የእርስ በርስ ግጭት፣ጦርነት፣ርሃብ፣እርዛት፣ ሥደት ለአያሌ ዘመናት የዜጎችን ትከሻ አጉብጦታል፡፡ የአገሪቱ እናቶች ከተፈጥሯዊ ምጥ የበረታ ሰው ሰራሽ ምጥ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ወንድ ልጅ ጸንሰው በወለዱ ጊዜ ራሳቸውን ይረግማሉ፡፡ አገራቸው ከእጃቸው እየነጠቀ ለጦርነት እሳት የሚዳርግ ሥርዓት ባለቤት ነበረች፡፡
የአርሶ አደር ወንድ ልጆች ገና ጉልበታቸው ሳይጠና ጀምሮ ጣቶቻቸው መሳሪያ ለመወልወል እንጂ እስክሪብቶና ደብተር ለማገናኘት አልታደሉም ነበር፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች እና ልፋታቸው እኩል እውቅና የተቸረው አልነበረም፡፡ እነዚህና መሰል አገራዊ ምስቅልቅሎች እና የፍትህ መጓደሎች አምጠው የወለዱት ኢህአዴግ ህዝባዊ ድጋፍ አገኘ፡፡
በአገሪቱ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል እውቅና አገኙ፡፡ ባህላቸው፣ ወጋቸው፣ ማንነታቸው መኩሪያ እንጂ ማፈሪያ መሆኑ ቀረ፡፡ በአለም የሚያስደምም እና የሚያኮራ ሃብት ሆኖ ቱሪስትን በመሳብ የኢኮኖሚው አጋዥ ሊሆን መንደርደር ያዘ፡፡ ማህበረሰቡም ለዘመናት ከተጫነው ድህነት ለመላቀቅ ውስጡን በተስፋ አጀገነ፤ ፊቱንም ወደ ለውጥ አዞረ፡፡
በኢህአዴግ የመሪነት ሚና ኢትዮጵያ ማንነቷ ይለወጣል በሚል የአገሪቱ ዜጋ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እምነት አደረበት፡፡ ኢትዮጵያን ከምትታወቅበት ችግር ለማላቀቅ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ደረጃ ዘርፈ ብዙ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ተጀመሩ፡፡ በሂደትም የአገሪቱን ገጽታ በበጎ ለአለም ማህበረሰብ የማስተዋወቁ አላማ ሥኬት እየታየበት መጣ፡፡ በመሆኑም ከአድዋ እና ከአትሌቶቻችን ገድል እኩል በአገራችን የእድገት ግስጋሴ መዘመሩን ተያያዝነው፤ ኢህአዴግም ዜማና ግጥሙን እየደረሰ ከፊት መገስገሱን ቀጠለ፡፡ ዓመታት ነጎዱ፡፡
የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አይናቸው ከአገራዊ ፍቅርና መዝሙር ይልቅ ብሔራቸውን እና ሰፈራቸውን ቦግ አድርጎ ያሳያቸው ጀመር፡፡ ለወትሮው ቁብ የማይሰጡትን በድሮው የፖለቲካ ፓርቲዎች በአሁኑ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ልፈፋ ቆም ብሎ ማዳመጥ፣ ማጣጣም እና በገሃድ ከሚስተዋለው ተግባር ጋር ማመሳከር ተጀመረ፡፡ ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ በአይን ሊታዩ የሚችሉና የሚያስመሰግኑ በርካታ ተግባራት መሰራታቸው የሚክድ አይኖርም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ለማመን የሚከብዱ አስነዋሪ ተግባራትም አገሪቱን ከሚመሩ አካላት በኩል በህዝብ ላይ መፈጸማቸው ይነገራል፡፡ አገሪቱ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ሥር ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን የምታራምድ መሆኗ ሲቀነቀን ቢቆይም ተጻራሪ ተግባራት በህዝቦች መካከል እንዲበቅል፤ መጠራጠርና አለመተማመን እንዲጎለብት በሰፊው መሰራቱ ውሎ አድሮ ገሃድ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሥልጣን ላይ የነበሩት አካላት የተነፈሱት መሬት ጠብ አይልም፡፡ ማንም በተግባር የተፈተነ እና በምክንያት የጠነከረ እውነት ይዞ ቢቀርብ በእነሱ ረዥም እጆች ካልተዳሰሰ ሃሰት ነው፡፡ በተጨባጭ ሞግቶ በማሳመን የሃሳብ የበላይነትን ለመቆናጠጥ መጣር ታርጋ ያስለጥፋል፡፡ እልፍ ሲልም አረንቋ ይከታል፡፡ ከአንደበታቸው የተተነፈሰ ጉዳይ ውኃ የማያነሳ ሃሳብ እንኳን ቢኖረው አለመቀበል አይቻልም፡፡ ማስተባበልም ዋጋ ያሥከፍላል፡፡
አገሪቱ በየዘርፉ ብዙ አዋቂዎችን አፍርታለች፡፡ በአለም ላይ አንቱ የተባሉ ምሁራን ከማህጸኗ በቅለዋል፡፡ ለመላው ዓለምም አስቷዋጽኦ አበርክተዋል፤ መነጋገሪያም ሆነዋል፡፡ በእናት አገራቸው አፍ ግን አይወደሱም፤ አይነሱም፡፡ ምክንያቱም ከመሪዎቿ ጋር ባለመጣባታቸው፤ ‹‹የራስ ወርቅ አያደምቅ›› የሚል ብሂላችን ውላጆች ነን፡፡ አንተ፣ አንቺ፣ እናንተ፣ እኛ፣ ሁላችንም፤ በእጀ ረዣዥሞቹ አካላት አንደበት የተነገረንን ብቻ የምናምን፤ በተቀደደልን ቦይ ብቻ ሥንፈስ የኖርን የዋሆች ነበርን/ነን፡፡
የሚያስተዛዝበው፤ የዚህ ተግባር ሰለባዎች ግለሰቦች ብቻ አለመሆናቸው ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ይበልጥ እንዲጠናከርና በሕዝቦች እንዲለመድ የሚያደርጉ የክልል አስተዳደር መዋቅሮች ጭምር የመወሰን ሥልጣናቸው በፌዴራሉ እጅ ሆኖ ኖሯል፡፡
ላለፉት ጊዜያት የህዝቦችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የተዋቀሩት ክልሎች ነጻ ሆነው ማሰብና መወሰን፣ ራሳቸውን ችለው መምራት የሚችሉ አልነበሩም፡፡ በተለይም ታዳጊ ክልሎች በሚል የተሰየሙት ይበልጡን በፌዴራል ባለሥልጣናት ጉልበት ሥር ‹‹ቅኝ›› ወድቀው ሲቸገሩ መኖራቸው ይነገራል፡፡
በታዳጊ ክልሎች የፕሬዚዳንቶቹ አማካሪዎች በሚል የፌዴራል ባለሥልጣናት ጉዳይ አስፈጻሚዎች ተሹመው ይላካሉ፡፡ እነዚህ አካላት የዚያ ክልል የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ በክልሉ የሚከናወን ማንኛውም ተግባር የሚነደፈው በእነዚሁ አካላት ነው፡፡ የየክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናትም ሲሾሙ የሚኖሩት በፌዴራል ባለስልጣናት እጅ አዙር ቁጥጥር ነበር፡፡
በየታዳጊ ክልሎች ኢንቨስተር በሚል ሥም የተሰገሰጉት የመሬት ወራሪ ከበርቴዎች በትዕዛዝ የገቡ ናቸው፡፡ ለእከሌ፣ ለእከሌ፣ለእከሌ ይሄን ያህል ሄክታር መሬት በዚህ አካባቢ ለክተህ በአስቸኳይ ሥጥ እስከማለት የደረሰ ጣልቃገብነት በአገሪቱ ተሰርቷል፡፡ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሀመድ (አብዲ ኢሌ) በሰሩት ጥፋት በሕግ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ‹‹አድርግ ተብዬ ታዝዤ ነው›› ያሉትን ለማመን ሲዳዳቸው የተስተዋሉ አካላት ነበሩ፡፡
የሌሎች ክልሎች ርዕሳነ ብሔሮችም ያሳለፉትን ጊዜያት ከአሁኑ የዶክተር አብይ የለውጥ ርምጃ ጋር ሲያነጻጽሩ የፌዴራል ባለሥልጣናት በእጅ አዙር ክልሎችን መርተዋል፤ አስተዳድረዋል ባይ ናቸው፡፡ ይህን መራር እውነት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአንደበታቸው ማረጋገጡን አስነብቦናል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ የአገሪቱ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች ሲመሩ የነበሩት በአቅራቢያቸው አማካሪና ምክትል በሚል በተወሸቁ አደገኛ ሰዎች እንደነበረ ዛሬ ላይ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡
አገርና ህዝብን ዋሽቶ መኖር አይቻልም፡፡ ላለፉት አመታት የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ረዣዥም እጆች ተዘርግተው በክልሎች የፈለጉትን አድርገዋል፡፡ የእነሱን የግል ጥቅሞች የሚያስከብሩ ተሹመዋል፡፡ ጠንካራ የድብቅ የጥቅም መዋቅሮች ጭምር ተደራጅተው መኖራቸው ይነገራል፡፡ በፈጠሩት አደገኛ ሰንሰለትም የሕዝብንና የአገርን ሃብት ከሚፈልጉት ጫፍ፤ በሚፈልጉት ዓይነትና መጠን ማፈስ አስችሏቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ካደረክለት አስበልጦ በተናገርከው እውነት የሆነ ቃል ይወድሃል፡፡ ያከብርሃል፡፡ ሥለዚህ ህዝብን እያታለሉና እየዋሹ ክብር የለም፡፡ ለዚህ ነው ውድ ህይወቱን ገብሮ በአገሪቱም፤ በሥርዓቱም መሻሻሎች ያመጣው፤ አሁንም የለውጡ ባለቤት ራሱ ህዝቡ ነው፡፡ ለመሪዎቹ እድል መስጠቱ እንጂ በእሱ ላይ ክህደት ፈጻሚ አመራሮች ጠፍተውት አይደለም፡፡ በአጠቃላይ፤ አሁንም የእነዚህ አካላት ሴራ የሴክተር መዋቅሮቻችን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ችግር ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል›› እንዳሉት አበው የእውነት አገርን ከሚወዱ እና በሃቅ አገርን ከሚመሩ የለውጥ መሪዎች ጎን እንቁም እላለሁ፡፡
ከፖለቲካችን በስተጀርባ ማርም እሬትም ነበር፡፡ በአገሪቱ የታዩት በርካታ ስኬቶች በማር ሲመሰሉ፤ ከእነርሱ በስተጀርባ የሚፈጸሙት ደባዎች፣ ተንኮሎች እና ተገቢ ያልሆኑ ስራዎች ግን እሬት ነበሩ፡፡ እኩዩን ነገር እየነቀስን በማውጣት መልካሙ ማበረታታት የፖለቲካችን መገለጫ መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
ሙሐመድ ሁሴን