አስቴር ኤልያስ
በየትኛውም ዘርፍ ቴክኖሎጂን የመጠቀሙ ነገር ትኩረት የሚደረግበት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ስላለው እንደሆነ ይታመናል። ቴክኖሎጂን የመጠቀሙ አንዱና ዋናው ነገር ስራዎችን ቀላል በማድረግ የተሻለ ህይወትን መምራት ስለሚያስችል ነው።
ከዚህም አንጻር በየጊዜው የሚወጡ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ሚናቸው ላቅ ያለ ስለመሆኑም ብዙዎቹን የሚያስማማ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ዛሬ ዛሬ ዓለምን ማስተዋል ለቻለ በየጊዜው አዳዲስ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ካለመታከት እየወጡ ስለመሆናቸው መገንዘብ ይቻላል።
እየወጡ ካሉት ቴክኖሎጂዎች መካከል ደግሞ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ሲሆን፣ ይህም በዘርፉ ያለውን የጉልበት ስራ እና አድካሚ የሆነውን እንቅስቃሴ እያቀለለው ስለመምጣቱ ይነገራል። ወራት ይወስዱ የነበሩ ግንባታዎችም ዛሬ ላይ ዘመኑ ባመጣቸው የዘርፉ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ እየተሰራ በመሆኑ በቀናት ውስጥ ወደመጠናቀቁም ላይ እንዳሉ ማስተዋል ተችሏል።
ይህ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ በአገራችን ኢትዮጵያ እንዴት እየተተገበረ እንደሆነና የአጠቃቀሙ ሁኔታም ምን መሆን እንዳለበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው አጠራሩ ህንጻ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ከሆኑት ዶክተር አስረግደው ካሳ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል ። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ሲባል ምን ምንን የሚያካትት ነው?
ዶክተር አስረግደው፡- የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ሲባል በፈጠራ፣ በጥናትና ምርምር አሊያም በሙከራ ቤቶች ተቋማት የተገኙ ማንኛውንም መሳሪያ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ የማምረቻም መሳሪያ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም ማሽነሪዎችም ሊሆኑ ይችላሉ፤ እነዚህን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ሶፍትዌሮችንም ሊያካትት ይችላል። ይህ ሁሉ አንድ ላይ ተደማምሮ ምርትን፣ ጥራትን እንዲሁም ፍጥነትን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ የኮንስትራክሽኑን ግብዓት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሲሆኑ፣ ሁሉን በአንድ ላይ የያዘ በመሆኑ ቴክኖሎጂ ይባላል።
አዲስ ዘመን፡– የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን በአግባቡ አለመጠቀም በዘርፉ ሊያመጣ የሚችለው ተግዳሮት ምንድን ነው ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር አስረግደው፡- በእኛ አገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታ ወደኋላ መለስ ተብሎ ቢታይ ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የቴክኖሎጂ ስራ አለ ተብሎ አይታሰብም። አንድ ኮንስትራክሽንን ለመስራት በሚታሰብበት ሰዓት አሁን ላይ የሚታዩ እንደ ኤክስካቫተርም ይሁን ሚክሰርም ይሁን የተለያዩ ማሽኖችም ቢሆኑ በወቅቱ አልነበሩም።
ሁሉ ነገር ይሰራ የነበረው በአብዛኛው ማለት በሚያስደፍር መልኩ በእጅ ነው። ከላይ የጠቀስኳቸው የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ሁሉ በጊዜ ሂደት የተፈጠሩ ናቸው።
በአገራችንም ደረጃ ከተወሰኑ ኮንትራክተሮች በስተቀር ብዙዎቻችን በቤታችንም ደረጃ ቢሆን የምንገለገልበት የኮንስትራክሽን እቃዎች ከማሽነሪዎቹ ይልቅ በእጃችን አሊያ እንደ ዶማ እና አካፋ የመሳሰሉትን በመጠቀም ነው ። ሌላው ቀርቶ ኮንክሪትም የምናቦካው በእጃችን ነው።
በአብዛኛው ታዳጊ አገሮች የሚታየው ነገር አብዛኛዎቻችን ስራዎቻችንን የምናከናውነው ዘመኑ ያፈራውን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች በመጠቀም ሳይሆን የሰው ጉልበትን መሰረት በማድረግ ነው። በብዛት የሚስተዋለውና ጎልቶ የሚታየው የሰው ጉልበት ነው ።
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስችል ግንዛቤ ባለመዳበሩም ጭምር እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራን ካለመስራት የተነሳ ደግሞ የሚታዩ ጉድለቶች በርካታ ናቸው። ለአብነት ያህል መጥቀስ ካስፈለገ የምርት ጥራት ላይ ጉድለት መታየቱ አንዱ ተጠቃሽ ነገር ነው ። እንዲሁም ጊዜ እና ጉልበት መባከኑም አይቀሬ ነው። በተለመደው አሰራር ሲቀጠል ደግሞ ወደፊት ብዙ ድክመቶች መኖራቸው የግድ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ እንደሚታወቀው አሁን አሁን አብዛኛው ስራን በወረቀት ላይ የማስፈሩ ነገር ቀላል ሆኖ ይታያል፤ ቀጥሎም በስልኮቻችን ላይ የተመሰረተ ነው። ምክንያቱም ስልካችን ራሱን የቻለ ቴክኖሎጂ የተተገበረበት በመሆኑ ነው ።
ከዚህ በተጨማሪ አሁን ጊዜው የግሎባላይዜሽን ነው። ሁሉም በአንድ አይነት አስተሳሰብ የሚሰራበት ጊዜ ላይ ነው የተደረሰው። ስለዚህም ተማሪዎቻችን በፈጠራ ስራ ላይ እንዲያተኩሩ እና ከየትምህርት ተቋማቱ የተሻሉ ምሩቃንን በማውጣቱ የትም አገር ሄደው መስራት እንዲችሉ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲራመዱ ማድረጉ ተመራጭ አካሄድ ነው ።
ራሳቸውን ማሻሻል እንዲችሉም ቴክኖሎጂ የግድ የሚል ነው። ነገር ግን ይህን ለማድረግ የቴክኖሎጂም ውስንነት ስላለብን እንደ አንድ ተግዳሮት ልናየው እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡– የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማዘመንና ለማስፋፋት የዘርፉን ቴክኖሎጂ መጠቀም ፋይዳው እምን ድረስ ነው?
ዶክተር አስረግደው፡– በእውነቱ ከሆነ ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም ያለምንም ጥያቄ ፋይዳው ከፍ ያለ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። በአሁኑ ወቅት ያሉትም ቴክኖሎጂዎችም ቢሆኑ የትየለሌ ናቸው። ከምርታማነት፣ ከደህንነት ፣ ከጥራት ፣ ከጊዜ ፣ ከዋጋ፣ የግንባታን ሂደት ቀድሞ ከማየት አንጻር እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ሁኔታዎች አኳያ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።
የቴክኖሎጂ ጠቀሜታ በስራ ላይ ስህተቶች እንዳይከሰቱ ከማድረጉም በተጨማሪ ድግግሞሽ እንዳይኖርም ጭምር የሚያደርግ ነው። ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻል የተዋጣለት ዲዛይንም እንዲኖር የሚያደርግ ጭምር ነው። የስራው ሂደት የተሳለጠ በማድረጉም በኩል ሚናው ጉልህ ነው።
ስለዚህ የተሻለ ውጤትን ለማግኘት እና የተሻለ አሰራርን ለመቀየር የሚያስችል ነው። ይህን ስንል ግን ትልቁ እና ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ቴክኖሎጂውን ወደራሳችን ነባራዊ ሁኔታ ማምጣቱ ላይ ሲሆን፣ በምናመጣበት ጊዜም ጥንቃቄ ማድረጉ መልካም ነው። ተማሪውም፣ ድርጅቶችም ሆኑ የተለያዩ ተቋማት የሰለጠነው ዓለም የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ ወደራሱ በማምጣት አሰራሩን ሊያበለጽጉለት እንዲችሉ ሲያደርግ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል።
ቴክኖሎጂን አምጥቶ መጠቀሙ መልካም ነገር ነው፤ ነገር ግን የምናመጣውን ቴክኖሎጂ መልሰን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ምርምር በማድረግ እና በጥናት በማስደገፍ ማላመድ ተገቢነት ያለው አካሄድ ነው ።
የሚመጣው ቴክኖሎጂ ከጊዜው ጋር የሚሄድ መሆኑን ማረጋገጥ ውጤታማ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። ቴክኖሎጂን የማላመዱ ሂደት ከትምህርት ቤት መጀመሩ ደግሞ የፈጠራ ክህሎታቸውን ስለሚጨምር ተማሪዎችን የመፍትሄ ሰዎች ያደርጋቸዋል።
ተማሪዎች ገና ከመጀመሪያው ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማመቻቸቱ ሁሌም የሌሎች አገሮችን ቴክኖሎጂ አምጥተን ከማላመድ ሊያላቅቀን በመቻሉ ነው ። የሌሎች አገሮችን ቴክኖሎጂ ለማላመድ በሚደረገው ጥረት መሰላቸትን ሊያመጣ ይችላል። ከዚህ አይነት መሰላቸት ለመላቀቅ በራስ ወደተፈጠሩ መሄድን ከወዲሁ መጀመሩ ተገቢነት አለው።
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ ውስጥ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከቴክኖሎጂው ጋር ያላቸው ቅርበት እንዴት ይገለጸል?
ዶክተር አስረግደው፡– በዚህ ጉዳይ ደፍሬ ለመናገር ይከብደኛል። አንዳንድ ተቋማት ፈቃደኛ ሆነው ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ግን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ላይ ናቸው ለማለት ያስቸግራል። ለዚህ ችግሩ ካፒታልንም ስለሚጠይቅ ነው። የካፒታሉ አለመኖር ብቻ ደግሞ አይደለም፤ የግንዛቤም ችግር በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል። አንዳንድ ሰዎች መረጃው ሊኖራቸው ይችላል። ያለውንም ቴክኖሎጂ በአግባቡ እየተጠቀመም ሊሆን ይችላል።
በእርግጥ ከግል ኮንትራክተር ጀምሮ ያለውን ቴክኖሎጂ በማምጣት እና በማላመድ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ማለትም እንደ ጊዜ ፣ ጥራት ፣ ጉልበት እና ምርታማነትን እንዲጨምርለት ቢያደርግ የበለጠ ተመራጭ ይሆን ነበር። በእርግጥ አንዳንድ ቦታ እንዳልኩሽ ጥረቶች መኖራቸውን ማስተዋል ይቻላል። ነገር ግን የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።
እንኳን ባልሰለጠነው አገር ቀርቶ በሰለጠነውም አገር ቢሆንም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ብዙ ጊዜ ለየት ያለ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን እንዳልኩሽ እየተሞከሩ ያሉ አሉ ማለት ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በየዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችም አሉ ። እነዚህ የቴክኖሎጂ ስራዎች ከመጻህፍት መደርደሪያ ወርደው በየኢንዱስትሪው መፍትሄ ፍለጋ ሲሄዱ አይስተዋልም። በመሆኑም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እየተሞከረ ያለው ነገር የዘርፉን ስራ ለማሳለጥ ሲሰራበት እምብዛም አይታይም ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡– በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ እየተሞከረባቸው ያሉትንም ሆነ ከውጭ በማላመድ የመጡትን ዘመናዊ የማምረቻ ቴክኖሎጂን መጠቀማቸው ከአገርም ሆነ ከእነርሱ አኳያ የሚያስገኘው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አስረግደው፡- ፋይዳው በጣም ትልቅ ነው። ትልቁ ነገር ሐሳብ ያለው ሰው እና ገንዘብ ያለው ሰው ብዙ ጊዜ አይገናኝም እንደሚባለው አይነት ነው ። ብዙ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች የገንዘብ እጥረት ይኖራቸዋል ።
በተቃራኒው ደግሞ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ሐሳብ ሲያጥራቸው ይስተዋላል። ስለዚህ በዚህ ላይ ፍቃደኛ የሆኑ ድርጅቶች ቴክኖሎጂን ኢንቨስት ቢያደርጉ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ትልቅ ፋይዳ አለው።
ትልቁ ነገር ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዛምዶ የመሄዱ ጉዳይ ነው። ከተማሪው ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪ ባለሙያው ድረስ ያለው ላይ መተግበር ከጀመረ በአጭሩ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ማለት ነው። ስለዚህ በጉዳዩ ዙሪያ አቅም ያላቸው አካላት ቅድሚያውን ቢወስዱ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡– የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር ለዘርፉ ያበረከተው አስተዋጽኦ ይኖር ይሆን?
ዶክተር አስረግደው፡- አዎ! ለዘርፉ በማበርከት ላይ ምንም ጥያቄ የለውም። ያልሽው የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር በአገሪቱ ካሉ ማህበራት ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ማህበር ለምሳሌ ያህል ከሚሰራቸው ነገሮች ውስጥ አንዱን ብጠቅስልሽ የተለያዩ ጥናቶችን ያስጠናል ። እነዚህም ጥናቶች ለምሳሌ ኢንዱስትሪው ላይ አሊያም ከተማው ላይ ያለውን ችግር የሚመለከት ሊሆን ይችላል። ጥናቱ ከተጠና በኋላ ደግሞ እሱን በተመለከተ ዎርክሾፖች አሊያ ስብሰባዎች ይኖራሉ።
የመሰባሰቡም ምስጢር በጥናቱ የተገኘውን ነገር ለባለድርሻ አካላት ለማስተላለፍ በመታሰቡ ነው። የተገኘው የጥናት ውጤት ደግሞ በስብሰባ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ለህትመትም የሚበቃበት ሁኔታም አለ። በተጨማሪም ማህበራቱ ላይ ያሉ ሰዎችም እንደዚሁ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ያማክራሉ።
ይህ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ማህበራት አሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተጠቃሽ ነው።
እነሱም ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ጋር በተለያየ መስክ እየሰሩ ያሉ ናቸው። ለአብነት ያህል ብጠቅስልሽ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የምርታማቱን ጥናት አስጠንቶ እየተሰራ ነው ። እንዲሁም የተለያየ የፕሮጀክት ማኑዋሎችን አስጠንቷል። ይህም በመሆኑ 19 የሚሆኑ ማኑዋሎችን የዛሬ ዓመት አካባቢ ተሰርተዋል።
ነገር ግን በሁሉም መስክ የሚሰራው ስራ በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ቢሆን የተሻለ ነገር ሊመጣ እንደሚችል ምንም ጥርጥር አይኖረውም ። ስለዚህም የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር ከሌሎች ጋር በመሆን እነዚህን ሁሉ ስራ የሚያካትት ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የግንባታ መረጃ ሞዴል ከንድፍ ስራ ጀምሮ ፕሮጀክቱ እስኪያልቅ ድረስ ያለው ሂደት በጥምረት የሚታይበት ቴክኖሎጂ እንደሆነ ይነገራልና ይህን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም መደረግ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው ብለው ይመክራሉ?
ዶክተር አስረግደው፡- በዚህ ጉዳይ በትልቅ ደረጃ የተያዘው ቅድም ካልኩሽ አንዱ ተቋም ማለትም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሚባለው የመንግስት ተቋም ሲሆን፣ እሱም የመጀመሪያን ተነሳሽነት ወስዷል።
ይህ ተቋም በዘርፉ ያለውን የተለያየ ግንዛቤን ለመፍጠር በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ መምህራን ጠርቶ ስልጠና ሰጥቷል። ቀድመው ስልጠና የወሰዱ መምህራን በወቅቱ ስልጠናውን የወሰዱት የአሰልጣኞች ስልጠና ሲሆን፣ ሌሎችንም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ ነው ።
እንዲህም ሲባል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በሁሉም የኮንስትራክሽን ዘርፎች ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት አዳዲስ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ በማካሄድም ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው ማለት ነው።
ኢንስትቲዩቱ ህጋዊ ሰውነት ተሰጥቶት ሲቋቋም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶት ነው። ከተሰጡት ተግባራት እና ኃላፊነት መካከል ጥናትና ምርምር ማካሄድ እና ከምርምሩ የተገኙ ውጤቶችን ወደ ኢንዱስትሪው እንዲስፋፉ እና እንዲሰርጹ ድጋፍ ማድረግም ጭምር ነው።
ቴክኖሎጂውን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን በትምህርት ስርዓት ውስጥ በዘርፉ ያለው ትምህርት መካተትም ይኖርበታል። የዘርፉን ባለሙያዎችም የበለጠ ማሰልጠን ይጠበቅብናል። በእርግጥ አሁን አሁን እኛም አገር የአይ.ቲ ክፍለ ትምህርት በጥሩ ሁኔታ እየተጠናከረ ነው ማለት ያስችላል። የተለያዩ ሶፍትዌሮችም እየተሰሩ ነው።
በጥቅሉ ግን እኛ አገር ያለው ችግር ምንድን ነው? ቴክኖሎጂው እኛ አገርስ ይሰራል ወይ? የሚለውም መታየት መቻል አለበት ። መስራት የሚቻለው ውጤታማነት ላይ ነው? ወይስ ምርታማነት ላይ ነው? ወይም የምርት ጥራት ላይ ነው? የሚለውን በአግባቡ መለየትም ይገባል።
ምክንያቱም ቀደም ብዬ እንደጠቅስኩልሽ ቴክኖሎጂውን ዝም ብሎ መገልበጥ መሆን አይኖርበትም። በሰለጠነው አገር ላይ ያለው ችግር ከእኛ ችግር ጋር ሲተያይ ልዩነት ስለሚኖረው እኛ ያለብንን ችግር በመጀመሪያ መለየት እና ለዛ ችግራችን መፍትሄ ሊሆን የሚችለውን ቴክኖሎጂ ከተቻለ መፍጠር አለበለዚያ ደግሞ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መጠቀም ነው ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለው።
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው ዓለም አቀፍ የሆኑ የውጭ አገር ኮንትራክተሮች በአገራችን በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው በመስራት ላይ እንደሆኑ ይታወቃልና የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ተሞክሮ በማካፈሉ ረገድ እያበረከቱ ያለ ነገር ይኖር ይሆን?
ዶክተር አስረግደው፡- እንዲህ ነው ብዬ ሙሉ ለሙሉ መናገር ባልችልም የተወሰነ ነገር ወደድንም ጠላንም ዓለም አቀፍ የሆኑ ኮንትራክተሮች ወደእኛ አገር መጥተው በሚሰሩበት ሰዓት የማየት እድሉ ይኖረናልና እናያለን።
በተለይ አንዳንዴ በዘርፉ ስራዎችን ተረክበው የሚሰሩትን ዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች የማየት እድሉ አለን። በዚህ አጋጣሚ ደግሞ የሚጠቀሙበትን ዘዴ ማስተዋል ይቻላል።
በመሆኑም እነዚህ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች የሚጠቀሙትን የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ በማስተዋል ወደእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታም በመቀየር (እኛ ማከናወን የምንፈልገው እነሱ እየተጠቀሙበት ያለውን ቴክኖሎጂ መሸከም የሚችል የኮንስትራክሽን ስራ ላይሆን ስለሚችል ከምንሰራው ተግባር ጋር አስማምተን) መጠቀም እንችላለን።
አንድ የምረዳው ነገር ቢኖር የውጪዎቹ ወደ አገር ቤት ሲመጡ የአገር ቤቱን ባለሙያ በተወሰነ በመቶ እንዲቀጥሩ ህጉ ያስገድዳቸዋል።
አሊያ ግን ኮንትራክተሮቹ የጉልበት ሰራተኛ ብቻ የሚቀጥሩ ከሆነ እውነተኛ የሆነ የእውቀት ሽግግር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ በግንበኝነቱም ሆነ በአናጺነቱ እንዲሁም በሌሎችም የሙያ አይነቶች የእውቀት ሽግግር ማግኘት በሚያስችልበት ሁኔታ ማሰራቱ ያስፈልጋል።
ተቀጥረው የሚሰሩ ባለሙያዎች ቴክኖሎጂውን ወደእኛ ማስፋፋት እንዲችሉ እና እግረመንገዳቸውም የራሳቸውን አቅም እንዲገነቡ እና በትክክል አሰራራቸውን ለመረዳት ቢያሰለጥኑን በተግባር የሆነ በመሆኑ በቀላሉ መማር እንችላለን። ይሁንና በትክክል የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በአግባቡ እየሰጡን ነው ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ ለሙስና እና ለብክነት የሚያጋልጠው የቴክኖሎጂው ክፍተት ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አስረግደው፡- እውነት ለመናገር የተወሰነ ድርሻ ይኖረዋል። ይሁንና በእኛ አገር ደረጃ ሚዛን የሚደፋው የአስተሳሰባችን ሁኔታ ነው። አስተሳሰባችንም የተሻለ ሆኖ የማይገኘው የድህነታችን ሁኔታ ማነቆ ስለሚሆንበት ነው።
አስተሳሰባችን እስካልተቀየረ ድረስ የቱንም ያህል ቴክኖሎጂን ወደ አገራችን ብናመጣ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ አስተሳሰብ ከሌለን በዘርፉ ለውጥ ልናመጣ አንችልም።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሰጠው ትኩረት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አስረግደው፡– መንግስት ለዘርፉ የሚያደርገው ጥረት አለ፤ ለዚህም እናመሰግናለን። ለምሳሌ በመሰረተ ልማት በኩል ያለው ነገር የሚበረታታ ነው። ደግሞም በየዓመቱ ከመንግስት የሚሰጠው በጀት ለኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ትልቅ አቅም ናቸውና ይበል የሚያስብል ነው። በየማህበራቱና በየተቋሙ የሚደረጉ ጥናቶችም አሉና ይህም መልካም ነው የሚባል ነው።
ነገር ግን የሚደረገው ነገር ሁሉ የተጣመረ መሆን ይኖርበታል። በዘርፉ ለሚስተዋለው ሙስና ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል። ሙስናን ለመከላከል የበሰለ አስተሳሰብ ሊኖር የግድ ነውና በዚህ በኩልም ግንዛቤ ሊኖር ይገባል። እኛም እንደ መምህራን ተማሪዎቻችን ላይ የተሻለ አስተሳሰብ ይኖር ዘንድ ከወዲሁ መስራት የግድ ይለናል።
በተለይ አንድ የኮንስትራክሽን ባለሙያ ዘርፉን ሲቀላቀል ወደሚበላበት ዘርፍ ተቀላቀለ የሚል አተያይ ነው ያለው። ወይም ደግሞ አንድ ነገር ተጣሞ ይሰራና ችግር የለውም በኋላ አስተካክለዋለሁ የሚባልም ሁኔታ ነው የሚስተዋለው።
እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ መወገድ አለበት ባይ ነኝ። ስለሆነም የተጀመሩ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው መንግስት እንደዚህ አይነት ነገሮችን ማስተካከል መቻል አለበት።
በሌላ በኩል ለምሳሌ ፖለቲካው ወደዘርፉ ብሎም ሙያተኞች ዘንድ ባይገባ መልካም ነው። ፖሊሲም ሲወጣ በባለሙያዎች እና በባለድርሾች ሐሳብ የተደገፈ ቢሆን ይመረጣል። ከዛ ውጭ ደግሞ በዘርፉ የላቀ እውቀት ያላቸውም አካላት ያሉ በመሆናቸው እነሱን አካቶ እንዴት መስራት እንደሚቻልም መገንዘቡ ጥሩ ነው።
ከዚህ ውጭ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች ደህንነትም የተጠበቀ ይሆን ዘንድ አስፈላጊው ሁሉ ሊደረግም የግድ ነውና እሱ ላይም ትኩረት ቢደረግ መልካም ነው። ለሰው ልጅ ህይወት የሚሰጠው ዋጋ የላቀ መሆን አለበት። የሚሰራውም የኮንስትራክሽን ውጤት የአንድ ወቅት ቆይታ ብቻ እንዲኖረው ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ ተደርጎ እንዲገነባ የማድረጉም ሁኔታ ከግምት መግባት ያለበት ጉዳይ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
ሌላው በሚሰራው ስራ ሁሉ ግልጸኝነት በጣም ሊሰፍን ይገባል። በዚህ ጉዳይ በውጭ ያለውም ተሞክሮ ሲስተዋል የመንግስት ተቋማት የፋይናንስ ኦዲታቸውን በግልጽ ያዩታል።
ይህንን አይነት ተሞክሮም ወደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በማምጣት ተጠቃሚ መሆኑ መልካም ነው። የአምስት፣ የአስር፣ የሃያ እና የሰላሳ ዓመት እቅዳቸውን በግልጽ ያዩታል ። በአንድ ጀምበር ዱብ የሚል ነገር አይኖርም። የሚሰራውም ስራ ለእነሱ እንግዳ አይሆንም። ሁሉም ነገር በጥናት የተደገፈና በባለሙያዎች የሚሰራ ነው።
ሌላው ደግሞ የዳታ አያያዛችንም ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ነው። ከመረጃ አሰባሰቡ ጀምሮ ያለው ሂደት በስነ ስርዓት መጠናቀር ያለበት ነው ። ከዚህ ውጭ ሌላው ደግሞ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ጡረታ በሚወጡበት ጊዜ ደግሞ ካካበቱት ልምድ ማካፈል የሚችሉት በምን አግባብ ነው የሚለው ነገር መታየት ያለበት ነው።
ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ወደ ዳታቤዝ መቀየር መቻል አለብን። እኛ ዘንድ ተማሪዎቻችን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ሲሰሩ በስፋት የሚቸገሩበት ነገር ቢኖር ዳታ የለም ስለሚባሉ ነው። ዳታ የት እንደተቀመጠ አይታወቅምና እነዚህንና ሌሎችን ችግሮች ለመፍታቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን የቤት ስራ በመስራት በዘርፉ ያለው ክፍተት ለመሙላት በመቀናጀት መንቀሳቀስ ነው ያለብን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
ዶክተር አስረግደው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2013