ወቅቱ የመኸር እርሻ ምርት የሚሰበሰብበት ነው፡፡ ግብርና የኢኮኖሚዋ መሰረት ለሆነው ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ወቅት በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ፣ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች እንቅልፍ የላቸውም፤ አርሶ አደሩ በየአውድማው ነው የሚያድረው፡፡ የግብርና መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሙሉ አቅማቸውን የሚያውሉት በአዝመራ ስብሰባ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው፤ የዘንድሮው የመኸር እርሻ በጣም ጥሩና ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የሰብሉ ይዞታ የምርታማነት መጠንም በጣም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በ2012/13 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 13ነጥብ4 ሚሊየን ሄክታር መሬት እስከ አሁን 10 ሚሊየን ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የሚገኝ አዝመራ ተሰብስቧል፡፡ ይህ መረጃ ከወጣ ወደ አንድ ሳምንት አካባቢ የሆነው እንደመሆኑ ደግሞ፤ ከዛ በኋላ የተሰበሰበው አዝመራ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ይህ ሲታይ የአዝመራ ስብሰባ ሂደቱ ጥሩ አፈጻጸም ላይ ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን ያለው ጸሀያማ የአየር ሁኔታም ለአዝመራ ስብሰባው ትልቅ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑ ቀሪውን አዝመራ ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በደረሰ ሰብል ላይ ዝናብ ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት የለም፡፡ እናም ይህን መልካም አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ይገባል፡፡ ይህን በማድረግ በአዝመራው የታየውን ተስፋ ይበልጥ የሚጨበጥ ለማድረግ የተቀረውን አዝመራ በወቅቱ የመሰብሰቡ ስራ አሁንም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በምርት ዘመኑ በመኸር እርሻ ለማግኘት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የዘንድሮው የግብርና ስራ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ለእርሻ የዋለው መሬት ስፋት፣ አገልግሎት ላይ የዋለው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ብልጫ ያላቸው ናቸው፡፡ ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታም ለተለያዩ አገልግሎቶች በሚል የተያዙ መሬቶች በሙሉ ጦም እንዳያደሩ አቅጣጫ ተቀምጦ ታርሰው በዘር እንዲሸፈኑ ተደርጓል፡፡
በዚህ ላይ ተፈጥሮም ለጋስ ሆናለች፡፡ የዝናብ መጠኑ ለእርሻ ስራው ምቹ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ምቹ ሁኔታዎች በመኸር ወቅት እርሻ ብዙ ምርት እንዲገኝ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሆናቸው አያጠያይቅም፤ የግብርና ሚኒስቴርም እምነት ይሄው ነው፡፡
ይህ ሲባል ግን ተግዳሮቶች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ ጎርፍና አንበጣ የዘርፉ ተግዳሮቶች ነበሩ፤ እነዚህ ተግዳሮቶች ለምርታማነት ከፍተኛ ስጋት ሆነው ቢቆዩም በህዝቡ በመንግስትና በባለሙያው ርብርብ ሊደርስ ይችል የነበረውን የከፋ ጉዳት ማስቀረት ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ ጎርፍ እና አንበጣ ሊያደርሱ ይችላሉ ተብሎ የተገመተው ጉዳት ሲገመገም በምርታማነት ላይ ያን ያህል የከፋ አለመሆኑን መረዳት እንደተቻለ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህም በተለይ በአንበጣ መከላከል ላይ የተደረገው ርብርብ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው፤ በ2012 የመኸር እርሻ ከ363 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ሲሰራ ነው የቆየው፡፡ በምርት ዘመኑ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት እስከ አሁን የታየው አፈጻጸም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የግብርና ስራውን አጨራረስም ማሳመር ያስፈልጋል፡፡ ምርት ሙሉ ለሙሉ ተሰብስቦ መግባት ይኖርበታል፡፡ የቀረውም ሄክታር መሬት ሰብል ለመሰብሰብ የእስከ አሁኑን ተሞክሮ በመቀመር መስራት ያስፈልጋል፡፡
ሰብል ከማሳ በመሰብሰብና በመከመር ብቻ መወሰን አይገባም፡፡ ወቅቶ ጎተራ ማስገባትም ያስፈልጋል፡፡ በአዝመራ ስብሰባ ወቅት የምርት ብክነት እንደሚከሰት ይገለጻል፡፡ አብዛኛው አዝመራ የተሰበሰበ ቢሆንም በውቂያና በማጓጓዝ ወቅት ሊደርስ የሚችለውን ብክነት ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ርብርብ ማድረግ ይገባል ፡፡
የግብርና ምርት ጉዳይ የአርሶ አደሩ ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እንኳን ሰው ጆንያም በእህል ነው የሚቆመው ይባላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የግብርና ምርት እጥረት እንደሚኖር ተሰግቷል፡፡ ሀገራችን በያዘችው እቅድ መሰረት ለማግኘት ያስቀመጠችውን የምርት መጠን ለማግኘት ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ ህዝቡ በአንበጣ እና በጎርፍን መከላከል ያደረገውን ርብርብ በቀረው የሰብል መሰብስብ ስራም በመድገም የምርት ዘመኑን የግብርና ስራ አፈጻጸም አጨራረስ ማሳመር ይጠበቅበታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሄደ ያልነው የአንበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል የሚል ስጋት አለ፡፡ በመሆኑም አንበጣው እንዳይስፋፋ የሚደረገውን የመከላከል ስራ ባለፈው ተሞክሮ ላይ በመመስራት አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ላይ አሁንም ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት ይገባል፡፡ በመሆኑ እስከ አሁን ስኬታማ ስራ ማሳየት የተቻለበትን የአዝመራ ስብሰባ አፈጻጸም፤ በቀጣይም ቀሪውን በመሰብሰብ አፈጸጻሙን ይበልጥ የሰመረ ለማድረግ ይሰራ!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2013