መልካምስራ አፈወርቅ
ባልና ሚስቱ በትዳር ዘመናቸው መልካም የሚባል ጊዜን አሳልፈዋል፡፡ በመተሳሰብና በፍቅር የገፉት ጊዜም ለብዙዎች ምሳሌ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአዳማ ከተማ ሲኖሩ በጋራ ባፈሩት ሀብትና ንብረት ሲተዳደሩ ቆይተዋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ ወይዘሮ አዜብን ከማግባታቸው አስቀድሞ በከተማው ማዘጋጃ ቤት የተረከቡትን ባዶ ቦታ ይዘው ቆይተዋል፡፡ ጋብቻው ጸንቶ አብሮነት ሲጀምሩ ደግሞ ከባለቤታቸው ጋር ተማክረው የመኖሪያ ቤት ግንባታውን ጀመሩ፡፡
ጥንዶቹ ቤቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በእኩል ሲለፉ ቆይተዋል፡፡ ሚስት ከደመወዛቸው እየቆጠቡ ባልም ከወር ገቢያቸው እየቀነሱ የቤቱን መሰረት ጀመሩ፡፡ በ180 ሜትር ካሬ ላይ ያረፈው ቤት ግርግዳው ቆሞ ጣራው ተመታ። ቀለሙ አምሮ በርና መስኮቱ ተገጠመ፡፡ አጥሩ ተከብሮ ወሰኑ ታወቀ፡፡
ትዳር በአዲስ ጎጆ ሲደምቅ ህይወት በተሻለ መንገድ ቀጠለ፡፡ ለቤቱ ዕቃዎች ተገዙ፡፡ ለጓዳና ሳሎኑ የጎደሉት ተሟሉ፤ ይሄኔ ከቤት ኪራይ እንክርት የተገላገሉት ጥንዶች በሆነው ሁሉ ተደሰቱ ፡፡
ደጋግመውም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ፡፡ ውሎ ሲያድር በግቢው ሌሎች ቤቶች ተሰሩ፡፡ ቤቶቹ ለንግድና መሰል ጉዳዮች ውለው ተጨማሪ ገቢ ማምጣት ያዙ፡፡ ገቢ ሲጨምር የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ታከሉ፡፡ በንብረቶቹ ባልና ሚስት በጋራ ሲጠቀሙ ቆዩ ፡፡
ቅያሜ…አሁን የባልና ሚስቱ ትዳር እንደቀድሞው አልሆነም። በጭቅጭቅ ውሎ የሚያድረው ጎጆ ሰላም ይታጣበት ይዟል። ትናንት መተሳሰብ የነበራቸው ጥንዶች ዛሬ ኩርፊያና ቅያሜ ይጎበኛቸው ጀምሯል፡፡
የባልና ሚስቱን አለመግባባት ያወቁ ችግሩን፤ በእርቅ ሊፈቱ ሞከሩ፡፡ ለጊዜው የዳነ የመስለው አብሮነት ቆይቶ በጠብ አገረሸ፡፡ ሽምግልና ይፈታው ዘንድ አሁንም መነጋገሩ ቀጠለ፡፡ ጉዳዩ ሁሉ እንደታሰበው አልሆነም። ንፋስ የገባው ትዳር ለመፍረስ ተንገዳገደ፡፡
አሁን የአቶ አለማየሁና የወይዘሮ አዜብ እህል ውሀ እያበቃ ነው፡፡ ከጊዚያት በኋላም ጋብቻው በፍቺ ሊጠናቀቅ ግድ ብሏል፡፡ ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤት የሀብት ንብረት ክፍፍል ይደረግ ዘንድ አዘዘ፡፡ ከጋብቻው መፍረስ በኋላም በህጉ መሰረት እንዲፈጸም ሂደቱ ቀጠለ።
የሀብት ንብረት ጉዳይ …ከፍቺው በኋላ አባወራው አቶ አለማየሁ ለፍርድ ቤቱ ማመልከቻ ጽፈው አዘጋጁ፡፡ የግለሰቡ ዶሴ በመኖሪያ ቤቱና በሚንቀሳቀሱ ሌሎች ንብረቶች ዙሪያ የሀብት ክፍፍል እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡
የፍርድ ቤት ውሎ
የመጀመሪያውን አቤቱታ የተመለከተው የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀድሞ በጋብቻ ህይወት የነበሩትን ጥንዶች ጉዳይ መመርመር ጀመረ፡፡ ግለሰቡ ንብረትን በሚመለከት ቤቱ የግላቸው ስለመሆኑ በስማቸው ባቀረቡት ካርታ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ቤቱን የሰሩት ከጋብቻቸው በፊት በወሰዱት ባዶ ቦታ ላይ መሆኑንና ይህን በተመለከተም በቂ ማስረጃ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ግለሰቡ ንብረቱን አስመልክቶ ባቀረቡት ተጨማሪ አቤቱታ የቀድሞ ባለቤታቸው መብት የሚኖራቸው በትልቁ ቤት ሳይሆን በጋብቻ በነበሩበት ጊዜ በተሰራው ተጨማሪ የሴቶች የውበት ሳሎን ላይ ብቻ እንደሚሆን አመልክተዋል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አባወራው ከዋናው ቤት ሌላ ለተሰራው ቤት ሀብት የማካፈል ችግር እንደሌለባቸው ተናገሩ፡፡
የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ግራ ቀኝ ከመረመረ በኋላ ተጠሪንና አመልካችን አቅርቦ አነጋገረ። ግለሰቡ ‹‹አለኝ›› የሚሉትን ማስረጃዎች ተመልክቶም የሰው ምስክሮችን ዋቢ አደረገ፡፡ ጋብቻው በ1999 ዓ.ም የተመሰረተ መሆኑንና ቤቱ የተሰራው ከጋብቻው አስቀድሞ እንደሆነ በማስረዳትም ንብረቱ የሚገባው ለግለሰቡ መሆኑን ወሰነ፤ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው በጋብቻ ውስጥ የፈራውና የሴቶች የውበት ሳሎን የሆነው ቤት ወይዘሮዋ እኩል መብት እንዳላቸውና መካፈል እንደሚችሉ አስታወቀ፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የደረሳቸው ወይዘሮ አዜብ በተሰጠው ብይን በእጅጉ አዘኑ፡፡ የተሰጣቸው ብይን ተገቢ አለመሆኑን አስረድተውም ምላሻቸውን አዘጋጁ፡፡
ወይዘሮዋ ከፍርድ ቤቱ የተሰጣቸውን ውሳኔ ይዘው በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቀረቡ። በይግባኝ ማመልከቻው ላይ የቀድሞ ባለቤታቸው ከጋብቻቸው በፊት ከመንግስት የተረከቡት ባዶ መሬት እንደነበር አልካዱም፡፡
መሬቱን ከተረከቡ በኋላ በቆዩባቸው የጋብቻ ዘመናት ግን አብረው በላብና ወዛቸው ባፈሩት ገቢ ቤቱን በጋራ ሰርተው በማጠናቀቅ ለዓመታት ሲኖሩበት እንደቆዩ አስረዱ። ወይዘሮ አዜብ በማመልከቻ አቤቱታቸው አያይዘው ለማስረዳት እንደሞከሩት የቀድሞ ባለቤታቸው ከመንግስት የተረከቡት የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ በሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ተሰርዞ በምትኩ የጋራ ለሆነው ቤታቸው በካርታ የተረጋገጠ ሰነድ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ምንም እንኳን የቤቱ ካርታ በቀድሞ ባለቤታቸው ስም ቢመዘገብም ግለሰቡ በፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባስመዘገቡት የሀብት ማረጋገጫ መኖሪያ ቤቱ ከወይዘሮ አዜብ ጋር በጋራ ያፈሩት የማይንቀሳቀስ ንብረታቸው ስለመሆኑ በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡ በማለት ጠቀሱ፡፡ አያይዘውም ፍርድ ቤቱ በመረጃዎቹ መሰረት ፍትሀዊ ውሳኔ ሊሰጠኝ ይገባል ሲሉ ጠየቁ፡፡
የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ፍርድ ቤቱ የወይዘሮዋን የይግባኝ ማመልከቻ አንድ በአንድ መረመረ፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤት የጥንዶቹ ጋብቻ በ1999 ዓ.ም ስለመመስረቱ ይጠቁማል፡፡ ክርክር የያዙበት መኖሪያ ቤትም ከጋብቻቸው በፊት ተሰርቶ የተጠናቀቀ ስለመሆኑ ማስረጃዎች ስለማረጋገጣቸው ያትታል፡፡
ቤቱ በባለቤትነት ሊሰጥ የሚገባው ለግለሰቡ መሆኑን የሚጠቁመው የፍርድ ቤቱ ማስረጃ በተጨማሪ የተገነባው ቤት ግን የግምቱ ግማሽ በገንዘብ ተሰልቶ ወይዘሮዋ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር በእኩል የመካፈል መብት እንደሚኖራቸው ይጠቁማል፡፡
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ወይዘሮዋ ባሉት መሰረት ግለሰቡ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ንብረቱ የጋራ ስለመሆኑ የፈረሙበት ማስረጃ ካለ በሚል ሰነዶቹን መረመረ። ወይዘሮዋ እንደጠቀሱት ሆኖ በኮሚሽን መስሪያ ቤቱ የተረጋገጠ ማስረጃ ከፋይሉ ጋር ተያይዟል፡፡
የወረዳው ፍርድ ቤት ማስረጃው በኮሚሽን መስሪያ ቤቱ መረጋገጡ ብቻ ንብረቱን የጋራ ሊያደርገው አይችልም ሲል ውሳኔውን አሳልፏል፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ ከመረመረ በኋላ የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ በማጽናት ውሳኔውን ዳግም አጸደቀ። ንብረቱ የሚገባው ለሴትዬዋ ሳይሆን ለግለሰቡ ብቻ መሆኑንም አረጋገጠ፡፡
ወይዘሮ አዜብ የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ የሰጣቸውን ውሳኔ ተቀብለው ለተጨማሪ ይግባኝ ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመሩ፡፡ እስካሁን በፍርድ ቤቶቹ የተሰጣቸው ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመውም ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሚዛናዊ የሆነ ፍርድ እንዲሰጣቸው ተማጸኑ፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት የወይዘሮዋን አቤቱታ አቅርቦ ከተያያዙት ማስረጃዎች ጋር በማዛመድ መረመረ፡፡ የስር ፍርድ ቤቶቹ እስካሁን የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ስለመሆኑ አልተጠራጠረም፡፡ ዳኞቹ ውሳኔዎችን በማጽደቅና ቀድሞ የተላለፈውን ፍርድ በመድገም ንብረቱ የሚገባው ለግለሰቡ ብቻ መሆኑን አረጋገጡ፡፡
ወይዘሮ አዜብ ውሳኔውን ተቀብለው ዳግመኛ ወደ ፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመሩ። አቤቱታው የቀረበለት ፍርድ ቤትም ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት አያስቀርብም ሲል አሰናበታቸው፡፡
ሌላ ሙከራ …ወይዘሮ አዜብ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ያቀረቡት የንብረት ይገባኛል ጥያቄ አልተመለሰላቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔውን አምነውና ተቀብለው መቀመጥን አልፈለጉም፡፡ ጉዳዩን ለኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት ጠየቁ፡፡
የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ የቀረበለት የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጉዳዩን ዳግመኛ መመርመር ያዘ፡፡ አመልካቿ ታህሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት አቤቱታ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር በጋብቻ ውስጥ እያሉ በጋራ ስላፈሩት ንብረትና የመብት ጥያቄ ያነሳል፡፡
ማመልከቻው በአዳማ ከተማ ቀበሌ 01 የሚገኝና በካርታ ቁጥር 4495/94 የተመዘገበው 180 ሜትር ካሬ ቦታ የጋራቸው ሆኖ ሳለ በአግባቡ ባልተሰሙ የሰው ምስክሮች በመታገዝ የተሰጠው ውሳኔ ተገቢነት እንደሌለው ያስረዳል። ወይዘሮዋ አሁንም በጸረ ሙስና ኮሚሽን የተረጋገጠው የጋራ ንብረት ማስረጃን ከሌሎች ተያያዥ ማረጋገጫዎች ጋር በማያያዝ ተገቢው ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡
የጉባኤው ምርመራዎችጉባኤው የወይዘሮዋን ማመልከቻ መሰረት አድርጎ ለአዳማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ደብዳቤ በመጻፍ በጉዳዩ ላይ ማጣራት ጀመረ፡፡ የሁለቱን ግለሰቦች የጋራ ንብረትን አስመልክቶም ተገቢው ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡
በደብዳቤ ጥያቄ የቀረበለት የአዳማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምላሽ ሰጠ፡፡ አቶ አለማየሁ በተጠቀሰው የካርታ ቁጥር በአዳማ ከተማ ግንቦት 21 ቀን 1994 ዓ.ም ከቀበሌ 01 180 ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ ወስደው በ2005 ዓ.ም የቤት ግንባታ ስራ ፈቃድ በማውጣት ሶስት ቤቶችን ሰርተው አጠናቀዋል፡፡ ለዚህም በስማቸው የተዘጋጀ ህጋዊ ካርታና ፕላን ወስደዋል፡፡
ጉባኤው ከኤጀንሲው የተሰጠውን ማረጋገጫ በመያዝ ቤቱን አስመልክቶ ለአዳማ ወረዳ የፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ደብዳቤ ጻፈ፡፡ በደብዳቤውም የተጠቀሰው ቤት በሁለቱ ጥንዶች ስም መመዝገብ ያለመመዝገቡን ጠየቀ፡፡ ከወረዳው የተሰጠው ምላሽ የተጠቀሰው ንብረት በአመልካችና በተጠሪ ስም የተመዘገበ ሆኖ የጋራ መሆኑን የሚያመላክት የሰነድ ማስረጃ መያያዙን ጠቆመ፡፡
አመልካቿ ባሰሙት ቅሬታ ተጠሪው የንብረቱን የጋራ መሆን በጸረ ሙስና ኮሚሽን በግልጽ ካሳወቁና ፍርድ ቤቶችም ይህንኑ ካረጋገጡ በኋላ መኖሪያ ቤቱ የእሳቸው ብቻ ነው መባሉ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 35 /1/ አንቀጽ 25 እና 37 የሚጥስ ነው፡፡
የአንድ ህገ መንግስታዊ መብት ጥሰት የሌላውንም ተያያዥ መብት የሚነካ በመሆኑ ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ካላቸው የህገ መንግስቱ አንቀጾች አኳያ ሊታዩ እንደሚገባ ጉባኤው አምኖበታል፡፡
ጉባኤው የማይንቀሳቀስ ንብረቶችን ለመመዝገብ ስልጣን ካለው የአዳማ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ በደብዳቤ ባደረገው የማጣራት ሂደት ግለሰቡ ባዶ መሬቱን የወሰዱት ከጋብቻው በፊት መሆኑን አረጋግጧል። ይሁን እንጂ የቤት ግንባታውን ጀምረው ያጠናቀቁት ባለቤታቸውን ካገቡ በኋላ መሆኑ ታወቋል፡፡
ተጠሪው በቀን 21/10/ 1994 ዓ.ም መሬት ወስደው በዚሁ ቀን የቤት ግንባታውን የስራ ፈቃድ ተረክበዋል። ቤቱን ሰርተው በማጠናቀቅ ካርታና ፕላን የወሰዱትም ከባለቤታቸው ጋር በቆዩባቸው የጋብቻ ጊዚያት ነው፡፡ ይህም ግለሰቡ ንብረቱ የጋራ ስለመሆኑ ማረጋገጣቸውን በግልጽ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሚሆን ጉባኤው አምኖበታል፡፡
ከዚህ ባሻገር አቶ አለማየሁ ለወረዳው ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባሳገቡት ማስረጃ ቤቱ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር በአንድነት የተገኘ የጋራ ንብረት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ይህም በህጋዊ ፊርማቸው በሰነድ ተያይዞ የተቀመጠ ሆኗል፡፡
በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንደኛው ተጋቢ የግል ሀብቱ ስለመሆኑ አስቀድሞ ካላስረዳ ንብረቱ በስሙ የተመዘገበ ቢሆን እንኳን የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል በሚል ተደንግጓል፡፡ ተጋቢዎቹ ከፍቺ በኋላ በአንድ ንብረት ላይ የይገባኛል ክርክር የሚያነሱ ከሆነም በህጉ የተቀመጠውን ግምት የሚያስተባብል ማስረጃን ሊያቀርቡ ይገባል፡፡
በጉባኤው ማረጋገጫ ፍርድ ቤቶቹ እስካሁን በግልጽ የቀረበውን ማስረጃ ባለመቀበልና ግልጽ ድንጋጌን በመጣስ የሰጡት ውሳኔ የአመልካቿን ከፍቺ በኋላ ንብረት የማግኘት መብት የሚጥስ ነው፡፡ ውሳኔው በጋብቻ አፈጻጸም፣ በጋብቻ ዘመንና በፍቺ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች እኩል መብት እንዳላቸው በህጉ የተቀመጠውን ድንጋጌም የሚጣረስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ውሳኔ
አጣሪ ጉባኤው በአመልካችና ተጠሪ መካከል ሲካሄድ የቆየውን ክርክር ሲመረምር ቆይቷል፡፡ በመጀመሪያ ውሳኔ በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ተላልፎ በየደረጃው ባሉ የኦሮሚያ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲጸና የሆነው ውሳኔ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9/1/ መሰረት ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም በማለት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ሊወሰን ችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013