ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት በማቅለል ረገድና የሚጫወተው ሚና በቀላሉ አይታይም፡፡ ይህ ችግሮችን የመፍታት ሚናውም በግንኙነት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በመሰረተ ልማት፣ በትራንስፖርት ፣በጦር አውድ ፣ወዘተ. እንደየፈርጁ ይገለጻል፡፡
የቴክኖሎጂ ችግር ፈቺነት ግን ቴክኖሎጂን አውቆ እና በተገቢው መንገድ አስተዳድሮ መጠቀም አለመጠቀም ላይ ይወሰናል፡፡ ቴክኖሎጂውን አውቆ በአግባቡ አስተዳድሮ መጠቀም ከተቻለ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እና የሚፈልጉትን ግብ ማሳካት የሚቻል የመሆኑን ያህል፤ ቴክኖሎጂውን ይዞ እና በአግባቡ አውቆ ከመተግበርና ከማስተዳደር አንጻር ዝንፈት ከተፈጠረ ግን ችግር ፈቺነቱ ቀርቶ ጉዳቱ የሚያመዝን ብቻ ሳይሆን የከፋም ሊሆን ይችላል፡፡
ለዚህም የህወሓት ጁንታ አገር ለማተራመስ ተግባሩ የሄደበትን መንገድ እና መንግስት ሕግን ለማስከበር የወሰደውን እርምጃ ማየት በቂ ነው፡፡ጁንታው በ1960ዎቹ አስተሳሰብ ላይ ተቸንክሮ ያለ ቢሆንም፣ በገንዘብ አቅም እና ቴክኖሎጂ ታግዞ በድጋሚ ወደ ስልጣን ለመመለስ ሲል የአገር አለኝታ የሆነውን የሐገር መከላከያ ሰራዊት ከማጥቃት በዘለለ በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስና የግንኙነት መስመሮች ላይ የሳይበር ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም ባወጣው መረጃ መሰረትም፤ ጁንታው ቡድን አገሪቷን በሁሉም መስክ ከጨዋታ ውጪ ሊያደርጋት የሚችል ተግባር ፈጽሟል፡፡ በዚህ ተግባሩም በአስራ አራት ቀናት ብቻ 39ነጥብ 8 ቢሊዮን ያልተሳኩ ጥቃቶችን ሰንዝሯል፡፡ ይህን ያደረገውም በአንድ በኩል ያልተፈቀዱ የአገር መረጃዎችን ለማግኘት ሲሆን፤ በሌላ በኩል እነዚህን አገልግሎቶች በማቋረጥ መንግስትን ሽባ ለማድረግና የቡድኑን የአሸናፊነት ልዕልና ለማረጋገጥ ነበር፡፡
ለዚህም ነው መከላከያ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ በክልሉ የመብራት፣ የስልክና ሌሎች የመገናኛ (የሰሜን ዕዝ የመከላከያ የሬዲዮ ግንኙነት ጨምሮ) አውታሮችን ማቋረጥና መጥለፍ ውስጥ የገባው፡፡ ሆኖም ቴክኖሎጂን መታጠቅ ብቻውን ለድል ስለማያበቃ ያሰበው ሁሉ ቅዠት ሆኖ እንዲያልፍ አርጓል፡፡
ይህም ኪሳራ ቴክኖሎጂን በአግባቡ አውቀው ካልተገበሩትና ካላስተዳደሩት ለማግኘት ካሰቡት የበላይነት በተቃራኒው ኪሳራው ያመዘነ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም እርሱ በገንዘብ አቅም ቴክኖሎጂን ታጠቀ እንጂ አውቆ አልመራውም፡፡ ይልቁንም ነገሮች በመንግስት በኩል በጥበብና በእውቀት ተነድፈው፤ በቴክኖሎጂ ታግዘው ቆራጥ አመራር እየተሰጠባቸው ጁንታው ከህልሙ ሳይደርስ በቅዠት እንዲቀር አድርገውታል፡፡
የሕግ ማስከበር እርምጃውም እንደ ጁንታው ባረጀና አሁን ላይ ፈጽሞ በማይሞከር የቆረጣና ጅምላ ድብደባ ውጊያ እሳቤ የተከናወነ አይደለም፤ጠላትን ከወገን በለየ ከሲሙሌሽን ክፍል በማዕከል ክትትል እየተደረገለት በሰው አልባ ድሮኖች የተከናወነበት ነው፡፡
ለራስና ለቡድን ስልጣንና ጥቅም ሳይሆን፤ ለአገርና ሕዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ፤ ንጹሃንን ከጠላት ለይቶ፤ የጦርነት ስነምግባሮችን ጠብቆ፤ በወታደሮች እልህ፣ ቁርጠኝነትና አስተዋይነት በተሞላበት ተጋድሎ ጁንታው ድል ተመትቷል፡፡
ሰሞኑንም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ሰራዊቱ ለተቀዳጀው ድል ቴክኖሎጂ አስተዋጽኦ ማድረጉንና ለቴክኖሎጂው መተግበር ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውም ይሄንኑ የቁርጠኛ አመራርና ቴክኖሎጂ ጥምረት የድል ጉዞ ያመለክታል፡፡
ሰራዊቱ ለተቀዳጀው ድል ልዩነት ከፈጠሩት ውስጥ አንዱ የታጠቀው ቴክኖሎጂ ቢሆንም፣ ለዚህ ቴክኖሎጂ መተግበርና ሰራዊቱ ቴክኖሎጂውን እንዲታጠቅ በማድረጉ በኩል ደግሞ አመራሩ ትልቅ ሚና እንደነበረው ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡
ለዚህ ዋናው ማሳያ ደግሞ፣ በአገሪቱ እውን ከሆነው ለውጥ ማግስት አንስቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀዳሚ ስራ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ ላይ መሆኑ ነበር፡፡ በዚህ ሪፎርም ቀዳሚ ቦታ ከያዙት አንዱ ደግሞ የመከላከያ ተቋም ነው፤ መከላከያውን በሰው ኃይል፣ በሎጀስቲክስ እና በቴክኖሎጂ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡
በዚህም እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ የተወሰደው መከላከያ የባህር ሃይል እና የሳይበር ደህንነት ዘርፎችን እንዲያደራጅ መደረጉ ሲሆን፤ የአየር ኃይሉም በተመሳሳይ ሰው አልባ ድሮኖችን ጭምር እንዲታጠቅ ተደርጓል፡፡
ይህ የአመራር ቁርጠኝነት ከቴክኖሎጂ ጋር ሲቀናጅ ቴክኖሎጂውን በእውቀት ለመምራትም ለመጠቀምም በማስቻሉ እንዲራዘም የተፈለገው ጦርነት በአጭሩ እንዲቋጭ፤ ብዙ ጉዳት እንዲፈጥር የተወጠነው ሴራም ባነሰ ኪሳራ እንዲጠናቀቅ ማድረግ አስችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2013