እፀገነት አክሊሉ “
የህወሓት ጁንታ ቡድን እራሱ በለኮሰው ጦርነት ተለብልቦ እንዳያንሰራራ ሆኖ እስከ ወዲያኛው ተሸኝቷል። ይህንን ተከትሎም አጥፊ ቡድኑን ለሰራው ስራና ላጠፋው ውድመት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎችም እስከ አሁን ድረስ ተጠናክረው ቀጥለዋል። እኛም የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑትን አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤልን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግረናቸዋል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን ፦ ጁንታው በመከላከያ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት የነበረው አካሄድ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ነብዩ፦ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈጸመው ክህደት ሁላችንንም ያሳፈረ። ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ሲበዛም አስነዋሪ የአገር ክህደት ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ተግባር ነው። ይህ ተግባርም ከህወሓቱ አጥፊ ቡድን በስተቀር ሌላ ሊፈጽመው የማይችል ፍጹም ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባህልና ስነ ልቦና የራቀ መሆኑን ያሳያበት፤ ከዚህ ቀደም በታሪካችን አይተነው የማናውቀው ነው።በዚህ ውስጥ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት አገር ሲመራበት የነበረው ሥርዓት ምን ዓይነት እንደነበር በደንብ አድርጎ ያሳየ ነው። ጁንታው ሃይል የጥፋትና የክህደት እንጂ ለአገር ሰላም አንድነት ምንም ዓይነት ደንታ የሌለው መሆኑን ያረጋገጠበት የመጨረሻው ተግባሩ ደግሞ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ግፍ ነው። ይህ የግፍና የጭካኔ ተግባር ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቶ አሳዝኖ በስተመጨረሻ ደግሞ ህግ የማስከበር ስራው ሁላችንንም ባሳተፈና ወደ ርብርብ ባስገባ መልኩ ተከናውኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንጸባራቂ ድል በማምጣት ተጠናቋል።
በመቀጠልም ሰላማችንን ደህንነታችንን አረጋግጠን ወደ ልማታችን ለመግባት የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ተጀምሯል። በተለይም ይህ የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ሁለት ገጽታዎች ያሉት ሲሆን ፤ አንደኛው አጥፊዎቹን ለህግ ማቅረብ ። ሁለተኛው ደግሞ ህዝቡን ተረጋግቶ ወደቀደመ ሰላሙና ልማቱ እንዲመለስ ማድረግ ነው። አሁን ባለው ሁኔታም እንደ መድሃኒት። የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰቱና ህዝቡም ችግር ላይ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይም ወደ ጦርነት የተገባበት ወቅት ምርት ያልተሰበሰበበት በመሆኑ አንደኛ ደረጃ የምግብ እህል እርዳታ ለሚፈልጉ በርካታ ወገኖች እንዳይጎዱ የርብርብ ስራ መሰራት አለበት።
ሌላው ማህበረሰቡ ወደቀደመው ኑሮው እንዲመለስ የማድረግ ስራ በቀዳሚነት እየተሰራ ሲሆን በተለይም ወደ ስደት የሄዱት ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ የዚህ ምዕራፍ አካል ነው። ከዚህ ከሁለተኛው ምዕራፍ ጋር ተያይዞ የሚነሳው በጁንታው የፈራረሱ የመሰረተ ልማቶች መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ በመሆኑ በዚህ በኩልም ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው። እዚህ ላይ ወሳኙ ደግሞ የፈረሰው የመንግስት መዋቅር መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ርብረብ እየተደረገ ነው፤ በጠቅላላ የተፈጸመው ነገር ሁላችንን ያሳዘነ ያስቆጣ ቢሆንም በዚያው ልክ ግን አጥፊው ቡድን ወደ ህግ የሚቀርብበት አግባብ ኖሮ ወደ ቀድሞ ሰላማችንና ልማታችን የምንመለስበት ምዕራፍ ተከፍቶ አጭር በሚባል ጊዜ በጣም ብዙ ሊባል የሚችል ስራ ተሰርቷል።
አዲስ ዘመን፦ ጥቃቱን በማውገዝም ሆነ ለምን ይሆናል በሚል የትግራይ ህዝብ የነበረው እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ነብዩ፦ እንግዲህ ይህ ክህደት ከላይም እንዳልነው ሊፈጽመው የሚችለው አጥፊው የህወሃት ቡድን ብቻ ነው። ተመሳሳይ እብሪት ላይ የሚገኙ ሃይሎች እንኳን የዚህን ያህል ወርደው አገራቸውንና ህዝባቸውን ሊክዱ አይችሉም። እዚህ ላይ ይህንን ክህደት ከትግራይ ህዝብ አንጻር ስናየው ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ ይታወቃል ፤ ከዚህ በፊትም መራራ ትግል ያካሄደው ለሁለት ዓላማ ነበር፤ አንደኛው ለፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚነት ሲሆን ሌላው ደግሞ ለአገራዊ አንድነት ነው። በተለይም የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትገነባ ያበረከተው አስተዋጽዖ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ የአገር አንድነት ጉዳዩም የሚያሳስበው እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ ቀደም ብሎም መራራ መስዋዕትነቶች በመክፈል እኩልነት አንድነት እንዲረጋገጥ እየጣረ የመጣ ህዝብ ነው፤ በአሁኑ ወቅትም እንዲህ አይነት ክህደት ሲፈጸም ህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምቷል፤ የመከላከያ አባላት የነበሩ የትግራይ ተወላጆችም ይህ በፍጹም ሊደረግ የማይገባው። የገባነውን ቃልኪዳን ማፍረስ ነው በማለት ከጓደኞቻቸው ጋር አብረው የተሰው አሉ።ከዚህ አንጻር ድርጊቱን እንኳን የትግራይ ህዝብ ማንም ሊደግፈው አይችልም። ይህ አጥፊ ቡድን በለየለት የስልጣን ስካር የፈጸመው የመጨረሻ ተግባሩ ነው። በመሆኑም የትግራይ ህዝብ እንዲህ አይነት ተግባር ውስጥ ሊሳተፍም። ሊደግፍም አይችልም።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ህዝቡ ከአጥፊው ቡድን ጎን ባለመቆሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን የመሰለ ደማቅ ታሪክ ለመመዝገብ በቅቷል። ህዝቡ ይህንን አጥፊ ቡድን የሚሸሽግበት አንዳች ምክንያት ቢኖረው ማድረግ ይችል ነበር። ነገር ግን የህዝቡ ጥያቄ ከጦርነት ወደ ጦርነት እየተገላበጡ መኖር ሳይሆን ሰላም ልማትና ብልጽግና ነው፤ ከዚህ ውጪ ያሉ ሌሎች አማራጮች የእብደት ስራዎች ናቸው።
የትግራይ ህዝብ የጁንታው ተባባሪ አለመሆኑ ከጦርነቱም በፊት በክልሉ ላይ የሚፈጠሩ ሰላማዊ ሰልፎችን ባለመውጣት ሲገልጽ ነበር። ነገር ግን ጥያቄው የነበረው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ችግሮችም ካሉ በውይይት እንዲፈቱ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤ ለጦርነትና ለእንዲህ አይነት ክህደት። እብደት የትግራይ ህዝብም ይሁን ተወላጆቹ ይሁንታ ሊሰጡት አይችሉም።
በልዩ ሃይል ውስጥ ሆነው እንኳን እድል ያጡት ካልሆኑ በቀር አብዛኞቹ የመከላከያ ሰራዊት ወገናችን። ወንድም አህቶቻችን ናቸው በማለት መሳሪያቸውን እንደተሸከሙ ነው እጃቸውን በሰላም የሰጡት። በአጠቃላይ የተፈጸመው ክህደት ከትግራይ ህዝብ ጋር የማይገናኝ ልዩ ሃይሉም ሚሊሻውም በተለያዩ ፕሮፓጋንዳዎችና በግዳጅ የገባበት በመሆኑ ውጤቱም ታይቷል።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ አንድ ዜጋ እንዲሁም ደግሞ ትግራይን እንደሚወክል ፖለቲከኛ እርስዎ አብሮ የኖረን በደስታም በኀዘንም ከጎን ያልተለየ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም ምን ዓይነት የሞራል ስብዕና ነው ይላሉ?
አቶ ነብዩ፦ ይህ አጥፊ ቡድን የህዝብና የአገር ታሪክና ስነ ልቦና የሌለው ከየት እንደመጣ ለመረዳት የሚያስቸግር በ60ዎቹ የተፈጠረው የኮሚኒዝም እብደት በቁንጽል የወረሰ የራሱ ታሪክና አመጣጥ ያለው ህዝብና አገር ላይ ይህንን ቁንጽል ሃሳብ ለመተግበር በመሞከራቸው በጣም ብዙ ምስቅልቅል ውስጥ አስገብተውናል፤ በመጨረሻም እራሳቸውን ጎድተዋል። እንዲህ አይነት የእብደት ተግባር ምን ዓይነት ውጤት እንደሚኖረው ይታወቃል። በታሪክም እንደዚህ አይነት አሳፋሪ ውድቀት የወደቀ ፖለቲከኛ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ስለዚህ ቁንጽል ሃሳብ ከየትም አምጥተው የ 3ሺ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ከዜሮ እንድትጀምር አድርገው በራሳቸው አምሳያና ቁመና ብቻ የሚያንጿት አገርና ህዝብ ነበር ያሰቡት፤ ይህ ደግሞ የማይሆን ነበር።ምክንያቱም አንድ መንግስት ኢትዮጵያን አስተዳድራለሁ ከማለቱ በፊት የግድ የአገሪቱን ታሪክና ስነ ልቦና መረዳት ይገባዋል፤ ምክንያቱም የራሱ አመጣጥ ያለው አገረ መንግስት ስላለን ያንን ማወቅና የሚስተካከሉ ነገሮችም ካሉ አስተካክሎ መቀጠል እንጂ እንዲሁ ሁሉንም ነገር ደምስሶ እንደ አዲስ እጀምራለሁ ማለቱ ትልቅ እብደት ነው።
ከዚህ አንጻር የአጥፊ ቡድኑ ተግባርና አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ታሪክና ስነ ልቦና ጋር ፍጹም የማይሄድ፤ አገርን ብዙ ኪሳራ ላይ ሲጥል የቆየ በመጨረሻም ለራሳቸው እንኳን ማሰብ ሳይችሉ የትም ጠፍተው የቀሩበት ነው። ከዚህ ሂደት ደግሞ ሁላችንም ትልቅ ትምህርት ልንማር፤ ጊዜ ስለደገፈን ብቻ አገርና ህዝብን ደስ ባለን መንገድ እናስጉዘዋለን ብሎ ማሰብ በእውነትም እብደት። ውጤቱም የከፋ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
አገርንና ህዝብን አለማወቅና አለማክበር። የሰው ሞራል አለመጠበቅ የት እንደሚያደርስ እያየን ነው፤ ይህ እብሪታቸው ደግሞ ራሳቸውን እንኳን እንዴት ማዳን እንዳለባቸው እንዳያስቡ አድርጓቸው በመጨረሻም ራስን በራስ ማጥፋት በሚመስል መልኩ ውድቀት ውስጥ ገብተዋል።
አዲስ ዘመን፦ የህግ ማስከበሩ ዘመቻ ከዓላማው ባሻገር ግን ለትግራይ ህዝብ የሚያመጣው እድል እንዴት ይገለጻል?
አቶ ነብዩ ፦ በጣም ጥሩ ነው ! የህግ ማስከበር ዘመቻው ለትግራይ ህዝብ የነጻነት ቀኑ እንዲመጣ ያደረገ ነው። እንደሚታወቀው አምባገነኖች የእኔ የሚሉት ያሳደጋቸውን ህዝብ ነው መልሰው የሚበድሉት። ህወሓትም ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለንን ሁላችንንም በድሎናል ፤ ነገር ግን በተለየ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ከከፈለው መስዋዕትነት አንጻር ቶሎ ቁስሉ እንዲድን ከማድረግ ይልቅ ከቁስል ወደ ቁስል እንዲገላበጥ ከመስዋዕትነት ትርክት እንዳይወጣ በሚገባው ደረጃ እንዳይለማና አገራዊ አንድነቱን እንዳያጠናክር በስሙ እየተነገደና ጠላት እየተፈጠረ ቁስል እየታከከ በሌላው የአገሩ ልጅ በጥርጣሬ እንዲታይ እየተደረገ በነጻነት በገነባት አገር ውስጥ ሰርቶ እንዳይገባ ሲያደርግ የነበረ ሥርዓት ነው።
የዚህ ሥርዓት መወገድ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ የነጻነት ቀኑ ተብሎ ነው ሊጠቀስ የሚገባው፤ የታገለላቸው የዴሞክራሲ የልማት የእኩል ተጠቃሚነት ዓላማዎች ከዚህ በኋላ ተሳክተው የሚያይበት ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይህ ሁኔታ በተለይም ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ ትርጉም ያለው የራሱ የሆነ ስራ እንዳይኖረውና አሻራውን እንዳያስቀምጥ እኛ ብቻ ነን የምናውቅልህ ተብሎ የኖረውን አሁን ግን የራሱ የሆነ ትውልዳዊ አስተዋጽዖ እንዲያበረክትና ወደ ሃላፊነት እንዲመጣ ህዝቡን እንዲያገለግል በጣም ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ነው፤ እንደውም ለወጣቱ ትውልድ ይህ አጋጣሚ ወርቃማ ጊዜ ልንለው እንችላለን።
ይህ ለውጥ ለትግራይ ህዝብ ትልቅ እድልና ሲናፍቀውም የኖረ ሲታገልለትም የነበረ በመሆኑ እንደ ነጻነት ብርሃን ማየት ትልቅ ዋጋ ያለው ምዕራፍ ነው ተብሎ ቢገለጽ ማጋነን አይሆንም።
አዲስ ዘመን ፦ በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት የትግራይ ህዝብ በሌሎች ኢትዮጵያውያን አይን ሲታየ የነበረው እንደ ልዩ ተጠቃሚ ተደርጎ ነበርና እንደው ከዚህ አንጻር የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?
አቶ ነብዩ፦ እኔ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የትግራይ ህዝብ የነበረበትን ሁኔታ በደንብ ይረዱታል ብዬ አምናለሁ፤ ነገር ግን ምናልባት ጥቂት ሰዎች እንደዛ ሊመስላቸው ይችላል፤ ምናልባት አንዳንዶቹም ለራሳቸው የፖለቲካ ትርፍ የትግራይን ህዝብ ተጠቃሚ አድርገው የመሳልና በሌሎች ዘንድም እንዲህ አይነት ምስል እንዲፈጠር ያደረጉም ይመስለኛል። የህዝቡ ኑሮና አስተሳሰብ ይታወቃል፤ የትግራይ ህዝብ በስሙ ሲነገድበት የኖረ። 29 በመቶ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው፤ ሴፍቲኔትን ጨምሮ በጣም መሰረታዊ የሚባሉ ድጋፎችን ጠባቂ ። አዲስ አበባ ላይ በልመና ስራ ከተሰማሩ ወገኖች ትልቁን ቁጥር የሚይዝ ነው። በነገራችን ላይ ለ17 ዓመታት ያህል መራራ ትግልን ያደረገውና ያንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለው በቶሎ ለመልማት ፈልጎ ቢሆንም የተፈጸመበት ክህደት ልፋቱን ድካሙን አልፎም መስዋዕትነቱን ገደል የሰደደ ተግባር ነው።
ከዚህ ቀደም የነበረው የትግራይ ወጣት ተቸግሮ የሚማር ተምሮም ነገ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ራዕይ ያለው ነበር፤ አሁን ግን ትውልዱን በመግደል ለመማርም ፍላጎት የሌለው የእነሱን እዚህ ግባ የማይባል ስልጠና ወስዶ የሆነች ሰርተፍኬት ይዞ የሚቦዝን ፤በህይወቱ ላይም ምንም ለውጥ የማያመጣ ትውልድን ነው የህወሓት ሥርዓት የፈጠረው።
በእርግጥ በትግራውያን ስም የሚነግዱ ጥቂት ሰዎች እንዲበለጽጉ ሆኗል፤ ህዝቡ ግን ከመስዋት ወደ መስዋት ከመድማት ወደ መድማት ከድህነት ወደ ድህነት እየተገላበጠ እንዲኖር ተፈርዶበት ድርብ በደልን ችሎ የኖረ ህዝብ ነው።
ይህ ህዝብ በታሪክም ካለው አስተዋጽዖ ። በቅርቡም ሥርዓቶች እንዲለወጡ የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ ከከፈለው መስዋዕትነት ከሌለው ላይ እያዋጣ ለልማት ግንባር ቀደም ሆኖ እንደመሰለፉ አሁን የካሳ ዘመኑ ሊሆን ይገባል። ባለፉት
46 ዓመታት የትግራይ ህዝብ ድርብ በደል እየደረሰበት ቆየ እንጂ ተጠቃሚነቱ በማንነቱ። በታሪኩና በመስዋዕትነቱ ልክ አልነበረም።
እዚህ ላይ ልዩ ተጠቃሚነት እየተባለ የሚነሳው ምናልባት በስልጣን ላይ የነበሩ ግለሰቦችና በዛ ኔትዎርክ ውስጥ የነበሩ የራሳቸው የሆነ ማንነት ሁሉ የገነቡ ሰዎች አገር ዘርፈው ተጠቅመው ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ እነሱ ማለት የትግራይ ህዝብ አይደሉም።ህዝቡ በጣም ብዙ ችግር ተሸክሞ የቆየ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ የህግ ማስከበር ዘመቻው በስኬት ተጠናቋል እንደው እርስዎ ይህንን እንዴት ይመዝኑታል?
አቶ ነብዩ ፦ ውጤቱ በጣም አንጸባራቂ ነው፤ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የብሔር ። የሃይማኖት። የፖለቲካ አመለካከትና ሌሎችም ወደ ጎን ተትተው አገር ለማዳን ሉአላዊነታችንን ለማስከበርና ሰላማችንን ለማረጋገጥ በአንድነት ስለተነሳን ነው። እዚህ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቱ በጣም እየተስፋፋና ረዘም ያለ ጊዜንም ሊወስድ ይችላል የሚል ስጋት ነበር፤ ነገር ግን በርብርብ ስንሰራ በአጭር ጊዜ ምን ዓይነት ድል እንደምናስመዘግብ በታሪካችንም የምናውቀው አሁንም ያረጋገጥነው ሀቅ ሆኗል።
ከዚህ በመቀጠል የጁንታውን ቡድን አድኖ ለህግ የማቅረቡ ስራ በጣም በተጠናከረ መንገድ ቀጥሏል፤ ህዝቡ ወደነበረበት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ወደ ልማት ስራው እንዲመለስ ለማድረግ እየተሄደበት ያለው ርቀትም የሚደነቅ ነው።
እዚህ ላይ እንደ አገር ስንደመር ስንተባበር ምን ዓይነት አንጸባራቂ ድል በአጭር ጊዜ ማስመዝገብ እንደምንችል ፤ በተለይም ደግሞ አንድነታችንን አንዳንድ አጥፊ ቡድኖች እንደገለጹት ሳይሆን በትክክልም ኢትዮጵያውያን በጣም ጠንካራ እንደሆንና የሚከፋፍሉን ሃይሎች ወደ ስልጣን ሲመጡ ነው እንጂ አንድነታችን የላላ የሚመስለው ወንድማማችነታችን በጠንካራ መሰረት ላይ የታነጸ መሆኑን ለዓለም አስረድተናል። ሁኔታው በአገራችን ባይፈጠር ጥሩ ነበር። ነገር ግን የቀድሞ አንድነታችንን ይበልጥ እንድናጠናክርበት ጠላቶቻችንን እንድናሳፍርበት እድል የሰጠ በመሆኑ ሁላችንንም አስተምሮናል።
አዲስ ዘመን፦ የጁንታው ሃይል በክልሉ የተራዘመ ጦርነትን የማካሄድ ዓላማ እንደነበረው ይታወቃል፤ ይህ ከትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት ፈላጊነት አንጻር እንዴት ይገመገማል?
አቶ ነብዩ ፦ ጁንታው ጦርነቱ እንዲራዘም ይፈልግ የነበረው ወደ ድርድር እስኪመጣ ድረስ ነበር።ነገር ግን ጦርነት የገጠመው ከመከላከያ ሰራዊት ለዛውም የትግራይም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ሳያገኝ በመሆኑ ያን ያህል አቅም ኖሮት አሸንፋለሁ በሚል ስሜት አልነበረም።
በሌላ በኩልም ጁንታው በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ትልቅ ሆኖ ቢታይም በተግባር ግን ያን ያህል ትልቅ ሆኖ አይደለም። ስለዚህ ዓላማው የነበረው ጦርነቱን በተቻለ መጠን በትንሹ እንዲረዝም አድርጎ የዓለም ማህበረሰብ ትኩረቱን እንዲሰጠውና መንግስት ላይ ጫና ተፈጥሮ ወደ ድርደር ለማስገባት ነበር።ነገር ግን መንግስትም ይህንን ግብን ስለሚያውቅ ስራዎችን በሚሰራበት ጊዜ ሁሉ ይህ ዓላማ ከግብ እንዳይደርስ በማድረግ ነበር።በዚህም ድል በመከላከያ ሰራዊታችን ተገኝቷል።
እዚህ ላይ የትግራይ ህዝብ አስተዋጽዖ በጣም ጎልቶ እንዲወጣ ያስፈልጋል፤ አዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ላይ ከደም መለገስ ጀምሮ ገንዘብ በማዋጣትና ሌሎችም ድጋፎችን በማድረግ ከመግለጽ ባሻገር አጥፊ ሃይሉ እንዳይሸሸግበትና ብቻውን ተነጥሎ እንዲቀር በማድረግ ያሳየው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህም የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይም ለህዝቡ ትልቅ ምስጋና ቀርቧል።
አንዳንድ በውጊያው የተሳተፉ የልዩ ሃይል አባላትም ቢሆኑ መሄጃ ሲያጡ የተቀላቀሉ ናቸው እንጂ ይህንን ተግባር ደግፈውና የመከላከያ ሰራዊቱን መውጋት አገርን መክዳት መሆኑን አጥተውት አንዳልሆነ እነሱም ያውቃሉ፤ እኛም እንረዳቸዋለን።
አዲስ ዘመን ፦የጁንታውን ከፍተኛ አመራሮች ለፍርድ ለማቅረብ እየተካሄደ ያለውን ጥረት የትግራይ ህዝብ እንዴት እየተመለከተው ነው?
አቶ ነብዩ፦ አንድን ነገር ህዝብ ካልደገፈው ውጤቱ መጥፎ ነው፤ ሁኔታው ደግሞ ግልጽ የሆነ የወንጀል ውጤት ያለው በአገር ክህደት የሚያስከስስ በመሆኑ እንደምናየው አንዳችም የህዝብ ይሁንታ አላገኘም፤ ስለዚህ እነዚህ አጥፊዎች የህዝቡን ሰላም አደፍርሰዋል። መሰረተ ልማቱን አውድመዋል። የተለያየ ችግር ውስጥ እንዲገባም አድርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ትግራዋይ በጥርጣሬ እንዲታይ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ከማንም በላይ የተጎዳው ፍትህ የሚፈልገው የትግራይ ህዝብ ነው። በመሆኑም እነዚህ አጥፊዎች በአጭር ጊዜ ታድነው ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ በኩል የህዝብ ተሳትፎ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ህዝቡ ተባብሮ ጁንታው ለፍርድ ቀርቦና የትግራይ ህዝብም የሚመኘውን ፍትህ አግኝቶ ውስጣዊ ሰላሙን አረጋግጦ ወደ ልማቱ በቶሎ የሚመለስበትን መንገድ ሁላችንም እየጠበቅን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ትግራይ በአሁኑ ወቅት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መዋቅሩን የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው፤ ስራው በህዝቡ ዘንድ ያገኘው ተቀባይነት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ነብዩ ፦ በዚህ ምዕራፍ ላይ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መካከል የፈረሰው አስተዳደር መልሶ በጊዜያዊ አስተዳደር መተካት አንዱ ነው። ይህ ጊዜያዊ አስተዳደርም የመጀመሪያ ስራው ህዝቡን የማነጋገር። የማወያየት ሃሳቡን የመስማትና መሪዎቹን እራሱ እንዲመርጥ የማድረግ ነው። በዚህም ከደቡብ ትግራይ እስከ ምዕራብ ትግራይ ጫፍ ህዝቡ ተወያይቶ እከሌ ከንቲባዬ ይሁን። እከሌ ደግሞ የወረዳ አስተዳዳሪዬ ብሎ እየመረጠ ነው፤ ይህ ደግሞ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነና በዚህን ያህል ደረጃ ህዝቡ በነጻነት በቀጥታ መሪዎቹን የመረጠበት ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደውም ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ የተለያየ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ በበጎ ፈቃደኝነት ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር የህዝቡን ስሜት ለመግለጽ አሁን ላይ ትግራዋይ በሙሉ ማለት ይቻላል ከጁንታው አገዛዝ ተላቅቆ ሰላሙንና ልማቱን ማፋጠን እንደሚፈልግ በግልጽ እያሳየ ነው።
እዚህ ላይ መተኮር ያለበት ነገር የትኛውም አገር ላይ ቢሆን ከጦርነት ማግስት በቶሎ አገርን ወደ መረጋጋት ህዝብንም ወደቀደመው እሱነቱ መመለስ በጣም ከባድ ነው፤ ከትንሽ ጊዜያት በኋላ ግን ሁሉም ሰው የሰላሙ የልማቱ ጠበቃ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
አዲስ ዘመን፦ በተለያዩ ዓለም ላይ ያሉ የጁንታው ደጋፊዎች የመሰረተ ልማት ወድሟል። ህዝቡ እንደ ውሃ። መብራትና ቴሌ ኮም ተቋርጦበታል ፤በማለትና ተቆርቋሪ በመምሰል በተለያዩ መንገድ ሃሳባቸውን እየገለጹ መንግስትንም እየከሰሱ ነው፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ነብዩ ፦ ይህ የሚሰማው ክስ ህዝባችን እንዳይጎዳ ከሚል ቀና ሃሳብ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፤ ነገር ግን ክሱን በማን ላይ እያቀረቡ እንዳሉ የተረዱት አይመስለኝም። ወደዚህ ተግባርና ሁኔታ ውስጥ ያስገባን አካል እነሱ እንደግፈዋለን የሚሉት አጥፊ ቡድን መሆኑን መገንዘብም ያስፈልጋል። ግን ደግሞ መርገምና መውቀስ ብቻ ነው የምፈልገው የሚል ካለ መርገምም ሆነ መውቀስ ያለበትን አካል በቅድሚያ ለይቶ ሊያውቅ ይገባል።
ከዚህ ውጪ ግን ቀይ መስመር ታልፏል። የአገር ሉአላዊነት ተደፍሯል። መከላከያ ሰራዊታችን ተጠቅቷል። የህዝብ ሰላም ተናግቷል። ይህ ሁኔታ ሲሆን ደግሞ መንግስት ህግ የማስከበር ስራ ካልሰራ መንግስት አይደለሁም እንደማለት ያስቆጥራል። እንደውም ከጥፋታቸው አንጻር በመንግስት በኩል ከፍተኛ የሆነ ሆደ ሰፊነት ታይቷል፤ ይህ ሁሉ ጥረት ደግሞ መብቃት ባለበት ሰዓት አብቅቶ ሁሉም የእጁን ያገኝ ዘንድ ወደ ህግ ማስከበር ስራ ተገብቷል።
እዚህ ላይ ግን በቀናነት ህዝባችን እየተጎዳ ነው በማለት ድምጻቸውን እያሰሙ ላሉት ምስጋናም ከበሬታም አለኝ፤ ነገርየው አንድ ሃላፊነት በማይሰማው ቡድን ተፈጥሯል፤ ተጀምሯል፤ መንግስት ደግሞ የተፈጠረውን ችግር አይቶ ወደ መፍትሔው ገብቷል ፤ አሁንም አገራዊ ርብርቡን እውን ባደረገ ሁኔታ ህዝቡ በቶሎ ወደ ሰላሙና መረጋጋቱ እንዲመለስ እየተደረገ ነው።
ለህዝቡ በጣም መሰረታዊ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ የለት ደራሽ ምግቦች። መድሃኒትና ሌሎች በጣም በፍጥነት እንዲደርሱ እየሆነ ነው ፤ ተቋርጠው የነበሩት መብራት ውሃና የቴሌኮም አገልግሎትም ስራቸውን ጀምረዋል፤ አጥፊው ቡድን ያፈረሳቸው ድልድዮችንና መንገዶች በቶሎ ተጠግነው ወደ ስራ ይገባሉ።
በመሆኑን እነዚህን ከግምት ውስጥ ማስገባት ነው እንጂ ተራ ጎራ በመፍጠር። ዘር ቆጥሮ መነታረክ የትም የሚያደርስ አይደለምና ሁላችንም በዚህ ጥላ ስር ቆሞ ማሰብም ያስፈልገናል።
አዲስ ዘመን:- ወጣቱ ከቀደመው አግላይና ከፋፋይ አስተሳሰብ ለመመለስ ምን እየተሰራ ነው፤ በተለይም ለውጡ ወጣቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና በተጨባጭም ተጠቃሚ እንዲሆን ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ነብዩ፦ ዋናው ትኩረታችን ይህ ነው ፤ ከዚህ በኋላ ህወሓትን መርገም ያለፈውን ነገር እያነሱ መቆዘም ዋና ስራችን ሊሆን አይገባም። በእርግጥ ይህ እኩይ ተግባር በልኩና በመጠኑ መግለጽ ያልገባውን ሰው ካለ ደግሞ በሚገባው መልኩ ማስረዳት ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ በህግ የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም እየገባ እንደፈለገው ማድረግ የለበትም። እዚህ ላይ እንደ ጁንታው አይነት ተልዕኮ ይዘው ወደ እንደዚህ ዓይነት ተግባር መግባት ወይም መሳተፍ የሚፈልጉ ቡድኖች ካሉ አሁንም የህግ የበላይነት እንደሚረጋገጥና እነሱም ከህግ በታች ሆነው በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀሱ ብቻ አዋጭ መሆኑን መረዳት አለባቸው።
ከዚህ በኋላ ትኩረታችንን የምናደርገው ህዝቡን በማገልገል በመካስ ወደ ልማቱና ብልጽግናው እንዲጓዝ በማድረግ ነው። እስከ አሁን ባለው አካሄድ ወጣቱ በብዙ መልኩ እየተጎዳ የመጣ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ያመነባቸውንና ህጋዊ የሆኑ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ራሱንም የሚጠቅምበትን ከእርሱ የሚጠበቀውን ትውልዳዊ አስተዋጽዖ ለራሱና ለአገሩ የሚያበረክትበት የዴሞክራሲ ምህዳር ይፈጠራል።
አዲስ ዘመን ፦ የጁንታው ቡድን “እኔ ከሌለሁ አገር ይፈርሳል” በማለት በፈጠረው ፕሮፖጋንዳ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ቁዘማ ውስጥ የወደቁ ወጣቶች አሉና ለእነሱስ ምን መልዕክት አለዎት?
አቶ ነብዩ፦ አንዳንድ መቆዘም ላይ ያሉ ወጣቶችም ግለሰቦችም አሉ፤ ግን ደግም የህወሓት ውድቀት የትግራይ ህዝብም ሆነ የወጣቱ ሊሆን አይችልም፤ የራሳቸው ብቻ ነው የሚሆነው። በመሆኑም መቆዘም ሳይሆን በተፈጠረው ትልቅ እድል በመጠቀም እራሳቸውንም አገራቸውንም ህዝባቸውንም ለማገልገል መዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል።
ስለ ወጣቶቹ ደጋግሜ መናገር የምፈልገው አንዳንድ ወጣቶች የህወሓት ውድቀት የራሳቸው ስለመሰላቸው በከፍተኛ ቁዘማ ውስጥ ናቸው፤ ህወሓት ከወጣቱ ። ከህዝቡ ከመንግስትና ከተለያዩ አካላት ብዙ ምክርና እድል ተሰጥቶት አልጠቀምም ብሎ በራሱ እብደትና ቅሌት ነው ለዚህ የበቃው ፤ በመሆኑም የጁንታው ውድቀት ከትግራይ ወጣቶችም ሆነ ከማንኛውን ትግራዋይ ጋር የማይገናኝ ሊሆን የማይችል ከመሆኑም በላይ የሆነ ቡድን በራሱ መንገድ ሲሄድ የጠፋ አድርጎ መውሰዱም ሳይሻል አይቀርም።
ለጁንታው ቡድን ምክር ሃሳብ ካዋጡ አካላት አንዱ የትግራይ ወጣት ነው። በመሆኑም “ምከረው ምከረው እምቢ ካለህ መከራ ይምከረው” እንደሚባለው አሁን ላይ ምንም ማድረግ አይቻልም። ወጣቱም ጁንታው ቡድን ማንም የማይወክል መሆኑን በመረዳት ራሱን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አስማምቶ መቀጠል ይኖርበታል።
በሌላ በኩልም አሁን የመጣው ለውጥ የራሱ እንደሆነ በመረዳት ይህንን ደማቅ ምዕራፍ እውን አድርጎ ለራሱም ተጠቃሚ የሚሆንበት አገሩንም ህዝቡንም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የሚያገለግልበትን እድል በአግባቡ ሊጠቀም ከአንዳንድ አላስፈላጊ ቁዘማዎችና መፋዘዞችም ሊላቀቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ በክልሉ ላይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመልሶ ግንባታውም ሆነ በቀጣይ የክልሉ ህዝብ የፖለቲካ ህይወት በሙሉ አቅማቸው እንዲሳተፉ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እየተሄደበት ያለው ርቀት ምን ይመስላል?
አቶ ነብዩ ፦ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቷል፤ መሪዎቹም ተሰይመዋል። ካቢኔም የወረዳ መዋቅርም በየደረጃው እየተመሰረተ ነው ፤ ህዝቡም እየተባበረና ያስተዳድሩኛል ያላቸውን በመምረጥ ላይ ነው፤ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተባለ የግድ ሁሉንም በተለይም በክልሉ ላይ ማህበራዊ መሰረት ያላቸውን ፓርቲዎች ማቀፍና ሃሳብና አቅማቸውን በመጠቀም ካለንበት ችግር ሊያወጣን ይገባል ፤ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ መንፈስ እየሰራ ነው፤ በመሆኑም ህጋዊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህበራት ግለሰቦችም ቢሆኑ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ይመለከተኛል ላገለግለው እፈልጋለሁ ካሉ እንኳን ኢትዮጵያውያን ከሌላ ዓለም ቢመጡ ሊሳተፉበት የሚችሉበት ሰፊ ምህዳር ተፈጥሯል።
ይህ ሁኔታ ምናልባትም በታሪካችን ትልቅ ምዕራፍ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል እንደመሆኑ እኛም እንደ ብልጽግና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር ታቅፈን ትልቅ ስራ እየሰራን ነው። ተናበን እየሄድንና እየደገፍን ነው፤ ከዛ በተጓዳኝም የአባላት ምልመላና ሌሎች ተግባሮችን ለማከናወን ዝግጅታችንን እያጠናቀቅን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በጦርነቱ ምክንያት ቁጥሩ ትንሽ የማይባል ሰው ተሰዷል፤ ከቀየውም ተፈናውቅሏልና እነዚህን ዜጎች ለመመለስና ለማቋቋም ምን ታስቧል?
አቶ ነብዩ፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከመመስረቱ በፊት መንግስት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ቆይቷል፤ በነገራችን ላይ ከተሰደዱት ዜጎች መካከል የአጥፊው ቡድን የሴራ ማስፈጸሚያ የሆኑም በጣም ብዙ ናቸው። አንዳንዶቹ እንደውም ወንጀል ሰርተውም ነው የሄዱት። ይህ ሴረኛ ቡድን ይህንን ምስቅልቅል በመፍጠር ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ትኩረት በመሳብ ወደ ድርደር ተጋብዞ እንዲመጣ ማድረግ ተቀዳሚ ዓላማው ነበር። በዚህም ጎንደር ባህር ዳርና አስመራ ላይ ሮኬቶች መተኮሱም ህዝቡን ለማፈናቀልና ትኩረትን ለመሳብ ነበር። እንደ ማይካድራ አይነትና ሌሎችን እስከ አሁን ያልተገለጹ አሰቃቂ እልቂቶችን በመፍጠር ህዝቡም ፍርሃት ነግሶበት እንዲሸሽና በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ እየተሰደደ ነው ተብሎ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ አጀንዳ እንዲያደርግለት በማሰብ የፈጠረው ነበር።
ችግሩ ግን በማንም ይፈጠር በማንም መንግስት ደግሞ ወገኖቹን የማዳን ሃላፊነት አለበት፤ በተለይም ከወንጀል ነጻ የሆኑትን ወደ ቀያቸው የመመለስና የማቋቋም ስራ እየተጠናከረ ነው።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይት በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ነብዩ፦ እኔም አመሰግናለሁአዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013