ዳንኤል ዘነበ
ማንኮራፋት የምንለው በምንተኛበት ጊዜ በመተንፈሻ አካላችን ላይ በሚፈጠሩ ለውጦች ምክንያት በሚመጣ ድምፅ ነው። ማንኮራፋት አብሮ የሚተኛን ሰው ከመረበሽ ባለፈ አንዳንድ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የጤና እክሎች ምልክት ሊሆን ይችላል። ማንኮራፋት አንድ ሰው በሚተኛበት ወቅት የጎረነነ ወይም የማይመች ድምፅ የአየር መተላለፊያ ቧንቧ በከፊል መዘጋት በሚኖርበት ወቅት የሚከሰት ነው።
አንዳንዴ ማንኮራፋት አሳሳቢ የሆነ የውስጥ ደዌ ችግርን ሊያሳይ ይችላል። ችግሩ የትዳር አጋርዎን ሊረብሽ የሚችል ሲሆን እስከ ግማሽ በሚደርሱ አዋቂዎች ላይ ችግሩ ሊታይ ይችላል። ማንኮራፋት በትናጋዎ ውስጥ ባሉ የላሉ ክፍሎች ውስጥ የሚተነፍሱት አየር በሚያልፍበት ወቅት እንዲርገበገቡ ስለሚያደርግ ማንኮራፋት እንዲከሰት ያደርጋሉ።
ምልክቶች
ማንኮራፋቱ እንዲከሰት የሚያደርጉ ችግሮች የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። በእንቅልፍ ሰዓት የሚረብሽ ድምፅ መኖር፣ ቀን ቀን እንቅልፍ መብዛት፣ ትኩረት ማጣት፣ የጉሮሮ ህመም፣ ያልተረጋጋ እንቅልፍ መኖር፣ የአየር ማጠር ወይም ትንታ መኖር፣ የደም ግፊትና ማታ ማታ የደረት ህመም መከሰት ናቸው።
ማንኮራፋት ለምን ይከሰታል?
የአፍና ሳይነስ አፈጣጠር፡- ዝቅ ያለና የወፈረ ትናጋ የአየር መተላለፊያን ያጠባል። በጣም ወፍራም የሆኑ ሰዎች በአየር መተላለፊያ ቱቦዎች (ጉሮሮ ጀርባ) ትርፍ አካል/ tissues ስላላቸው የአየር መተላለፊያ ቱቦው እንዲጠብ ያደርጋል። በተጨማሪም እንጥልዎ ረጅም ከሆነች የአየር መተላለፊያን ሊዘጋ ስለሚችል መርገብገቡ እንዲጨምር ያደርጋል።
አልኮሆል/መጠጥ መጠጣት፡- ከእንቅልፍ በፊት አልኮሆል አብዝተው የሚወስዱ ከሆነ ማንኮራፋት እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ። መጠጥ የጉሮሮ ጡንቻዎች እንዲላሉ ስለሚያደርግ ሰውነታችን በተፈጥሮ የአየር ቧንቧ እንዳይዘጋ የሚከላከልበትን መንገድ እንዲቀንስ ያደርጋል።
የአፍንጫ ችግሮች፡- ለረጅም ጊዜ የአፍንጫ
መጠቅጠቅ ችግር ከነበረ ወይም የአፍንጫ ውስጥ ችግሮች ካሉ ማንኮራፋት እንዲከሰት ያደርጋል። በተደጋጋሚ የአተነፋፈስ መቆራረጥ መኖር/ Sleep apnea:- ይህ ዋና መገለጫው ካንኮራፉ በኋላ ለተወሰኑ ሰከንዶች መተንፈስ ማቆም ሲኖር ነው። ከዚያን ድንገት አየር አጥሮት ከእንቅልፍዎ በድንገት ይነቃሉ።
ለማንኮራፋት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች
የሰውነት ክብደት መጨመር:- በተፈጥሮ የሚኖር ጠባብ መተንፈሻ አየር የምናስገባበት አካል መጥበብ የምንስበው አየር ግፊት እንዲጨምር በማድረግ ድምፅን ይፈጥራል። አልኮል መጠጥ ማብዛት፡- የአልኮል መጠጥ የጉሮሮ ጡንቻዎችን በማፍታታት አየር በሚገባበት ወቅት ርግብግቢት በመፍጠር ድምፅ እንዲጨመር ያደርጋል።
በአፍንጫ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች፡- በአፍንጫ ላይ የሚኖሩ ተፈጥሮአዊ የአቀማመጥ ችግሮች የማንኮራፋት ዕድልን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራሉ። እንዲሁም ጠባብ የአየር መተላለፊያ ያላቸው፣ በቤተሰብ ውስጥ መሰል ችግር መኖር ለማንኮራፋት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ናቸው።
ከማንኮራፋት ጋር ተያይዞ ምን ዓይነት ችግሮች ሊታዩ ይችላሉ?
የሚያንኮራፉ ሰዎች ቀን ቀን የእንቅልፍ ስሜት መሰማት፤ ቁጡነት/ብስጩነት መጨመር፣ ለነገሮች ትኩረት ማጣት፣ የደም ግፊት፣ የልብ በሽታ እና ስትሮክ ተጋላጭነት መጨመር፣ እንደ ሃይለኝነት፣ የመማረር ችግርና የመሳሰሉት የባህሪ ለውጦች መጨመር (በተለይ በሕፃናት ላይ)፣ የትደር/ፍቅር አጋርዎን እንቅልፍ ማሳጣት እና መረበሽ፣ በእንቅልፍ እጦት ምክንያት ለሰው ሠራሽ አደጋዎች መጋለጥና የመሳሰሉት ምልክቶች ይታይባቸዋል።
ማንኮራፋትን ለመከላከል ምን ይመከራል?
አስተኛኘትዎን ያስተካክሉ በጀርባዎ መተኛት ምክንያት እና ለስላሳ ላንቃዎን ወደ ጉሮሮ እንዲወርዱ ስለሚያደርግ በእንቅልፍ ጊዜ የመርገብገብ ድምፅን እንዳናሰማ ያደርጋል። ስለዚህ በጎን መተኛት መፍትሔ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ሲተኙ የመኝታዎን ራስጌ ከፍ ማድረግ። የሰውነት ክብደትዎን ይቀንሱ የሰውነት ክብደት የሌላቸው ሰዎችም ቢሆኑ ያንኮራፋሉ።
ነገር ግን ማንኮራፋቱ የመጣው የሰውነት ክብደት ከጨመረ በኋላ ከሆነ መንስዔው ሊሆን ስለሚችል ክብደትዎን ይቀንሱ። የአልኮል መጠጥ አይውሰዱ የአልኮል መጠጥ የምንወስድ ከሆነ በጉሮሮ አካባቢ የሚገኙ ጡንቻዎችን ስለምናፍታታ ማንኮራፋት እንጀምራለን። ከመተኛታችን በፊት ባለው ከ4 – 5 ሰዓት ጊዜ ውስጥ አልኮል መጠጥን መውሰድ ማንኮራፋትን ያባብሳል።
የእንቅልፍ ሰዓትዎን ያስተካክሉ ለረጅም ሰዓታት ያለዕረፍት የሚሠሩ ከሆነ እና በመጨረሻ እጅግ በጣም እራስዎን ካዳከሙ በኋላ የሚተኙ ከሆነ የጉሮሮ ጡንቻዎች በጣም ስለሚፈታቱ የማንኮራፋት ድምፅ ያሰማሉ።
አፍንጫዎን ከመደፈን ይከላከሉ፣ አፍንጫዎ በቅዝቃዜም ሆነ በአለርጂ ምክንያት ከተደፈነ የማንኮራፋት ዕድልን ስለሚጨምር ከመተኛትዎ በፊት በሙቅ ውሃ ገላን መታጠብ በተጨማሪ ውሃ በጨው በማድረግ አፍንጫን ማፅዳት ተገቢ ነው።
ይህ የአፍንጫን ቀዳዳዎች ስለሚከፍት ማንኮራፋትን ይከላከላል። ትራስዎን ይቀይሩ፣ በትራስዎ ውስጥ በዓይን የማይታዩ ብናኞች ተከማችተው ሊገኙ ስለሚችሉ መቀየር ተገቢ ነው። ፈሳሽ በብዛት ይውሰዱ ፈሳሽን በብዛት መውሰድ ከአፍንጫችን የሚመነጨውን ፈሳሽ ስለሚያቀጥን ማንኮራፋት እንዳይኖር ይረዳል።
ሐኪምዎን መቼ ያማክሩ?
የማንኮራፋቱ ድምፅ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የትዳር/ ፍቅር አጋርዎን የሚረብሽ ከሆነ፤ ትንፋሽ እያጠረዎ ወይም በትንታ ምክንያት ከእንቅልፍዎ የሚነቁ ከሆነ፤ የእነዚህ ነገሮች መከሰት ማንኮራፋቱ እንደ ኦብስትራክቲቭ እስሊፕ አፕኒያ ባሉ አሳሳቢ/ serious በሆኑ የጤና ችግሮች የመጣ ሊሆን ይችላል።
ሕፃናት ማንኮራፋት ካላቸው ለሕፃናት ህክምና ባለሙያ ማሳየት ያስፈልጋል። ኦብስትራክቲቭ እስሊፕ አፕኒያ የሚባለው ሕፃናትም ላይ ሊታይ የሚችል ሲሆን እንደ ቶንሲል፣ ውፍረትና የአፍንጫ/ጉሮሮ ችግሮች ለችግሩ መከሰት መንስኤ ናቸው።
ምንጭ – ከዶክተር ጤና
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013