በኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በወርሃ የካቲት 2010 ዓ.ም የስልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸው ይታወሳል፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በእርሳቸው እግር የተተካው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ከነዚህም መካከል ከሀምሌ 13ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲተገበር የታወጀው የምህረት አዋጅ አንዱ ነው፡፡ አዋጁ በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን ቅሬታ በመፍታት ግጭትና ሁከት እንዲቀንስ የበኩሉን እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡ ለመሆኑ አዋጁ ግቡን ከማሳካት አኳያ ምን ያህል ውጤት አመጣ? በሂደቱስ ምን ችግር አጋጠመ? ከዚህ ሂደት በአገሪቱ ምን መማር ይገባል? በሚሉትና ከአዋጁ ጋር በተያየዘ የፌዴራል የየቅርታና ምህረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዳላሎን አነጋግረን እንደሚከተለው አቀርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት አብዛኛውን ታራሚ በይቅርታ ከፈታ በኋላ ለምን የምህረት አዋጅ አዋጣ?
አቶ ዘለቀ፡- ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ሁሉም ጫፎች በርካታ ችግሮች ተከስተው ነበር፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ ሲታሰሩ ነበር፡፡ በዚህ መነሻነት በተደረገ ትግል በአገሪቱ ለውጥ መጥቷል፡፡ የመጣው ለውጥ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ መስጠት ነበረበት፡፡
ለዚህም መንግስት በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ፣ ስራ የለቀቁ እና እዚህም እዚያም አመጽ አስነሱ ተብለው ሲፈለጉ የነበሩ ሰዎችን ከታሰሩበት ወይም ከተፈላጊነት ለማውጣት ለሁሉም የሚያገለግል ህግ ማውጣት ስላስፈለገው ነው፡፡
መንግስት በዚህ መነሻነትም አመጽ ላይ ያሉም ሆኑ ታራሚዎች በተደራጀ ሁኔታ የተፈጠረውን አለመረጋጋት አስክነውና የፖለቲካ ልዩነታቸውን ትተው ወደ አንድነት እንዲመጡ፤ በአገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አዋጁ ወጥቷል፡፡ ለሁሉም ዜጎች አዋጅ አውጥቶ የወንጀል ተጠያቂነታቸው በማስቀረት ወደአገር ግንባታ ማሰለፍን ግብ አድርጎ ነው የምህረት አዋጅ የወጣው፡፡ አዋጁ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተደራጀ መልኩ የወጣ ነው፡፡
የምህረት አዋጁን ለማውጣት በመጀመሪያ አዋጅ ቁጥር 1088/2010 ዓ.ም የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ስርዓት ከወጣ በኋላ ምህረት ለማን? አንዴትና በምን መልኩ እንደሚሰጥ በአዋጅ ቁጥር 1089/2010 ወጥቷል፡፡ በህገ መንግስቱ የተፈረደባቸው ሰዎች በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ይቅርታ እንደሚፈቱ ግልጽ ህግ ቢኖርም ምህረትን በተመለከተ ግን በግልጽ የተደነገገ አልነበረም፡፡ አዋጁ የወጣው ይህን ለመሸፈን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተያዙ ሰዎችን በይቅርታ መፍታት ስለማይቻል ነው የምህረት አዋጅ የወጣው?
አቶ ዘለቀ፤ የምህረት አዋጁ ከመታወጁ በፊት እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም በርካታ ዜጎች በይቅርታ ተፈትተዋል፡፡ ይቅርታ የሚደረግላቸው፤ ተከስሰው የተፈረደባቸው ግለሰቦች ባጠፉት ጥፋት ተጸጽተው ‹‹አጥፍቻለሁ፣ ከዚህ በኋላ ወደዚህ ጥፋት አልመለስም፡፡ አምራች ዜጋ እሆናለሁ ብለው በማመልከቻ ሲጠይቁ፤ መንግስትም ጥያቄያቸውን አይቶ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከእስር ነጻ እንዲሆኑ የሚያደርግበት ነው፡፡ ይቅርታ መጠየቅ የሚችሉትም የፍርድ ውሳኔ ያገኙ ሰዎች ናቸው፡፡ የተጠረጠሩ፣ በሌሉበት የተፈረደባቸውና በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ይቅርታ መጠየቅ አይችሉም፡፡ ይቅርታ መዝገብን አይሰርዝም፡፡ በወንጀሉ ምክንያት ካሳ የሚጠይቁ ካሉ አያስቀርም፡፡ እናም የምህረት አዋጅ የተጠረጠሩ፣ በሌሉበት የተፈረደባቸውና በፍርድ ሂደት ያሉ እንዲሁም ከአገር ሉዓላዊነት፣ ከፖለቲካ አመለካከትና ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡ በዋናነት ምህረት የሚደረገው ለቡድን ነው፡፡ ዓላማውም በአገሪቱ መረጋጋት መፍጠር ነው፡፡
የሚሰጠው ምህረት ፖለቲካዊ፣ አገራዊና ህዝባዊ ጥቅም ሲኖረው፤ ምህረት የሚሰጣቸው ሰዎች ወደመደበኛ ህይወት መመለሳቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡ ምህረት የሚሰጠውም መንግስት አጥንቶ በራሱ ጊዜ ነው፡፡ ምህረት የሚሰጠው ለተወሰኑ ወንጀሎችና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ምህረት መጠርጠርን፣ መታሰረን፣ ክርክር ላይ መሆንን ከግምት ሳያስገባ በሁሉም ደረጃ ላለ ዜጋ ይሰራል፡፡ ምህረት ሲደረግ ወንጀል እንዳልተፈጸመ ይቆጠራል፤ መዝገብ ሙሉ በሙሉ ይሰረዛል፡፡ በተለየ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር የመንግስት ዕዳም ይሰረዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዋጁን ማን አረቀቀው?
አቶ ዘለቀ፡- የምህረት አዋጁን ለማርቀቅ ኃላፊነት የተሰጠው ጠቅላይ አቃቢ ህግ ነበር፡፡ አዋጁን ያረቀቀው የክልሎችን ጥያቄ መሰረት እንዲያደርግ ወይም በራሱ እንዲያጠና በአዋጅ ቁጥር 1088/2010 ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የምህረት ረቂቅ አዋጅ መንግስት የሚፈልገውን ግብ ያሳካል ብሎ ሲያምን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በረቂቁ ሲያምኑ አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ ረቂቁን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይልካሉ፡፡ አሁን የወጣው አዋጅም በዚህ ሂደት ያለፈ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዋጁ ሲወጣ መንግስት የሚያስቀምጣቸው ሁኔታዎች አሉን?
አቶ ዘለቀ፡- መንግስት የምህረት አዋጁ ሲወጣ ሶስት መነሻ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ የወንጀል ድርጊቱ በአገር ሉኣላዊነት ላይ ችግር የማያስከትል መሆኑን፤ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የተሻለ አማራጭ እንደሆነና ምህረት የሚደረግላቸው ሰዎች ወደሰላማዊ ህይወት ለመመለስ የሚያሳዩት ፍላጎት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዋጁ ምህረት የተደረገላቸው በዋናነት የትኞቹ የወንጀል አይነቶች ናቸው?
አቶ ዘለቀ፤ ምህረት እንዲደረግ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ 12 አይነቶች ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም፤ በህገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል፤ የህገ መንግስት ስልጣንና ተግባራትን ማሰናከል፤ ማመጽ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ማስነሳት፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ግዛትና አንድነት ለማናጋት የሚደረግ ወንጀል፤ የአገር መከላከያ ሀይልን መጉዳት፤ የአገር ክህደትና ከጠላት ጋር መተባበር፤ አገርን መሰለል፤ በአገር ላይ የተንኮል ድርጊቶች መፈጸም፤ የመከላከያና የፖሊስ አባላት ኩብለላ፤ የሀሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳት፤ በ2001 ዓ.ም የወጣው የሽብር አዋጅ እንዲሁም በ2009/10 በአገሪቱ አለመረጋጋት ወቅት በተደነገጉ ሁለት የአስቸኳይ አዋጆች ጊዜ የተፈፀሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ወንጀሎች ለተሳተፉ ዜጎች ከሐምሌ 13/2010 እስከ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ምህረቱ ተግባራዊ እንዲሆን ታውጇል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምን ያህል ሰው የምህረት የምስክር ወረቀት ሰጣችሁ?
አቶ ዘለቀ፤ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በክስ ሂደትና በፍርድ ላይ ያሉ ከ18ሺ በላይ ዜጎች በይቅርታ ተለቅቀዋል፡፡ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በይቅርታ ብዙ ሰው ስለተለቀቀ ቁጥሩ ቀንሶ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የተሰጠው የምህረት የምስከር ወረቀት በሚጠበቀው ደረጃ አልሆነም፡፡
በአምስት ወር ውስጥ ከሶማሌ፣ ከአፋርና ከጋምቤላ ክልሎች ውጭ ከ13ሺ በላይ ዜጎች በምህረት አዋጁ መሰረት ጥያቄ አቅርበው የምህረት የምስከር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ጥሪ ስለተደረገ ሪፖርቱ ገና በሂደት ላይ ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡ በፌዴራል ደረጃ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በርካታ ሰዎች ቀርበው የምስክር ወረቀት ወስደዋል፡፡ ከአገር ቤት በተጨማሪ በውጭ ያሉ ዜጎችም በዌብ ሳይት እንዲመዘገቡ በማድረግ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰዎች ምን ምን ሁኔታዎችን አሟልተው ነው ምህረት የተሰጣቸው?
አቶ ዘለቀ፡- በአዋጁ እንደተጠቀሰው ከግንቦት 30 ቀን 2010 በፊት የተፈጸሙ ወንጀሎች ያለምንም ቅድመ ሆኔታ አጥፊዎች ቀርበው እስካመለከቱ ድረስ የምህረት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ ቀን በፊት በአዋጁ በተካተቱት ወንጀሎች የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱና የተፈረደባቸው ሰዎችም ጊዜው አስከተጠናቀቀ ድረስ ቀርበው ካመለከቱ የምህረት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምህረት ከተደረገላቸው ሰዎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የትኞቹ ናቸው?
አቶ ዘለቀ፡- የምህረት አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በእስራትና በክስ ሂደት ላይ ያሉ ከ18ሺ በላይ ሰዎች በይቅርታ ተለቅቀዋል፡፡ አዋጁ ከወጣ በኋላም በርከት ያሉ ሰዎች በምህረት አዋጁ ከእስር ተለቅቀዋል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በክስ ሂደት የነበሩ ምህረት የተደረገላቸው አሉ፡፡ ምህረት የተደረገላቸውን ሰዎች በጥፋት ዓይነት ገና መለየት ቢያስፈልግም በሁሉም ደረጃ ግን ምህረት የተደረገላቸው ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዋጁ ከታለመለት ግብ አንጻር የእናንተ ግምገማ ምንድን ነው?
አቶ ዘለቀ፡- ተጨባጭ ቁጥር ይዞ ማውራት ባይቻልም፤ የምህረት አሰጣጡ በአዋጁ ተጠቃሚዎችም ሆነ በሌሎች ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል፡፡ አንዱ ሰው ሲታሰር ከበስተጀርባው በርካታ ቤተሰብ አለ፡፡ በታሳሪዎቹ አመለካከት ትክክል አይደለም ባሉት ሁኔታ ሲታሰሩ ብዙሃኑን ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሲለቀቁም ብዙ ሰው ይደሰታል፡፡ እዚህ ድረስ በመምጣት “አሁን ጸሐይ ወጣልን!” በማለት ደስታቸውን የገለጹ ሰዎችም አሉ፡፡ በርግጥም ታስረው የነበሩና የተፈቱ ሰዎች አሁን የሰላም አየር እየተነፈሱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ከውጭ ወደአገራቸው መጥተዋል፡፡ አገራቸውን የራሳቸው አገር አድርገው መቁጠር ጀምረዋል፡፡ በርካታ ስልክ ከውጭ በመደወልም መረጃ ይጠይቃሉ፡፡ በተጨባጭ መረጃ ባይገመገምም በእኛ ምልከታ ከ95 በመቶ በላይ ህዝብ ደስተኛ ያደረገ ውሳኔ ነው የሚል እምነት አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የምህረት አዋጁ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በእኩል ደረጃ አልተተገበረም በማለት ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ዘለቀ፡- በክልል ቅሬታ የነበራቸው ሰዎች በአካል እየመጡ፣ በደብዳቤና በስልክ አናግረውናል፡፡ እኛም ውክልና ለሰጠናቸው ክልሎች በማነጋገር ችግር ያለባቸውን ፈትተናል፡፡ በአዋጁ በተካተቱ ወንጀሎች የተጠረጠረ፣ የታሰረና የተፈረደበት ወንጀለኛ የሚጠየቅበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ክልሎችም አናስተናግድም ማለት አይችሉም፡፡
ነገር ግን ክልሎችንም ሆነ በፌዴራል መንግስት የተቸገርነው በምህረት አዋጅ የሚመለከታቸውና የሚካተቱት ነጻ ቢደረጉም በሌላ ወንጀል የተፈረደባቸውና የተጠረጠሩ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የሌላ ወንጀል ተጠያቂነታቸው ይቀጥላል፡፡ ይህ ሲሆን ሰው ነጻ መውጣት ስለሚፈልግ ብቻ ቅሬታ የሚያቀርቡ ነበሩ/አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ቅሬታዎች በጋምቤላ፣ በትግራይና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቀርበዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎችም ያላቸውን መረጃ አምጥተው መርምረናል፡፡ ከክልል ኃላፊዎችም ጋር ተነጋግረናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዋጁ በሁሉም የአገሪቱ ከፍሎች መቶ በመቶ ተፈጽሟል ብላችሁ ታምናላችሁ ማለት ነው?
አቶ ዘለቀ፡- በግለሰቦቹ በኩል ሊያሟላቸው የሚገባቸው ቀርተው ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተደጋጋሚ ገልጸን ሁሉም የአዋጁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰርተናል፡፡ በስድስት ወር ውስጥ የመጡ ሰዎች መቶ በመቶ ተጠቀሚ ሆነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዋጁን በማስፈጸም ሂደት ምን ችግር አጋጠማችሁ?
አቶ ዘለቀ፡- በአዋጁ ላልተካተተ የወንጀል አይነት የነጻ የምስክር ወረቀት ማግኘት አለብን የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በማረሚያ ቤት ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሽብርተኛ ተብሎ የሞት ፍርድ የተፈረደበት በምህረት ሲወጣ፤ የሆነ ቤት ገብቶ እቃ በመስረቁ አምስት ዓመት የተፈረደበት ግን አዋጁ አይመለከተውምና በማረሚያ ውስጥ ይቀራል፡፡ እናም፤ ከፍተኛ ፍርድ የተፈረደበት ሰው እየተፈታ እኔ የማልፈታው ለምንድነው በማለት ካለመረዳት ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የተከሰሱበትን የማያውቁ የምስክር ወረቀት ስጡን የሚሉም ነበሩ፡፡ ማን እንደከሰሳቸው፣ በምን እንደተከሰሱ የማያውቁና ቅጣታቸውን ሳያውቁ የምስክር ወረቀት ለሚሉ መስጠት አለመቻላችን ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደባለሙያ ከዚህ ሂደት አገር ምን መማር አለበት ይላሉ?
አቶ ዘለቀ፡- እንደባለሙያ የምሰጠው አስተያየት ህዝብን ያለፍላጎቱ መምራት አይቻለም፡፡ ህዝብን መምራት የሚገባው በማሳመን ነው፡፡ ህዝብን የሚጠቅመው ይህ ነው፤ የሚጎዳውም ይህ ነው ብሎ በማስረዳት በመወያየት ችግሮችን እየፈቱ መሄድ ይገባል፡፡ ህዝብ ጥያቄ እያነሳ በዚህ መንገድ ነው መሄድ ያለብህ ብሎ እርምጃ መውሰድ ህዝብ አንድ ቀን እንዲገነፍል ያደርጋል፡፡ ይህ ሲሆን አለመረጋጋት ይፈጠራል፡፡ በየቦታውም አመጽ ይነሳል፡፡
አገር በሰላም መቀጠል ካለበት መንግስት ዜጋውን አክብሮ፤ ዜጋው የሚፈልገውን አጥንቶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መመለስ የማይችል ከሆነም ያልመለሰበትን ምክንያት ለህዝብ ግልጽ ማድረግ አለበት፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ ሌላው ቡድን ጥያቄ ያነሱትን ዜጎች ለቅሞ እስር ቤት ያስገባል፡፡ ይህ መፍትሄ አልሆነም፡፡ ለቅመህ እስር ቤት ስታስገባ ቀሪው ይነሳል፡፡ በዚህም መሞት፤ መፈናቀል፣ የእርስ በእርስ ግጭት አስከትሏል፤ አገርን ቀውስ ውስጥ አስገብቷል፡፡ እናም አማራጭ መፍትሄ አልሆነም፡፡
ይህን አርሞ መሄድና መማር አለብን፡፡ መንግስትም ከዚህ መማር አለበት፡፡ ህዝቡም ለአገር ተቆርቋሪ በመሆን ከርሱ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡ ሰው ሁልጊዜም ዜሮ አይሆንም፡፡ ህዝብ እንደህዝብ በሰራው ልክ ማመስገን፤ ባጠፋው ልከ ምክንያታዊ ሆኖ መውቀስ ይገባል፡፡ ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ አናመሰግናለን!
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
አቶ ዘለቀ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አጎናፍር ገዛኽኝ