መንግስት እውቀትና ቴክኖሎጂን ያሸጋግሩልኛል፤ በራስ አቅም ፕሮጀክቶችን ይገነቡልኛል፣ ዘመናዊ ምርቶችን በማምረት በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎችን፣ የሀይል ማመንጫዎችን ወዘተ ይገነቡልኛል ብሎ ካቋቋማቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል የብረታ ብረትና ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አንዱ ነው። ተቋሙ ምንም እንኳን መንግስትና ህዝብ የጣለበትን ታላቅ ኃላፊነት ባይወጣም በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችን አምርቶ በሀገር ውስጥ ለገበያ በማቅረብ በኩል ድርሻ እንዳለው ይታወቃል። ለእዚህም የሚገጣጥማቸውን አውቶብሶች በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ይህ የሀገር ልጅ የማር እጅ እየተባለ ሲንቆለጳጰስ የቆየ ድርጅት የቀድሞ ኃላፊዎች በሀገር ሀብት ምዝበራ ውስጥ ክፉኛ ተዘፍቀዋል በሚል ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ክስ እየተመሰረተባቸው ይገኛሉ፡፤ በየእለቱ የሚሰማው የተጠረጠሩበት ወንጀልና የተመሰረተባቸው ክስ እንደሚያመለክ ተውም ምዝበራው እጅግ ግዙፍ ነው፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በመንቀሳቀስ ጭምር አገርን የኋሊት ያስኬደ ምዝበራ ተፈጽሟል፡፡
የቀድሞ የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች ጉዳይ በህግ እየተያ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ተቋሙ በርካታ ድርጅቶችን የሚያንቀሳቅስ እና በርካታ ሰራተኞችም ያሉት እንዲሁም በርካታ የሀገር ሀብት በእጁ የሚገኝ እንደመሆኑ እጣ ፈንታው ምን ይሆናል? አሁንስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? መጻኢ እድሉስ ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ለሆኑት ለብርጋዴር ጀነራል አህመድ ሀምዛ አቅርበን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
ሜቴክ አሁን የሚገኝበት ቁመና፣ስሙና አደረጃጀቱ
ሜቴክ አዲስ ስም አላወጣም። አዲስ አደረጃጀትም ገና አልተሰራም። ሆኖም ስያሜውን ለመቀየር የሚያስችል ጥናት (ፕሮፖዛል) ቀርቧል። ይህንን ለማድረግ ግን አንድ የልማት ድርጅት እንደገና ሲቋቋም መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ቀድሞ የነበረበት እዳ፣ እንደ አዲስ ሲቋቋም የሚኖረው የተከፈለ ካፒታልና የመቋቋሚያ ካፒታሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከሌላ አካል ወስዶ ያልፈጸመው ውል ካለ እንዲሁም ሌሎች ከእርሱ ጋር ውል ገብተው ያልፈጸሙት ካለ ማጣራት ያስፈልጋል። አሁን እነዚህን ነገሮች የማጣራት ስራው ባለመጠናቀቁ ወደ አዲሱ ስሙም ሆነ አደረጃጀቱ አልሄደም። ግን ወደዚህ ለመግባት እየተሰራ ነው።
በአዲስ ስም እና አደረጃጀት ለመስራት እያደረገ ያለው ዝግጅት
በአሁኑ ወቅት በስድስት ወራት ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ የሪፎርም እቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ እቅድ ሲዘጋጅ ይሳካሉ ተብለው የተቀመጡ ግቦች አሉ፤ ከነዚህም መካከል ዋናው የተቋሙን የጠፋ ስም መመለስ ሲሆን ለዚህም ተቋሙ በህግና ስርዓት ብቻ እንዲሰራ ማድረግ ነው፤ ምክንያቱም በአብዛኛው ሜቴክ መበላሸት የጀመረው ራሱን ሌላ መንግስት አድርጎ ከህግ ውጪ ስለሰራ ነው።
ከተቋሙ ጋር አብረው ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን ማድረግ የሚለውም ሌላው ስራው ነው። ምክንያቱም በጥናት ከተለዩት ችግሮች መካከል ኮርፖሬሽኑ ከመንግስትም ሆነ ከግል ተቋማት ጋር የነበረው የስራ ግንኙነት በጸብና በግጭት ላይ የተመሰረተ ነበር። በመሆኑም እኛ አገልግሎት ሰጪ እስከ ሆንን ድረስ ከአገልግሎት ፈላጊው ዝቅ ብለን ነው መታየት ያለብን፤ ሆኖም ለከፈሉት ገንዘብ እንኳን አገልግሎት ሲጠይቁ ይሰጣቸው የነበረው ምላሽ በጣም አደገኛና በጸብ የተሞላ ነበር።
ለምሳሌ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር የነበረው ግንኙነት ጥሩ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ስኳር ኮርፖሬሽን በጣም ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሏል፤ እኛ ግን ጨርሰን ያስረከብነው አንድም ፕሮጀክት የለም፡፡ ፕሮጀክቶቹን ካለማጠናቀቅም በላይ አንዳንዶቹን ፕሮጀክቶች ወገብ ወገባቸው ላይ እያደረስን ነው በሀይል እንዲረከቡን ስናደረግ የነበረው፡፡ በመሆኑም አሁን እያስረከብን ካለናቸው ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ ቀድሞ ሲቀርብባቸው የነበረው የአፈጻጸም ሪፖርትና በተግባር የታየው በጣም የተለያየ ነው፤ በጣም ዝቅተኛ አፈጸጸም ነው ያላቸው፡፡
በመሆኑም ይህን ድርጊት የሆኑ አካላት ፈጽመውት ሊሆን ይችላል፡፡ ሜቴክ ግን በርካታ ሰራተኞችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ሜቴክ ይቅርታ መጠየቅና እርቅ ማውረድ ካለበት አካል ጋር ሁሉ ይህንን ያደርጋል፡፡ ወደፊት አብረን በምንሰራባቸው መንገዶች ላይ በውይይት መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን ፡፡ ተቋሙም የህዝብ እንደመሆኑ መጠን ከዚህ በኋላ ሚስጢር የሚባል ነገር እንዳይኖር ይደረጋል፡፡እቅዶች ድረ ገጾች ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ለመገናኛ ብዙሀን ክፍት መሆን ደግሞ የእቅዱ ዋና ግብ ይሆናል።
ሌላው መልካም ስምን ከመገንባት አንጻር አደረጃጀቱን መቀየር ያስፈልጋል። አንደኛ ሜቴክ ከአሁን በኋላ መልዐክ ሆኖ ቢመጣ እንኳ ሰው ሰይጣን ብሎ ነው የሚያነበው፤ በዚህም ምከንያት ስሙ መቀየር ስላለበት ይህንን ለማድረግ መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ነው።
መረጃ አልባው ሜቴክ
የሜቴክ ሌላው በጣም ትልቁ ችግር መረጃ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ የመንግስት ተቋም ሆኖ መረጃ ያለመኖር ደግሞ እጅግ የሚገርም አልፎ ተርፎም የሚያሳዝን ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ተቋሙ እንደ ተቋም ላለፉት ስድስት ዓመታት ምንም ዓይነት ኦዲት አልተደረገም።
እዚህ ላይ ለሜቴክ መጥፋት የመንግስት እጅ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ማለት እችላለሁ። ምክንያቱም በብዙ ቢሊየን የሚቆጠር ብር ከሰጠ በኋላ የት አደረስከው? ምን ሰራህበት? ብሎ አለመጠየቅ በራሱ ያስጠይቃል።
ይህ የመረጃ አለመኖር ከላይ የተነሱትን የስምና የአደረጃጀት ለውጦችን ለመስራት ጭምር ትልቅ ፈተና ሆኗል። አሁን ግን እነዚህን ክፍተቶች እየሞላን በመሆኑ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አደረጃጀቱንና ስሙን መቀየር በአዲሱ ስሙም አዲስ ሆኖ መቅረብና አንደ ማንኛውም የልማት ድርጅት ህግን ተከትሎ መስራት ይጀምራል።
እንደ ቀድሞው የገንዘብ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ
አሁን የተቋሙ ትልቁ ችገር የገንዘብ እጥረት ነው፤ ከፍተኛ እዳ አለበት፣ የያዛቸው ሀብቶች በቀላሉ ወደ ጥቅም የሚቀየሩ አይደሉም። ለምሳሌ ከፍተኛ የግብዓት ክምችት አለው፤ ሆኖም ግብአቶቹ በውድ ዋጋ የተገዙ ቢሆኑም አሁን የትኛውንም ኢንደስትሪ የሚያገለግሉ አይደሉም።
ለምሳሌ የውሃ መቆፈሪያ መሳሪያ ተብሎ በጣም በውድ ዋጋ ከውጭ ተገዝተው የገቡ ስድስት ማሽነሪዎች አሉ። አንዱን ደቡብ ክልል ቢወስደውም ብዙ ሳይጠቀምበት ተበላሽቷል፡፡ ሌሎቹ ግን ቆመዋል፤ ከዚህም በኋላ እንደ ተረፈ ምርት ካልሆኑ በቀር ጥቅም የላቸውም። ቢሾፍቱ ላይም ጠያቂ ሳይኖር ተገዝተው ለአራት ዓመታት የቆሙ መኪኖች በርካታ ናቸው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ተቋሙ አሁን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ ወድቋል ።
እናም እነዚህን ችግሮች የምናልፍበትንና አቅማችንን የምናሳድግበትን መንገድ ስናስብ ደግሞ አንደኛው መንገድ ሊሸጡ የሚችሉ ሁሉ መሸጥ ነው፣ በዚህ አቅም ከተገኘ በኋላ ትእዛዝ ያላቸውን የተቋሙን ኢንደስትሪዎች ደግሞ ወደ ስራ በማስገባት አጠናቅቀው ገንዘብ የሚያመጡበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደ ድሮው በጉልበት ትዕዛዝ አምጡ ሳይሆን በህግና በስርዓት ተወዳድረን ስራዎችን አሸንፈን በመስራት ትልቅ ተቋም የምንሆንበት መንገድ ለመፍጠር በመስራት ላይ እንገኛለን።
ተቋሙ ብዙ ተሽከርካሪዎች አሉት፡፡ በወር የሚጠቀመው ነዳጅም በጣም ትላልቅ የመንግስት ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ከሚጠቀሙት በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በስራው ያስመዘገበው ውጤት ግን ከእነሱ የበለጠ አይደለም። በመሆኑም አቅምን ለማጎልበት ወጪን መቀነስ አንዱ ስትራቴጂ በመሆኑ እነዚህን የነዳጅ ወጪዎች እንቀንሳለን ።
ሌላውና ትልቁ ነገር ግን ተቋሙ ያለበት እዳ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ የሚከፈልም የማይከፈልም መኖሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚሰጠው ገንዘብ አንጻር ስራው ተመጣጣኝ ነወይ ብሎ ባለመጠየቁ ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው።
ተቋሙ ስላልሰራ አይደለም እዚህ ሁሉ እዳ ውስጥ የተዘፈቀው፡፡ ሰጪና ተቀባይ የት አደረስከው ባለመባባላቸው ነው፡፡ አሁን ኮርፖሬሽኑ ይህንን ያህል እዳ አለብህ ተብሎ ቢጠየቅ ከየትም አምጥቶ አይከፍልም፡፡ ይክፈል እንኳ ቢባል 40 ዓመት አይበቃውም። በመሆኑም መንግስት በራሱ ውሳኔ ሊሰርዝ የሚገባውን በመሰረዝ ተቋሙ በተረጋጋ መልኩ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ ይኖርበታል።
ከእኛ የልማት ድርጀት እንደ ሌሎች የልማት ድርጅቶች ለምሳሌ ከባንኮች በብድር የተወሰደ፣ አንዳንዴ ደግሞ አገልግሎት አግኝተን ሆኖም ሂሳብ ሳናወራርድ የቆየንባቸው አካላት ገንዘባቸውን በግድ ማግኘት አለባቸው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ድርጅት ነው። ሜቴክ ያጓጉዛል፤ ይጠቀማል፤ ሆኖም ግን አንድም ቀን ኪራይ ከፍሎ አያውቅም፡፡ ተቋሙ ሜቴክ ያልከፈለውን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ካላገኘ ወደ ኪሳራ ይገባል። በመሆኑም አንደዚህ ዓይነት ሊታለፉ የማይችሉ እዳዎችን በረጅም ጊዜ መክፈል የምንችልበት አግባብ ቢፈጠር መንግስትም ቢያስማማን ጥሩ ነው።
በወደቦች አካባቢ የተከማቹ ንብረቶች
በወደብ ማቆያዎች አካባቢ አምስት ዓመት የቆዩ 344 ኮንቴነሮች አሉን፡፡ አንድ ኮንቴነር ደግሞ እንደ ርዝመቱ መጠን በቀን ከ 6 እስከ 11 ዶላር ይቆጥራል። ይህ የሚከፈለው ደግሞ ለባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሳይሆን ለውጭ ድርጅት ነው። በአንድ በኩል አገሪቱ ላይ ዶላር ጠፋ ይባላል፤ እኛ ደግሞ በቀን ለአምስት ዓመት ያህል ይህንን ሁሉ ዶላር ለኪራይ ከፍለናል፤ በጣም ያሳዝናል።
አሁን እቃዎቹን በፍጥነት ማንሳት ተጀምሯል፡፡ ወደ ህዳሴ ግድብ የሚሄዱትን ወደዚያ ሌሎቹን ደግሞ ወደ ፕሮጀክቶች እንዲጓጓዙ እየተደረገ ነው። ከዚህ በኋላም አዲስ ገንዘብ አናመጣም፤ አዲስ ወጪም አናወጣም።
እንደ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ፕላስቲክ ፋብሪካ ያሉት ድርጅቶች ጉዳይ
እነዚህ ስራዎች ወደፊትም ከሜቴክ ጋር የሚቀጥሉ ናቸው፤ እንዲያም ሆኖ የአዋጭነት ጥናት እየተካሄዳባቸው ያሉም አሉ። ቢሾፍቱ ላይ በጣም የሚያስደንቅ ለውጥ መጥቷል፤ቀድሞ ከሰበሰባቸው የማይሸጡ እቃዎች አንጻር እዳ አለበት፤ ግን እስከ አሁን በቀን አንድ መኪና ያመርት የነበረው አሁን ሰራተኛው በሁለት ሽፍት እንዲሰራ በመደረጉ የማሳያ ቦታዎቹን በማስፋት በቀን የማምረት አቅሙ ወደ አራት ደርሷል፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ ስድስት መኪናዎችን መገጣጠም ላይ እንደርሳለን ብለን አቅደናል፤ እንደርሳለንም።
ሌላው ኢትዮ ፕላስቲክ ባለፉት ወራት ገንዘብ ጠፍቶ የሰራተኞች ደመወዝ ከኮርፖሬሽኑ ነበር የተከፈለው። አሁን የራሱን ሰራተኞች ደመወዝ ከፍሎ ለኮፖሬሽኑም ትርፉን ማስገባት ጀምሯል፤ መወዳደርም ማሸነፍም ጀምሯል። ይህ መሆን የቻለው ደግሞ በስርዓት ግብዓት ስለሚገዛ ዋጋው ቀንሷል ፤ይህ ቅናሽ በመሸጫ ዋጋው ላይ ልዩነት አምጥቷል። ኢንደስትሪዎቹ ብዙ ትርፍ አመጡ ባይባልም ከኪሳራቸው እየወጡ በማገገም ሂደት ላይ ስለመሆናቸው ግን መናገር ይቻላል።
እዚህ ላይ ግን አሁንም ወደ መስመር ያልገቡ እንዳሉ መናገር ይገባል፡፡ ለምሳሌ «የመሰረተ ልማት መሳሪያዎች አቅራቢ» ድሮም ቢሆን ማሽን እያመጣ ነበር የሚሸጠው፤ ማምረቻ ቦታ ሰራሁ ይበል እንጂ ባዶ ቤት ነው የተገኘው። አሁን እንደ ድሮው ማሽን አምጥቶ መሸጥ፣ ገበያው ሳይፈልግ ሜቴክ ነውና ግዙት የሚባል ነገር ስለማይቻል ይህ ተቋም በሪፎርሙ እንዴት ነው ወደ ልማቱ የሚገባው የሚለውን እናያለን።
በሜቴክ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ችግር ለመፍታት
በመጀመሪያ ተቋሙ አዲስ አመራር እንደተመደበለት እነዚህን ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ለመካስም እንደ አገርም የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር፤ ለምሳሌ ስኳር በሁለት ወር እንጨርሳለን ብለን አስበን ነበር፤ ግን በሁለት ወሩ እቅዱም ተሰርቶ ማለቅ አልቻለም።
ህዳሴ ግድቡ ላይም ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም አቅማችን እንደማይቻል ስለተረዳን ህዳሴ ግድብ አገራዊ ነው ይህንን ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ሀብት እያበላሹ መኖር እንደ ዜጋ አስነዋሪ በመሆኑ ተረከቡን ብለን ጥያቄ አቅርበናል፤ ስኳር ላይም ኮርፖሬሽኑ ራሱ አስረክቡኝ ብሏል፤ ያዩ ማዳበሪያ ላይም የኬሚካል ኮርፖሬሽን እንድናስረክበው ጠይቋል፤ ይህንንም እናደርጋለን።
ሜቴክ ተወዳዳሪ ሆኖ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እንዲሰራ
ድሮም ቢሆን ተቋሙ በዚህ ልክ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን የሚሰራበት አቅም አልነበረውም። አሁን ስናስረክብ እኮ የኦሞ ኩራዝ 94 በመቶ ደርሷል የተባለው ርክክቡ ላይ የተገኘው ውጤት 80 ነጥብ 5 ነው። የበለስ ከ 80 በመቶ በላይ ነበር የተባለው ሁሉን በርክክብ ወቅት 60 በመቶ ነው የሆነው። በመሆኑም እኛም አቅም ያለን ሳንሆን አገርንም እየጎዳን የምንቀጥል መሆን ስለሌለብን ያሉንን እናስረክባለን፤ ከዚህ በኋላም ምንም ዓይነት ፕሮጀክት አይኖረንም።
አቅማችን ላይ መቶ በመቶ እርግጠኛ ከሆንን ሌላ አካል የማይሰራው ሆኖም ግን ለአገር ይጠቅማል ብለን ካሰብን በትዕዛዝ ሳይሆን በህግና ደንብ ተወዳድረን ሶስተኛ ወገን ብቃታችንን አረጋግጦ ሲሰጠን ወደ ፕሮጀክት ስራ መግባት የምንችልበት ቀን ይመጣል።
የሰራተኞች ጉዳይ
አሁን የቀነስነው ካስረከብናቸው ፕሮጀክት ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሰራተኞች ብቻ ቀንሰናል። ከዚያ ውጪ ግን ሜቴክ ሰራተኛ አልቀነሰም፡፡ የሚቀንስበት ወቅት ግን ይኖራል፡፡ እነዚህንም የቀነስነው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ 377/96 የሚፈቅድላቸውን ሁሉ በማከናወን ነው ።
በእርግጥ ተቋሙ ብዙ ሰራተኞች አሉት፤ ለማሰናበት ግን ለስራው የሚያስፈገው ሀይል ምን ያህል ነው ?የሚለው መለየት አለበት በስሜት የሚሆን ነገር የለም፤ አሁን ይህንን የመለየት ስራ እየተከናወነ ነው።
ይህ ልየታ ከተሰራ በኋላ ደግሞ ሌላስ መንገድ አለወይ? ብለን እናያለን፤ ለምሳሌ ቢሾፍቱ ላይ ሰራተኛው በጣም ብዙ ነው፤ ለስራው የሚያስፈልገውንም ሰው ለየን፤ ግማሽ ሆነ፤ ግን ሰዎቹን ከማሰናበት በሁለት ፈረቃ እንዲሰሩ ሆነ። ይህ ሲሆን ደግሞ ሰራተኛና ወሬኛው ይለያል፤ ሁሉም ስራውን ሰርቶ የሚያገኝበት መንገድ ተከፈተ ማለት ነው።
ሆኖም አማራጭ ጠፍቶ ወደ መቀነሱ ከተሄደ ተቋሙ የማይጎዳበትን እነርሱን ደግሞ ሊያቋቁም የሚችል መንገድንም እናያለን። ለመቀነስም ላለመቀነስም ግን ሰራተኛው ሚና አለው። ሜቴክን ሲመሩ የነበሩት አካላት ማሽኖችን ሳይቀር ወደ ሆነ ሰው እያነካኩ ነው ሲያጠፉ የነበሩት፤ ከታች ያለው ደግሞ ጊዜውን በአግባቡ ባለመጠቀም፣ ተረፈ ምርትን በግብዓትነት ተጠቅሞ ሀብትን ባለማፍራት፣ በየቦታው የወዳደቁ ነገሮችን ወደ ሀብትነት ባለመቀየር ሚና ነበረው። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ኃላፊነት የማይሰማው ሰው አይቆይም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በሰራተኛወም በአመራሩም ላይ ይተገበራል።
ሰራተኞቹንና አመራሩን ማቀራረብ
ሰራተኛውና አመራሩ አይጥና ድመት ናቸው፤ ሰራተኛው አልተጠቀምኩም ይላል፤ በእውነትም ደግሞ ስናየው ሜቴክ ለሰራተኞቹ የሚከፍለው ደምወዝ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ በባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ላይ እንኳ እንዲህ የወረደ ደመወዝ የለም፡፡ ለምሳሌ ኢንጂነር ሆኖ ከ2ሺ 500 እስከ 4ሺ ብር የሚከፈለው ሰራተኛ ነው ያለው፤ በዚህም የተነሳ ሰራተኛው አቅሙን በሙሉ ተጠቅሞ እየሰራ አይደለም።
በመሆኑም የሰራተኛውን ፍላጎት ለማርካት መቀራረቡ ወሳኝ ነው የሰራተኛ ማህበር እንዲመሰረት እየተደረገ ነው፡፡ በየጊዜው ውይይቶች ይካሄዳሉ፡፡ በዚህም ጥሩ ለውጥ እየመጣ ነው።
እኔ ማለት የምፈልገው ነገር ሜቴክ እንደዚህ ሆኗል ይህ እውነት ነው። ሰራተኞች ግን ከሚባለው ፍጹም በተቃራኒው ወገን ያሉ ናቸው። አሁን ከሜቴክ መጣሁ ለማለት በጣም አሳፋሪ ሆኗል። እነዚህ ሰራተኞች ግን ቀደም ብዬም እንደገለጽኩት ደመወዛቸው በጣም አነስተኛ ከመሆኑም ባለይ በመልካም አስተዳደር እጦት ሲሰቃዩ የኖሩ ናቸው፤ ከነዚህ መካከል ደግሞ ጠጋ ጠጋ እያሉ የሆነች እንጥብጣቢ የሚያገኙ ወደ ውጭ ሀገር በተደጋጋሚ የሚመላለሱ ነበሩ።
እናም ሜቴክ ብሎ በጀምላ መጨፍጨፍ ተገቢም አይደለም፡፡ ህብረተሰቡም ይህንን ቢረዳ መልካም ነው። ያለፈውን ጊዜ እንዳለፈ ቆጥረን መጪውን ለማሳመር እየሰራ መሆኑን፣ ወደፊት ደግሞ መለወጥ የሚችል አሁንም ብዙ ለውጦች እያመጣ እንደሚገኝ እንዲገነዘቡ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
እፀገነት አክሊሉ