ጽጌረዳ ጫንያለው
አቶ ደጀኔ ጥሩነህ ይባላሉ። ከ47 ዓመታት በላይ በአውቶሞቲቭ መስክ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ላይ አገልግለዋል። በተለይ በራሳቸው አቅም ተምረውና እውቀት ቀስመው ጥሩ ደረጃ ላይ ቢደርሱም ‹‹ያለኝን ለአገሬ ልጆች›› ማለታቸውን አልዘነጉም። እናም ወደ አገር ቤት የተመለሱትም ይህንን ያካበቱትን ልምድና የተማሩትን ትምህርት ለማካፈል ነው።
ይህን በማድረጋቸው ደግሞ በርካታ ተማሪዎችን ከማፍራት ባለፈ የራሳቸውን ጋራዥ እንዲከፍቱ አስችሏቸዋል። በተለይም በተግባረዕድ የሚማሩ የማታ ተማሪዎችን በማስተማርና እውቀታቸውን በማካፈል ኃላፊነታቸውን ስለተወጡ እጅጉን መደሰታቸውን አጫውተውናል።
ዛሬም ቢሆን እንደመንግሥት እገዛና ድጋፍ ባይደረግላቸውም በዘርፉ የሚማሩ ተማሪዎችን ከማገዝ ወደኋላ አላሉም። አንተ ጋር መሰልጠን እንፈልጋለን ያሏቸውን ሁሉ ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኛ ናቸው። ከዚያም አለፍ ብለው በተለይ በሙያ መስኩ ዙሪያ መንግሥት ማድረግ ያለበትን ነገር በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩም ስለመሆናቸው ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል።
አሁን በተለያዩ ምክንያቶች በዚህ ለመቆየት አልቻሉምና ወደነበሩበት ካናዳ ለመሄድ ተነሱ እንጂ ይህ ልምዳቸው እንደሚቀጥል ያምናሉ። ምቹ ሁኔታ የማገኝ ከሆነ ለአገሬ ልጆች የማጋራው ብዙ ልምድ አለኝም ብለውናል። እኛም እውቀታቸውን የሚያጋሩበት ዕድል ቢሰጣቸው እያልን ህይወታቸው ብዙ ተሞክሮን የያዘ በመሆኑ ለዛሬ ‹‹የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና ተማሩባቸው አልን።
ትንሹ የትራክተር ሹፌር
ተወልደው ያደጉት በወዶገነት ልዩ ስፍራው አበዬ ቡሳ ሚካኤል ሲሆን፤ እስከ 14 ዓመታቸው ድረስ በዚያ ቆይተዋል። ስለዚህም በዚህ ስፍራ ቦርቀዋል፤ ብዙ ዓይነት ጨዋታም ተጫውተዋል። የተለያዩ የሥራ ዓይነቶችንም የሞከሩባትና ልዩ የሥራ ልምድን የቀሰሙባት ስፍራም እንደሆነች አጫውተውናል። እንደውም በዚህ ስፍራ እርሳቸውም ሆኑ ቤተሰባቸው ህይወትን አጣጥመን ኖረናል የሚሉበት ጊዜ እንዳሳለፉ ይናገራሉ።
ምክንያቱም አባታቸው አርሶአደር ሲሆኑ፤ ብዙ ከብቶችም አሏቸው።ከዚያ በተጨማሪ የማይሞክሩት የሥራ ዓይነት የለምና በመልጌ ወንዶ የቲማቲም ድልህ ፋብሪካ ሠራተኛም ነበሩ። ይህ ደግሞ ለታዳጊው ደጀኔ ብዙ ዕድሎችን ያጎናጸፈ ነበር። መብል መጠጡ ብቻ ሳይሆን የዘመኑን ቴክኖሎጂ የማወቅ ዕድሉንም የሰጣቸው ነበር። በተለይም በዚህ የሥራ ቦታ በዕረፍት ጊዜያቸው የማይሞክሩት ሥራ አልነበረም። ከዚያም ውጪ ቢሆን መሥራትን ከአባታቸው ለምደዋልና ከብት ማገዱ ላይም ያግዛሉ።
በባህሪያቸው ፈጣንና ያዩትን ማድረግ የሚቀናቸው ሲሆኑ፤ አዕምሯቸውን ወደ ትምህርትና ሥራ ማድረግ ይቀናቸዋል። በተለይ በብየዳና አናጺነት እንዲሁም በመካኒክነት ሥራ ማንም እንዲበልጣቸውም አይፈልጉም። የፈጠራ ሙያቸውም ላቅ ያለ ነው። ስለዚህም የጨዋታ ጊዜያቸውን በመቀነስ እነዚህን ሥራዎች ወደመልመዱ ያተኩሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁንና በትምህርት ውስጥ ግን ጨዋታ ወዳድና በተለይ በእግርኳስ ጨዋታ ማንም የማያክላቸው ናቸው።
ብዙ ጊዜ መሆን የሚፈልጉት ጎበዝ ተማሪና በኑሯቸው የተሻለ ሰው መሆን ነው። ስለዚህም የካናዳ ሚሲዮናዊያን በአካባቢያቸው ስለሚኖሩ ስለካናዳ መልካሙን ሁሉ ይነግሯቸዋልና ካናዳ መሄድ የልጅነት ህልማቸው ሆነ። እንዳሰቡትም ህልማቸውን ከአደጉ በኋላ አሳኩት።
ትምህርትን ከአዲስ አበባ እስከ ካናዳ
መጀመሪያ ትምህርትን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት በእግራቸው እየተጓዙ ዘመድ ጋር ሆነው በሻሸመኔ አጼ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረውበታል። ከዚያ አባታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያሟሉላቸው ነበርና ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንዲማሩ ሆኑ። ልደታ ቤተክርስቲያን አጠገብ በሚኖሩት የወንድማቸው ልጅ ጋርም በአደራ መልኩ ሰጥተዋቸው ነው።
በዚህም በእግራቸው ከልደታ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተመላለሱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማሩ። ከዚያ ሚኒስትሪ እንደወሰዱ ሆለታ ኢትዮ ጀርመን ኮሌጅ በኋላ ጀነራል ሙሉጌታ የሚባው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ገቡ። ከአስር ወር ትምህርት በኋላ ግን ወታደር ቤት ነው የምታገለግሉት በመባላቸው ትምህርቱን አቋርጠውታል። ግን መማር የት እንደሚያደርሳቸው ያውቃሉና ዳግም በማታ ተግባረዕድ ለመማር ተመዘገቡ።
ሦስት ዓመታት ተምረው ለማጠናቀቅ ጥቂት ወራት ሲቀራቸውም ቀይሽብርን የመሰሉ ችግሮች በአገሪቱ ውስጥ በመፈጠራቸው ትምህርቱን ትተው ስደትን መረጡ። ከትምህርቱ ጋርም ዳግም የተገናኙት ካናዳ ከገቡ በኋላ ነው።
በካናዳዊያን ዘንድ አንድ ትምህርት ቤት ለመቀላቀል ይማር የሚል ደብዳቤ ያስፈልጋል።እናም እንግዳችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሠሩበት የነበረውን መረጃና የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ መማር የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለማግኘት ወደ ‹‹ሚኒስትሪ ኦፍ ስኪልስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት›› የሚባል የአገሪቱ ፈቃድ ሰጪ ተቋም አመሩ። መማር እንደሚችሉም ተነገራቸው።
ይህም ቢሆን በቀጥታ ለትምህርት አያበቃምና የመግቢያ ፈተና ለመውሰድ ይዘጋጁ ጀመር። ግን ባለቤታቸውን ትቶ መሄድ። የገንዘብና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች በተደጋጋሚ ፈተናዎቹን ቢወስዱም ማለፍ እንዳይችሉ አደረጓቸው። ነገር ግን ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንዲሉ ሆነና አንድ ሰሜን አፍሪካዊ ኃላፊ የሆነበት የቮልስዋገን አሻሻጭ አገኙ።
ትቀጥረኛለህ ወይ ለማለት ሄደው በተደጋጋሚ መውደቃቸውን ሲነግሩት በሁኔታው እርሳቸውም ተፈትነውበት ስለነበር ያውቁታልና የሚማሩበትን ዕድልም አመቻቹላቸው። የሚከፍሉትን 450 ዶላር ሲቀጠሩ እንደሚመልሱም ቃል አስገብቷቸው ሰጥቷቸው ትምህርት ተጀመረ።
በካናዳዊያን ህግ ሳይሰለጥኑ መሥራት አይፈቀድምና እንዲሰለጥኑ ዕድሉን የሰጧቸው ቀጣሪያቸው ማይክ የሚባሉ ሰው ሲሆኑ፤ ስልጠናው ምን ያህል አቅማቸውን እንደገነባላቸው ሲረዱም ነው ወዲያው በማታ ተመዝግበው በአንድ አፍሪካዊ አማካኝነት መማር የቻሉት።ግን አሁንም ብዙ የሚፈትኗቸው ነገሮች ገጠሟቸው። ለአብነት ትምህርቱን በቀን ካልሆነ በማታ አለመማር መቻላቸው አንዱ ነው። እናም ባለቤቱን ስለሁኔታው አስረድተው በቀን እንዲማሩ ሆኑ።
‹‹ሴንቴኒያን ኮሌጅ››ንም ተቀላቀሉ። ለአምስት ዓመት ያህል ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ፈተና ከባድ ነበረ። የሚያገኙት ገንዘብም ቢሆን አይደለም ቤተሰብ ለመምራት ለራሳቸውም አይበቃም። ስለዚህም ጠዋት ማታ ረጅም ርቀት በዚያ በበረዶ ላይ በእግራቸው መሄድን ግዴታ ጥሎባቸው እንደነበር አይረሱትም። ቤት ሲገቡ ደግሞ ቤተሰቡ ተኝቶ ስለሚያገኙት ላለመቀስቀስ ሲሉ መኮሮኒ ያለ ስጎ ጨው ነስንሰው ይመገቡ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ግን ላይችል አይሰጥም ነውና ነገሩ መወጣት ችለዋል። በእርግጥ በዚህ ህይወት ውስጥ እያሉ በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት እንዲያመጡ ሆነዋል። ግን ኃላፊዋ ዕድል ሰጠቻቸውና ቀጠሉ።ማለፊያ ውጤትም አመጡ። በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ እየተሻሻሉ የደረጃ ተማሪም ሆነው ነው በአውቶመካኒክ የትምህርት መስክ ሰርተፍኬታቸውን ለመያዝ የበቁት።
‹‹የዚህ የትምህርት ጉዞ ብዙ ሰው እጁ ያለበት ነው። ከእነዚህ መካከል የሚያሠራኝ ሚስተር ማይክ አንዱ ሲሆን፤ አንዳንድ ነገሮችን ያግዘኝ ነበር።›› ይላሉ። በሻሸመኔም ሆነ በአዲስ አበባ በነበራቸው የትምህርት ቆይታ በጣም የሚገርማቸውና አሁንም ቢሆን የሚመኙት ለትምህርት ያለውን ፍቅር ነው።
ተማሪውም ሆነ መንግሥት ልዩ ትኩረት ይሰጠውም ነበር። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ተማሪው ረጅም መንገድ በእግሩ ተጉዞ ሲማር ምንም አይሰማውም። በተመሳሳይ መንግሥት ከምግብ ባለፈ ቦኩራ የሚባለውን የታሸገ ወተትና ክፍል ውስጥ ደግሞ በጆግ ሙሉ ወተት እየሰጠ ነበር የሚያስተምረው። እናም ዛሬ ድረስ የድሮ ተማሪ እየተባለ የሚጠቀሰው የተሻለ ሆኖ ስለተማረ እንደሆነ ያነሳሉ።
በትምህርት ዙሪያ በኮሌጅ ደረጃ ከተመረቁት ውጪ አልወሰዱም። ሆኖም እንደ ካናዳ በአሉ አገራት በዓመት ሦስት ጊዜ በሚሰጠው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ስልጠናዎች ላይ ተሳትፈው የተሻለ እውቀት አግኝተዋል፤ አቅማቸውንም አጎልብተዋል። ልምዳቸውም ቢሆን ሌላው ትምህርት ቤታቸው ሆኖ አልፏል።
ሥራን በልጅነት
የሥራ “ሀ–ሁ–“ን የጀመሩት አባታቸው በሚሠሩበት በመልኬ ወንዶ የቲማቲም ድልህ ፋብሪካ ውስጥ ሲሆን፤ ክረምት ሲመጣ የዕረፍት ጊዜ ስለሆነ በዚያ ወቅት በወር ሰባት ብር ከ50 ሳንቲም ይከፈላቸው ነበር። በዚህ ቦታ ከብየዳ እስከ ትራክተር ማረስ የሚደርሱ ሥራዎችን ገና ጉልበታቸው ሳይጠና መሥራት ጀምረዋል። እንደውም በ14 ዓመታቸው ትራክተሩን ይዘው መሬቱን ያገላብጡት ነበር። ለያውም እግራቸው ፍሬኑ ጋር ስለማይደርስ በሥራው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ መርገጫ በእንጨት ሠርተውላቸው ነበር ሲያርሱ የቆዩት።
በዚህ መስሪያ ቤት ቲማቲምና መሰል ፍራፍሬዎችን አሽገው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡም ናቸው። ለዚህ ደግሞ መሰረታቸው አባታቸው ብቻ ሳይሆኑ በወቅቱ አሠሪ የነበሩት ጣሊያኖች ናቸው። ከኢትዮጵያኑ በሚበልጥ ሁኔታ በተቋሙ ውስጥ በኃላፊነትም ሆነ በሥራው ላይ ይገኛሉ። ኑሯቸውንም በዚያው ግቢ ያደረጉ በርካታ ናቸው። ስለዚህም ከእነርሱ ሥራ ብቻ ሳይሆን ባህላቸውን።
ቋንቋቸውን እንደለመዱ እንደውም እኔ ብቻ ሳልሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ጭምር ከአማርኛ። ከኦሮምኛና ሲዳምኛ በበለጠ ጣሊያንኛ መናገርና መስማት እንዲችሉ ሆነዋል ይላሉ። አሁንም ድረስ የሚናገሩ አዛውንቶች እንዳሉም አጫውተውናል።
ከቤተሰብ ተነጥለው በሥራ ህይወት ውስጥ የገቡት ደግሞ አዲስ አበባ ሲመጡ ሲሆን፤ በ ‹‹ ሰፈሪያን ኩባንያ ወይም ቮልስዋገን›› ውስጥ ሲሆን፤ ከዚያ ወጥተው ደግሞ ሚቸልኮትስ ጋራዥ ውስጥ በእግር ኳሱም እየተሳተፉ ለመሥራት ገቡ።ግን እግር ኳሱ በጀት ስለሌለው የተሻለ ደሞዝ ማግኘት አልቻሉምና ሥራውን ትተው በጀርመኖች የሚተዳደርው አውሮፓ ሞተርስ ኩባንያ ውስጥ በመካኒክነት ተቀጠሩ።
ጥሩ ክፍያም እያገኙ መሥራታቸውን ቀጠሉ። ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የሚያስችላቸው ሁኔታ ገጠማቸው። ይህም በቀይ ሽብር ጊዜ አንበሳ አውቶቡስ ውስጥ ተቀጥረው እየሠሩ ሳለ በአውቶቡሱ ውስጥ ሆነው ክንፈ የሚባል ካድሬ ተገደለ። በቦታው ላይ ስለነበሩም ገዳይ ተብለው ታፍሰው ታሰሩ።
‹‹በጊዜው መሞቱን እንጂ ገዳዩን አላየሁትም።›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ በወቅቱ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ተሳትፈው ባያውቁም እውነተኛና ፊት ተናጋሪ በመሆናቸው ይጠረጥሯቸው ስለነበር እንዳሰሯቸውም ይገምታሉ። በዚህም ‹‹ገዳይ ነህ›› በሚል ለስምንት ወር ያህል ማረሚያ ቤት አቆዩዋቸው።
ገዳዩ ተገኘ ሲባልም ፈቷቸው። ይህ ነገር ያበሳጫቸው አቶ ደጀኔ በአገራቸው ምቾት እየተሰማቸው አለመሆኑና የዕድሜ እኩዮቻቸው የሚደርስባቸው ስቃይ ስጋት ውስጥ ስላስገባቸው ከአገር ውጪ መሄድን አሳሰባቸው። በተለይም ጓደኞቻቸው እዚያ የተሻለ ዕድል እንዳለ ሲነግሯቸው የበለጠ ልባቸው ተነሳሳ። በኬኒያ በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባትም ጉዞ ጀመሩ።
ኬኒያ ሲደርሱ እንደሌላው ስደተኛ ችግር አልገጠማቸውም። ተቀባይ የአጎታቸውን ልጅ አገኙ። ስለዚህም ባለቤቷ ጋራዥ ነበረውና በሙያቸው የሚሠሩበትን ዕድል አመቻቸላቸው። በዚያም ለዓመት ያህል እንደሠሩ ያነሳሉ።ግን የመጡበትም ጉዳይ ያሳስባቸዋልና ክትትላቸውን አልተውም። በዚህም አሜሪካ ለመግባት ያለውን የስደተኞች ሰልፍ ሲያዩ ሃሳባቸውን ወደ ካናዳ ቀየሩት። ምክንያቱም ከአሜሪካ ካናዳ እንደምትበልጥ በልጅነታቸው ይሰሙ ነበርና።
እናም ሰዎችን ጠይቀው ወደ ካናዳ ኤምባሲ አመሩ። ከዚያ በፊት ግን እንግሊዝኛቸው ፈቃዱን ሊያሰጣቸው እንደማይችል ስለፈሩ በአንድ ኬኒያዊ አማካኝነት ተስተካክሎ ተጽፎላቸው ወደ ቦታው አቀኑ። ማመልከቻውን ሲሰጡ ለምን ካናዳን እንደመረጡ ተጠየቁ። መልሳቸውም በልጅነታቸው የተነገራቸውን ነገሯቸው። ወዲያውም ምንም ዓይነት ቃለ መጠየቅ ሳይደረግላቸው ‹‹ተቀብለንሀል›› ተባሉ። ሚስትና ልጆቻቸውን ጨምረውም ጉዞ ወደ ካናዳ አደረጉ።
ወደ ካናዳ እንደገቡ ሥራ አላገኙም።ከ20 ቀን በኋላ ነው ሙያው ተፈላጊ ነበርና ባልና ሚስት ፊሊፒኖች የሚያስተዳድሩት ጋራዥ ውስጥ በዘይት ቀያሪነት የተቀጠሩት። ባልዬው ሚስተር ማይክ የሚባል ሲሆን፤ ለሳምንታት ያህል ስልጠና እንዲወስዱም ካደረጋቸው በኋላ ነው ወደ ሥራ ያሰማራቸው።
በዚህም ለሁለት ዓመት ያህል በቦታው አገልግለዋል። ከዚያም በኋላ ቢሆን ትምህርት ቢገድባቸውም ቅዳሜና ዕሁድ እንዲሁም ማታ ላይ እየሠሩ ነበር የቆዩት። ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁም ሰውዬው ባለውለታቸው ስለሆነ በመጀመሪያ ክፍያቸው ለዓመት ያህል አገልግለዋል።
በእርግጥ በወቅቱ እርሱ ‹‹ለአንተ የሚሆን ክፍያ የለኝም›› ብሏቸዋል። እርሳቸውም ምንም ሳይገዳቸው ተስማምተው መሥራት ችለዋል። ይህ ደግሞ ለተሻለ የሥራ ዕድል አሳጭቷቸዋል። ውለታውን ያልዘነጋው ቀጣሪያቸው ማይክ በካናዳ ሥራ ለመቀጠር ቀጥታ ወደ አምራቹ ጋር መግባት አይቻልምና መጋቢ የሆነው ድርጅቱ ጀነራል ሞተር ውስጥ ገብተው የሚሠሩበትን ሁኔታ አመቻቸላቸው። በዚህም ታማኙና ለእውቀት ጉጉ የሆኑት ባለታሪካችን ለ17 ዓመታት ያህል መሥራት ቻሉ።ከዚያ ወደ አሜሪካ ልባቸው ስለተነሳ ጓዛቸውን ጠቅልለው ሄዱ።
በፖርት ላንድ ውስጥ ለአራት ዓመት እንዲሁም ቨርጂኒያ ለሦስት ዓመት ሠሩ።ቶዮታም ሆነ አዩንዳ ሞተር አምራች ድርጅቶች ውስጥም በመቀጠር ልምድ አካበቱ። ከዚያ ቀጣዩ የሥራ ቦታቸውን አገራቸው አደረጉ። በልምድና በትምህርት የቀሰሙትን እውቀት ለአገራቸው ልጆች ለማጋራት በሚል መጥተው ጋራዥ ከፈቱ። በመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከግል ተቋማትም ጋር በመፈራረም ለ10 ዓመታት ያህል አገለገሉ።
በዚህም በአውቶሞቲቩ አስተምረው ለቁም ነገር ያበቋቸው በርካታ ተማሪዎች እንዲኖራቸው ሆኑ። በተለይ ከሁሉም የሚያስደስታቸው ተግባረዕድ የሚማሩ የማታ ተማሪዎችን ማስተማራቸው ነው። ምክንያቱም በዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎችም ሆነ የሚያስተምሩ መምህራን አይመጣጠኑም።
አገልግሎቱን ሲሰጡ ምንድነው የጎደላችሁ በማለት እየጠየቁ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያበሳጫቸው ነበር። በእነርሱ ፍላጎት ላይ ብቻ መሥራት ውጤታማ አያደርግም። ለተማሪዎች አዳዲስ ነገር ማስተማር ከሁሉም በላይ ያስፈልጋቸዋል።እርሳቸው በሙያው ላይ በቆዩበት ሥራ በሙያው የሰለጠነ መምህር እጥረት።
የእውቀት ማነስ የለም።እዚህ ግን ይህ ይታያል።ለዚህ ደግሞ ያበቃቸው ተማሪዎች በኢንተርኔት በሚያገኙት መረጃ የተሻሉ ሆነው ይገኛሉ። በተቃራኒው መምህሩ ደግሞ ጥንት በተማረው ብቻ ነው የሚጓዘው። በየጊዜው ዘመኑን የዋጀ ስልጠና አይሰጠውም። ስለዚህም ሁለቱ እንዳይመጣጠኑ ሆነዋል። እናም ይህንን ማስታረቅ ያስፈልጋል።
የአውቶሞቲቭ ሥራ ሁልጊዜ ከቴክኖሎጂው ጋር አብሮ መዘመንን የሚጠይቅ ነው። የአገራችን መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት አልወጡም። የማሰልጠኛ ተቋማት በእውቀት የዘመነ መምህር ያለባቸው ናቸው ለማለት የማያስደፍሩ ናቸው። የማሰልጠኛ ተቋማት ራሳቸውን በየጊዜው እያዘመኑ የሚሄዱ መምህራን የሌላቸው በመሆኑ ብሎን እንኳን መፍታት የማይችል ዜጋን እንድናመርት አድርጎናል። ራሱን በአዲስ እውቀት እያጎለበተ የማይሄድ መምህር የበቃ ባለሙያ ሊያፈራ አይችልም።
ስልጠና በሚሰጡበት ጊዜ ከተግባረዕድ ተመርቆ 20 ዓመት ሙሉ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳያደርግ የቀረ ተማሪ እንዳገኙ ያጫወቱን አቶ ደጀኔ፤ በራሱ በተማሪው ችግር ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ለሙያው ትኩረት አለመስጠትም የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ። ጋራዦች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋልና መንግሥት ሊጠቀምባቸው ይገባል ባይ ናቸው።
በውጪው ዓለም አንድ ሠራተኛ ለስልጠና በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ኮሌጅ ይሄዳል። ከአዲሱ ቴክኖሎጂም ጋር ይተዋወቃል። ይህ የሚሆነው ደግሞ መንግሥት ሰፋ ያለውን ገንዘብ በጅቶ ማሰልጠኛ ተቋማት ደግሞ የተወሰነውን ሸፍነው በየጊዜው መምህራን ደሞዛቸው ሳይቋረጥ በማሰልጠን ነው።
በዚህ ደግሞ የእኛ ጎረቤት ኬኒያም ሳትቀር አሠራሩን ትከተላለች። ኢትዮጵያ ግን ይህ ሲሆን አይታይም። በአውቶሞቲቭ ሥራ ሁልጊዜ ለውጥ አለው። ለውጡ ደግሞ ውስጣዊና ውጫዊ ሊሆን ይችላል። እናም አዲስ ዲዛይንና አዲስ ምርት ሲመጣ ሳያውቁ ለመሥራት መሞከር ንብረትን ከማጥፋት አይተናነስም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ታዳጊ አገራት መኪናው የሚመጣው በውድ ዋጋ በመሆኑ ብዙ ኪሳራ ያጋጥማል። እናም መንግሥት ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ አለበት ይላሉ።
‹‹በዚህ ሙያ አገሬን ባገለግል እደሰት ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ጡረታ አይከፍለኝም። እስከ አሁን የከፈልኩትም አይበቃኝም። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ሥራው ስለተቀዛቀዘ የቤት ኪራዩ ሠርቼ ለመክፈልም እንዲሁ ከባድ ነው። የራሴ ቦታ ተመቻችቶልኝ ቢሆን ኖሮ ከአገሬ በላይ የሚሆን አንድም ነገር አይኖርም። በተጨማሪ የመኪናዎች መለዋወጫ ችግር መኖር ሠርቶ ለሠራተኞች የመክፈል አቅምም እንዳይኖረኝ እንቅፋት ሆኖብኛል።
ስለዚህም እነዚህና መሰል ችግሮች ዳግም ወደ ካናዳ እንድመለስ አስገድደውኛል›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን በካናዳ በቂ ጡረታ የሚከፈላቸውን ሁኔታ ስላመቻቹ ሊሄዱ ጓዛቸውን እያዘጋጁ ይገኛሉ። ሙያውን ስለሚወዱም ከቻሉ እንደሚሠሩበትም ነግረውናል።
የአውቶሞቲቪ ፍቅር
በውጭ አገር 26 ዓመታትን ሲሠሩበት ያላዩት ስቃይ አልነበረም። በተለይም ጠዋት ተነቶ በረዶ መጥረጉ ስቃይ ነበር። ከባለቤታቸው ጋር መጋጨቱና ትታቸው መሄዷም እንዲሁ የማይወጡት ነገር ውስጥ እንደከተታቸው ያስታውሳሉ።ሁሉም ግን በመታለፋቸው ደስተኛ ናቸው።
ከሙያው ፍቅር ጋር በተያያዘ የማይረሱት አንድ ገጠመኝ አላቸው። ይህም ቀጥቃጭ የተባሉበትና ከስድስት ወር ፍቅረኛቸው ጋር ያለያያቸው ነገር፤ ነገሩ እንዲህ ነው። አዲስ አበባ የተሻለ ደሞዝ ተከፋይ ሆነው እያማረጡ በሚበሉበት በልብስም ቢሆን ሽክ እያሉ በሚታዩበት ወቅት ነው ተግባሩ የተፈጸመው።
ዘወትር በሰፈራቸው አንዲት መልከመልካም የባላባት ልጅ ከመኪና ስትወርድና በአሽከሮች ጥላ ተጠልቶላት ምግቧን ተመግባ ስትወጣ ያዩዋታል። አጃቢዎቿ ደግሞ ማንንም አያስጠጉም። እናም እንግዳችን ይህችን ልጅ ለማግኘት ፈለጉ። የምግብ ሰዓቷን ጠብቀው ይለክፏት ጀመር። ጋርዶቿ ደግሞ ብዙ ጊዜ ያስፈራሯቸው እንደነበር አይረሱትም።
አንድ ቀን ግን እነርሱን አስቁማላቸው የሚፈልጉትን ጠየቀቻቸው። እርሳቸውም የዓይን ፍቅር እንደያዛቸውና እንዲሸኟት ብቻ እንድትፈቅድላቸው ጠየቋት። በጊዜው ስቃ አለፈቻቸው። አልፋታ ሲሏትም ታቀርባቸው ጀመር። ከዚያ ቅርርባቸው ሲጠነክር ጋርዶቹ ቀርተው ሸኚም አምጪም እርሳቸው ሆኑ።
ከቤተሰብ ጋርም ተተዋውቀው ይጋበዙ ጀመር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አንድ ነገር በመካከላቸው ተፈጠረ። እናት ወደ እርስታቸው በመሄድ ላይ ሳሉ መኪናቸው ተበላሸ። በዚህም ለእርሷ ደውለው መኪናውን እንድታስነሳ ነገሯት። እርሳቸው ሌላ መኪና አስመጥተው ሄዱ።
ከዚያ ምን ማድረግ እንዳለባት ስላላወቀች ለእንግዳችን ደውላ ነገረቻቸው። ከሥራ አስፈቅደውም የመኪና ማንሻቸውን ይዘው ከተፍ አሉላት። መስሪያ ቦታቸው ወስደውም አሠርተው ለሳምንት ያህል ዘና ብለውበት ቤት አቆሙት። ከ15 ቀን በኋላ እናት ሲመለሱ ለእንግዳችን ነገሮች ተቀየሩ። ራት። ምሳ እየተባለ የሚጋበዙትና ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ባለታሪካችን ዝር እንዳትል ተባሉ። ምክንያቱ ደግሞ መኪናው ተሠርቶ ወደ ቤት መመለሱ ነበር።
ማን አደረገው ሲባል የተረዱበት ሁኔታ የተለየ ሆነ። በጊዜው ሙያው ምንድነው ስትባል መካኒክ አለቻቸው። በተለያየ መልኩ ብትነግራቸውም ሳይገባቸው ቀረና ‹‹ቀጥቃጭ ማለትሽ ነው›› ሲሏት ‹‹አዎ›› የሚል ምላሽ ሰጠች። አዋረድሽኝ በማለትም ካህን አስጠርተው ምንም እቃ ሳይቀር አስረጩ።ከዚያ ይባስ ብለውም ክብራቸው እንዳይነካባቸው በማሰብ ዘሩ ተቆጥሮ በዝቅተኛ ደሞዝ ለሚተዳደር የመዘጋጃ ቤት የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ዳሯት።
በሙያቸው ምክንያትም ፍቅራቸውን አጧት።ግን ሙያቸው ሁሌም ታሪካቸው እንደሆነ ያምናሉ። ምክንያቱም በርከት የሚሉ ልጆችን አስተምረው ለቁምነገር አብቅተዋል። የጋራዥ ባለቤትም አድርገዋል። የተቀጠሩት እንኳን ታሪክ ሠሪ እንዲሆኑ አስችለዋል።
ኢትዮጵያዊነት ሲጣራ
በካናዳ ውስጥ ቶሮንቶ ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደውን ፌስቲቫል ለመሳተፍ በሄዱበት ጊዜ ነበር የዛሬዋን ባለቤታቸውን የአምስት ልጆቻቸውን እናት የተዋወቋት። እጅግ መልከመልካምና ጸባየ ሰናይ ሴት ነች። በወቅቱ ከፌስቲቫሉ ባለፈ የያዙት ሆቴልም አንድ ላይ ነበርና የተጀመረው ወጋቸው ሆቴሉም ድረስ ይዟቸው ዘለቀ። ማንነታቸውንም አስተዋወቀው።
ውስጣቸውም ቢሆን ሁለቱም ደነጋግጦ ነበርና በደንብ እንዲተዋወቁ ዕድል ሰጣቸው። እናም ከዚያ በአካል ቢለዩም በመንፈስ አንድ ሆነው ወራት አለፉ።ግን ሥራ ስላልነበራት እርሳቸውን እያገዘች ለመኖር ጠቅልላ ከእርሳቸው ጋር ስትሆን ሁሉ ነገር በአንድነት ወደመተግበሩ ገባ።
በዚህ ግንኙነታቸው ደግሞ የመጀመሪያ ልጃቸው ተረገዘች። ይህ ደግሞ ይበልጥ አንድ አደረጋቸው።ኑሮ በአንድ ጎጆ ውስጥም ሞቀ። ከዚያ በኋላ ምንም እንኳን በባልና ሚስት መካከል መጋጨቶች ቢኖሩም ሁሉንም አልፈው ከመጀመሪያ ባለቤታቸው የወለዷትን ጨምረው ስድስት ልጆቻቸውን ወደ ማሳደጉም አመሩ። ዛሬ ደግሞ እፎይ የሚሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። እርሷ እናቷን ለማገዝ ኢትዮጵያ መታለችና አብረው ብዙ ጊዜያቸውንም እንዳሳለፉ አጫውተውናል።
ሁሉም ልጆቻቸው ኑሯቸውን በውጭ አገር ያደረጉ ሲሆን፤ አንዷ ልጃቸው ተምራ የአንድ ትልቅ ካንፓኒ ዳሬክተር ነች። ሁለቱ ልጆቻቸው ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ አንዱ ኮሌጅ ገብቷል። ቀሪዎቹ ትንንሾቹ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ባለታሪካችን በሁሉም ነገራቸው ደስተኛ ሆነው ይኖራሉ።
መልዕክት
መጀመሪያ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ለወጣቱ ሲሆን፤ በተለይም በአውቶሞቲቭ ሙያ ላይ የተሰማራ ወጣት ሁልጊዜ ተማሪ መሆን አለበት ይላሉ። አዳዲስ እውቀቶችን ለመቅሰምም ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። ከገንዘብ ይልቅ የማወቅ ፍላጎትን ማስቀደምም አለበት። ጊዜው በጣም ጥሩና ለማወቅ ዝግጁነቱ ያለው ሰው ውጤታማ የሚሆንበት እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ደጀኔ፤ በኢንተርኔት አማካኝነት ከየትኛውም አቅጣጫ የሚወጡ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ጥበቦች መማርን ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
ምክንያቱም የአውቶሞቲቭ ሙያ ሳይንስ ነው። ከዘመኑ ጋር ሙያውን እያሻሻለ መሄድንም ይጠይቃል። ስለዚህም ዛሬን አልፎ ነገን ለማየትና ታሪክ ያለው ትውልድን ለማፍራት ሁሌም ለመማር ዝግጁ መሆንን ይፈልጋልና ይህንን ማድረግ ይገባል ይላሉ።
መንግሥትም ለእነዚህ የሙያ መስኮች ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ምክንያቱም መኪናው እየዘመነ ስለሚመጣ ያልተማረና ከወቅቱ ጋር ያልተዛመደ ሰው አይሠራውም። በመሆኑም በተለይም በስልጠና ሙያቸውን የሚያጎለብቱበትን ሁኔታ እንደሌሎቹ አገራት በዓመት ሦስት ጊዜ ባይችል እንኳን በአንድና በሁለት ጊዜ የሚሰለጥኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገበዋል የሚለው ሌላው መልዕክታቸው ነው።
በመጨረሻ ያነሱት ሃሳብ ማንኛውም ሙያ ውስጥ ሲገባ በፍላጎት ሆኖ ደንበኛን በሚያረካ መልኩ መሆን አለበት የሚለው ነው። ደንበኛን ሳያረኩ መሥራት ራስን ከመግደልም አይተናነስም። ምክንያቱም ነገ ወደዚያ ተቋም ሥራውን ወዶ የሚመጣ አይኖርም። ይህ ደግሞ እንጀራን ብቻ ሳይሆን የሚዘጋው ኑሮንም ያከብዳል። ትውልዱን የተበላሸ በማድረግ አገርንም ቢሆን ይገላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013