ዘመኑ ለቱሪዝም ምቹ እየሆነ መጥቷል። ብዙ ሀገራት የኢኮኖሚ ምንጫቸውን በቱሪዝም ዘርፍ ካደረጉ ሰንበትበት ብለዋል። በተለይ በራስ ባሕል እና እሴት በዓለም አቀፋ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ እንደመገኘት አርኪ እና ተፈላጊ ነገር አልተገኘም። ለእዚህ መሠረቱ የሠለጠነ የሰው ኃይል ነው። ከእዚህ ጋር በተያያዘ ከሚሠሩ አካላት መካከል ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘው የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት አንዱ ነው።
ኢንስቲትዩቱ በዋናነት በሥልጠና፣ በጥናት እና ምርምር፣ እንደዚሁም ዘርፉን በማማከር እየደገፈ የሚገኝ ሲሆን፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ስምምነት መሠረት ተጠሪነቱን ለሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በማድረግ በሥልጠና የበኩሉን እያደረገ ይገኛል።
በራስ ባሕል እና እሴት በዓለም አቀፉ ገበያ በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ከሰሞኑ ይኸው የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ከኩሪፍቱ ሪዞርት ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት አድርገዋል። ስምምነቱን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ጋር ባደረግነው ቆይታ፤ ከኩሪፍቱ ሪዞርት እና እስፓ ጋር ያደረጉትን የጋራ ስምምነት በሚመለከት አራት በሚሆኑ ነጥቦች የአብሮ መሥራት የትብብር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል።
‹‹በሆቴል በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ላይ በጋራ ልንሠራ ተነጋግረናል። በእዚህም ኢትዮጵያን የማይመስለውን የሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ ልማድ በማሻሻል ኢትዮጵያዊ ቀለም በመስጠት ባሕል እና እሴትን ለቱሪዝም ልማት በማዋል ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት መስማማት ላይ ተደርሷል›› ሲሉ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሆቴሎች መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ ዜጎችን በማሠልጠን በኢትዮጵያዊነት ቀለም ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አብዛኞቹ ሆቴሎች በውጪ ሀገር ማንነት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ቡራቡሬ ዓይነት መልክ ያለውን የመስተንግዶ ዘዬን በማስተካከል ለሆቴል ቱሪዝም ምቹና ተስማሚ ዓለም አቀፍ የአገልግሎት ተቋም ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
ኩሪፍቱ ሪዞርት ባለፉት ሃያ ዓመታት ከማህበረሰቡ ባሕል እና እሴት ጋር ተናብቦ በመሥራት ተሞክሮ ያለው በመሆኑ፤ ኢንስቲትዩቱ ከያዘው ዓላማ ጋር በማዋሃድ ኢትዮጵያዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ልማድ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ሚና እንደሚወጣ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሌላው ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ በባሕላዊ ምግቦች በትብብር መሥራት ነው። ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ሀገር በመሆኗ የብሔረሰቦችን ባሕላዊ ምግቦች በማጥናት ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ የባሕል ምግቦችን ለመጠቀም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ ሀገር በቀል ባሕላዊ ምግቦችን በማጥናት፣ አሠራራቸውን በመሰነድ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ በሥልጠና፣ በምርምር እንደዚሁም በሌሎች ሁኔታዎች እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ አቶ ይታሰብ ይገልጻሉ። አያይዘውም ባሕላዊ ምግቦች በባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች እና በባለአራት ኮከብ ሆቴሎች ለተጠቃሚ እንዲውል እየተደረጉ እንደሆኑ ገልጸውልናል።
በእዚህ ዓመት በኃይሌ ግራንድ ሆቴል እና በካፒታል ሆቴል በምግብ ዝርዝር ደረጃ እንዲካተቱ ጥረት ማድረጋቸውን አመልክተዋል። ከእዚህ ጋር ተያይዞ ቡራዩ ላይ የሚገኘው የኩሪፍቱ ሪዞርት አካል የሆነው በአፍሪካ ቪሌጅ ሆቴል ነባር ሥራው የአፍሪካን ባሕልና ምግባቸውን የሚያስተዋውቅ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያንም ባሕል እና ምግቦች እንዲያስተዋውቅ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። ሆቴሉ የአዲስ ዓመት መግቢያ መስከረም ወር የኢትዮጵያ ወር ብሎ እንደሚያከብር አስታውሰው፤ በእዚህ ወር ያሠለጠኗቸውን ባለሙያዎች ከራሳቸው፣ ከክልል፣ ከእናቶቻቸው እና ከባሕሉ ባለሙያዎች ጋር ተጣምረው ከፍ ባለ ደረጃ ለማስተዋወቅ የባሕል ዝግጅት እያደረጉ እንዳሉ ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ቱሪዝም እና አገልግሎት የማይነጣጠሉ ናቸው። በጥናት እንደተረጋገጠው ሰባ ከመቶ ቱሪስቶች ወደ አንድ ቦታ ለመሄድ ከመወሰናቸው በፊት ከምግብ ጋር የተያያዘ ለየት ያለ ነገር እንደሚፈልጉ ታውቋል። ይህንን መሠረት በማድረግ በራስ ባሕል የራስን ባሕላዊ ምግቦች ለአገልግሎት ማዋል በብዙ መልካም አጋጣሚ ሊታይ ይገባል። እስካሁን ሰላሳ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ባሕላዊ ምግቦች በጥናት በመለየት በትላልቅ ሆቴሎች ለአገልግሎት እንዲውሉ ተደርጓል።
ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ የራስን ባሕል ከመረዳት አኳያ ላቅ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውሰው፤ በተለይ ትውልዱ የአያት ቅድመ አያቶቹን ባሕል፣ ታሪክ፣ የምግብ አዘገጃጀት ለማወቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
አንድ ቱሪስት ወደ ካፒታል ሆቴል ገብቶ የጋሞን ወይም የሀዲያን አልያም የኮንሶን ባሕላዊ ምግብ አዝዞ ማግኘት ቻለ ማለት ‹‹ይሄ ቦታ የት ነው?›› የሚል ጥያቄ ይነሳል። በጥያቄው መሠረት ወደ ቦታው በመሄድ የአካባቢውን ባሕል፣ ሥርዓት በማየት እንደዚሁም ተጨማሪ የቱሪስት አገልግሎት እድል በማስገኘት ለዘርፉ እምርታ ይሰጣል ብለዋል።
‹‹ባሕላዊ ምግቦቻችን የማንነታችን መልኮች በመሆን እኛነታችንን በይበልጥ ገላጭ ናቸው። ቢሠራባቸው ኮንፈረስ ቱሪዝም እንደሚባለው ራሳቸውን ችለው የቱሪዝም የኢኮኖሚ አመንጪ አካል መሆን የሚችሉ ናቸው›› የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተጨማሪ እነዚህ ባሕላዊ ምግቦች የሚሠሩበት መንገድ ቀላል እና አመቺ በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ በበጎነት መነሳት የሚችሉ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በእዚህ ዓመት ለመሥራት ከያዙዋቸው እቅዶች አንዱ በጎዳና ምግብ ስም ባሕላዊ ምግቦችን ለተጠቃሚ ማቅረብ ነው። እነዚህን ምግቦች አሁን ላይ ከኮሪዶር ልማት ጋር አያይዘው የጎዳና ምግቦች በሚል ስያሜ ለመሥራት ወጣቶችን በማሠልጠን ላይ ይገኛሉ።
ይህም የሥራ እድልን በመፍጠር፣ ሰዎች ምግብ እየበሉ እንዲዝናኑ በማድረግ ረገድ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተው፤ ፒያሳ ዓድዋ ሙዚየም አካባቢ ኮሪዶሮች ባዶ ናቸው። ሰዎች ይዝናናሉ፤ ውሃ ይራጫሉ የሚበላ ግን የለም። ለእዚህ ክፍተት ምላሽ እንዲሰጥ ተንቀሳቃሽ የማዕድ ማብሰያ አሠርተው ወጣቶችን አሠልጥነው ወደ ሥራ እንደሚያስገቡ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከሥልጠና አኳያ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማፍራት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ዓይነተኛ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኢንዱስትሪ እና በማሠልጠኛ ማዕከላት መካከል የሚሰጡ ነባር ሥልጠናዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ይህንን ሥልጠና ከማከናወን አኳያ ከብዙ ተቋማት ጋር በመሥራት ላይ መሆናቸው ጠቁመዋል። ይሁንና ከኩሪፍቱ ሪዞርት ጋር ለየት ባለ መልኩ በትብብር ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ሠልጣኞች በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ከተለማመዱ በኋላ በዘርፉ ላይ ሲሠሩ ባልተለመደ እና ለየት ባለ ሁኔታ አቅማቸውን አጎልብተው የተሻለ ነገር ይዘው እንዲወጡ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸው አስታውቀዋል።
በተጨማሪ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በሥልጠና በማብቃት በሙያቸው ከሀገር ውስጥ አልፈው ለውጪ ሀገር እንዲበቁ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ከተለመደው የቤት ሠራተኛነት ውጪ በሆቴል እና ቱሪዝም ሠልጥነው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች እንዲተርፉ ሥራዎች እንደተጀመሩ ጠቁመዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ተፈላጊ በመሆናቸው ቀጣሪዎች በሚፈልጉት መልኩ የቋንቋ፣ የክህሎት፣ የእውቀት እና የልምድ ሥልጠናዎችን በመስጠት መላክ እንደሚቻል በመግባባት በእዚህ መልኩ ለመሥራት ተስማምተዋል።
ሌላው ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። ሆቴል እና ቱሪዝሙን በቴክኖሎጂ በማዘመን ምቹ እና የተቀላጠፈ የአገልግሎት ተቋማትን በማስፋት ለቱሪስቶች ተመራጭ ሁኔታን መፍጠር ተገቢ በመሆኑ እየሠሩ እንደሚገኙ ይገልጻሉ። የሆቴል እና የቱሪዝም ዘርፍ ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከሥልጠና ባለፈ ለዘርፉ ግልጋሎት እንዲውሉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አያይዘው አንስተዋል።
በእዚህ ዓመት ባጠኑት ጥናት መሠረት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደ ኩሪፍቱ ካሉ ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማሳደግ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረጉ መሆኑን ይገልጻሉ። ከእዚህ አኳያ አየር መንገድ የሚጠቀሙበትን ሶፍትዌር ሠልጣኞች እንዲሠለጥኑበት በማድረግ በቀጣይ ልክ እንደ አየር መንገድ ተጨማሪ ሥራዎችን እንዲሠሩ በሚቻልበት ሁኔታ ከስምምነት መድረሳቸውን አመላክተዋል።
እነዚህ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ከጥቅም አኳይ ላቅ ያለ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ እያደገ ለመጣው የሀገሪቱ የቱሪዝም መነቃቃት መንገድ ጠራጊ በመሆን የሚገለጽ ነው ይላሉ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የቱሪዝም ዘርፍ በዋናነት የሰው ሀብት ልማት ይፈልጋል። በእዚህ ዘርፍ ላይ ወሳኝ ነገር ማስቀመጥ የግድ ከሆነ የሰው ሀብት ልማት ነው።
የሆቴል እና የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት መሠረቱ የሰዎች ለሰዎች ግንኙነት ነው። አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አገልግሎት ተቀባዩ የሚጋሩት ነገር አለ። በሁለቱ መካከል የምርት ልውውጥ ብቻ ሳይሆን መስተንግዶው፣ ትህትናው፣ አክብሮቱ፣ ፈገግታው፣ እንክብካቤው በወሳኝነት የሚቀመጥ ነው። ይህ የሰው ለሰው መስተጋብር ከሰዎች ውጪ በሌላ ቴክኖሎጂ ሊሠራ የማይችል በመሆኑ ለሆቴል እና ቱሪዝሙ አስፈላጊ ነው ሲሉም ያመለክታሉ።
ከእዚህ አኳያ የሚሠራው ሥራ በደንብ መሬት እንዲረግጥ ከተፈለገ የብዙ ባለድርሻ አካላት ትብብር፣ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ በሰው ሀብት ዙሪያ ልምድ ካለው እና በሆቴል ቱሪዝም የኢትዮጵያን ባሕል ከተረዳው ኩሪፍቱ ጋር አብሮ መሥራት መቻላችን ብዙ እድሎችን ከፋች ነው።
ላለፉት ብዙ ዓመታት ያካበተውን ኢትዮጵያዊ የመስተንግዶ ልምድ ከተቋሙ ዓላማ እና ግብ ጋር በማዋሃድ ባለሙያዎችን በማሠልጠን፣ በማብቃት፣ ባሕላዊ ምግቦችን በማስተዋወቅ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሆቴል አገልግሎት ከመስጠት አኳያ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
ቱሪዝም ከአምስቱ ኢኮኖሚ አመንጪ ዘርፎች መሀል አንዱ በመሆኑ በመንግሥት አቅጣጫ ተቀምጦለት እየተሠራበት ይገኛል። በእዚህም መንግሥት ለቱሪዝሙ አመቺ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በመሥራት፣ የመስህብ ቦታዎችን በማልማት እና በማደስ በአጠቃላይ ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ንቅናቄዎች በየቦታው ተባዝተው ዘርፉን ለተሻለ እምርታ እያበቁት መሆኑን ያመላክታሉ።
የኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ ባለቤት አቶ ታዲዮስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ስምምነቱን በመልካም እንደሚመለከቱት ይገልጻሉ። በተለይ የሰው አቅምን በማሳደግ እድል ለሌላቸው እድል በመፍጠር፣ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት በደንበኛ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ጠቃሚ እንደሆነ አመላክተዋል።
አሁን ላለው የሀገሪቱ የሆቴል እና ቱሪዝም ልማት መልካም ጅማሮ እንደሆነ ጠቁመው፤ በራስ ባሕል እና እሴት እንዴት መለወጥ እንደሚቻል የሚጠቁም ከመሆኑም በላይ በትስስር እና በውህደት የሚሠራ በመሆኑ ጥቅሙ ሰፊ ነው ብለዋል።
ስምምነቱ እድል ያላገኙ ዜጎች ሥልጠና ወስደው በራሳቸው ሠርተው እንዲለወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። የተጀመሩ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች በሰው እውቀት መደገፍ እንዲችሉና ከሀገር ውጪ እየሄዱ በርካሽ ገንዘብ የሚሠሩ ወገኖች ዋጋ በማሰጠት ጥሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ጠቁመዋል።
ቱሪዝም ከራስ ወደ ሌሎች የሚፈስ እንደመሆኑ የራስን ሀብት፣ ተፈጥሮ፣ ባሕል እና እሴት መጠበቅ፣ ማስተዋወቅ ዓይነተኛ ሚና አለው። በራስ ቀለም ሌሎችን መሳብ መቻል የዘርፉ አንድ አካል ሲሆን፤ በተለይ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ሚናው የእዚያኑ ያህል ነው።
ዘላለም ተሾመ