ለምለም መንግሥቱ
ሙሉ ነጭ የባህል ልብስ ለብሰዋል፡፡ አናታቸውን የጠመጠሙት ጥቁር በነጭ የተሰራ የሀገር ባህል ልብስ ውጤት ነው፡፡ በእጃቸውም አለንጋ ይዘዋል። ተክለሰውነታቸው ከአለባበስና አጋጌጣቸው ግርማ ሞገስ ሰጥቷቸዋል። ስምንት ዓመት የአባገዳ የሥልጣን ዘመናቸውን ጨርሰው ከኃላፊነታቸው እስኪወርዱ እንዲህ አምረው ነው የተጣላ በማስታረቅ ፍትህ የሚሰጡት፣ የሚመርቁትና ለሀገር ሰላም ፈጣሪያቸውን የሚማጸኑት። ይህን ሥርአት ሲያከናውኑም በእጃቸው እርጥብ ሳር ይይዛሉ፡፡
ሁሉም ትርጓሜ አለው፡፡ አለንጋውም ሆነ እርጥብ ሳር ይዘው ሲያስታርቁ እሺ ያለው ይመረቅበታል። ሽምግልናውን አልቀበልም ብሎ ያፈነገጠው ደግሞ ይረገምበታል፡፡ መንግሥት ለተለያዩ ነገሮች አዋጅ እንደሚያወጣው ሁሉ አባገዳዎችም አለንጋቸውን ይዘው በተመሳሳይ አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበትን ደንብ ያወጣሉ፡፡ የሚይዙት እርጥብ ሳርም ጫፉ ያልተቆረጠ፣ ከብት ያልነካው መሆን አለበት።
የአባገዳ መለያ የሆነውን አልባሳት ይህን ዓይነት ሹመት የሌለው ሰው አይለብስም፡፡ ለብሶ የተገኘ ይወቀሳል፤ እንደ አታላይም ይቆጠራል፡፡ አባገዳዎች የሚለብሱት ከሌሎች የባህል ልብሶች ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም በአለባበስ ሥርአቱ ይለያል፡፡
እንዲህ ባለው የአለባበስ ሥርአት በኦሮሚያ አካባቢ ስለሚሰጠው ማህበራዊ አገልግሎት ያጫወቱኝ አባ ገዳ ሲሳይ ታደሰ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ሊበን ጩቃላ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በአካባቢያቸው የተጣላን በማስታረቅ፣ የተበደለ እንዲካስ በማድረግ፣ ለሀገራቸውና አካባቢያቸው ሰላም በመመኘትና ጥሩ የሰራውን በመመረቅ ሌት ተቀን እየተጉ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ ይሄን የሚያደርጉት በዕድሜ ጠና ያሉ ስለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በኦሮሞ ባህላዊ የገዳ ሥርአት ውስጥ ተመርጠው ኃላፊነት ሥለተሰጣቸው ነው፡፡
ባሉበት አካባቢ ቱለማ ተብሎ በሚጠራው ውስጥ አባ ሴራ ሆነው ነው የሚያገለግሉት፡፡ አባላቱ ዘጠኝ ሲሆኑ የሥልጣን ተዋረዱም አባገዳ፣ አባሴራ፣ አባአለንጋ የሚል የስልጣን ክፍፍል አለው፡፡ በሥልጣን ክፍፍሉ መሠረትም የሴቶችን፣ የህፃናትንና የተለያዩ ጉዳዮችን በማየት ሥልጣንና ተግባራቸውን ይወጣሉ፡፡ አባገዳ ሲሳይ ከተመረጡ አራተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ የሥልጣን ጊዜያቸው የሚያበቃው ከአራት ዓመት በኋላ ነው፡፡
ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት ግዴታ አለበት የሚሉት አባገዳ ሲሳይ ስለሚጠበቅባቸው ተግባር እንዳስረዱት ሽምግልና ሲያዝ በአንድ ወገን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እስከ ቤተሰብ የሚዘልቅ በመሆኑ የሽምግልና ዕርቅ ሥርአቱ ቤተሰብንም ያካትታል፡፡ ይሄ የሚሆነው በተጎጂውና በጎጂው ቤተሰብ መካከል ቂምና ቁርሾ እንዳይኖር ነው፡፡ በደሉን እንዲተውት ማድረግ ካልተቻለ ለተጨማሪ ጥቃት ይነሳሳሉ፡፡ በመሆኑም እጁ ወይንም እግሩ የተቆረጠ፣ ዓይኑ የጠፋ፣ ጥርሱ የተሰበረ፣ የሞት አደጋ እኩል አይዳኝም፡፡
የሚሰጠው ፍርድና ለተጎጂው የሚገባው ካሳ እንደጉዳቱ አይነት ይወሰናል፡፡ በሽምግልና እርቁን አልቀበልም ያለ ወገን ከአካባቢው ማህበራዊ አገልግሎት እንዲገለልና ከዕድርም እንዲወጣ ይወሰንበታል፡፡ እርሱም የሚደርስበት ተጽዕኖ የከፋ እንደሆነ ስለሚገነዘብ ዕርቁን አልቀበልም ለማለት አይደፍርም፡፡ ፀቡ እስከመገዳደል የደረሰ ቢሆን እንኳን ሰው የሞተበትን መካስ ከባድ ቢሆንም የአባገዳዎችን ትዕዛዝ የማይፈጽም እና የሚያፈነግጥ አይኖርም።
የተበዳይና በዳይ አቤቱታ በሚገባ ታይቶ ሲጠናቀቅ ዕርድ ታርዶ የጎጂና ተጎጂ ቤተሰቦች አብረው እንዲበሉ በማድረግ ነው በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት የደረሰው ጉዳት መፍትሄ የሚያገኘው፡፡ አብረው ማዕድ ከተቋደሱ ይቅርታው ሰምሯል፤ በመካከላቸውም ቂም እንዳይኖር ተስማምተዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ምግቡና መጠጡ ማሳረጊያ ይሆናል፡፡
አባገዳ ሲሳይ ሰው ገድሎ የሚጠፋ እንደሌለ በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡ ለጊዜው ቢሸሽ እንኳን ቤተሰቡ ፈልጎ እጁን እንዲሰጥ ማድረግ አለበት፡፡ ቤተሰቦችም በፍርሃት ከሀገር እንዳይወጡና የታዘዙትንም እንዲፈጽሙ አባገዳዎች ግፊት ያደርጋሉ፡፡
አባገዳዎች እንዲህ በየስምንት ዓመቱ እየተፈራረቁ በየአካባቢያቸው ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታት ፍትህና ሰላም ሲያሰፍኑ የወር ደመወዝም ሆነ የዓመት ቀለብ የሚሰፍርላቸው፣ የሚያለብሳቸው የለም፤ እነርሱም አይጠብቁም፡፡ በፍላጎታቸው ነው ህዝባቸውን የሚያገለግሉት፡፡ እንደ ጥቅም ከታየ የያዙት ሽምግልና ሰምሮ በዳይና ተበዳይ ስምምነት ፈጥረው አንድ ላይ መአድ ለመቋደስ ወስነው ሲያዘጋጁ ስለሚጋበዙ ይታደማሉ፡፡
ሽምግልናው ራቅ ወዳለ ቦታ ሲሆንና መጓጓዣ ካስፈለገ ሽምግልና የተያዘላቸው ሰዎች ወጭያቸውን ይሸፍናል። ከዚህ ውጭ ፍርድ ለመስጠት የያዙቱ አለንጋ ህዝብን በንጹህ ልቦና ያለጥቅም እንዲያገለግሉ የተሰጣቸው በመሆኑ ልባቸውን ለንዋይ አይከፍቱም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው እንረገማለን ብለው ያስባሉ፡፡ ከተበዳይም ከበዳይም ጥቅም ማግኘት ሀጢያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በሚያገለግሉት ማህበረሰብ ውስጥ ስላላቸው ከበሬታም አባገዳ ሲሳይ እንዳጫወቱኝ ማህበረሰቡ ከልጅነቱ ጀምሮ የአባገዳን ሥልጣንና ኃላፊነት ስለሚያውቅ ከፍ ያለ ከበሬታ ይሰጣቸዋል፡፡ አባገዳዎች በአለባበሳቸውም ስለሚታወቁ ያንን በማየት ብቻ ከመጥፎ ድርጊቱ የሚታቀብና የሚታዘዝ ማህበረሰብ እንደሆነ ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የማህበራዊ ሀብት ግንባታ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፋንታሞ ፋካና የሀገር በቀል ፍትህ የማሥፈኛ ሥርአቶች ዘርፈብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ሙያዊ ሀሳብ አካፍለውናል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የዕርቅ ወይንም የፍትህ ሥርአት በሁለት ወገኖች መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረግ ጥረት ሲሆን የፍትህ ሥርአት ግን ከሽምግልናው ከፍ ባለ ሁኔታ ነው የሚከናወነው፡፡
የፍትህ ሥርአት ከዘመናዊው የህግ ሥርአት ጋር ይያያዛል፡፡ የሀገር በቀል የእርቅም ሆነ የፍትህ ሥርአት እውነትን መሠረት ያደረገና ለሁሉም ተገልጋይ ክፍትና አሳታፊ ነው፡፡ የይቅርባይነት ባህሪም አለው፡፡ ለሚያሳልፏቸው ውሳኔዎችም ሆነ ለሚያደርጓቸው ድርድሮች ተጠያቂነትን በማስቀመጥ ነው ኃላፊነታቸውን የሚወጡት፡፡ ውሳኔያቸው ከማሥፈራራት ይልቅ ማሳመን ላይ ያተኩራል፡፡
በዳይና ተበዳይ ተማምነው ውሳኔያቸውን እንዲቀበሉ ነው የሚያደርጉት፡፡ በሥብዕናቸው በማህበረሰቡ የተፈሩ አይደሉም፤ ይከበራሉ፡፡ በሚሰጡት ፍትህም አሸናፊ እንዲኖር ሳይሆን በዳይም፣ ተበዳይም ሦስተኛው ወገንም የጋራ አሸናፊ እንዲሆኑ ነው የሚያደርጉት፡፡ ሥራቸው በአደባባይ ስለሚከናወን ጥርጣሬ ካለመፍጠሩም በላይ ግልጽ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ተቀባይነትና ከበሬታ አላቸው፡፡
ወጪ ቆጣቢና ተደራሽ መሆናቸውም ያስወድዳቸዋል አልፎ ተርፎም የህዝብ ውክልና አላቸው። አካባቢያቸውን ወክለው በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ነቀፌታ አይገጥማቸውም፡፡ መንግሥት በሚኖረው የተለያየ መድረክ ላይ በመገኘትም የውክልና ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፤ ይመክራሉ፣ ይመርቃሉ፡፡
ስለሥራ መዋቅሮቻቸው ወይንም ተቋማዊ አደረጃጀታቸው ባለሙያው እንዳስረዱት፣ የተጻፉም ይሁን ያልተጻፉ የፍትህና የዕርቅ መዋቅሮች አሏቸው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በዕድሜ ከፍ ያለ፣ የተለየ ሥብዕና ያለው፣ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ በማየትና በመፍታት ችሎታ ያለውን ሁሉ መሠረት ባደረገ ባህላዊ አሰራር የተከተለ ሥርአት አላቸው፡፡
እንደ ሀገር በማህበረሰብ ውስጥ መተማመን እንዲፈጠር፣ አንዱ ለሌላው አጋዥ እንዲሆን፣ እንዲሁም አንዱ የሌላውን መሠረታዊ እሴቶች እንዲገነዘብ፣ አብሮነትን እንዲያጠነክር፣ በአጠቃላይ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያዊ ሥርአትን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ጥሩ መሠረትና ማሳያ ናቸው፡፡
የማህበረሰብ መሪዎች ወይንም አገልጋዮች ከፍተኛ አስተውሎት እና ሞራል የሚባለው ሥብዕና ያላቸው፣ ከራሳቸው ይልቅ ህዝብን የማስቀደም፣ ታማኝ መሆን፣ ህዝብ እንዲርቃቸው ሳይሆን እንዲቀርባቸው ማድረግ የመሪዎቹ ሥነባህሪ መገለጫዎች እንደሆኑ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ መሪዎቹ ከመንግሥት ተቋማት ጋርም ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ከመንግሥት አደረጃጀቶች ጋር በመሆን ማህበረሰብን ለልማትና ለበጎ ነገር በማነሳሳት አብሮነትን የማጎልበት ሚና ይወጣሉ፡፡ የሚሠሩት ሥራ ከመንግሥት ስትራቴጅና ፍትህ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ በመሆኑ በመንግሥት መዋቅር ከተደራጁ የማህበራዊ ፍትህ ተቋማት ጋር እንዲሰሩ በማድረግ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የሚሄዱ ጉዳዮች በማስቀረት ጫና ለመቀነስ ተችሏል፡፡ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርአቶች ከዘመናዊው ፍርድ ቤት የፍትህ አሰጣጥ እውነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል። ፍርዱ እውነተኛ መሆኑም ተመልሶ የማገርሸት ባህሪ የለውም፡፡
ባለሙያው የሌላውን ዓለም አሠራር አማራጮችን ለመቃኘት ከመሞከር ማህበረሰብን ለዘመናት እያስተሳሰረ፣ እያግባባና አብሮነትን እያጎለበተ እስካሁን የዘለቀውን መልካም እሴት ሀገር በቀሉን መፈተሽ ይገባል ይላሉ፡፡ እነዚህ መልካም የሆኑ ባህላዊ የማህበረሰብ እሴቶች ተሰንደው ለትውልድ እንዲተላለፉ፣ አንዱ ከሌላው መልካም ተሞክሮ እንዲቀስም፣ ከሀገርም ባለፈ ዓለም እንዲያውቀው እና ለቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ገቢ እንዲያስገኝ ሰላም ሚኒስቴር እየሰራ ይገኛል፡፡ ሥራው ሰላም እሴትና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ተብሎ በተደራጀ በሚኒስትር ዴኤታ እየተመራ የሚከናወን ሲሆን አቶ ፋንታሞ በዚህ ክፍል ውስጥ የማህበራዊ ሀብት ግንባታ ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ነው የሚሰሩት፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚተገበሩና እንደ ሀገር በብሔራዊ መግባባት ላይ ለሚሰራው ሥራ አዎንታዊ ሚና ያላቸውን ሀገር በቀል የእርቅ፣ ፍትህና አሥተዳደራዊ ሥርአቶችን በማሰባሰብ ተመልሶ ለማህበረሰቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በጥናት እየለየ ይገኛል፡፡
ባለሙያው እንደተናገሩት ዕምቅ ማህበራዊ ሀብቶች ተብለው እንደሀገር የተያዙት እየተሸረሸሩ ሥለመሄዳቸውና የነበረውን ይዘው መቀጠላቸውን፣ ማህበረሰቡ ምን ያህል እየተጠቀመባቸው እንደሆነ እና ሌሎችም መታየት ያለባቸው ነገሮች ካሉ የመለየት ሥራ ነው በጥናቱ የተካተተው፡፡ ሥራዎች ከተለዩ በኋላ ደግሞ የአሰራር ሥርአት ለመዘርጋት የማህበራዊ ሀብት ግንባታ አሠራር ሥርአት እየተዘጋጀ ነው፡፡ ሥራዎች ሲጠናቀቁ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፀድቆ ይፋ ይሆናል፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጀመረው ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ የመጨረሻው ግብ ምን እንደሆነ ባለሙያው ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በአንዱ አካባቢ የሚተገበር፣ በሌላው ግን የማይታወቀውን በጋራ በመሰነድ ሀገራዊ እሴቶች እንዲሆኑ የማድረግ፣ ጥቅሙና አስፈላጊነቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ጎልብቶ ተጠቃሚነቱ እንዲያድግ ነው፡፡
ማህበራዊ መሥተጋብሮችና ብሔራዊ እንዲሁም የእርስ በርስ መግባባቶችን ለማጎልበትና ለማሥረጽ፣ እውቅናም የመሥጠት ዓላማ አለው፡፡ ባለሙያው የራሳቸውንም ተሞክሮ አብነት አድርገው እንደተናገሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከተማን በሥራ አጋጣሚ እስኪያዩ ዘመናዊውን የፍትህ ሥርአት አያውቁም ህግ አስከባሪውን ፖሊስም ያዩት ከተማ ሲገቡ ነው፡፡
እርሳቸው በተወለዱበት ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖው ህዝብ የሚያውቀውም የሚዳኘውም በሀገር በቀሉ የፍትህ ሥርአት ነው፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ ማህበረሰቡን በማነጽ ለጥሩ ነገር ያበቃውና ግጭትን ቀድሞ በመከላከል ማህበረሰቡን በመጠበቅ ኃላፊነቱን የሚወጣውን ይህን መልካም የሆነ እሴት ለትውልድ እየተላለፈ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባና ሚኒስቴር መሥሪያቤታቸውም ይህንኑ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተጀመረው ሥራ ይበል የሚባል ነው፡፡ ግን የተሰነደው ሰነድ ማህበረሰቡ ጋር በአግባቡ ደርሶ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ጎን ለጎን መሥራት ይጠበቃል፡፡ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡ በሰላም ሚኒሥቴር የተሰጠው ትኩረት ባህላዊው የሽምግልናና የፍትህ ሥርአት ዘመን ተሻጋሪነቱን አንዱ ማሳያ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013