አደገኛው ውድቀት

አስመራ እና ዓለምን አንድ የሚያደርጋቸው ብዙ ነገር አለ። ሁለቱም በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። የሁለቱም ባለቤቶች ወጣቶች ናቸው። ሴቶቹ አብዝተው ይዋደዳሉ። በአንድ ግቢ ውስጥ ተከራይተው ሲኖሩ፤ ቀሪዎቹ የጊቢው ተከራዮች ይቀኑባቸዋል። ‹‹የእነርሱ ፍቅር የተለየ ነው።›› እየተባለ ይወራላቸዋል። በአጋጣሚ ሁለቱም በተቀራራቢ ጊዜ ነፍሰ ጡር ሆነዋል። አንዷ ሌላዋ ቤት ገብታ ትበላለች፤ ትተኛለች፤ እንዳሻት ትሆናለች። ማንም ጣልቃ አይገባም። የሁለቱም ባሎች በሁለቱ ሴቶች ግንኙነት ደስተኛ ናቸው። አንደኛዋ ስለሌላዋ አውርታ አትጠግብም።

ሁለቱም ሴቶች አዲስ ባለትዳር በመሆናቸው ገና አልወለዱም። ነገር ግን ሁለቱም ነፍሰ ጡር ናቸው። አስመራ ወረታው ቀድማ ወለደች። ደስታ በሁለቱም ቤት ሞላ። ዓለም ዘለቀ ገና ለመውለድ ከሁለት ወር በላይ ይቀራታል። ዓለም አስመራን ማረስ ጀመረች። በሌሊት ቁርስ እየሠራች ትሠጣታለች። ቀን ሰው ስታስተናግድላት ትውላለች። አስመራ ገና በ25 ዓመቷ በመውለዷ ለመንቀሳቀስ አልተቸገረችም። ቀልጠፍ ብላ ተነሳች። ገና በአንድ ወሯ ልጇን ማጠብ ጨምሮ የቤት ሥራዋን መሥራት ጀመረች። ባለቤቷን ገብሩን ስትንከባከበው ተወዳዳሪ የላትም። ቁርስ እና ምሳው ተከሽኖ ይሠራለታል። ማታ ለእግሩ እና ለእጁ ውሃ ይሞቅለታል። ከእራት በኋላ ቆሎ ተቆልቶ ይቀርብለታል። ቡና እየተፈላ እየተጨዋወቱ፤ ስለጎረቤታቸው ዓለም እና ስለታዘበ እያወሩ ይሳሳቃሉ።

አስመራ ከባሏ የምትደብቀው ምንም አይነት ሚስጥር የለም። እንኳን የሰማችውን ስለሰው ያሰበችውን ሳይቀር ትነግረዋለች። የታዘብ ባለቤት ዓለምም በበኩሏ በተመሳሳይ መልኩ ባሏን አብዝታ ትንከባከበዋለች። እርሱም ሁሉም ነገር በግልፅ ይነገረዋል። ዓለም ለአስመራ ምን እንዳደረገች፤ ብቻ ሳይሆን በዝርዝር ምን እንዳወሩ ሁሉ ለታዘብ ትነግረዋለች።

መሐንዲሱ

ታዘበ ያለው የተወለደው ደቡብ ጎንደር እስጢፋኖስ ቀበሌ ነው። አባቱ ያለው ገረመው እና እናቱ ወይዘሮ ዓለምነሽ ዘገየ ታዘብን በመውለዳቸው ደስታቸው ወደር አጥቶ ነበር። እንደአካባቢው ልጆች ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ በአጭሩ ሕይወቱ እዛው አካባቢ በአርሶ አደርነት ተገድቦ እንዳይቀር ብዙ ጥረት አድርገዋል። በሌላቸው ገንዘብ ቀለብ እየሰፈሩ ቤት እየተከራዩ እስከመጨረሻው ለማስተማር ወስነው አምቦ ሜዳ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቡት። ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ሲማር፤ ተከታትለው እንዲያጠና እየመከሩ አሳደጉት።

ታዘብ ጥናት ልማድ ሆነ። ከክፍል ተማሪዎች መካከል አንደኛ መውጣት ለእርሱ አዲስ አስደሳች ነገር አልነበረም። በተለይ አዲስ ዘመን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማር ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ 1ኛ እየወጣ ጉብዝናውን አስመሠከረ። በመጨረሻም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ማጠቃለያ ፈተና ወስዶ ዩኒቨርስቲ ለመግባት በቂ ነጥብ አስመዘገበ። ታዘብ ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በሲቪል ኢንጂነሪንግ በ2006 ዓ.ም ዲግሪውን አገኘ።

ታዘብ ሕልሙ ትልቅ ነው። ታላቅ ተቋራጭ መሆን ይፈልጋል። በመንግሥት ተቋም ተቀጥሮ መሥራት አልፈለገም። አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በግሉ አነስተኛ ግንባታዎችን ማከናወን ጀመረ። ገቢ ሲገኝ ሚስት ፈለገ። ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር መዝናናት ተለማመደ። በዛው በአጋጣሚ ከዓለም ጋር በፍቅር ወደቀ። ሰው ሳይጠሩ፤ ሰፊ ድግስ ሳይደግሱ ትዳር መሠረቱ።

የጓደኛሞቹ ቅራኔ

ታዘበ እና ዓለም ቀን ቀንን ሲተካ ልጅ ለመውለድ አንድ ወር ብቻ ቀራቸው። በሌላ በኩል በወዳጅነታቸው ብዙዎችን ሲያስቀኑ የነበሩት ዓለም እና አስመራ ቅራኔ ውስጥ ገቡ። ምንም እንኳ ዓለም አስመራ አራስ እያለች አብዝታ ብትንከባከባትም የአስመራ ምላሽ አስደሳች አልሆነም። ዓለም ለታዘብ እንደነገረችው፤ ዓለም በጠዋት ቆንጆ ፍርፍር ሠርታ ልትሠጣት ስትሔድ፤ አስመራ ከባሏ ገብሩ ጋር ስታማት ደርሳለች። ዓለም ለአስመራ ‹‹ቁርስ ምሳ ብዬ ባበላሁሽ እንዴት እንዲህ ትይኛለሽ?›› ስትላት፤ አስመራ በበኩሏ ትሰድባታለች። ይህንን ግጭት ታዘብ ከሚስቱ ከዓለም በደንብ ሰምቷል። ከዛ ቀን በኋላም ሴቶቹ በተገናኙ ቁጥር መናቆር ጀምረዋል።

አንድ ቀን አስመራ ከዓለም ጋር ስትጋጭ፤ አስመራ ለዓለም ‹‹ሳትገላገዪ በሞትሽ›› ብላ ሰደበቻት። ዓለም በብስጭት እስከ ማልቀስ ደረሰች። እንደተለመደው ባሏ ግጭታቸውን ሰማ፤ የሚለው ጠፋው። በተለይ ‹‹ሳትገላገዪ በሞትሽ›› የሚለው ስድብ ሊያሳብደው ነበር። እንደምንም ራሱን ተቆጣጥሮ ቤቱ ቁጭ አለ።

አደገኛው ውድቅት

የመስከረም ወር መሆኑን ተከትሎ የግቢው ጭቃ መጠጥ ብሏል። በዚህም የግቢው ሰው ተደስቷል። በተቃራኒው ደግሞ በክረምት ከዝናብ የሚገኝ ውሃ ማጣት በመጀመራቸው የውሃ ችግር እያሰቃያቸው ነው። በአካባቢያቸው ከቧንቧ ውሃ የሚገኘው በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ለዛውም ውሃው የሚመጣው ሌሊት ከሰባት ሰዓት በኋላ ነው።

የእንቁጣጣሽ በዓል ባለፈ አራተኛው ቀን ዓለም የስምንት ወር እርጉዝ በመሆኗ እና ከአስመራ ጋር ተጣልታ በመከፋቷ በጊዜ እንቅልፍ ወስዷታል። ታዘበ በበኩሉ የጎረቤታቸው የአስመራ ስድብ እጅግ አበሳጭቶታል። እንቅልፍ አልወሰደውም። እኩለ ሌሊት ሰባት ሰዓት አካባቢ ተነስቶ ከቤት በመውጣት ውሃ መምጣቷን አየ። ውሃዋ መጥታለች። ጀሪካን ደቅኖ መጠባበቅ ጀመረ። እርሱ ተነስቶ እየቀዳ መሆኑን የሰማችው አስመራ፤ እርሷም ተነስታ የውሃዋን መምጣት አረጋገጠች። ወደ ቧንቧ ተጠግታ የያዘችውን ጀሪካን አሰለፈች። ታዘብ ዝም ብሏት የሞላለትን ጀሪካን አንስቶ የያዘውን ደቀነ። ዓለም ተናደደች። ‹‹የቆምኩት አሻንጉሊት መሰልኩህ፤ ደነዝ ደደብ።›› ብላ ሰደበችው።

ታዘብ ራሱን መቆጣጠር አቃተው በቀጥታ ወደ ቤቱ ገብቶ 45 ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለውን የፌሮ ዘነዘና ይዞ ወጣ። አስመራ በምንም መልኩ አልጠረጠረችም። አጎንብሳ በጀሪካን ውሃውን መሙላት አለመሙላቱን እያረጋገጠች ነበር። ታዘብ ከጀርባዋ በቅድሚያ ዘነዘናውን ማጅራቷ ላይ ሲያሳርፈው በግንባሯ ወደቀች፤ በዛ በውድቅት ሌሊት ኡኡታዋን ስታቀልጠው በድጋሚ በያዘው ዘነዘና ጭንቅላቷን መታት። ከዛ በኋላ አስመራ የሆነውን አታውቅም።

የአስመራን ጩኸት ባሏ ገብሩ ሰማ። ዘሎ ሲወጣ ከታዘብ ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ። ታዘብን ዘሎ አነቀው። ታዘብ በበኩሉ በያዘው ዘነዘና ጭንቅላቱን መታው። ዓለም ከእንቅልፏ ነቅታ ከቤት ስትወጣ። ጎረቤቶቿ ባል እና ሚስቱ መሬት ወድቀዋል። ባልዋ ታዘብ በበኩሉ ዘነዘናውን ይዞ እርሷን አልፎ ወደ ቤት ገባ። ዓለም በድንጋጤ የጨው ሐውልት ሆና ቆመች። የግቢው ሰዎች ተጯጯሁ።

የዓለም ሰውነት መንዘፍዘፍ ጀመረ። ጎረቤቶች ለአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ጥቆማ ሰጡ። በፍጥነት የዕለቱ ተረኛ ፖሊሶች መጥተው ሁለቱንም ባል እና ሚስት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱ፤ ተጎጂዎችንም ወደ ሕክምና ቦታ አደረሷቸው። አስመራ ምንም እንኳ በቶሎ በቅርብ ወዳለው ጤና ጣቢያ ብትደርስም ሕይወቷን ማትረፍ አልተቻለም። ባለቤቷ ግን ተረፈ።

የፖሊስ ምርመራ

የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ ባካሔደው ጥረት፤ መስከረም 4 ቀን 2015 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ወይዘሮ አስመራ ወረት በተባለች ሴት ላይ ወንጀል ተፈጽሟል የሚለውን ማረጋገጥ ቻለ። ድርጊቱ የተፈፀመው ሟች ወይዘሮ አስመራ እና ተጠርጣሪ አቶ ታዘብ በአንድ ግቢ ተከራይተው የሚኖሩ ሲሆን፤ ሌሊት ውሃ ሲቀዱ ‹‹ለምን በተራ አንቀዳም ውሃዋ ልትሔድ ትችላለች፤›› በሚል በነበረ ጭቅጭቅ ተጠርጣሪ አቶ ታዘብ ሟች ወይዘሮ አስመራን ጭንቅላቷ እና ማጅራቷን በመምታት ሕይወቷ እንዲያልፍ ማድረጉ ተረጋገጠ።

ከአስመራ በተጨማሪ ባለቤቷ ገብሩ ላይም ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ይህንንም ድርጊት የፈፀመው ተጠርጣሪ አቶ ታዘብ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን አሰባሰበ። የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአስከሬን የምርመራ ውጤትን፣ ተጠርጣሪው የሰጠውን የእምነት ክህደት ቃል እንዲሁም ስድስት የሰው ምስክሮችን አሟልቶ ለዓቃቤ ሕግ አቀረበ።

የዓቃቤ ሕግ ክስ

የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ታዘብ ያለው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን ተላልፎ ተገኝቷል። የወንጀሉ መነሻ ውሃ እኔ ቀድሜ ልቅዳ በሚል አለመግባባት የተነሳ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ይላል። በዚህ ሳቢያ ታዘብ ወረታው ከፌሮ በተሠራ ዘነዘና የወይዘሮ አስመራን ጭንቅላት እና ማጅራት በመምታት ሕይወቷ እንዲ ያልፍ አድርጓል።

ይህ ድርጊት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በተካሔደ የአስከሬን ምርመራ ውጤትንም አቀረበ። በአስከሬን ምርመራው በወይዘሮ አስመራ ጭንቅላት እና ማጅራት ላይ እስከ ጡንቻ ድረስ ጥልቀት ያለው ጉዳት በግራ የግንባር ጎን ላይ ተገኝቷል። የራስ ቅል ሽፋን መበለዝ እና የፊተኛው የራስ ቅልም መበለዙን ለማወቅ ተችሏል። የአንጎሏ የላይኛው ሽፋን የተወጠረ ሲሆን፤ የመሞቷ መንስኤም ስለታማ ባልሆነ ቁስ አካል በራስ ቅል ላይ ጉዳት በመድረሱ መሆኑ ታውቋል ሲል ዓቃቤ ሕግ የወንጀሉን ዝርዝር ለፍርድ ቤት አቅርቧል። በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም እንኳ ቀድሞ ፖሊስ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ የተጠየቀው ተከሳሽ ታዘብ ያለው ‹‹ያገኘኹዋት ወድቃ ነው።›› ብሎ ክዶ የነበረ ቢሆንም፤ በመጨረሻ ድርጊቱን ራሱ መፈፀሙን ከማመን አልፎ መፀፀቱን ገለፀ።

 ውሳኔ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ተከሳሽ ታዘብ ያለው ገረመው በሰው መግደል ወንጀል ጉዳይ ለቀረበበት ክስ ውሳኔ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ሕጉን እንዲሁም ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You