አጼ ኃይለሥላሴ ከአባታቸው በውርስ ያገኙትን ቤተመንግስት” ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” ብለው በመሰየም መርቀው የከፈቱት ከ58 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታህሳስ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ነበር። ጥቅምት 23 ቀን 1952 ዓ.ም ተቋቁሞ “ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዲስ አበባ” በመባል ይታወቅ የነበረው የትምህርት ተቋም በኋላ ታህሳስ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ስድስት ኪሎ የሚገኘውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት መቀመጫ በማድረግ “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚል ስያሜ ተመርቆ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በቃ። ከ12 ዓመታት በኋላ የዘውዳዊው መንግሥት ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ የተመሠረተው ወታደራዊ መንግሥት የቀደመ ስሙን ሽሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲል ጠራው።
ማክሰኞ ታህሳስ 10 ቀን 1954 ዓ.ም የታመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 21ኛ ዓመት ቁጥር 297 እትም ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲውን መርቀው ሲከፍቱ ያደረጉትን ሙሉ ንግግርና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ኬኔዲ እንዲሁም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዕለቱን በማስመልከት የላኩትን መልዕክት አስነብቦ ነበር። አጼ ኃይለሥላሴ “ይህን ቤተ መንግስት ከቦታው ጋር ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክተናል” በሚል ርዕስ ተከታዩን ንግግር አድርገው ነበር።”
በዚህ የታሪክ ስፍራ ላይ ዩኒቨርሲቲ እንዲመሰረትበት የፈቀድነው በትምህርት ስራ ላይ ላደረግነው የረጅም ጊዜ ትግልና ለህዝባችንም ባለውለታነት ምስክርና የጋራ ሐውልት ሆኖ እንዲኖር በማሰብ ስለሆነ ይህ ቦታ ከዚህ ዓላማ ውጭ ለሆነ አገልግሎት እንዳይውል አደራውን የምንተወው ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ነው። … ይህ ዛሬ የምንመርቀው ዩኒቨርሲቲ እንዲመሰረትብትና የኛና የህዝባችን ሐውልት ሆኖ እንዲኖር ከአባታችን ከልዑል ራስ መኮንን የወረስነውን የግል ርስታችንን ይህን ቤተ መንግስት ከቦታው ጋር ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክተናል። ይህን ዩኒቨርሲቲ ስንመርቅ። ይህ ቀን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት ላደረግነው የረጅም ዘመን ድካምአክሊል ይሆናል ብለን በመገመት ነው።”
በወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሬዚደንት ኬኔዲ የዩኒቨርስቲውን ተመርቆ መከፈት አስመልክተው ለግርማዊ ንጉሠ ነገስት በላኩት መልዕክት “… ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋመውን መንግስት ብቻ ሳይሆን መላውን የሰው ልጅ ሊያገለግሉ የሚችሉ ልዩ ልዩ ሀሳቦችንና ፍልስፍናዎችን ሊያስገኝ የሚችል ነው።
በዚህ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል የጋራ የትምህርት መግባቢያ ሥፍራ በሳይንትፊክና ካልቸራል ጉዳዮች ረገድ ታላቅ
መገኛ ቦታ ይኖራታል። … ለኢትዮጵያ ህዝብ ዩኒቨርሲቲ ይውል ዘንድ ቤተ መንግስትዎን ከነርስቱ በሰጡበት ዕለት “በሀገሬና በራሴ ስም ሆኜ የጋለ የወዳጅነትና ከልብ የመነጨ መልካም ምኞቴን ስገልጽ ክብር እየተሰሰማኝ ነው” ብለው ነበር። የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም ዕለቱን በማስመልከት አዲስ አበባ በሚገኙት የእንግሊዝ አምባሳደር በኩል በላከው መልዕክት “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሚመረቅበት ለዚህ ለማይረሳና እጅግ ለሚያስደስት ሁናቴ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለግርማዊነትዎ የጋለ ደስታውን ሲገልጽ ከፍ ያለ ደስታ
ይሰማዋል። … በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ለብዙ ጊዜ የነበረው ምኞት ከፍጻሜ ስለደረሰ በጣም ተደስተናል።”ብሎ ነበር።
የ58 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ጥናት በማድረግ። የቀጠና ደረጃን የጠበቀ ጥናት በማድረግ። በማሳተም። በመጽሐፍ አቅርቦት። ኮንፈረንሶችን በማካሄድና ‘ሳይት’ በመደረግ ብቃት አፍሪካ ውስጥ ካሉ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑን የዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ አውጪ ተቋም ጥናት አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013