የቀድሞው የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የአሁኑ ግብርና ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባደረገው ኦዲት በርካታ ጉድለቶች ተገኝተውበታል፡፡ የኦዲተሩን ሪፖርት ተከትሎ ጉድለቱን እንዲያስተካክል የእንደራሴዎች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፎም ነበር፡፡
ከምክር ቤቱ ትዕዛዞች መካከል በሚኒስቴሩና በተጠሪ ተቋማት ሳይወራረድ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ 90 ሚሊዮን 694 ሺህ 883 ብር ተሰብሳቢ ሂሳብ ማስተካከል፤ ተቋሙ ያልከፈለውን 26 ሚሊዮን 834 ሺህ 178 ብር ከፍሎ ሂሳብን ማወራረድ፤ በግብርና ኮሌጆች ውል ተገብቶላቸው በወቅቱ ያልተጠናቀቁ ግንባታዎች እንዲጠናቀቁ፤ የተጠናቀቁትም ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ያልተገባን የመንግስት ወጭ ማስቀረት፤ ያለጨረታ የተከፈለ የሆቴል መስተንግዶ 1 ሚሊዮን 711 ሺህ 979 ብር፤ የቀድሞው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር ያልፈቀደው 172 ሺህ 198 ብር የትርፍ ሰዓት ክፍያ፤ ለሚኒስትር ዴኤታ የስራ ግብር ሳይቀነስ 43 ሺህ 500፤ ከመመሪያ ውጭ ለውሎ አበል 39 ሺህ 664 ብር፤ እንዲሁም በሶስት ግብርና ኮሌጆች ለለቀቁ ሰራተኞች የተከፈለ 19 ሺህ 594 ብር ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም፤ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት የካፒታልና የውስጥ ገቢ ስራ ላይ ያልዋለ 68 ሚሊዮን 534 ሺህ 180 ብር፤ እንዲሁም ሳይፈቀድና ዝውውር ሳይደረግ ወጪ የሆነ ብር 1 ሚሊዮን 460 ሺህ 297 ፈጻሚዎቹ ላይ ርምጃ መውሰድ፤ በግዥና በእርዳታ የገቡ ግምታቸው 105 ሚሊዮን 770 ሺህ 570 ብር የሆኑ ዕቃዎች ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ፤ ከ2002 ጀምሮ የተቀመጡ እቃዎችን በመለየት አገልግሎት የማይሰጡትን በማስወገድ እንዲያስተካክሉ ታዝዘው ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በምክር ቤቱ የተሰጠው ቀጭን ትዕዛዝ ከምን ደረሰʔ ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከዋና ኦዲተርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሚኒስቴሩ የሥራ አፈጻጸም ላይ ገምገማ አድርገዋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱም የተሰጠውን ትዕዛዝ እየፈጸመና በመፈጸም ላይ መሆኑን ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በሚኒስቴሩ የፋይናንስ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሰፋ ቦንገር፤ ምክር ቤቱ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ መሰረት በማድረግ ቡድኖችን በማቋቋም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የነበረውን የኦዲት ግኝት ወደ 90 ሚሊዮን ብር በማስተካከል አውርዷል፡፡ ቀሪውንም የኦዲት ግኝት በማጥራት ዜሮ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከግዥ መመሪያ ውጭ 1 ሚሊዮን 711 ሺህ 979 ብር ለአርሶ አደሮች በዓል የተከፈለ መሆኑን አንስተው፤ ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑ ተገምግሟል፡፡ ከዚህ በኋላ ከመመሪያው ውጭ እንዳይፈጸም መተማመን ላይ ተደርሷል፡፡ የትርፍ ሰዓት ክፍያው ለቦሌ ኳራንቲን ሰራተኞች የተከፈለ ነው፡፡ ይህም የሆነው የቀድሞው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር ቶሎ ባለመፍቀዱና ስራተኞቹ በፍርድ ቤት ከስሰው በህግ ስለተፈረደላቸው ነው፡፡ ስራው ባይሰራ ደግሞ የውጭ ንግዱ ቆሞ በአገር ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያደርስ ነበር፡፡ ለሚኒስቴር ዴኤታ ግብር ሳይቀነስ የተከፈለው ብር 43 ሺህ 500 ገንዘብ ሚኒስቴር እንድንከፍል ስላዘዘ ነው፡፡ ከዚህ ጋር የሚጋጭ ህግ አለ። በዚህ ላይ ቋሚ ኮሚቴው መፍትሄ መስጠት አለበት፡፡
ተመላሽ የሆነው 68 ሚሊዮን 534 ሺህ 180 ብር፤ በጀቱ የተያዘው ለጸረ ተባይ መድሃኒት መግዣ ነበር፡፡ ሆኖም መድሃኒቱን የሚያቀርበው የአዳሚ ቱሉ ድርጅት ሙሉ ለሙሉ ማቅረብ አልቻለም፡፡ በግዥና በእርዳታ ከውጭ ገብተው ለክልሎች የተሰጡ እቃዎች መግባታቸውን በሞዴል 19ኝ ሚኒስቴሩ የማረጋገጥ ችግር አለበት፡፡ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በተሰራው ስራ ከብር 105 ሚሊዮን 770 ሺህ 570 ውስጥ የተወራረደው ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱ በሞዴል ተረጋግጧል፡፡ ቀሪውን ለማስተካከልም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሰግድ በበኩላቸው፤ የሚወገዱ ንብረቶችን ለማስወገድ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ በርካታ መለዋወጫዎች ተለይተው መረጃው ለግዥ ኤጀንሲ ተልኮ ነበር፡፡ ሆኖም ወደአፈጻጸም ሲገባ እንደገና መጥራት አለበት ተብሎ በመወሰኑ እየተለየ ነው፡፡ የህንጻ መሳሪያዎችና ቧንቧዎች ግን መወገዳቸውን ተናግረዋል፡፡
መወገድ ያለባቸው ለጤና አስጊ የሆኑ ኬሚካሎች ቀደም ሲል በበርሜል የተቀመጡ ሲሆን፤ አስከሚወገዱ ድረስ በአገር ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጦ ማከማቻ ቦታ እየተሰራ ነው፡፡ ኬሚካሎቹን ለማስወገድም አስቸጋሪና ወጭውም ከፍተኛ በመሆኑ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት፡፡ የ15ቱ ተሽከርካሪዎች ሊብሬዎች የተገኙ ሲሆን፤ ቀሪዎቹም እየተፈለጉ ነው፡፡ የማይገኝም ከሆነ ተቋሙ በኃላፊነት እርምጃ እንደሚወስድ አመላክተዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ደምሴ፤ የኦዲት ባለሙያዎችን ለመቅጠር በመደቡ ላይ ያለው ደመወዝ አላስቻለንም፡፡ የተቀጠሩትም ቶሎ ይለቅቃሉ፡፡ በሚዛን ግብርና ኮሌጅ ኦዲተር የለም፡፡ በሌሎችም ያሉት ባለሙያዎች በጣም ጥቂት ናቸው ብለው፤ ችግሩን ለመፍታት አለመቻላቸውን አብራርተዋል ፡፡
የአላጌ ግብርና ኮሌጅ ተወካይ አቶ ከበደም፤ ኮሌጃቸው 49 ሚሊዮን ተሰብሳቢ ብር ያለበት ሲሆን፤ አሁን ላይ 923 ሺህ ብር ብቻ መቅረቱን አንስተዋል፡፡ ከገዋኔ ግብርና ኮሌጅ የመጡት አቶ ሰለሞን በቀለ፤ ኮሌጁ ለመስኖ የሚሆን የውሃ መስመር ስራ ቢጀምርም በኮንትራክተሩና በአማካሪው መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሥራው አለመጠናቀቁን፤ በተጨማሪም፤ በውል ያልተካተቱ ስራዎች በመሰራታቸው ምክንያት የተከፈለው ገንዘብ የኦዲት ግኝት ሆኖብናል፡፡ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ህንጻዎችም የፍሳሽ ማስወገጃ ስለሌላቸው አገልግሎት እንደማይሰጡ በመጥቀስም ለጊዜው ደረቅ መጸዳጃ በማዘጋጀት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ፤ በቀጣይም የፈሳሽ ማስወገጃ ለማስገንባት ዲዛይን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፤ ሳይሰሩ የተከፈለ ገንዘብ የተባለው፤ የአንዱ ሲመለስ የአንድ ሰው ግን መገኘት ባለመቻሉ ያለመመለሱን፤ ከህግ ውጭ ለውሎ አበል የተከፈለ ገንዘብ እየተመለሰ መሆኑን ተናገረዋል፡፡ የአርዳይታ ግብርና ምርምር ኃላፊ አቶ ማህዲን፤ የ20 ቤቶች ግንባታ ለማከናወን ውል ተገብቶ ስራ ቢጀመርም ተቋራጮቹ ስራውን ትተው መውጣታቸውን ገልፀው፤ አማካሪውም ላከናወነው የአስተዳደርና ስራውን ቆጥሮ የመያዝ ተግባር 115ሺህ ብር መከፈሉን በማብራራት የኦዲት ግኘቱ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታዛቢ በየነ፤ በተቋሙ ከ1994 ዓ.ም እስካሁን ሲወራረድ የመጣውን የኦዲት መጓደል ለማጣራት ቡድን ተዋቅሮ በመስራቱ ውጤት መጥቷል፡፡ የሁሉም የኦዲት ግኝት ችግር ተለይቷል፡፡ ከተለየው ግኝት ሰነድ በማደራጀት ማወራረድ የቻለውን ለማወራረድ፤ ማወራረድ ያልቻለውን ተቋም በህግ ለመጠየቅ ተዘጋጀተናል ብለዋል፡፡
በኦዲት ግኝቱ ሪፖርት መሰረት ማስተካከል ያልቻሉ ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ይገኛሉ፡፡ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መክፈል ወይም ማወራረድ ከነበረባቸው ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከ5 ሚሊዮን በላይ፣ የጎዴና የጋምቤላ ግብርና ኮሌጆች እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ሊከፍሉና ሊያወራርዱ አልቻሉም። በመሆኑም ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ በህግ እንጠይቃቸዋልን ብለዋል፡፡
የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ ንብረት አጥርቶ ለማስወገድ ቡድን አደራጅተው አለመስራታቸውንና ባለው አሰራር ግን እየሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ከ20 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ኬሚካሎች በሚኒስቴሩ እጅ እንደሚገኝና ለዚህም በአገር ደረጃ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ስራ ላልሰሩ ሰዎች የተከፈለውን የማስመለሱ ተግባር ጥሩ ቢሆንም፤ ያልመለሱትን ተጠያቂ ከማድረግና አሰራሩን ከማጠናከር አኳያ አሁንም ክፍተት አለ፡፡ በጀት በእቅድ የመምራትና ሳያስፈቅዱ የመክፈል ችግርም ይታያል፡፡ መሰብሰብ የነበረበት 78 ሚሊዮን ብር አለተሰበሰበም፡፡ ይህ ማለት የአንድ ወረዳ በጀት ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር 100 ፐርሰንት የኦዲት ግኝቱን አልስተካከለም የሚል ሪፖርት አለው ይህን አብራሩ፡፡ ተጨማሪ በጀት አስፈቅዳችሁ ካልተጠቀማችሁ ለምን ፈሰስ አላደረጋችሁም? በርዳታ ቁሳቁስ ገቢ ሞዴል 19 ካልተቆረጠ በምን አረጋግጣችሁ ሰጣችሁ? በርካታ ሰው ዲግሪ ይዞ ስራ ባጣበት አገር እንዴት ሰራተኛ ታጣላችሁ? በንብረት አወጋገድ ላይ የሰራችሁት በቂ ነወይ? ለመስራት ፍላጎትስ አላችሁ ወይ? ሲሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽም፤ አቅራቢዎች የጸረ አረም መድሃኒት እንደሚያመጡ ይጠበቅ ስለነበረ በጀቱን ተመላሽ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ተሰብሳቢው በማን እጅ ምን እንዳለ እናውቃለን፤ መረጃዎችን የማደራጀት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለክልሎች ዕቃዎች በእርዳታና በግዥ ሲሰጡ በሞዴል 19 ለማስረከብ አሰራር እየዘረጋን ነው ብለዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ተወካይ በወቅቱ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሚኒስቴሩ ቁጥጥር ሲያደርግ ስራዎች ቢጀመሩም የተስተካከለ ኦዲት በተጨባጭ አልተደረገም ነበር፡፡ እኛ ቁጥጥር ካደረግን በኋላ ስራዎች ተሰርተው ሊሆን ይችላል፡፡ ሚኒስቴሩ የኦዲት ግኝት እያስተካከለ መሆኑ ርግጥ ቢሆንም አሁንም ግን ግዥውን በዓመታዊ እቅድ ውስጥ አስገብቶ የመሄድ ችግር አለ፡፡ በኮሌጆች ግንባታ ዙሪያ ለሚጠፋው ጥፋት ተጠያቂነት የለም፡፡ የወሰዱትንም በጀት ለሌላ ስራ ያውላሉ፡፡ ውል ሲቋረጥ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት አያሳውቁም በማለት በሚኒስቴሩ ስራዎች ውስጥ አሁንም መጓደል እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን፤ ከተሳታፊዎቹ የተሰጡት አስተያቶች በአጠቃላይ ጥሩ መሆናቸውን በማንሳት የጀመሯቸውን ስራዎች ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡ ኬሚካሎች አደጋ እንዳያደርሱ ቋሚ መፍትሄ ይፈልጋል፡፡ ለክልሎች መተላለፍ የሚገባቸውን ንብረቶች የተወሰኑትን በሞዴል አስተላልፈናል፡፡ ቀሪውን የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ስራችን ለማሻሻል በስፋት እየሰራን ነው፡፡ ብዙ ያልሄድንበት ነገር የተጠያቂነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም መረጃዎችን ሰብስበን እንደጨረስን በህግ ወደመጠየቅ እንገባለን ሲሉ የባለሙያዎቹን ሀሳብ ደግመውታል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርንም በዚያን ወቅት የነበረው መግለጫ ተገቢ ቢሆንም፤ የተላከለትን ማስተካከያ አንብቦ ራሱም ማስተካከል አለበት ሲሉ ተችተዋል፡፡ ግዥን በእቅድ መምራት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን፤ የግዥ ኤጀንሲው ስልጠናዎችን የመስጠት፤ ከቁጥጥር ባለፈ ክፍተቶች ለማስተካካል የሚያስችል አካሄድ ማየት አለበት፡፡ ኦዲቱ ያለፈውን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን የአሁኑንም እንዳይበላሽ ለማድረግ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
የፌዴራል ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ፤ ሚኒስቴሩ የማስፈጸሚያ መርሃ ግብር አውጥቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ በመርሃ ግብሩ መሰረትም አስተካክሎ ያቀረባቸው የተሰብሳቢና የተከፋይ ሂሳብ ሰነዶች አሉ፡፡ ይህም ትክክል ስለመሆኑ እየተጣራ እንደሆነና ሲጠናቀቅም እንደሚረጋገጥ ገልጸዋል፡፡
ዋና ኦዲተሯ ያነሱት ሌላው ጉዳይ የትርፍ ሰዓት ክፍያን እንደመጨረሻ አማራጭ አድርጎ ከማየት ይልቅ ሰራተኞችን በመቅጠር በፈረቃ ማሰራት አለበት፡፡ አጣዳፊ ግዥ ካገጠመውም አስፈቅዶ መፈጸም አለበት፡፡ ያልተከፈለውንም ግብር መክፈል ይገባዋል፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴርም ላወጣው ህግ መገዛት አለበት፡፡ ለአማካሪ የተከፈለው 115 በመቶ ከህግ ያፈነገጠ ስለሆነ መስተካከል ይገባዋል፡፡ በህግም ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ የሰው ሀይልን ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው፤ ሚኒስቴሩ ከሌሎች ተቋማት አንጻር በኦዲት ግኝት ማስተካከል የተሻለ ነው፡፡ መርሀ ግብር ቀርጾ ወደ ስራ ከመግባት አንጻርም መልካም ስራዎች ሰርቷል፡፡ ሆኖም፤ በመናበብ የጀመራቸውን ስራዎች ከዳር በማድረስ ከኦዲት ግኝት ነጻ ማድረግ ይገባዋል፡፡ በተሰብሳቢና በተከፋይ ሂሳብ ላይ ያለው መጓተት ለረጅም ዓመታት የቆየ ከመሆኑ አንጻር ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት፡፡ የሂሳብ አያያዙን፤ የጨረታ አወጣጡንና አተገባበሩን ህግና አሰራር በመከተል እያስተካከለ መሄድ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ