ከመዝናኛው ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የፊልሙ ኢንዱስትሪ አንዱ ነው። በዓለም ላይ ረብጣ ንዋይ ከሚፈስባቸው እንዲሁም ለሚሰሩበት አገር ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ከሆኑ ዘርፎች መካከልም ይጠቀሳል፡፡
ፊልሞች የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ መሆናቸው ይታወቃል። የፊልም ጥበብ የአንድን ሀገር እና ህብረተሰብ ታሪክ፣ ባህልን እና ወግን ለተመልካች ያደርሳል፤ ከዛም አለፍ ሲል ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞች የዓለምን መፃኢ እድል ቀድመው ይተነብያሉ፤ ለዚህም ማሳያ የዓለም ስጋት ሆኖ የቀጠለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የተነበየውን፣ በ2009 ዓመተ ምህረት የተሰራውንና ለተመልካች የቀረበውን “ኮንታጂን” ፊልምን ማስታወስ በቂ ነው፡፡
ለዛሬ ግን የወደፊት መፃኢ እድልን የሚያሳይ ፊልም ሳይሆን በእውነተኛ ታሪክ ላይ መሰረቱን አድርጎ ያለፈን አሰቃቂ ድርጊት ቀርፆ ለሌሎች መማሪያ እንዲሆን ለዓለም ህዝብ ያቀረበውን ፊልም እና ገፀ ባህሪን ለእናንተ ለማንሳት ወደናል፡፡ ፊልሙ ለዕይታ ከበቃ ረዘም ያለ ጊዜ ቢወስድም፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ የሚችል አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚዛመድ እውነትን ያዘለ ነው፡፡
ፊልሙ በ2004 ዓመተ ምህረት ለእይታ የበቃው እና በእውነተኛ ታሪክ ላይ መሰረቱን ያደረገው “ሆቴል ሩዋንዳ” የተሰኘው ፊልም ነው፡፡ በ1994 በሩዋንዳ የነበረውን የዘር ጭፍጨፋ ያመለክታል፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ለዘመናት በአብሮነት በቆዩ ህዝቦች መካከል በተሰራጨ ፀብ አጫሪ መልእክት ምክንያት አንዱ ጎሳ ሌላኛው ጎሳ ላይ ያደረሰውን የዘር ጭፍጨፋ ያስቃኛል። የዛሬው ትኩረቴ ፊልሙ ሳይሆን፣ በፊልሙ መሪ ተዋናይ ገጸ ባህሪ ላይ ነው፡፡
በ1994 በሩዋንዳ የተከሰተውን ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ ያደረሱትን የዘር ጭፍጨፋ በሚያሳየው ሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናኝነት የሚሰራው ፖል የተባለው ገፀ ባህሪ ለብዙዎቻችን አስተማሪ ይሆናል። ፖል የዘር ግንዱ ከሁቱዎች የሚመዘዝ ሲሆን፣ ባለቤቱ ታቲያና ደግሞ ቱትሲ ከሚባለው ጎሳ ነች፤ ሁቱዎች ጥቃት ሊያደርሱበት ከሚፈልጉት ጎሳ የተገኘች ናት፡፡ እነዚህ ሁለት ጥንዶች የዘር ልዩነት ሳይገድባቸው በትዳር ተጣምረው አራት ልጆችንም አፍርተዋል፡፡
ይህ ፖል የተባለው ገፀ ባህሪ ሁቱ ቢሆንም፣ ቱትሲ የሆነችውን ሚስቱን፣ ጎረቤቶቹን እና ወዳጆቹን ከሁቱዎች ጥቃት ለመታደግ የሚያደርገው ጥረት እና የከፈለው መሰዋዕትነት ልብ የሚነካ እና በሰውነት የተሞላ ነው፡፡
በአንድ ሆቴል ውስጥ በማናጀርነት የሚሰራው ይህ ገፀ ባህሪ፣ ቱትሲዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተቀጥሮ ወደሚሰራበት ሆቴል አስገብቶ ከለላ ሲያደርግላቸው እና ለጸጥታ ሀይሎች ጭምር ክፍያ በመስጠት ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ሲያደርግ ይታያል፡፡ ይህ ሌሎችን ለማዳን የሚያደርገው ጥረት፣ መሰዋዕትነት፣ እሳቤው አመለካከቱ እና አዛኝነቱ የእውነት ሰው የሚለውን እሳቤ ያላብሰዋል፡፡ ቤተሰብ፣ ጉርብትና እና ወዳጅነት በተድላ ብቻ ሳይሆን በፈተናም ጊዜ የማይለያይ መሆኑን በተግባር ፍንትው አድርጎም ያሳያል፡፡
በእኛም ሀገር በሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ላይ እንደተመለከትነው በፊልሙ ውስጥ “ፖል” በሚል ስያሜ ዋና ገጸ ባህሪ ሆኖ የሚተውን አለ፡፡ ይህ “ፖል” የተባለው ገጸባህሪ በፊልሙ ውስጥ የሚያሳየው የመልካም ጉርብትና የወዳጅነት የፍቅር … ልብና ስሜት ነው፡፡
ሰዎች በማንነታቸው ሳቢያ ለጥቃት የተዳረጉበት ሁኔታ በሀገራችን በትህነግ ጁንታ ቡድን እና ተላላኪዎቹ ተፈጽሟል፡፡ በዚህም በርካታ ንጹኃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል። ጁንታው በማይካድራ በቅርቡ ከ700 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን በማንነታቸው የጨፈጨፈበት ሁኔታ ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። ጁንታው ይህን ያድርግ እንጂ እንደ ሆቴል ርዋዳው ተዋናይ ሰዎች በማንነታቸው ሳቢያ ለጥቃት እንዳይጋለጡ ያደርጉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡
ለዘመናት በአብሮነት እና በፍቅር አብረው የኖሩ ጎረቤቶቻቸውን ከጥቃት እና ከጥፋት ሃይሎች የሚጠብቁ አብሮነታቸው በጊዚያዊ ስሜት እና ድርጊት ያልተናደ፣ የተሳሰሩበት ገመድ የብሄር እና የሃይማኖት ሳይሆን የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሁም የኢትዮጵያዊነት መሆኑን በተግባር ያስመሰከሩ ብዙ ንፁህ ኢትዮጵያዊንን ተመልክተናል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ እውነታ የተሸረሸረበት ሁኔታ አጋጥሟል፡፡ በሀገራችን በተፈጠረው የጥፋት ሀይልና ተላላኪዎቹ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ለእዚህም በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀስ በነበረው የትህነግ ጁንታ ሀይል በማይካድራ በማንነታቸው የተጨፈጨፉ ከ700 በላይ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
በእዚህ አስቸጋሪ ወቅት በማንነታቸው ጥቃት ሊደርስባቸው የሚችሉ ንጹሃን ዜጎችን ከጭፍጨፋ የታደጉም ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ “ፖል” አይነት ልቦና ያላቸው ናቸው፡፡ ግለሰቦች ጎረቤቶቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ከጥቃት ሲያስጥሉ ቅድሚያ እኔን ብለው ደረታቸውን ሰጥተዋል፤ ይህ የአብሮነት ስሜት በአሸዋ ላይ የተገነባ ሳይሆን፣ እንደ አለት በጠነከረ በልብ ውስጥ በታተመ ኢትዮጵያዊነት ላይ የተገነባ ነው፡፡
ልክ “ፖል” በሆቴሉ ውስጥ ወዳጆቹን እና ጎረቤቶቹን እንዳስጠለለው ሁሉ እነዚህ በአብሮነት ለዘመናት የቆዩት ኢትዮጵያዊያንም ጎረቤት ወዳጆቻቸውን ከጥቃት ለመታደግ በጉያቸው አስጠልለው በር ዘግተው ንብረታቸውን ጠብቀው ክፉውን ቀን አሳልፈዋል፤ ይህም ወደፊትም በአብሮነት በፍቅር፣ በመተሳሰብ እና በፍፁም ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዘመናት ለመኖር ቃልኪዳን እንዳላቸው ያሳያል፡፡
ጉርብትና አብሮ መብላት፣ አብሮ ቡና መጠጣት ብቻ ሳይሆን፣ በደስታ እና በችግር ጊዜ ደራሽ መሆንን ወትሮም የነበረ ኢትዮጵያዊ ባህላችን መሆኑን ጠንቅቀው የሚያውቁ ብዙዎችን አይተናል፡፡ የአብሮነታችን መንፈስ በጥቂት የጥፋት ሃይሎች ይሸረሸር ይሆናል እንጂ ጨርሶ አይናገድም። ለዚህ ደግሞ ያለንበት ወቅት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡በማንነት ላይ ተመስርቶ በዜጎች ላይ ጥቃት ሊሰነዘር ይችል ይሆናል፤ የዜጎችን ትስስር መበጠስ አይቻልም። ኢትዮጵያዊነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እና በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ ነው፤ ይህም የኢትዮጵያዊነት አርማ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ልክ “በሆቴል ሩዋንዳ” ፊልም ላይ እንደተመለከትነው ፖል በኢትዮጵያም ብዙ ጎረቤቶቻቸውን ጠባቂ በችግር ጊዜ ቀድሞ ደራሽ ኢትዮጵያዊ ጎረቤቶች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በፍቅር እና በመረዳዳት ፀንተው የኖሩ ጎረቤታሞችን የጥላቻ መርዝ በመርጨት አብሮነትን ለመሸርሸር፣ አንድነትን ለመናድ የቆሙም እንዳሉ ተመልክተናል፤ በተለይ ያለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡
አሁንም ወደፊትም ልክ እንደ ፖል በቋንቋ፣ በማንነት፣ በዘር እና በሃይማኖት ሳይሆን በሰውነት፣ በአብሮነት እና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ ሰዎችን ያብዛልን፡፡ ኢትዮጵያም የመቻቻል የአብሮነት የአንድነት የብልጽግና ምድርነቷ ይቀጥላል…!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013