አዲስ አበባ:- ለከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉትን ‹‹ቪ8›› መኪኖች በሌሎች አዳዲስና ወጪ ቆጣቢ ተሽከርካሪዎች የመተካቱ ሂደት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለፀ።
ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የአዳዲሶቹ ተሽከርካሪዎች ግዢ የተፈፀመ ሲሆን፤ ከየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተተኪዎቹ ወደ ስራ ይገባሉ።
የመስሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ለከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትን ቪ8 መኪኖች ይተካሉ ተብለው የተመረጡት አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ግዢ ተጠናቅቆ ወደስራ የማስገባቱ ሂደት የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይገኛል።
400 አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ለስራው ዝግጁ ሆነዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ 397ቱ ከየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደስራ የሚገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ይህ ማለት ግን የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ስራ ይጀምራሉ ማለት አይደለም። ለስምሪት ብቁ የሚያደርጋቸውን የትራፊክና የመንገድ ደህንነት ደንብና ስርአት የማሟላት ተግባራት ይጠብቋቸዋል ያሉት አቶ ሀጂ፤ ተሽከርካሪዎቹ ታርጋ የማግኘት፣ የሻንሲ ቁጥር ምዝገባና የመሳሰሉትን የመንገድና ትራንስፖርት ሥርዓቶችን እስኪያሟሉ ቢያንስ ከ15 እስከ 20 ቀናት ሊወስድባቸው ይችላል ሲሉም አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፤ በአሁኑ ሰአት ድልድሉ የሚመለከታቸው አካላት የተለዩ ሲሆን፤ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ በሚኒስትርና በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ የሚገኙ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች የሚጠቀሙባቸው ‹‹ቪ8›› ተሽከርካሪዎች በድልድሉ መሰረት በአዳዲሶቹ ይተካሉ። በአዳዲሶቹ የሚተኩትን ‹‹ቪ8›› ተሽከርካሪዎች በተመለከተም መኪኖቹ ባሉበት በመንግስት ይዞታ ስር እንደሚቆዩና ለመስክ ስራ አገልግሎት እንደሚውሉ አስታውቀዋል።
በዶክተር አቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት ወደአመራር መምጣቱን ተከትሎ ለወጪ ቁጠባ ሲባል በከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለስልጣናት ይዞታ ስር የነበሩ ‹‹V8›› ተሽከርካሪዎች የሚሰጡት አገልግሎት እንዲቋረጥና በሌሎች ወጪ ቆጣቢ ተሽከርካሪዎች እንዲተኩ መወሰኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
ግርማ መንግሥቴ