊበራላይዜሽን) ተጀምሯል። በማሳያነት ቴሌን መውሰድ እንችላለን። ሳፋሪኮም ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ደንበኛ አለው። ደንበኛ እና ውድድር መኖሩ ብቻ ሳይሆን ሳፋሪ በመግባቱ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ዛሬ ተወዳዳሪ ስለሆነ ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው። ውድድሩ የተለያዩ አገልግሎቶቹን እንዲያስተዋውቅ ዕድል እየፈጠረለት መጥቷል።
ከሐምሌ ጀምሮ ያየነው የግብይት ሥርዓታችን፤ የፋይናንስ፤ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓታችን ገበያ መር እንዲሆን በማድረጋችን የውጭ ምንዛሪ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን የውጭ ባለሀብቶች ወደዚህች ሀገር ለመምጣት ያላቸው አቅምና ጉልበት፤ ፍላጎት በጣም እየጨመረ መጥቷል። ኢትዮጵያ የዛሬ 10 ዓመት የነበራት ዓመታዊ በጀት ቢሊዮኖቹ ቤት እንኳን ያልገባ ነበር። ዛሬ ላይ ይሄ እንደ ሀገር ይመደብ የነበረ በጀት ከ300 እስከ 400 ሺ ሕዝብ የሚኖርበት ዞን የሚበጀተው ዓመታዊ በጀት ወደመሆን አድጓል። እንደ ሀገርም ከትሪሊየን ያለፈ ዓመታዊ በጀት መበጀት ጀምረናል። ይሄ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችን በማደጉ፤ ሰው ተኮር ልማት በማልማታችን፤ በአዋጅ በአሠራር ሥርዓት ገቢያችንን በማጠናከራችን፤ የሕዝብ ተሳትፎን በማሳደጋችን የተገኘ ተጨባጭ ሀገር በቀል ውጤት ነው።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የትምህርት፤ የጤና ተቋም፤ የተለያዩ ማኅበረሰብ አገልግሎት መንገድ ሥራን ጨምሮ ማኅበረሰቡን በማስተባበር ይሠራሉ። ማኅበረሰቡ የልማት ባለቤት እኔ ነኝ በማለት ከ10 እስከ 30 ኪሎ ሜትር መንገድ እየሠራ ነው። የልማቱ ባለቤት እኔ ነኝ የሚል ሕዝብ መፍጠር ተችሏል። ይሄ ሁሉ የለውጡ ውጤት ነው። መጠቀምም፤ መልማትም፤ መሳተፍም የሕዝቡ ድርሻ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከሰብዓዊ መብት አኳያ ከለውጡ ወዲህ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ አዝመራው፦ ሰብዓዊ መብት ሃሳቡ በጣም ብዙ ነው። ውሃ የማግኘት፤ ጤና የማግኘት፤ የተሻለ አካባቢ፤መንገድ ላይ መንቀሳቀስ ሁሉ በሰብዓዊ መብት ውስጥ ይፈረጃል። ይሄን በሁለት ፈርጅ ማየቱ ጠቃሚ ነው። አንዱ ፍርድ ቤቶች፤ ፍትሕ፤ ፖሊስ ሪፎርም አድርጎ ምርመራውን በዘመናዊ፤ በተደራጀ፤ በተጠና ቴክኖሎጂ ከሚመረምርበት ሂደት ጋር በማያያዝ የሚታይ ነው።
ሁለተኛው እጅግ ከተለጠጠ ነፃነት እና ካለፉ ትርክቶች ጋር ይሰናሰናል። ኢትዮጵያ የግጭት ዓውድ ውስጥ ነው ያለችው። ይሄ የግጭት ዓውድ አንዱ መንስኤ በጣም ከተለጠጠ ነፃነት ጋር ይያያዛል። ሰዎች በር እና መስኮት ስለተከፈተ ካለመበልፀጋችን እና ካለመለማመዳችን በመነጨ በተሳሳተ መንገድ ጉዳዮችን የምናይበትና የምንተረጉምበት እሳቤ የወለዳቸው በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች አሉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ለውጡ ድረስ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይፈጸም ነበር። በለውጡ እንደ ሥርዓት ተወግዷል።
ሁለተኛ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑት የኖሩ፤ ለብዙ ዓመታት ያደሩ ጉዳዮች ናቸው። አንደኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ መግባባት አልተፈጠረም። ሀገር ምንድነው፤ ሕግ ምንድነው፤ ተቋም ምንድነው፤ ማን ምን ይሠራል የሚለው ነገር ገና ከስምምነት ላይ አልተደረሰም። አንዱ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፈታዋል ብለን የምናስበው ኢትዮጵያ ውስጥ የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት የሚለውን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ተበደልኩ፤ ተጨቆንኩ እንጂ በድያለሁ ጨቁኛለሁ የሚል የለም። ከዚህ ጋርም ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። አፋኝ የነበረን ሥርዓት ክፍት በመደረጉ ማንም ከመንደር እየተነሳ ሰው ይገላል፤ ይጋጫል። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ጥፋቶች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን ፦ ለውጡ አሳታፊ እንደመሆኑ የሴቶች ተሳትፎ ምን ላይ ነው?
አቶ አዝመራው፦ በለውጡ ባልተለመደ ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎ አድጓል። እርግጠኛ መሆን ባይቻልም የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ካቢኔ አባላት ፆታ ስብጥር ተቀራራቢ ቁጥር ላይ ነው ያለው። ፓርላማ ላይ ሲመጣም የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ ምክትል ሰብሳቢ፤ የማይናቅ ቁጥር አለ። ፓርላማ ውስጥ ከ41 በመቶ በላይ ሴቶች ናቸው። 50 በመቶ መምጣት እንዳለበት ይታመናል፤ አለበትም። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን የሴቶች ተሳትፎ ከፍ ብሏል። ፓርላማ ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥራቸው ፓርላማ የሚተዳደርበት ሥነ-ምግባር ደንብ ላይ ከገዢ ፓርቲ ቀጥሎ ሁለተኛ ተፎካካሪ ፓርቲ ተብሎ የሚወሰደው ቢያንስ 25 ወንበር ሲኖር ነው። እዚህ ውስጥ የአካባቢም፤ የክልላዊ ፓርቲም ተደምሮ 25 ወንበር አይሞላም። እንዲህም ሆኖ የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ ሁለት ሦስት የሆኑት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቋሚ ኮሚቴዎችን ይመራሉ። ይሄ አካታችነት ክልሎች ላይ፤ ዞኖችም ላይ፤ ወረዳ፤ ቀበሌ ላይ ስንወርድ ተሠርቷል፤ ግን በቂ አይደለም። በደንብ መሠራት አለበት። ወንበር ላይ ሴቶችን በማምጣት ብቻ ሳይሆን በተሳትፏቸው ብዙ ወንዶችን በብዙ እጥፍ የሚበልጡ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ሴቶችን በማምጣት ረገድ በብርቱ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፦በ2018 የሚካሄደውን ምርጫ የበለጠ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እንደመንግሥት ከወዲሁ ምን መሥራት አለበት ይላሉ ?
አቶ አዝመራው፦ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ልዩ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይካሄዳል። አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ በየወቅቱ የተገደበ ምርጫ የሚያደርግ እና በሕዝብ የተመረጡ መሪዎች፤ ፓርቲዎች፤ ሀገርን የሚያስተዳድሩበት ማኅበራዊ ስምምነት ሲኖር ነው። አንዱ ዴሞክራሲ አለ የለም የሚለው መለኪያም ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ማድረግ ለፓርላማ እንደአማራጭ የሚወሰድ ሳይሆን ሀገርን የማስቀጠል፤ ያለማስቀጠል የሕልውና ጉዳይ ነው። ስለሆነም ይሄን እንዲሠራ የተቋቋመ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አለ። ነፃ ሕግና ሥርዓት አለው፤ ጠንካራ መሪዎች አሉት፤ ቦርዶች አሉት፤ እስከ ቅርንጫፍ ድረስ ያላቸው ተቋሞች አሉት። እኛ ይሄን የምንከታተል ቋሚ ኮሚቴ እንደመሆናችን መጠን ለምርጫው በቂ የእቅድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠናል።
ቦርዱ የጨዋታ ሜዳውን ነፃ ማድረግ ነው ተግባሩ። ለዚህ የመገናኛ ብዙኃን ተቋሞቻችን፤ ማኅበረሰቡ፤ በሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት፤ በተቋቋሙት አዋጅ መሠረት የራሱን ዝግጅት እያደረገ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው የፓርቲ ሥራ ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠንካራ ፖሊሲ፤ ጠንካራ ሞጋች ሃሳብ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ቅቡልነት ያለውን እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ይዘው መምጣት አለባቸው።
ገዥው ፓርቲ በየወቅቱ እያደገ፤ ከፍ ያለ የራሱ ማኒፌስቶ እያዘጋጀ ከሕዝቡ ጋር የገባቸውን ኮንትራቶች በሚያድስ መልኩ ራሱን ያዘጋጃል። በፓርላማ ደረጃ ግን ምርጫው አምስት ዓመቱን ተከትሎ 2018 ላይ ይካሄዳል። እኛ በሕዝብ ተመርጠን እንደመጣ አካል የምናስተላልፈው መልዕክት ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ሥነ-ምሕዳር እንዲሠለጥን የጨዋታ ሜዳን፤ አጫዋቾቹን ነፃ ማድረግ ብቻውን በቂ አይደለም። ሕዝብ ተባባሪ መሆን አለበት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተባባሪ መሆን አለባቸው። የመገናኛ ብዙኃን ተቋሞቻችን ተባባሪ መሆን አለባቸው። የውጭ ኃይልና ሌሎቹ ተጨማሪ አቅም ናቸው።
ለእኛ አቅም የሚሆነው ሕዝባችን፤ አቅም የምንሆነው ሜዳ ውስጥ የምንፎካከር ፓርቲዎች ነን። ለእኛ አቅም የሚሆነው በእጃችን ያሉ ሕግና ሥርዓቶች ናቸው፤ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ተዋናዮች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጤናማ፤ ሰላማዊ፤ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ የኢትዮጵያን ልዕልና ማስቀጠል የኢትዮጵያን ቀጣይነት ብልፅግና ማረጋገጥ ነው።
ስለዚህ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት። ዛሬ መንግሥት የሆነው በመጪው ዓመት ምርጫ ውስጥ እንደ አንድ ተወዳዳሪ እንደ ተጫዋች ነው የሚገባው። በመሆኑም እስካለን ድረስ ምሕዳሩን አዋጆቹን፤ የአሠራር ሥርዓቱን ትክክለኛ ነፃ፤ አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ሥርዓት ማጠናከር ነው። እንደማስበው የተጠናከረ ሕግና ሥርዓት በዚህ ዙሪያ ላይ አለ። ምርጫ ቦርድ አቅም በፈቀደ መንገድ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ለማዘመን ለማቀላጠፍ ጥረት የሚያደርግበት አለ። ለዚህ ምርጫ ይደርሳል አይደርስም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ አዋጆቹን ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ነው።
የማረጋግጠው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው የዴሞክራሲ ፍንጣሪ ወደ ኋላ አይመለስም። በየትኛውም የግጭት ዓውድና ጭቅጭቅ ውስጥ እንኑር ወደ ትላንት መመለስ አይቻልም። የኢትዮጵያ ሴቶች፤ እናቶች፤ አባቶች ዛሬ በኤፍ ኤስ አር መኪና ቡና አውጥቶ እየሸጠ ያለ አርሶ አደር ወጣቶች በአጠቃላይ ሕዝቡ አናርኪዝም እንዲመጣ አይፈልግም። የራሱን ቋንቋ፤ ባህል፤ ታሪክን ተናግሮ የተለማመደ ማኅበረሰብ ይሄ ወደ ኋላ እንዲመለስ አያደርግም። ይሄ እንዲመለስ የማይፈልግ ከሆነ የሌላውን ችግር እየተረዳ ነው የሚመጣው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ለኔ ያስፈልገኛል፤ በተሳሳተ ትርክትና እይታ ስለመጣን ለአንቺም ያስፈልግሻል የሚለው እሳቤ ላይ ልዩነት አለ። ይሄን እየቀረፉ መሄድና ወደ ጋራ መምጣት ያስፈልገዋል። ልዩነቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያ የምትባለው የጋራ ጉዳያችንን ታሳቢ አድርጎ ምርጫውን ወደ ሰላም ማምጣት አለብን።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተካሄደ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የሚታዩ ግጭቶች ወደ ጠረጴዛ መምጣት አለባቸው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው አካባቢዎች ሰላም ናቸው። መገዳደል መጨቃጨቅ ከ100 ዓመት በላይ ተጉዘንበታል፤ ነገር ግን አላሻገረንም። የዛሬ የሚያስደምሙን ሥራዎች እየተሠሩ ያሉት የዛሬ 30 እና 40 ዓመት መሠራት የነበረባቸው ናቸው። የተሻለ ንፁሕ፤ ፅዱ ቦታ ላይ መኖር ፤ ስለሚበላው ምግብ የመሳሰለውን ማሰብ የዛሬ 40 ዓመት መዘጋት ያለባቸው ፋይሎች ነበሩ። አሁን እንደ አዲስ እየሠራናቸው ያሉት።
መገዳደልና መጨካከን ግጭት በበዛ ቁጥር የሠራነውን እያፈረስን ተመልሰን ከችግር አንወጣም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለምክክርና ለንግግር በሩ ክፍት ነው ብለዋል። ይሄን ተጠቅመው ወደ ውይይት እየመጡ በማንስማማቸው ጉዳዮች ላይ ባለመስማማት መስማማት ይቻላል። ጊዜም ይፈታቸዋል። አንዳንዶቹ በ30 ዓመት የማይፈቱ ጥያቄ ሊኖረን ይችላል። ለዛ ብዬ እየሞትኩ መሄድ የለብኝም፤ ትውልዴ መሞት የለበትም። እነዚህ ማሰቡ ለምርጫው መደላድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ፦ ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፦
አቶ አዝመራው፤ እኔም በቋሚ ኮሚቴው ስም አመሰግናለሁ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም