የሰው ልጅ ሮቦቶችን ሲሰራ በብዙ ሰራተኞች የሚሰራውን ስራ በጥቂት ሮቦቶች ለመስራት ወይም እፎይ ማለትን አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ሮቦቶች በእርግጥም ሰዎችን ተክተው በመስራት ያሳርፋሉ፡፡
ባደጉት ሀገሮች ሰዎችን በመተካት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በማደግ ላይ ላሉ እንደ ኢትዮዽያ ላሉ ሀገሮች የሚዋጥ ላይሆን ይችላል፡፡ የስራ እድል መፍጠር ሲገባ የሚዘጋ ተብሎም ሊፈረጅ የሚፈረጅበት ሁኔታም ይኖራል፡፡ የቅንጦት መሣሪያዎች ይባሉም ይሆናል፡፡
በተለይ ከስራ እድል ጋር በተያያዘ የጎሪጥ አይታዩም ተብሎም አይታሰብም፡፡ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ዜጎችዋን ሥራ ያሳጣሉ የሚል ስጋት ነው፡፡ ወደ ሀገራችን እንዲገቡ ቢደረግ መጡብን ብለን ነው የማናስበው እንጂ መጡልን ብለን ጮቤ አንረግጥም ።
ሰሞኑን በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተከፈተ አንድ መዝናኛ ቤት ሮቦቶች የአስተናጋጅነት ስራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመዝናኛ ቤቱ ውስጥ ሁሉንም ነገር ሲከውኑ ይታያል፡፡ ምግብና መጠጥ በማቅረብ ያስተናግዳሉ፡፡
ሮቦቶቹ እንዲሰሩ ከተደረገው አኳያ ሲታይ ማስናገድ የሆቴሉን እንደ ምግብና መጠጥ ያሉትን ማቅረብ ብቻ አይደለም፡፡ ሮቦቶቹ ቀልዶችን ያቀርባሉ፣ ከህፃናት ጋር ይጨፍራሉ፣ ይወዛወዛሉ፡፡ አንዳንዴም ከደንበኞች ጋር ለጨዋታ ቁጭ ይላሉ። ሁሉንም ነገር የሚሠሩት በደስታ ነው። ይህም ከፍትፍቱ ፊቱ ያሰኛቸዋል፡፡
መዝናኛ ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለሀብት ንብረት ነው። የመዝናኛ ቤቱ ሠራተኛ ሁሉ የተሞላው በሮቦቶች ቡድን ሲሆን ዓላማው ደግሞ የሰራተኞቹን ድካም ማቃለያ ከሆነው የቴክኖሎጂ አብዮትና ሰው ሠራሽ ግኝቶች ጋር ሰዎች እንዲተዋወቁ ማድረግ ነው።
በመዝናኛ ቤቱ የሮቦት አስተናጋጆች ከደንበኞች የሚታዘዘውን ምግብና መጠጥ ለማቅረብ የተመደበላቸውን ቦታ የሥራ ድርሻ ጠብቀው የሚታዘዙ ናቸው። ደንበኞች በመረጃ ቋት ላይ በሰጡት ግብረ መልስ መዝናኛ ላይ የሚሠራው ሮቦት አንዳንዴ ሲቦርቅ በሚያሳየው እንቅስቃሴ መማረካቸውን ይገልፃሉ። ባለቤቱ በጃፓን ኩባንያ የተመረተው አንደኛው ሮቦት በቡና ቤቱ ውስጥ ጫጫታ ባለበት ሆኖ የደንበኞቹን ትዕዛዝ ለመስማት መቸገሩን ጠቅሰው፣ መሻሻል እንዳለበትም ባለቤቱ ይናገራል ።
ሮቦቶችን በስጋት፣ በጥላቻና በፍራቻ የማየት ነገሮች ቢኖሩም፣ በቡዳፔስት መዝናኛ ቡና ቤት ከሥራ ውጭ የሆነ ወይም የተሰናበተ አንድም ሰው አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል። የሰው ልጆችን የመቀጠርና ሥራ የማግኘት ዕድል እየጨመሩ መምጣቸው ነው የተጠቆመው፡፡
የመዝናኛ ቤቱ ባለቤት የተቀነሰ ሰራተኛ እንደሌለ ይልቁንም ተጨማሪ ሰራተኞች መቀጠራቸውን ይገልጻሉ፡፡ እኛ በርግጥም በፊት ከነበረን የሰው ኃይል በእጥፍ ሠራተኞች ቀጥረናል ሲሉ ነው የተናገሩት። ‹‹በቀን ከ16 እስከ 20 የሚሆኑ ሮቦቶችን እናንቀሳቅሳለን፤ ለዚህም የሚረዱ እና ከመዝናኛ ቤቱ ጀርባ ሆነው የሚሠሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልሂቃንን እንጠቀማለን›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
ኃይለማርያም ወንድሙ