ወርቅነሽ ደምሰው
ወዳጆቼ! እንደምን ከረማችሁ? አሁንማ እድሜ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይሁንና በየደቂቃው እያገናኘን ነው። ሰላምታችን፤ ውሎ አዳራችንና ትኩስ ትኩስ መረጃዎችን እያፈሰሰለን ግንኙነታችን ጠንክሮ ተራቀቅን አይደል! ።
ዓለም በግሎባላይዘሽን አንድ መንደር ከሆነ በኋላማ የምን ችግር ፤ ‹‹ችግር በአፍንጫችን ይወጣ ›› አስብሎናል። ዘንድሮማ! ለእኛ መረጃ ማድረስ ሲሉ ላይ ታች ብለው ወጥተው፤ ወርደው የተጉ በርካቶች ነበሩ። ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በየደቂቃውና በየሴኮንዱ አዳዲስ መረጃዎች እያደረሱን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉና ሳትታክቱ የሰሩ ጀብደኞች።
በሀገር ውስጥ ተከወኑ ያሏቸውን፤ ሊከወን የታሰበውና ወደፊት የሚሆነውን ትንቢት ጨምሮ ቀን በቀን አጀንዳ ቀርጸው በሀገሪቱ ዙሪያ እየተሽከረከሩ መረጃን ሊያደርሱ ደክመዋል። በመረጃቸው የሀገር ጉዳይ፤ የብሔርና የሃይማኖት ወዘተ… የማያነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች የሉም ነበር።
‹‹ድንቄም ! መረጃ ›› አሉ እማማ። ታዲያ እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ጀግኖች ዛሬ የት ገብተው ይሆን ? ምነዋ ! ዱካችው ጠፋብን? እለታዊ መረጃዎቻቸውስ የት ደረሱ ? ፈጣሪና አድራጊ ስልጣናቸውን ከማህበራዊ ሚዲያ ማን ነጥቆ ወሰደው? የተቀረጸው አጀንዳቸው አልቆባቸው ይሆን እልም ብለው የጠፉት ?
የማይሆነውንና መቼም ሆኖ የማያውቀውን እየሰበኩ በበሬ ወለደ ትርክት ሲያሸብሩን ኑረዋል እኮ! አብደው ሊያሳብዱን ፈልገው፤ ከብርሃን ዓለም ፈጥነው ወደ ድቅድቁ ጨለማ ሲወስዱን አልፈራንም እንዴ? ፈርተናል እንጂ።
እነዚህ ወገኖች እኛን አጀግነው ከፊት ቀድመው እየመሩ እንድንከተላቸው ሲጎተጉቱን ቆይተው የለም እንዴ? ታዲያ እነዛ ጀበደኞች እንዴት ደፈረው እጃቸውንና ጭንቅላታቸው ማዘዝ ቻሉ ? ይግርማችሁ ብለው ዛሬን ከአይናችን ሊሰውሩ ? ወዴት ወዴት…. ጉድ ፈላ ! ጉድ።
ወዳጆቼ ! ዘንድሮማ እድሜ ከሰጠን የማንሰማው ጉድ አይኖርም። ይኸው ‹‹እንቶኔ›› የሚባለው ኔትወርክ ጠፍቶ ጉዳቸው ተጋልጦ አረፉት። ‹‹ጉድና ጅራት ከወደኋላ›› እንዲሉ ቀጣሪና አሰሪአቸው የጁንታው ቡድን ባላሰቡት ሰዓት የአህያ ባል ሆነባቸው፡‹‹የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም›› አይደል የሚባለው። አዎ! አያስጥልም። አጣብቂኝ ውስጥ ከቶአቸው እርፍ አሉት።
አሁን ሰማይና ምድር ተገለባብጦ መሬት ተከፍታ አትውጣቸው ነገር፣ መግቢያ ጠፍቶባቸው እጅና ጭንቅላታቸው ባዶ ሆነው እየተንቀዋለሉ ይገኛሉ። አይ እናንተ የድል ዜናን ልታበስሩን ቃል ገብታችሁ ነበረ እኮ! የሃያአራት ሰዓቱ ልፋታችሁ መና ቀረና ! የእያንዳንዱ ደቂቃ ቀልዳችሁ መከነ። በሚዲያው እንዲያ እንዳልተንደላቀቃችሁበት ዛሬ ምነው ድምጻችሁን አጠፋችሁ። የመቀባጠሩ ሱሳችሁንስ እንዴት አድርጓችሁ ይሆን። ወይኔ ! ሚስኪኖች ስታሳዝኑ!
ወዳጆቼ ! ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው ጅግና የለውም›› እንዲሉ አበው። ጆሮአችሁ፣ አይናችሁና ልባችሁ ከእኛን ጋር ብቻ ይሁን ሲሉን ፣ ከኛ ሌላ ማን አዋቂ እያሉ በምናብ ሲወስዱን፣ በእውናችን የእልሙን ዓለም ሲያስጎበኙን ነበረ ።
የእድሜ ልክ ራዕያቸውን እየተረኩልን ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንዳናይ፤ ጆንያ ሙሉ ወሬ የሞሉን፣ ባለራዕዮቻችን ዛሬ የት ደረሱ። ቴክኖሎጂን ታከው ዓለምን እያስቃኙን፣ ሀገራችንን የማናውቃት ያህል እያስተዋወቁን የኖሩት ተራኪዎቻችን የት ናቸው። እነዛ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ጀግነው ሊያጀግኑን የቆረጡ ቁርጠቶች ወዴት አሉ?
መቼም ወገኖቼ! አናውቃቸውም እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ። ቢያንስ ሁላችንም የገፈቱ ቀማሾች ነበርንና። እንዲያ በምላሳቸው ጤፍ የሚቆሉ የማህበራዊ ሚዲያ አሽከሮችን ጥቂት እንታዘብ።
‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ›› ይላሉ አበው ሲተርቱ። አባባሉ ጦርነት የከፋና አውዳሚ ስለመሆኑ ይገልጻል። ወሬ ደግሞ ከጦርነት የማያንስ ሀገር አፍራሽ መሆኑን ያመላክታል። ድሮ ድሮ በአሉባልታ ወሬ ከአንዱ ወደ አንዱ የሚተላለፍበት መንገድ በሰው አማካይነት በመሆኑ ለሁሉም በአንድ ጊዜ መድረስ ሀገር ሊያምስ የሚችልበት እድሉ የጠበበ ነበር።
አሁንማ ወሬ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጉርሻ ሆነና ባሉበት ቦታ፤ ለፈለጉት አላማ ፤ ያሻውን ወሬ በአንዴ ለብዙ ሚሊዮኖች ማድረስ የሚችል አደገኛ የጦር መሳሪያ እየሆነ ነው ። ታዲያ እነዚህ የጁንታው የሾማቸው የወሬ ቅጥረኞች የሃያ አራት ሰዓት ሥራቸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተከልሎ የተሰጣቸውን ተልዕኮ መወጣት ነው። ለዚህም ዳጎስ ያለ ክፍያ ይቸራቸዋል።
በጁንታው የተመለመሉት የማህበራዊ ሚዲያ ቅጥረኞች ዋንኛ ሥራቸው እንደ ፌስ ቡክ፤ ዩቲዩብ ና መሰል ሌሎችንም ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተጠቀሙ ሀገር የማፍረስ አላማን አንግበው፤ የሃያ አራት ሰዓት ተልዕኳቸው ብሔር ከብሔር፤ ጎሳን፤ ከጎሳ፤ ሃይማኖትን፤ ከሃይማኖት በማጋጨት፤ በሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን በማድረግ ሀገርን ማተራመስ ሆኖ ቆይቷል።
ከጁንታው በሚሰፈርላቸው ቀለብ የሚኖሩ የሚዲያው ጡረተኞች ህሊናቸውን በብር ሸጠው፤ ወገኖቻቸውን እርስ በእርስ በማላተም የአንደኛውን ብሔር መለዮ በመልበስ፤ የሌላኛው ብሔር ላይ ሲያነሳሱ፤ እንዲሁም የአንደኛው ሃይማኖት ካባ ለብሰው ሌላኛው ላይ እያዘመቱ፣ ከጎናችን ሆነው ጎናችንን እየወገኑ፣ ናላችን ሲያዞሩት ነበር።
የኢትዮጵያን ሰላም ከጁንታ በስተቀር የሚያረጋገው እንደሌለ የትግራይን ሰላም በምሳሌነት እያነሱ ኃያሉና አይበገሬው ጁንታው ብቻ ያለውን ሰላም ሊያሳዩን ሲጥሩ ነበር። እነሱ እንዳሰቡት ካልሆነም ኢትዮጵያ ፍርስርሷ ወጥቶ ሰማይና ምድር ሊገለባበጡ የሚችሉበት ሁኔታዎች አይቀሬ እንደሚሆንም ሲነግሩን ቆይተዋል።
የሁሉን ነገር አዋቂነት ለጁንታ እየሰጡ፣ ሀገር መሪ፤ መንገድ ጠቋሚ፤ አስተማሪና ጦረኛ እንደእሱ የለም ሲሉን ነበር ። በብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ላይ የተመሠረተውን ህገመንግስት የሰራ የኢትዮጵያ መጀመሪያ ሆነ መጨረሻም ሊሆን የሚችል እንደሆነ ሲደሰኩሩልን ቆይተዋል።
የጁንታውን ጀግንነት የጦር አዋቂነት ተርከው ሲያጀግኑት፤ ተዋግተው ሲያወጉ፤ ፊት ፊት እየቀደሙ የሚያስከትሉትን የእኛን አእምሮ ገዝተው፤ እንቅልፋችን ሲነጥቁን እንድናምናቸው ጭምር በሰማይና በምድር ተገዝተው ሲነግሩን ነበር።
እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ወሽካቶች የውሽት ጽዋ አቅምሰውን፤ በሀሰት ትርክት አስክረውን ሲያበቁ፤ መሸምጠጥን ምን አመጣው። ያሁሉ የተስፋ ቃል አሁን ላይ የትገባ ? እነሱስ ወዴት ገቡ። ትናንት ፈልገውን እንዳልመጡ ሁሉ ዛሬን ፈልገን ማግኘት አቃተንሳ! ። እግዚኦ! በተቃራኒ መደበቂያቸው ወዴት ይሆን ምን ጉድጓድ ገቡ ። ኡኡቴ አሉ እማማ ! እዩኝ እዮኝ ደብቁኝ ደብቁኝን አመጣ ።
አያችሁልኝ ወዳጆቼ! እነዚህ የታሪክ ተወቃሾችና ተላላኪ ቅጥረኞች ተነግሮ አያልቄ ፕሮፖጋንዳቸውን እንደ ህጻን ልጅ በግድ ሲግቱን ። ‹‹ድንቄም ለሀገር አሳቢ! ›› ለሰላም የቆሙ መስለው ሰላምን ሲያሳጡን፤ ሀገር ሰላም እንዳይኖራት መርዛማ ፅሁፎች እየረጩ ለወገን ተቆርቋሪዎች ለህዝብ አሳቢዎች መስለው የእውነትን ደብዛ እያጠፉ የሀሰት ትርክት ዶስክረዋል።
‹‹ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኑኝ»አሉ እማማ! የሰላምን ዋጋ አውርደው ሀገራችንን እንደሶሪያ ለማፈራረስ ሲያሴሩ፤ ለኢትዮጵያ ሰላም የህልውና ጉዳይ መሆኑን እያወቁ ደብቁን ሴራ በማጧጧፍ ጅምሩን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ ያልማገዱት ማገዶ ያላቀጣጠሉት እሳት የለም።
ጉድጓድ ምሰው የማይጠፋ እሳት ለኩሰው፣ በንጹሀን ህይወት ሲቀልዱ፣ አንዱ ቦታ ላይ የለኮሱት ሌላ ቦታ ሲቀጣጠል እረፍት የለሽ ዓመታት እንዳናሳልፍ ፈርደውብናል።
ጁንታው በሚለቅላቸው ገንዘብ እነሱ እየተንደላቀቁ ሌላውን እያሸማቀቁ፤ አንዱን ከአንዱ እያማቱ፣ የውሸት ድሪቶ እየደራረቡ ያልሆነውን ሆነ ተፈጠረ ብለው የስንት ወገኖቻቸውን ደም በከንቱ ሲያፈሱ ኖሩ፤ እነሱ ህዝቡ ሰላም አጥቶ በስጋት እንዲኖር፣ እርስ በእርሱ እንዳይተማመን ሲያደርጉን ኖረዋል። ድብቁ መጋረጃቸው ሲገለጥ ቆመንለታል ለሚሉት ዓላማ ከመታየት እውነት እንዴት አጠራቸው።
በሀሰት ፕሮፖጋንዳቸው ያለጁንታ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አትኖርም ትፈራርሳለች ሲሉን ነበር። ዛሬ ታዲያ አይበገሬነቱን ሲተርኩልን የነበረ ጦር አዋቂ ጁንታቸው የት ገባባቸው። የያዙት የጨበጡት የመሰላቸው የእነሱ ጀግና ለራሱ መደበቂያ ቀዳዳ ጠፍቶበት በዱር በገደሉ እየተሽሎኮለከ በስጋትና በጭንቀት ውስጥ ሆኖ እድሜውን እየረገመ ነው።
‹‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል›› እንዲሉ የተማመኑበትና ለዓመታት ህሊናቸውን የሸጡበት መሪዎቻቸው የገነቡት ግንብ ፈራርሶ አነሆ! እውነታው ተገለጠ። አዎ አሁን በሀፍረት መግቢያ ጠፍቷቸው ሰላም አጥተው እየዋለሉ ነው።
እስኪ አንዴ አድምጡኝማ! ለመሆኑ ትናንትና እውነትነቱን አምናችሁ እኛን ለማሳመን የለፋችሁት ልፋት ምን ውሃ በላው ? ለእውነት ቆመናል ብላችሁ ሞግታችሁ አልነበር ? ዛሬ ታዲያ እውነታችሁን ምን ወሰደው ? ህሊናን ሽጦ ሀገር ማፍረስ ይሉትን በእናንተ አይተን ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር እንዲሉ ሆኖብናል። አዎ አፍረናልም ይብላኝላችሁ ለእናንተ።
በኢትዮጵያ ታሪክ ሆኖ የማያውቀውን አጸያፊ ድርጊት የፈጸመ ጁንታ ፤ አብሮት የኖረውን የመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው የግፍ ግፍና በማይካድራ ንጹህን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ በሰው ህሊና ሊታሰብ የማይችል ነው። ሀገርን ሰላም አሳጥቶ መቀሌ ከከተመም በኋላ እጁን እያረዘመ ሲያስቸግር ኖሮ ይህ አልበቃ ብሎት ጦርነት ሲያውጅ፣ ኑ ተፋለሙኝ ፣ ግጠሙኝ ሲል፣ እኔ ጀግና ጦርነት አዋቂ ነኝ እያለ ሲፎክር፣ ከእኔ በቀር ላሳር እያለ ሲደሰኩር አብራችሁ ስታጫፍሩ የነበራችሁትስ ዛሬ የት ናችሁ።
መንግሥት ህግ የማስከበር እርምጃ ሲወስድ አንድ ብሔር ላይ የተደረገ ዘር የማጥፈት ዘመቻ ታወጀ ብላችሁ ስታወሩ አልነበር። ታዲያ እውነት ተገላልጦ ሲወጣ ምን አስፈራችሁ? እናንተ እንደሆን የእውነት አምባሳደሮች መሆናችሁን አሳምናችኋል እኮ ! አሁን ታዲያ ምን አስደበቃችሁ? ብቅ አትሉም እንዴ !
እስኪ እናንተዬ አንዴ ጆሮአችሁን አውሱኝ። የጁንታውን አላማ ስታራምዱ በዋሻችሁት ውሸት ስንት ወገኖቻችሁን ለሞት፤ ስንቱን ለአካል ጉዳትና ስንቱን ለበሽታ ዳረጋችሁት። ታዲያ ይህች እውነት መቼም መሬት አትወድቅምና የእጃችሁን የምታገኙበት ጊዜው ቅርብ ነው። ተመስገን ነው ! የትናንትናው ጭለማ ተገፎ ለዛሬ ብርሃን አየን። እንጂማ እንደ እናንተ የውሸት ዲስኩር ቢሆን ዛሬን ለማየት ባልታደልን ነበር።
እናንተዬ! ለህሊናችሁ መገዛት አቅቷችሁ ላያዋጣችሁ ብዕራችሁን ሰብቃችሁ የውሸት ትርክት የደሰኮረውን አእምሮችሁን መርመራችሁ ወደራሳችሁ ተመለሱ። መሪያችሁ ጁንታ እንደሆነ ዳግም ላይመለስ ተፈረካክሷል።
በቅርቡ ደግሞ ከተደበቀበት የአይጥ ጉድጓድ ወጥቶ ሊያፈርሳት ባሰባት ሀገር ለፍርድ አደባባይ ይቆማል። እናንተም ውስጣችሁን በንሰሃ እጠቡ። ለህሊናችሁ እንጂ ለብር አትገዙ። ሀገራችን ለሁላችን ትበቃናለችና የሀሰትን ወሬን ወዲያ ጥላችሁ በለውጥ ጎዳና ወደፊት ገስግሱ መልካም መንገድ ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013