በሁለት ፊልሞች ብቻ እልፍ ያሳየው ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ በጥቂት ሥራዎቻቸው፣ በዘመን ርዝማኔ የማይበጠስ ስምና ዝና ከቋጠሩ ድንቅ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተሮች መካከል አንደኛው ነው። ይድነቃቸው ሹመቴ፤ በሥራው ብቃትና በልዩ የፈጠራ ችሎታው፣ በሁለት ፊልሞቹ ብቻ እልፍ ያሳየን የጥበብ ልጅ ነው።

የሀገራችን የፊልም አፍቃሪም ቢሆን ለዘብተኛ ተመልካች ማንም “ስርየት” የተሰኘውን ፊልም ‹አላውቅም› ሊል አይችልም። ያኔ የተመለከተው ሁሉ ዛሬም ድረስ ከዓይነ ሕሊናው አይጠፋም። ስርየት የጊዜው ምርጥ ፊልም መሆኑ ብቻ አልነበረም፤ ድንገት ከተፍ ብሎ እስከእዚያ ጊዜ ድረስ በሲኒማው ውስጥ ያልተለመዱና ያልታዩ ነገሮችንም ማሳየቱ ነበር።

ታዲያ ይህንን ፊልም ዳይሬክት ያደረገው ይድነቃቸው ሹመቴ ነበር። “ኒሻን” መንደሩን ካደመቁ ምርጥ ፊልሞቻችን መካከል አንደኛው ነበር። በእዚህ ፊልም ላይ ደግሞ፤ ደራሲውም ዳይሬክተሩም ይድነቃቸው ነው። በእነዚህ ፊልሞች ላይ ከየትኛውም በበለጠ ስምና ዝናውን ከፍ አድርጎባቸዋል።

ከኒሻን ፊልም መልስ ግን ይድነቃቸው ከፊልም ኢንዱስትሪው ድንገት ዱካውን አጠፋ። ዕውቁ የፊልም ባለሙያ ዳግም የታየው ከአሥር ዓመታት በኋላ ነበር። ለእኛም እንደፍለጋ ቢቆጠርልን፤ ወደኋላ መለስ ብለን ከወደ ልጅነቱ እናስሰው። ከአራት ኪሎም ለተነሳን ከመርካቶ፣ በአባኮራን ላሳለጥንም በአብነት፤ ፍለጋ የወጣን ሁላችን፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይን ሳንጠይቅ እንዳናልፍ። ምክንያቱም እሱን ገባ ብሎ ካለው ሮዛ መንደር ውስጥ ይድነቃቸው አለና። 1973ዓ.ም በእዚሁ መንደር ውስጥ ነበር የተወለደው። መንደሯ ዙሪያዋን በጥበብ ልምላሜ የፈካች የመቅረዝ ላይ አበባ ናት። ከውስጧም ከአቅራቢያዋም የተወለዱ የጥበብ ልጆች በርካቶች ናቸው። በተለይ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ በሙዚቃና በፊልም ኢንዱስትሪ ብቅ ብለው አይረሴ ትዝታዎቹን ጭምር የጣሉብን፣ ዛሬም ድረስ አጃኢብ! ያስባሉን ከወዲህ በቅለዋል።

በልጅነት ዘመኑ ፊልም ሳይሆን ቴሌቪዥኑ ራሱ ብርቅ ድንቅ ነበር። ዕድለኛ የሆነ ልጅ ከጎረቤት ወይም ከሰፈር ዞር ዞር ብሎ ቴሌቪዥን ሊመለከት ይችላል። ፊልም ማየት ያማረው ልጅ ግን፤ ፊልም ቤት ፍለጋ ከሰፈሩ ሊወጣም ይችላል። ይሁንና ይድነቃቸው እምብዛም ርቆ አይሄድም ነበር፤ ጎረቤት ካልሆነም ዘመድ ጋር ቱር! ይላል። አብዝቶ ፊልም መመልከት የሚወድ ነውና ከመርካቶ አቅራቢያ መሆኑ በጀው።

ከታናናሾቹ አሊያም ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር እየሆነ ልቡ በፊልም ፍቅር እስክትሰምጥ ያዘወትር ነበር። ትምህርቱም አለና ይህ ተግባሩ ከእዚያ በተረፈው ጊዜ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው፣ በቀድሞው አትክልት ተራ በሚገኘው በአፍሪካ አንድነት ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ ከተማ ነበር የተከታተለው። በጊዜው ይድነቃቸው፤ ለፊልም ያለው ፍቅር የተለየ ቢሆንም፤ ልጅነቱ በስዕልም የተማረከች ነበረች። ይድነቃቸው ከቤት ውስጥ ብቻውን ከሆነ ወይም መሆን ከፈለገ ስዕል ሊስል ነው ማለት ነው። አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ፣ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ይሰጡ በነበሩ የስዕል ሥልጠናዎች ላይም ይሳተፍ ነበር። ወደ ፑሽኪን ጥበባት ጎራ ብሎም ተሰጥኦውን የሚያለመልምለትን ሌላ ሥልጠና ለማግኘት ችሏል።

ፊልም አብዝቶ ከመውደድ አልፎ ወደ አንዳች ተግባራዊ ግስጋሴ ለማቅናት ሳያስብ አልቀረም፤ የቪዲዮ ትምህርት ስለመማር አስቧልና። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነበር ወደ ዩኒቨርሳል ኦዲዮ ቪዡዋል ማሠልጠኛ ያቀናው። በእዚህም አጠቃላይ የካሜራና ካሜራ ኦፕሬሽን ተማረ። ስለ ካሜራ ለማወቅ፣ ስለፊልም ለማሰላሰል ይህም በቂ አልነበረምና ወደ ቶም ቪዲዮግራፊና ፊልም ማሠልጠኛ ገብቶ፣ ዕውቀትና ፍላጎቱን ይበልጥ አሰፋ። ይድነቃቸው የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ራሱን ማብቃት ብቻ ሳይሆን፤ የእርሱ የሆነችውን የሕይወት መንገድ በመፈለጉም የተጠመደ ይመስላል። ከፊልም ወጣ ያለ ሙያ ለመቅሰም፣ ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛም አምርቶ ነበር። በእዚያም በጀነራል መካኒካል የትምህርት ክፍል ውስጥ፣ የጠቅላላ ብረት ሥራን ለሦስት ዓመታት ተምሯል።

ወዲያም ቢል ወዲህ፤ የእርሱ ልብ ከፊልም ዓለም ለመለየት አልተቻላትም ነበርና ፊልም ቤት ከፈተ። በወቅቱ ዕድሜው 20 ደርሷል። በልጅነት ያደረበት የፊልም ፍቅር በወጣትነቱ መላ ሊያበጅለት አስቦ በ1993ዓ.ም የፊልም ቤቱን ሥራ ጀመረ። ለመንቀሳቀሻ እናቱን ጠይቆ ካገኛት ሳንቲም ጋር ካሴቶችን አሳዶ ማሰባሰቡና ግብአቶቹን ማሟላቱ ከመክፈቱ በላይ ፈታኝ ቢሆንም፤ ምኞቱን ለማሳካት ችሏል። ህልሙ ግን የፊልም ጥሙን የማርካት ሳይሆን፣ ከምንጩ የመድረስ ነበርና በጎን ሥልጠናውን አጠናክሮ ቀጥሎት ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ሲማር በነበረበት ቶም ውስጥ የማስተማር ዕድሉን አገኘ። ለተወሰነ ጊዜ በፎቶግራፍ ዘርፍ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ፣ ወደ ቪዲዮ ካሜራ መምህርነት ቀየረ። በእዚህ ቆይታው፣ ይድነቃቸው በተለምዷዊው የማስተማሪያ መስመሮች ውስጥ ብቻ መጓዝን አልወደደም ነበርና አንድ አዲስ መንገድ ለመቀየስ ጥሯል።

ተማሪዎቹ መቅረጽን ብቻ ሳይሆን፣ በአቀራረጽ ውስጥ ታሪክ ነጋሪ የምስል አወሳሰድን እንዴት መከሰት እንደሚችሉ ብዙ በማሰብ የራሱን የማስተማሪያ ረቂቅ ንድፎችን አዘጋጅቷል። ይህን ሃሳብ ወደተግባር በመለወጥ ለዓመታት አስተምሮ ብቁ የካሜራ ባለሙያዎችን ማፍራት ችሏል።

በማስተማሩ ሂደት ውስጥ ሲያደርጋቸው የነበሩ ግላዊ የፈጠራ እንቅስቃሴዎቹ፣ የዳይሬክተርነትን ጎህ የቀደዱለት ጅምሮች ሆነውለታል። በወቅቱ ከተማሪዎቹ ጋር አጫጭርና ዘጋቢ ፊልሞችን አብሮ ይሠራም ነበር። ለአብነትም በ1995ዓ.ም “የጭቃ ቀለበት” የተሰኘ ታሪክ ነጋሪ ፊልም ሠርቶ ለእይታ አብቅቷል። ከእዚህ በማስከተልም፣ “የቀለማት ፍቅር” እና “ሽልማቱ” የተሰኙ ሌሎች ሁለት አጫጭር ፊልሞችን ለማሳካት ችሏል። በትምህርት ቤቱ ቆይታው ውስጥ እኚህን ሦስት ፊልሞች በዳይሬክተርነት በመምራት ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።

የይድነቃቸው ሹመቴ የስኬት መንገዱም ሆነ በሩ ከእዚያው ከተማረበትና ከሚያስተምርበት ቤት የራቀ አይደለም። በቶም ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ላይ እያለ፣ አንድ ጊዜ ላይ የፊልም ፕሮዛል ቀርጾ ለትምህርት ቤቱ ያስገባል። ያቀረበው ንድፈ ሃሳቡም ተቀባይነትን አገኘ። ይህ ፊልምም ስርየት ነበር። ፊልሙንም ይድነቃቸው በዳይሬክተርነት እየመራው በስተመጨረሻ ባመረ መልኩ ሊጠናቀቅ ቻለ። በ1999ዓ.ም፣ በሁለት ክፍለ ዘመናት መካከል ድልድይ ሆኖ በወርሃ የካቲት ለእይታ በቃ። የ20ኛው ክፍለ ዘመን ችሮታ፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ልዩ ስጦታ ነበር። በታሪክ አወቃቀር፣ በቦታ መረጣ፣ በገጸ ባሕሪያቱ አሳሳልና የትወና ብቃት በሲኒማው ልዩነት መፍጠር ችሏል። ያለ ጎበዝ ዳይሬክተር፣ ጎበዝ ደራሲ እጀ ሰባራ መሆኑ የማይቀር ነው። ልቦለድ ቢሆን የምንፈትሸው የደራሲውን ችሎታ ነበር፤ ፊልም ሲሆን ግን ከደራሲው በላይ ምናልባትም ዳይሬክተሩ ይፈተንበታል። ምክንያቱም ደራሲው በምናብ የፈጠረውን ነገር ወደ እይታ መቀየር፣ በአዕምሮ ውስጥ የነበረን ሃሳብ እንደ ገሀድ አድርጎ ወደ ዓይን ማምጣት ነውና። በስርየት ውስጥም የደራሲው ችሎታ እንዳለ ሆኖ፤ የዳይሬክተሩ የፈጠራ ክህሎት ሁሉን ነገር እውነት አስመስሎታል። ይድነቃቸው በአዲስ ፈጠራ የመጣ እንጂ፣ እንደ አዲስ ጀማሪ ዳይሬክተር እንዳይቆጠር አድርጎታል።

ስርየት ፊልም ለይድነቃቸው የመጀመሪያው ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ ነገሩ ነው። ከእዚያ ፊልም በኋላ ዝና ብቻ ሳይሆን እልፍ በርካቶች ደጁን ጎብኝተውታል። ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ የተለያዩ ሥልጠናዎችን የመውሰድና ቁልፍ በሆኑ መድረኮች ላይ የመሳተፍ ዕድሎችን አግኝቷል። ከእነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ የፊልም ባለሙያዎች በቡርኪናፋሶ በተዘጋጀው በታሪክ ነጋሪው (ስቶሪይ ቴለር) ላይ ለሁለት ወራት ሥልጠናዎችን ወስዷል። በቆይታው ከሥልጠናው ባለፈ፣ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከመጡ የፊልም ባለሙያዎች ጋር የመገናኘትና ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን የመካፈል ዕድል አስገኝቶለታል። ከእዚያ በኋላም በኬንያና በደቡብ አፍሪካ ተገኝቶ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን ወስዷል።

ሌላኛው የድል ጀንበር ከወደ ኒሻን መስኮት አዘቅዝቃ ትታያለች። ከአራት ዓመታት በኋላ፣ በ2003ዓ.ም ሁለተኛውን የተጨበጨበለት ፊልም ይዞ ከተፍ አለ። ራሱ ደርሶ፣ ራሱ ዳይሬክት ያደረጋት “ኒሻን” የተሰኘችው ፊልሙ፣ በብዙ የፊልም አፍቃሪያን ዘንድ ተወድሳለታለች። ችሎታውን ያለጥርጥር አምነው ‹ይድነቃቸው ይችላል!› ብለውለታል። ፊልሙ በሀገር ውስጥ ከዝናና ተወዳጅነት ያለፈ ሽልማቶችንም ሰብስቧል።

ከሀገር ውጭ ፌስቲቫሎችን አድምቋል። ለአብነትም ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተሰጠውና “ቡር” በተሰኘው የአፍሪካ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ቀርቧል። በአውሮፓ፣ በብራዚል እንዲሁም በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየዞረ ለመታየትም ችሏል። በሁለቱም ፊልሞቹ፣ በተለያዩ ዓመታት በኢትዮጵያ የፊልም ቬስቲቫል ላይ አሸናፊ አድርገውታል።

በአራተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል፣ በተመረጠው የስርየት ፊልም የምርጥ አዘጋጅነቱን ክብር ተቀዳጅቷል። ከአራት ዓመታት በኋላ በሠራው ኒሻን ፊልምም እንዲሁ ያንኑ ኒሻን ለማጥለቅ ችሏል።

ዝነኝነት ከአንዳንዶች ጀርባ ድንገት እንደ ክረምት ምንጭ ቡልቅ! ፍልቅልቅ! ብሎ ከክረምቱ ቀድሞ ሲደርቅ ይታያል። እኚህን መሰሉ፣ ድንገት አንዳች ያለጊዜና ቦታ የከሰታቸውና በራሳቸው ትክክለኛ ማንነት ያልመጡ ናቸው። እናም ገና በጋው ሳይደርስ ስምና ዝናውም በፈለቁበት ክረምት ይሟጠጣል። ለአንዳንዶችም ከገባር ወንዞች የሚፈጠር ሀይቅ ነው። ክረምት ከበጋው ብዙ የሚጥሩና የሚፍጨረጨሩ፣ ግን ሁልጊዜም ተመሳሳይ ከሆነው ፍሰታቸው የተነሳ፣ ዝናቸው በአሰልቺነትም ጭምር ነው። ለጥቂቶች ደግሞ ጊዜውን እየጠበቁ የሚወርድ ራሱን ዝናብን የሚመስል ነው። እነዚህ ልክ እንደ ይድነቃቸው ሹመቴ ያሉ ናቸው። ከረዥም በጋ በኋላ እየተከሰቱ ምድር፣ ሳር ቅጠሉን የሚያለመልሙ ናቸው። ገበሬው በተስፋ የሚጠብቃቸው፣ ለጥቂት ጊዜ ዘንበው በረዥም የሚያረሰርሱ እንቁዎች ናቸው። ይድነቃቸው ሁለት ፊልሞችን ሠራ፣ በሁለቱም እስከ ጥግ ከፍ አለ። ሁለቱንም ፊልሞቹን አይተን እንደዛሬ ስናወራላቸው፣ እርሱ ግን ትናንት ላይ ወደኋላ መቅረቱን እንኳን ልብ አላልንም ነበር። ስሙ እያለ፣ ዝናውም ሳይሳሳ ከአሥር ዓመታት በፊት እግሩን ከፊልም ኢንዱስትሪው ነቅሎ ነበር። ግን ለምን?

ጀርባውን እንዲሰጥ ያስገደደው፣ በፊልም ኢንዱስትሪያችን የተንሠራፋው አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። አጃኢብ! እያስባሉን እንዲህ እልም ብሎ ለመጥፋት ይድነቃቸው የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ሰው አይደለም። ከዓመታት በፊት ቆመን ያጨበጨብንላቸውን የፊልም ደራሲና ዳይሬክተሮችን ዛሬ ላይ ብንፈልጋቸው፣ በእርግጠኝነት ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን አናገኛቸውም። ዝብርቅርቅ ባለው የፊልም ኢንዱስትሪያችን ውስጥ መቆየት መቻል እንደ ተአምር የሚቆጠር ከሆነ ውሎ ሰነባብቷል። የኢንዱስትሪው የጀርባ አጥንት እኚሁ ደራሲና ዳይሬክተሮች ቢሆኑም፤ አብዛኛዎቹ ቤሳ ቤስቲን የሌላቸው ናቸው። ፊልም ለመሥራት የሚሆን፤ ስፖንሰር ፍለጋ ለታክሲ መንቀሳቀሻ የሚቸግራቸው ጥቂቶች አይደሉም። ከእዚህ ቀደም ፊልም ሠርተው ነበር፤ ግን ገቢው ጨርቅ ማቁን ሰብስቦ የሚሄደው ወደ ፕሮዲዩሰሮቹ ነው።

የባለፈው ፊልማቸው በተመልካቹ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል፤ ግን በፊልም ቤቶችና በዩትዩብ በሕገ ወጥ መንገድ ሲቸበቸብ፣ ባለሙያው በዝምታ ዓይኑን አቁለጭልጮ ቁጭ ብሏል።

ትንሽ ሻል ያለውና የሚተነፍሱት ቦታ ሲኒማ ቤቶቹ ናቸው፤ ይሁንና ሲኒማ ገብቶ ፊልም የሚያየው ተመልካችን ቁጥር እንደምናውቀው ነው።

የደራሲና ዳይሬክተሩ ጣጣ፣ እንደተዋንያኑ ‹እዳ ገብስ› የሚባል አይደለም። ምክንያቱም ተዋናንያን የሚያስፈልጋቸው ችሎታና ሁኔታ ነው። ደራሲና ዳይሬክተሩ ግን ለቀረጻ ተጠርቶ የሚመጣ ሳይሆን፣ ፕሮዲዩሰር የሚያደርገውን የፊልሙን ባለቤት ለመፈለግና ለማግኘት የሚወጣው ግዙፍ፣ እልህ አስጨራሽ ተራራ አለበት። ቢያንስ በትንሹ የቁሳቁስ ግብአቶች የሌለው ከሆነ ደግሞ፣ ሰማይ የመቧጠጥ፣ አየር ላይ በእግር የመቅዘፍ ያህል ፈተና ነው። እኚህና መሰል ተግዳሮቶች ባለሙያውን ከኢንዱስትሪው መንበር ሲያበራዩት ኖረዋልና የይድነቃቸውም ከእነዚህ ችግሮች የራቀ አይደለም። ከአሥር ዓመታት በላይ የጠፋበት ምክንያት፣ የሲኒማው መቀዛቀዝ እንዳሰበው ለመጓዝ ባለማስቻሉ እንደሆነ ገልጾታል። ታዲያ በእነዚህ አሥር ዓመታት ይድነቃቸው ከወዴት ነበር?

ስለመጥፋቱ ስናነሳ ከፊልም ኢንዱስትሪው እንጂ፤ ከዓይን ወይም ከሀገር አይደለምና ግራና ቀኝ ማማተር የሚወደው ይድነቃቸው፤ ብዙም ባልራቀው ሌላ ዓይነት ዘርፍ ውስጥ ሰጥሞ ነበር። ራሱን ከሲኒማው ቢሸሽግም፣ ከጅምሩ አንስቶ እንደጥላው ከሚያስከትለው ካሜራ ጋር ግን የእዚህን ጊዜም አልተለያዩም። በእነዚህ ጊዜያቶች ሲሠራቸው ከነበሩ ነገሮች አንደኛው ትምህርታዊ ዘጋቢ ፊልሞች ነበሩ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ በርከት ያሉ አስተማሪ ሥራዎችን አበርክቷል። በጎን ደግሞ የማስታወቂያና ተያያዥ ሥራዎችንም ሁሉ ሲሠራ ቆይቷል። “ሰማዩ የእኛ ነው” የሚለውን ዘጋቢ ፊልምን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሀገራዊ ሥራዎችን ያበረከተው ይድነቃቸው፤ ሁሌም ጥበብን ለሀገር የማዋል ምኞትና ጥረት የሚታይበት ነው። ጥንታዊ ታሪኮችንና የባሕል እሴቶቻችንን በማውጣት፣ ሀገር በቀል ጥበባትን ለማጉላት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎቹ ምስጉን ያስብሉታል።

በግሉ ሕይወቱ ከዙሪያው ካሉት የሁለቱን ስም ሳንጠቅስ እንዳናልፈው፤ ሌላኛው የጥበብ በረከት የሆነው ያሬድ ሹመቴ የይድነቃቸው ወንድም ነውና። የመጀመሪያው የነበረው ስርየት ደግሞ ሌላም መጀመሪያ ሳትሸልመው አልቀረችም፤ በእዚሁ ፊልም ላይ የተወነችው ተዋናይት ብርቱካን በፍቃዱ ባለቤቱ ናት። በሁለተኛው ኒሻን ላይም ተውናለች። በተለይ ደግሞ “ፍቅርና ዳንስ” በተሰኘው ፊልም ላይ የነበራትን የትወና ምስል የምንረሳው አይደለም። ዘጠኝ ሞትና ዴዝዴሞናን ጨምሮ በሌሎችም ድንቅ የትወና ብቃቷን ስንመለከት ‹የማንዘር ጎመንዘር› ማለት አይቀርም።

አድናቂዎቹ ግን፤ የሚያደንቁት በፊልም ጥበብ ችሎታው ብቻ አይደለም። ከእዚያ ባልተናነሰ ስብዕናው በርካቶችን ይገዛቸዋል። ከምንም በላይ ሰውን ማገዝ፣ ለሰዎች ችግር መፍትሔ መሆን ጸጋው ነው። ጸባየ ሠናይ፣ እርጋታው ቀልብን የሚገዛ ዓይነትም ነው። ከእዚያ ሁሉ ከሲኒማው መጠፋፋት በኋላ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሚዲያው ብቅ ብሎ “አሁን ልመለስ ነው” ብሎ ነበር።

በፊልሙ ዙሪያ ያሰባቸው ነገሮች እንዳሉም ጭምር ገልጾ፤ ባልራቀ ጊዜ በአዲስ ሥራ ብቅ እንደሚል ተናግሮም ነበር። ከስርየት የደመቀ፣ ከኒሻን የገዘፈ በረከት ይዞ እንደሚመጣም ምኞታችን ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You