ፍሬህይወት አወቀ
ትሁት ናቸው፤ሰው አክባሪና ቅን። ቀጠሮ አክባሪ መሆናቸውን ደግሞ ለቃለ መጠይቅ በፈለግናቸው ጊዜ ኑራቸውን እና ሥራቸውን ከመሰረቱበት ጅግጅጋ ከተማ በመነሳት አዲስ አበባ መጥተው አስመስክረዋል – አቶ ክፍለገብርኤል ወልደተንሳይ ።
አቶ ክፍለገብርኤል በሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በትምህርት ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን የቻሉ ባለሀብት ናቸው። ወደ ዘርፍ ከመግባታቸው በፊት በቀድሞው ምድር ጦር በጦር መኮንነት አገልግለዋል። በምድር ጦር ውስጥ በቆዩባቸው ዓመታትም የፖለቲካ መምህር በመሆን ወታደሩን በፖለቲካ በማንቃትና በማደራጀት ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ ባጋጠማቸው ጉዳት ከምድር ጦር በጡረታ መገለላቸውን ያስታውሳሉ።
በ1982 ዓ.ም ከምድር ጦር በ158 ብር ከ68 ሳንቲም ጡረታ ቢሰናበቱም የነበራቸው የማስተማር ፍቅር ግን እውስጣቸው አድሯል። በምድር ጦሩ የሞከሩትንና በውስጣቸው ያለውን የመምህርነት ፍላጎት ደምረው ምኞታቸውን በተግባር ለማዋል በቀድሞ አጠራሩ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አመሩ። በዚያም በጂኦግራፊ ወይም በመልክዓ ምድር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመረቁ።
ከዚያም ጦማር ተብሎ በሚታወቀው ጋዜጣ በምክትል ዋና አዘጋጅነት ተቀጥረው ማገልገል ቀጠሉ። በዚህ ሁኔታ እያሉ መክሊታቸውን የሚያገኙበት እና ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉበት አጋጣሚ ተፈጠረ። አጋጣሚውም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት እሳቸውን ጨምሮ የጦማር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩት ግለሰብ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ መታሰራቸው ነበር። በእስር ቤት ጥቂት ቆይተው አቶ ክፍለገብርኤል ተፈቱ።
በዚህ ጊዜ ታድያ በእስር ላይ ያሉትን ባልደረባቸውን ስንቅ እያቀበሉ ቆይታቸውን በጅግጅጋ ያደረጉት አቶ ክፍለገብርኤል ዘስፓርክ አካዳሚን ለመክፈት ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው። በወቅቱ በጅግጅጋ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ቤት እጥረት መኖሩን እና ብዙ ወላጆችም ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ማስተማር የሚፈልጉ መሆኑን ከአንድ ወዳጃቸው አረጋገጡ። ይህን መረጃ እንዳገኙ በውስጣቸው ያለውን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ ጊዜ ሳያጠፉ በ1995 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ዘስፓርክ አካዳሚን አቋቋሙ።
የዛሬ 17 ዓመት አካባቢ ከህጻናት መዋያ የጀመረው ዘስፓርክ አካዳሚ በአሁን ወቅት ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል። ወደ ሥራ በገቡበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ፍላጎትና 12 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ይዘው ነው።
ሥራ በጀመሩበት የመጀመሪያው ዓመት ስድስት ወላጅ አልባ ህጻናትን በነጻ ለማስተማር ከከተማው ቀይ መስቀል ተቀብለዋል። ከስድስቱ ህጻናት በተጨማሪ በከተማ ውስጥ ምዝገባ በማድረግ ተጨማሪ 74 ተማሪዎችን በመመዝገብ በድምሩ 80 ህጻናትን ይዘው ማስተማርን አሀዱ አሉ።
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የትምህርት ሥራ በአሁን ወቅት በዓመት ስድስት ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት የሚችል ተቋም ሆኗል። ዘስፓርክ አካዳሚ ከቀለም ትምህርት ባሻገር በስነምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት በሚያደርገው ጥረት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቶ በአሁኑ ወቅት 1ሺህ400 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል።
ወደ ትምህርት ቤቱ የሚመጣው ተማሪ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ የመጀመሪያ ሳይክል ተጨማሪ ቅርንጫፍ ለመክፈት በሂደት ላይ መሆኑን ይናገራሉ ።
ከ17 ዓመት በፊት በጅግጅጋ የሚገኙ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ወደ አዲስ አበባ ይልኩ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ክፍለገብርኤል ዛሬ እዚህ ለመድረሳቸው ከቀድሞው የሥራ ቤታቸው ከምድር ጦር ብዙ ተምረዋል። በጥረታቸውም በስድስት ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ የህንጻ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። በቀጣይም ኮሌጅ የመክፈት ዕቅድ ያላቸው በመሆኑ አበክረው እየሠሩ ነው።
መንግሥት በማንኛውም ኢንቨስትመንት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ክፍለገብርኤል፤ ወደ ዘርፉ ሲቀላቀሉ ከልማት ባንክ ያገኙት የሦስት ሚሊዮን ብር ብድር በሥራቸው ላይ ከፍተኛ እገዛ አድርጎላቸዋል። እርግጥ ነው ማንኛውም ሥራ ሲጀመር ከፋይናንስ ጀምሮ የሚገጥመው ችግር ከባድና ፈታኝ እንደሚሆን ይታመናል። በተለይም የትምህርት ዘርፍ ትውልድ የማፍራት ጥያቄን መመለስ በመሆኑ ሥራውን ፈታኝ ያደርገዋል።
የትምህርት ዘርፍን ማሳደግ ሀገርን መገንባት መሆኑን የሚያምኑት አቶ ክፍለገብርኤል፤ የትምህርት ዘርፍ እንደ ንግድ መታሰብ የሌለበትና ጥንቃቄን የሚፈልግ በመሆኑ ትምህርት ቤታቸው ትውልድን በማነጽ ላይ ይበልጥ ይሠራል። ዛሬ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ላይ መስራት ሀገርን ማልማት እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም በምድር ጦር ውስጥ በነበሩበት ወቅት የሰለጠኑት ሥልጠና ከዓላማቸው ወደኋላ ሳያስቀራቸው የትምህርት ዘርፉን በአግባቡ በመምራት ብቁ ዜጋን ለማፍራት ትልቅ አቅም ሆኗቸዋል።
ባለሀብቱ በወቅቱ በጉርሶና በሀረር አካዳሚ የሰለጠኑት ወታደራዊ ትምህርት ተስፋ ባለመቁረጥ፤ የተፈጠሩ ችግሮችን ሳይሆን የወደፊቱን ማየት፤ ነገን ተንትኖ መረዳት የሚያስችል ወታደራዊ ሳይንስን አስተምሯቸዋል። ይህም በተሰማሩበት ኢንቨስትመንት የገጠማቸውን ችግሮች በቀላሉ ማለፍ አስችሏቸዋል። ተማሪዎቻቸውንም በአግባቡና በሥነምግባር መምራት በመቻላቸው ‹‹እነሱኮ ሀይለኞች ናቸው›› የሚል ቅጽል ወጥቶላቸዋል።
ወታደር ጠንቃቃና ቆፍጣና እንደመሆኑ በህይወታቸው ጥሩ ውሳኔ በመወሰን ግባቸውን ማሳካት እንዲችሉ አግዟቸዋል። በውትድርና ትምህርት በጠላት ላይ የበላይነትን ለማግኘት የጠላትን አጠቃላይ ኃይል፣ የታጠቀውን መሳሪያ፣ ከኋላ ያለው ደጀንና የያዘውን ቦታ በማጥናት ደምን በላብ የማዳን ሁኔታዎች ግድ ናቸው።
ትምህርትም እንዲሁ የተሻለ ዜጋን ለማፍራት ትውልዱን የማነጽ ሥራ ሆኖ ዛሬ በሚሠራ የቀለም ትምህርት ነገ ሀገርን ከውድቀት ማዳን የሚችል ሰው ማፍራት የሚቻልበት ዘርፍ ነው። እሳቸውም ተማሪዎች በተማሩት ትምህርት ነገ ሀገራቸውን ማገልገልና ገበያው የሚፈልገውን ምርት ማምረት እንዲችሉ በማሳየት ተማሪዎቹን ወደ ትክክለኛው ግባቸው እየመሩ ናቸው።
ትምህርት ቤቱን ሲከፍቱ የነበሩበት የትምህርት ደረጃ ዲፕሎማ ይሁን እንጂ እየሠሩ በመማር በትምህርት አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተከታትለዋል። በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸው ቋንቋቸውን ማዳበር አስቻላቸው እንጂ ከዚያ ውጭ ያለውን የመሪነት ሚናቸውን ከፍ ያደረገላቸው በውትድርና ያገኙት ሥልጠና ነው። ውትድርና ሰዎች የተሻለ ስብዕና መገንባት የሚችሉበት ስፍራ በመሆኑ ያገኙትን መልካም ሥነምግባር በተማሪዎቻቸው ላይ በማጋባት ትልቅ ተጽዕኖን በመፍጠር እውቀትና ስነምግባር ላይ ሰፊ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።
ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ባሻገር ጠንካራ የሆነ የሥነምግባር ትምህርት ይማራሉ። በዚህም በከተማ ውስጥ ካሉት ትምህርት ቤቶች መካከል ዘስፓርክ አካዳሚ የተለየ ሆኖ ቀጥሏል። ትምህርት ቤቱ ከማይደራደርባቸው ነጥቦች መካከል አንድ ሰው የማንንም ስብዕና የማይነካ፣ ሰዓት በማክበር ላይ ያለው የጸና አቋም ከፍተኛ በመሆኑና እኩይ የተባሉ ተግባራትን እንዲጠየፉ ሆነው መቀረጻቸውን ያነሳሉ። በዚሀም የተሻለ ስብዕና ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ችለዋል።
ተማሪዎች በመልካም ስብዕና መገንባታቸው ከገንዘብ በላይ የሆነ ትርፍ ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን፤ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብም በዚሁ ቅኝት ውስጥ ያሉና ለሥርዓቱ ተገዢዎች ናቸው፤ ይህ ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን እጅግ ምቹና የተሳለጠ እንዲሆን ከማስቻሉ በላይ ትልቁ ስኬታቸው ነው።
አቶ ክፍለገብርኤል ባቋቋሙት ትምህርት ቤት ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት በመምህርነት አገልግለዋል። በአሁን ወቅት ደግሞ የአስተዳደር ሥራውን በመምራት ከወላጆችና አጠቃላይ ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር በጋራ በመሆን ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ችለዋል። ይህም ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡና ጠያቂና ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር የሀገር ግንባታ ላይ አሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ።
ተማሪዎቹ ከሚያስመዘግቡት የቀለም ትምህርት ውጤት ባሻገር መልካም ዜጋ በመሆን ነገ የህይወት ምስክር ሆነው ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ የሚችሉበትን መንገድ ተከትለዋል። ይህ ምኞታቸውን ዕውን ለማድረግ ከቀለም ትምህርቱ እኩል በተማሪዎች ምግባር ላይ ቀን ከሌሊት በሚያደርጉት ትጋት በአካባቢው ማህበረሰብ ይታወቃሉ። ምንም እንኳን የአካባቢው ማህበረሰብ ጠበቅ ያለ ሥርዓት ያልተለማመደ ቢሆንም ማህበረሰቡ ራሱ ወደ ትምህርት ቤቱና ወደ ተማሪዎቹ ባህሪ እንዲመጣ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ።
ትምህርት ቤቱ በቆይታው ለአምሥት ተከታታይ ጊዜ ሀገር አቀፍ ፈተና አስፈትኗል። ተማሪዎቹ በክልሉ ካሉት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ዙር 25 ተማሪዎችን አስፈትኖ 21 ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግባት መቻላቸውን አቶ ክፍለገብርኤል ይናገራሉ።
በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ካስፈተናቸው 40 ተማሪዎች 36 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል። ዝቅተኛው ውጤት አመጡ የተባሉትም ከ500 ጥያቄዎች 476 የመለሱ ተማሪዎች ናቸው። ይህ ውጤት በተለይም ዝቅተኛ የትምህርት ሽፋን አለ ተብሎ በሚታሰብበት በሱማሌ ክልል መመዝገቡ የሚበረታታ ነው። ከዚህ በመነሳትም በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ደረጃ ክልሉን ለማስጠራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ከመሆኑም በላይ እንደሚሳካላቸውም ሙሉ እምነት እንዳላቸው ነው የገለጹልን።
ትምህርት የተሻለ ዜጋን ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ከሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ጀምሮ በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓት መቃኘት አለበት። የግል ትምህርት ቤቶች ከሚያገኙት ገንዘብ በላይ ጥሩ ዜጋ መፍጠር መቻላቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል። ይህን ማድረግ ሲቻል ነው አሁን የሚታየውን የመንጋ አስተሳሰብ መቀንስ የሚቻለው የሚል እምነት አላቸው።
ተማሪዎች ከማንም ድጋፍ ሳይጠብቁ በራሳቸው መቆም እንዲችሉና ተነሳሽነታቸውን የሚጨምር መዝሙር ያላቸው ሲሆን፤ መዝሙሩን በየዕለቱ ከብሔራዊ መዝሙር ቀጥለው ይዘምራሉ። ይህ ብቻ አይደለም ትምህርት ቤቱ የእስቴቲክስ ትምህርትን ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለየ መንገድ ይሰጣል።
ይህም ተማሪዎቹ በሚፈልጉት ዘርፍ ብቁ ሆነው መውጣት እንዲችሉ እንደየዝንባሌያቸው የሙዚቃ፣ የስዕል፣ የስፖርትና የእጅ ሥራ ትምህርት በመደበኛነት ያስተምራል። ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል እንዲያስችላቸው የተለያዩ ግብዓቶችን በማሟላት ላይ ናቸው።
የፀሀይ መውጫ በሆነችው በስተምሥራቅ በምትገኘው ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ላይ እውቀትን ተቋደሱ የሚለው ዘስፓርክ አካዳሚ ስያሜው ከጮራ ፍንጣቂ ጋር የተያያዘ ነው። በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የፀሀይ ብልጭታ እንደሚወጣ ሁሉ የዕውቀት የትምህርት ብልጭታም በክልሉ ይታይ እንደማለት መሆኑን ያስረዳሉ።
ትምህርት ቤቱ በአሁን ወቅት ለ72 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በወር 512 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ለሠራተኞች ደመወዝ ይከፍላል። በተጨማሪም ለመንግሥት የሚከፍለውን የሥራ ግብር ጨምሮ በወር ከ560 እስከ 610 ሺህ ብር ወጪ ያደርጋል። በመጨረሻም ከሰሞኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት በመቃወም እንዲሁም ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በአካባቢው ላሉ የሰራዊት ልጆች የነጻ የትምህርት ዕድል ለመስጠት ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2013