በኢትዮጵያ የፌስታል የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ችግር መሆናቸው ይታወቃል ። ችግሩ የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የብዙ ሀገሮችም ጭምር ነው። ፌስታል እና ፕላስቲክ አገልግለው በየቦታው ሲጣሉ አካባቢን ይበክላሉ ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት እስከ መቶ ዓመት ሳይበሰብሱ ስለሚቆዩ ለሰዎች ለእንስሳት ለእፅዋት ጠንቅ ይሆናሉ ።
ፌስታል እና ፕላስቲክ ጠርሙሶች በየቦታው የምናያቸው ቆሻሻዎች ናቸው። ሀገራችን ደግሞ ምርቶቹን ከውጪ በማስገባት ገፋችበት እንጂ እነዚህን ፕላስቲክ ጠርሙሶችና ፌስታሎች ከአገልግሎት ውጪ ሲሆኑ በዳግም ምርትነት( recycle) ለመጠቀም የሚደረግ እንቅስቃሴ አይታይም ።
ሰሞኑን ከወደ ናይጄሪያ የተሰራጨ ዜና ግን የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመጠቀም መኖሪያ ቤት መገንባት እንደሚቻል ያመላከተ ሆኗል። ይህ
ደግሞ ቆሻሻ ሀብት ነው የሚሉ የሰዎችን አባባል የሚያጠናክር ማስረጃ ነው። የናይጄሪያ ብሔራዊ ስነምህዳር ጥናትና ትንተና ማዕከል በ2025 የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በዓለም ላይ በየጠረፉ በአንድ ርምጃ 100 የፕላስቲክ ጠርሙሶች ሊገኙ እንደሚችሉ ይገመታል።
እንደ ናይጄሪያ ብሔራዊ ተፋሰስና አካባቢ ጥበቃ አስተዳደር በወንዞች ላይ የሚጣሉ ፕላስቲክ ጠርሙሶች በዓመት ወደ 100 ሺህ የሚደርሱ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ አጥቢ እንስሳትን እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወፎችንና ዓሳዎችን ይገላሉ።
በቀቢፀ ተስፋ ውስጥ የነበሩ የናይጄሪያ ሥራ አጥ ወጣቶች በተለምዶ የሃይላንድ ላስቲኮች የምንላቸውን ፕላስቲክ ውድቅዳቂዎች በዳግም ምርትነት በመጠቀም ለዕይታ የሚማርክ የፈጠራ ውጤት የሆነውን የፕላስቲክ ቤቶች ሠርተዋል። ወጣቶቹ ቤቶቹን የሠሩት ፕላስቲኮቹን በአፈር ሞልተው እንደ ጡብ በመጠቀም ሲሆን ድምቀትና ውበትን በመጨመር ቤቶቹ እንዳይሰነጣጠቁ፣ ሰዎችም እንዳይጎዱ ረጅም ዓመት እንዲያገለግሉ እርስ በእርሳቸው በገመድ እንዲያያዙ ተደርጓል።
አንዳንድ የናይጄሪያ ኤክስፐርቶች በፕላስቲክ ጠርሙሶች የተገነቡት ቤቶች ለዘለቄታው የሚቆዩና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ናቸው። በኮንክሪት ከሚገነቡት ቤቶችም እያንዳንዱ የፕላስቲክ ጠርሙስ ቤት በሲሦ ዋጋ ያነሰ ነው። በናይጄሪያ የታዳሽ ኢነርጂ ልማት ማህበር የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ኢንጅነር የሆኑት አቡጃ ሳኒ የፕላስቲክ ቤቶቹ በጣም አነስተኛ ሙቀት ስለሚሰጡ የአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያ በፍፁም አያስፈልጋቸውም ይላሉ።
በተገባደደው የፈረንጆች ሦስተኛ ሩብ ዓመት የናይጄሪያ የሥራ አጥ ምጣኔ ከ23ነጥብ 1 በመቶ በላይ ደርሶ ነበር። የናይጄሪያ ታዳሽ ኢነርጂ ልማት ማህበር ወጣቶች ሙያውን ሰልጥነው ሥራውን እንደሚፈልጉት ተስፋ ያደርጋል አብዛኞቹ ነዋሪዎች ጅምሩን በማድነቅ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን ወደ ቤቶች የመለወጥ አስፈላጊነትን በመረዳት አካባቢን ለመጠበቅ የውሃና የዱር እንስሳትን ዓሳዎችንና ወፎችን ከጉዳት ለመከላከል እንደሚረዳ ተገንዝበዋል።
በሀገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የፕላስቲክ ጠርሙሶች በውሃ ፍሳሾች ላይ እና በየብስ በየዓመቱ ሲጣሉ አካባቢን በመበከል የመሬት መሸርሸር በማስከተል መስኖዎችን በማገድ እና የጤና ጠንቅ በመፍጠር ችግሮችን ያስከትላሉ በናይጄሪያ የታዳሽ ኢነርጂ ልማት ማህበር ተመጣጣኝ ማራኪና ቤቶችን በመገንባት እንደ ጡብ ወይም ብሎኬት እየተጠቀመባቸው ነው የኛ ወጣቶችም ንቁ ለሥራ ተነቃነቁ ከምርቃና ከቃናና ምርቃና ሱሰኝነት ተላቀቁና እንዲህ ዓይነት ቤት ሠርታችሁ ባለሀብትና ባለቤት ሁኑ።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
ኃይለማርያም ወንድሙ