ሰላማዊት ውቤ
በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የምትገኘውን ቃናት ቀበሌ በምናብ ልናስቃኛችሁ ነው። 982 እማወራና አባ ወራ አርሶ አደሮች ይኖሩባታል። የሁሉም አርሶ አደሮች ዋና መተዳደሪያ ግብርና ነው።
ግብርናውን በጓሮ አትክልትና በእንስሳት እርባታ ይደግፉታል። የእንስሳት ተዋጽኦ የሆነውን ወተት ለገበያ በማቅረብም ይታወቃሉ። በደን ልማትም ገቢያቸውን በማጎልበት ኑሯቸውን ይደጉማል።
ጠባብ ማሳቸውን የበለጠ ምርታማ በማድረግ ለማካካስ ከዘመናዊ ማዳበሪያ ጎን ለጎን ተግተው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ያዘጋጃሉ። ሌቱን አጋምሰው ቢያርፉም ከመኝታቸው የሚነሱት ማልደው ነው። በሬዎቻቸውን ማልደው ይጠምዳሉ። ወተቱም እንዲሁ ይታለባል። ወተቱን ጨምሮ አትክልትና እህል በእንስሳት ተጭኖ በዚሁ ሰዓት ወደ ደብረ ታቦር ገበያ ይጓጓዛል።
ጉዞው የመጫን አቅማቸው ፈቅዶ ሲገኝ በጥሪታቸው በገዟቸው የየግል ባጃጆች ይታገዛል። ከብቶችን ሜዳ ላይ ለቆ ማሰማራት በዚህች ቀበሌ ነውር ነው። ምክንያቱ ደግሞ ሜዳ ላይ የተሰማራ ከብት አካባቢውን ያጠፋና ለተፈጥሮ ሀብት አደጋ መሆኑ በመታመኑ ነው።
ከብቶቹ ታድያ በየደጃፎቻቸው ታስረው የሚመገቡ ሲሆን፤ የውሃ ገንዳ እና የመመገቢያ ግርግምም ይቀርብላቸዋል። በመሆኑም የእነዚህ አርሶ አደሮች ገፀ-ምድር ፀአዳና ለምለምነትን የተላበሰ ነው። የወንድ፤ የሴት ተብለው የተለዩና ከቆርቆሮ የተሰሩ መፀዳጃ ቤቶች በየቤቱ ተዘጋጅተዋል። አጠገባቸው የእጅ መታጠቢያና በሲሚንቶ የተለሰነ የገላ መታጠቢያ ቤት ይገኛል።
በቅርብ ርቀት የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ አለ። አብዛኞቹ የንፁህ መጠጥና ለእርሻና ለአትክልት የሚውል ውሃ ተጠቃሚ ናቸው። መኖሪያ ቤቶቻቸውም በሲሚንቶ ሊሾና በቆርቆሮ ዘምነዋል።
አኗኗራቸውና አለባበሳቸውም ቢሆን ዘመናዊ የሚባል ዓይነት ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎችም ናቸው። እነዚህ ሁሉ ተዳምረው ቃናት ቀበሌን መሰረቷን ገጠር ላይ ሳይሆን ከተማ ላይ የጣለች አስመስለዋታል።
ቃናት ቀበሌ ልምድ የተቀመረባትና በወረዳው ያሉ አርሶ አደሮች ሰፊ ተሞክሮ የሚቀስሙባት ነች። ለዚህ ሁሉ የቀበሌዋ ለውጥ በአርአያነት የሚጠቀሱት ሴት አርሶ አደር አለሜ ደሞዝ ናቸው።
ይሄን ያካፈሉን ከቢሮ ሥራቸው ጎን ለጎን ሰርክ በሬ በሚጠምዱበት አርሶ አደሮች ማሳ ውስጥና በአካባቢያቸው ተገኝተው የመስክ ቅኝት የሚያደርጉት የቃናት ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገደፋው አበጀ ናቸው። ኃላፊው እንደነገሩን በአርሶ አደሯ የተገኘው ተሞክሮ በፋርጣ ወረዳ ሁሉ ሰፍቷል። ቀበሌዋን የአርሶ አደሩ ሰርቶ ማሳያ ማዕከል ለማድረግም በቅቷል።
አርሶ አደር አለሜ ደሞዝ ተሞክሯቸው ለሌሎች ትልቅ አርአያ መሆን ይችላሉ ብለን በማመን አነጋግረናቸዋል። አርሶ አደሯ እንዳጫወቱን የዛሬን አያድርገውና ያኔ ቀበሌዋ የምትታወቀው በዚህ ገጽታዋ አልነበረም። አርሶ አደሩም ቢሆን እንዲህ አይታትርም። የእርሻው ሥራ የዕለት ጉርሱን አልሸፍን ሲለው እንዲህ እንደዛሬው ሌሎች አማራጮችን ከመሞከር ይልቅ እጁን አጣጥፎ እርዳታ ይጠብቃል።
አመጋገቡ የተመጣጠነ ባለመሆኑ ጤናውም ቢሆን እክል ነበረበት። የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው ባለማደጋቸው በአብዛኛው ሕፃናቱ እየቀነጨሩበት ሲቸገር ቆይቷል። ለበሽታም ተጋላጭ ናቸው።
አዋቂውም ሆነ ልጁ አዘወትሮ ይመገብ የነበረው አንድ ዓይነት ምግብና ድንች ወጥ ነበር። እንደ ዛሬው የተለያየ የጓሮ አትክልት ማምረት አልተለመደም። የማሳ አስተራረሱም ቢሆን ባህላዊና ኋላ ቀር ነበር፡፡
በዚህም ማሳው ለረጅም ጊዜ ምርታማ ላለመሆን ተገድዷል። ‹‹በአጠቃላይ ኑሯችን ድካም ነበረበት›› ሲሉ በማስታወስ አርሶ አደሯ የቀድሞ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ይጠቅሳሉ። አሁን ዕድሜ ለግብርና ባለሙያዎች ይህ ሁሉ በነሱ ድጋፍ ተቀይሯል ሲሉ የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸውን ሙያዊ ድጋፍ በማንሳትም ያመሰግናሉ።
‹‹ከዚህ ቀደም ያለ ዕውቀት ዘርተን ያለ ዕውቀት ነበር የምንለቅመው›› የሚሉት አርሶ አደሯ አሁን ላይ ግን ባለሙያው ለዚህ ማሳ ይሄን ያህል ማዳበርያ ያስፈልገዋል ይሏቸዋል። በዚህ ሰዓት እንዲህ ዓይነት ኬሚካል መረጨት አለበት፤ ይሄን ጊዜ ይታረምና ይኮተኮታል የሚል ሙያዊ ትምህርት ይሰጧቸዋል። በመስመር ሲዘሩ አብረው እየተከተሉ ያሳያቸዋል።
ከሚቀርብላቸው ዘመናዊ ማዳበርያ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ማዳበርያ እያዘጋጁ መጠቀምንም አስተምረዋቸውል። እሳቸው ይህን ማዘጋጀት ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። ማሳቸው 10 በ 20 ወይም 200 ካሬ ሜትር ብቻ ብትሆንም በመስኖ ተጠቅመው በዓመት ሦስት ጊዜ ያህል ያመርቱበታል።
16 ሜትር ተኩል ባለ መለቅለቂያ ዘላቂ ውሃ ያግዛቸዋል። እንዲሁም በእሳቸውና በባለቤታቸው ጉልበት ከከርሰ ምድር ተቆፍሮ የወጣ ሌላ 16 ሜትር ውሃ ለቋሚ አትክልት አላቸው። ለዚህ ማስገንቢያና ሲሚንቶ ለማስጫን 40 ሺ ብር ወጪ ማድረጋቸውንም ነግረውናል።
በተከራዩአቸው አምስት ቦታዎችም የእርሻ ሥራቸውን አስፋፍተዋል። ቀድሞ ከሦስት ኩንታል ያልበለጠ በሚያገኙበት በአንድ ቃዳ ማሳ አሁን ላይ 10 ኩንታል ምርት ማፈስ ችለዋል። የቀበሌዋ የአየር ንብረት ወይና ደጋ እንደመሆኑ ምቹ የሆነው ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ ማምረት አስችሏቸዋል።
እነዚህ እሳቸው በዋናነት ከሚያመርቷቸው ለገበያም ከሚያቀርቧቸው ይጠቀሳሉ። በጓሯቸው ደግሞ ካሮት፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ቆስጣ፣ ቲማቲምና ድንች ያለማሉ። እነዚህን አትክልቶች ማልማት በመቻላቸው ቤተሰባቸውን የተመጣጠነ ምግብ እንዲመግቡ ረድቷቸዋል።
በገበታቸው አምስትና ስድስት ዓይነት ወጥም ለማቅረብ አስችሏቸዋል። አጥሚት፣ ገንፎ፣ ወተት፣ ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦ እና ቋንጣ አመጋገባቸውን ለማሻሻል እንደረዷቸው አጫውተውናል።
የአትክልት ምርት በተለይ ካሮት ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለደብረ ታቦር ገበያ ያቀርባሉ። በቅርቡ ካሮት ሸጠው ሰባት ሺህ ብር አግኝተዋል። ሌላው ገቢያቸው ከተሻሻሉ ሁለት የውጭ የወተት ላም ዝርያዎች የሚያገኙት ወተት ነው። በቀን ሰባት ሊትር ያልባሉ። ከራሳቸው ተርፎም ለገበያ ያቀርባሉ።
‹‹ሙያተኛ ያለኝን ሳልጠራጠር በመሥራቴ ውጤታማ መሆን ችያለሁ›› ይላሉ፡፡ ያኔ ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እስከ ቅርብ ዓመታት መኖሪያ ቤት አልነበራቸውም፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በሚያገኙት ገቢ ቃናት ላይ ቤት ሰርተዋል።
ደብረ ታቦር ከተማ ላይም አንድ ትልቅ እልፍኝ ያለው መኖሪያና ስድስት ክፍል ቤቶችን ገንብተው እያከራዩ ነው። ሦስት ሴትና ሦስት ወንድ ልጆቻቸውንም አስተምረውበታል።
አሁንም እያስተማሩበት ነው። ገሚሶቹንም ሥራ አስይዘውበታል። አንዲት ባጃጅ ለመግዛትም አስችሏቸዋል። በቤታቸው ሁሉም ነገር ሞልቶ እንዲተርፍ አድርጓል። የከተማ ነዋሪዎች የሚጠቀሙበት ዘመናዊ የቤት ቁሳቁስ፣ በኤሌክትሪክ የሚሰራ የምግብ ማብሰያ ምድጃን ጨምሮ በሙሉ በአርሶ አደሯ ቤት ይገኛሉ።
አብዛኞቹ የአካባቢው አርሶ አደሮች እርሳቸውን እያዩ ተለውጠዋል። ምርታማ መሆንና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ማሻሻል ችለዋል። ለዚህም አርሶ አደሮቹን በግልም ሆነ ሰብሰብ አድርገው ይህን እንስራ እንዲህ እናድርግ ማለታቸው አስተዋጽኦ አድርጓል።
‹‹የባለሙያን ምክር እኔ ከሞከርኩትና ውጤት ካየሁበት በኋላ ሳልታክት አካፍላለሁ›› የሚሉት አርሶ አደሯ በማሳ ብቻም ሳይሆን በእንስሳትና በሌሎች ተግባራትም ይፈጽሙታል። አሁን ከእሳቸው አልፎ ሁሉም የሚያደርገው ሆኗል።
ከፋርጣ ወረዳና ከደቡብ ጎንደር ዞን እየመጡ የቀበሌዋን ተሞክሮ እንዲቀስሙ አስችሏል። እንደሚባለው በተለይ ለሴት አርሶ አደሮች ዓይን ናቸው። የቤተሰብ ምጣኔ፣ ድህረ ወሊድና ቅድመ ወሊድ አገልግሎት እንዲጠቀሙ አድርገዋል።
በቀበሌ ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ አቅራቢነታቸው ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሀሰት ምስክርና በጉልበት መሬታቸውን የተነጠቁ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ አስችለዋል። የሕብረት መሬት ከአርሶ አደሩ እኩል እየታጨደ እየተከፈለ ገንዘብ የሌላቸውም እየሸጡ የሚያገኙበትን ዕድል አመቻችተዋል።
የቃናት ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገደፋው አበጀ እንደነገሩን አርሶ አደሯ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለመሸለምና ሞዴል ለመባል በቅተዋል። የግብርና ባለሙያዎች የሰጧቸውን ምክር በመተግበር ቀበሌዋንም በሞዴልነት አሸልመውና አስጠርተዋል። በተለይ በቀበሌዋ አንድ ሺ 280 ሄክታር የሚታረስ መሬት ብቻ ከመሆኑ አንፃር የሚሰጣቸውን ይተገብራሉ። እንደ መብዛታቸውና መሬቱ እንደ መጥበቡ ሳይሆን እንደ ጋራ ጥረታቸው ውጤታማ ሆነዋል።
በተለይ የተሻሻለ የወተት ላም ዝርያ መጠቀማቸው ረድቷቸዋል። የወተት ላምም ከ25 እስከ 30 ሺ ብር አውጥቶ ያልገዛ የለም። አብዛኛው አርሶ አደር ሁለት የወተት ላም ያላቸው በመሆናቸው በቀን ሰባት ሊትር ወተት ያገኛሉ።
በቀበሌዋ በከፍተኛ መጠን የወተት ምርት ይመረታል። ወተቱንም እስከ ደብረ ታቦር ወስደው በመሸጥ ይጠቀማሉ። አርሶ አደር አለሜን ጨምሮ አብዛኞቹ ትምህርት የመማር ዕድል ባያገኙም እዚህ ደረጃ የደረሱት እርስ በእርሳቸው በመማማር መሆኑን ይናገራሉ።
የፋርጣ ወረዳ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መአድነው ብርሃኑ እንደገለፁልን ፋርጣ ወረዳ በ32 ቀበሌ የተደራጀ ነው። ቃናትን ጨምሮ 14ቱ የገጠር ቀበሌዎች ናቸው። በእነዚህ የገጠር ቀበሌዎች የግብርናውን ሥራ የሚያሳልጡ 115 ሙያተኞች ይገኛሉ። በወረዳ ደረጃም ስምንት የሥራ ቡድኖች አሉ።
የድጋፍ ሰጪዎችን ጨምሮ 65 ሠራተኞች ይገኛሉ። እነዚህ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሌት ተቀን ተግተው ይሠራሉ። ማሳን ደጋግሞ በማረስ፣ ግብዓትና ምርጥ ዘር በማቅረብ፣ የአፈር ለምነትን የሚጨምሩ ሥራዎችን በመሥራትና የተፈጥሮ ማዳበርያ በማዘጋጀት አርሶ አደሩ ውጤታማ እንዲሆን አስችለዋል።
ወይዘሮ ዓለሜ ደሞዝ ደግሞ እንደ ቃናት ቀበሌ ይህን ቀድሞ በመተግበር አስተማሪ የሆኑ ሴት አርሶ አደር ናቸው። እንደ ወረዳ ብዙ ሞዴል አርሶ አደሮች አሉ። በግብርና ሥራ በእንስሳት እርባታና በተለያየ ተግባር ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ማፍራት ተችሏል።
‹‹አርሶ አደሯ ሲደክሙ የነበሩት ከአቅም በላይ ነበር። ገቢያቸውም የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን ተስኖቸው ኖሯል›› ያለችን የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያ ሙሉ ቀን ስንታየሁ ናት። እንደ ባለሙያዋ አሁን ግን ጉልበታቸው እየተቆጠበ መጥቷል። የተሻለ ኑሮ እየኖሩና ለአካባቢውና ለወረዳው አርሶ አደሮች አርአያ እየሆኑ ነው። አብዛኛው እሳቸውን እያየ የተሻለ ሥራ መሥራት ችሏል።
ለውጡ የመጣው የእንስሳት በእንስሳት፤ የተፈጥሮ ሀብት በተፈጥሮ ሀብት ባለሙያዎች ድጋፍ በመደረጉ ነው። በተለይ በተፈጥሮ ሀብት የሚሰራው ግጦሽ መሬት፣ አፈር፣ ሥርዓተ ምህዳርን የያዘ በመሆኑ ፈጥኖ ለውጥ ለማምጣት ይጠቅማል። የተፈጥሮ ሀብት ሲለማ ወንዞች ምንጮች ይጎለብታሉ።
መስኖ ማልማት ይቻላል። የገጠሩን አርሶ አደር ሕይወት ለመለወጥም እንደ አቅጣጫ የተቀመጠውም ተፈጥሮ ሀብትን ማልማት ነው። አርሶ አደሩ አካባቢውን እንዲንከባከብ የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች እንዲሰራ ምክር ትሰጣለች። በቀጣዩ ወር ከጥር አንድ ጀምሮ የጎርፍ መቀልበሻ ወይም ማስወገጃ፣ የአፈር ለምነትን የሚጨምሩ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነግራናለች። የአርሶ አደሮቹ ትጋት የባለሙያዎች እገዛ ለውጤታማነት አብቅቷቸዋል።
ይሄም የአርሶ አደሩን ኑሮ በእጅጉ ቀይሯል። ጤናቸው የተጠበቀ የትምህርትን ገበታ የጨበጡ ልጆችን ማሳደግም ችለዋል። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ልምድ በመሆኑ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ሊሰፋ ይገባል እያልን ሀሳባችንን ቋጨን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013