ዝናቡ ያለማቋረጥ እየዘነበ አካባቢውን ከማረስረስ አልፎ አጨቅይቶታል። ዝናብ እና ብርዱ ቆፈን ያስያዘው ታደሰ መላኩ፤ ክረምቱን እንደለመደው ደጀኔ ግሮሰሪ ሄዶ በማርታ እቅፍ ውስጥ ለማሳለፍ አሰፍስፏል። በሐምሌ 05 ቀን 2015 ዓ.ም ታደሰ አዘውትሮ ወደሚመላለስበት በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ስሙ አረቄ ሠፈር ተብሎ ወደሚጠራው መንደር ገባ።
ደጀኔ ግሮሰሪ ሲደርስ ማርታ በፈገግታ ተቀበለችው። ማርታ ቀጠን ያለች ዓይነ ትልልቅ ለግላጋ ወጣት ናት። ማርታ እና ታደሰ አብረው ቁጭ ብለው እየጠጡ መጨዋወት ጀመሩ። እየመሸ ሲሔድ ወደ ግሮሰሪው የሚገባው ሰው ቁጥር ጨመረ። ጫጫታውና ሁካታው ደመቀ። ማርታ ለአሥር ደቂቃ ከታደሰ ጋር ከተቀመጠች፤ ተነስታ ደግሞ ለሃያ ደቂቃ ሌሎች ሰዎችን እየታዘዘች እና እያነጋገረች ዞር ዞር ብላ ወደ ታደሰ መለስ ትላለች። ታደሰ የማርታ መለስ ቀለስ ማለት ብዙ አላሳሰበውም፤ አብራው እንደምታድር ርግጠኛ ነው።
ታደሰ እየጠጣ ሞቅ እያለው ቢሔድም፤ መጠጡን ከመደጋገም ይልቅ ከማርታ ጋር ከግሮሰሪው እስከሚወጣ ቸኩሏል። የማርታ ወጣትነት እና ውበት እየሳባቸው ታደሰ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የግሮሰሪው ተጠቃሚዎች አብረዋት እንዲያድሩ እየጠየቋት ነው።
የወጣቷ ሕይወት
ማርታ ሥራውን እንደጀመረች ከአንድ ወንድ ጋር እሺ ካለች፤ ለሌሎቹ ወንዶች ተይዣለሁ የሚል መልስ ትሰጣለች። ለሁሉም ያላት ስሜት ተመሳሳይ ነው። ሥራ ሆኖባት እንጂ ለየትኞቹም ፍቅር የላትም። አንዳንዴ አብረን እንሁን አብረሽን ተቀመጪ ሲሏት ይቀፋታል። ነገር ግን ዕጣ ፈንታ ሆኖባት ከቀፈፉዋት ሰዎች ጋር አብራ አንሶላ ትጋፈፋለች።
ሳትወድ ሕይወት አስገድዷት የገባችበትን ሥራ አትወደውም። እንደውም የሰዎች ጭካኔ እና ግፍ እያንገፈገፋት የእርሷም አመል ተቀይሯል። አሁን አሁን ወደ ሥራው የገባችው ለገንዘብ ስትል በመሆኑ፤ ከፍተኛ ገንዘብ የሰጣትን ሰው አስቀድማ ታገለግላለች። በርግጥ አንዳንዶች ከስሜታቸው ማብረጃነት አልፈው ፍቅር ውስጥ መውደቃቸውን ቢነግሯትም አታምናቸውም። ነገር ግን ለሁሉም ጥርሷን እያሳየች፤ ‹‹አይደል›› ትላለች።
ከታደሰ ጋር ከተዋወቁ ረዥም ጊዜ አስቆጥረዋል። ደጋግሞ በፍቅሯ እንደወደቀ ቢነግራትም አላመነችውም። እርሱም አንድ ወንድ አንዲት ሴትን ሲወድ ማድረግ ያለበትን እያደረገላት አይደለም። ባለው አቅም ሊያኖራት እና ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ሊያላቅቃት ጥረት ሲያደርግ አይታይም። እንደሌሎቹ ወንዶች ሁሉ ሲፈልግ ይመጣል። አብሯት ያድራል። በዚህ ምክንያት ማርታም ታደሰን ከሌሎች ወንዶች ለይታ አታየውም። አንዳንዴ ‹‹ እወድሻለሁ›› ሲላት ግን እንደሌሎቹ ወንዶች ጥርሷን አታሳየውም፤ እንደውም ትበሳጭበታለች።
ታደሰ በበኩሉ ምንም እንኳ ማርታን ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ባያወጣትም ደጋግሞ እንደሚወዳት ይናገራል። ነገር ግን ደፍሮ ሊያገባት አይፈልግም። ከእርሷ ጋር ትዳር መስርቶ ልጆች ለመውለድ ድፍረቱን አጣ። ስለዚህ እርሷን ከሌሎች ጋር እየተጋራ መኖርን መረጠ። በሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም እንደለመደው ታደሰ ማርታ ጋር ሲሔድ ገንዘብ ፈልጋ ስለነበር በደስታ ተቀበለችው። አብረው ለማደር ተስማሙ።
አታላይዋ
ታደሰ ‹‹አብረን እናድራለን›› ሲላት፤ እሺታዋን ገልፃለታለች። ነገር ግን ከታደሰ ጋር አብራ ለማደር ብትስማማም፤ በየመሃሉ ከታደሰ ጠረጴዛ ርቃ ወደ ሌላ ጠረጴዛ ስትሔድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍል ደንበኛ አገኘች። አላቅማማችም ከዚህኛው ጋርም አብራ ለማደር ተስማማች። ሁለቱም ጠረጴዛ ላይ ወዲያ እና ወዲህ እያለች ቀኑ መሸ። ሶስት ሰዓት ሲሆን፤ ለታደሰ አልጋ ቤት እንዲከራይ መከረችው። እንደነገረችው ሔዶ እዛው ከደጀኔ ግሮሰሪ ብዙም ሳይርቅ አልጋ ቤት ተከራየ።
ማርታ ታደሰን አታላ ከፍተኛ ብር ሊከፍላት ከተስማማው ሰው ጋር ከግሮሰሪው ወጣች። ታደሰ አልጋ ቤት ተከራይቶ ወደ ደጀኔ ግሮሰሪ ሲመለስ ማርታ የለችም። ምንም እንኳ ቢጠራጠርም ቁጭ ብሎ ጠበቃት። ማርታ ብቅ ብላ አልታየችውም። ደጋግሞ ስልክ ቢደውልላትም ስልኳ አይሠራም። ቁጭ ብሎ መጠጣቱን ቀጠለ። ትመጣለች ብሎ ቢጠብቅም ማርታን ማግኘት አልቻለም። እየጠጣ ከመስከር ይልቅ፤ እየተናደደ መብሰክሰክ ጀመረ።
የማርታን ጓደኛ አስጠርቶ የት እንደሔደች ጠየቀ። ጓደኛዋ ከሌላ ወንድ ጋር መውጣቷን ነገረችው። እርሱ ሌሊቱን አጋምሶ እየጠበቃት ከሌላ ወንድ ጋር ለማደር መውጣቷ በጣም አበሳጨው። ተስፋ አልቆረጠም፤ ግሮሰሪው እስከሚዘጋ እስከ ሌሊት ስድስት ሰዓት ድረስ ቢቆይም ማርታ አልተመለሰችም።
እየተብሰከሰከ ብቻውን ሊያድር ወደ ተከራየው አልጋ ቤት አመራ። የተከራየው አልጋ ቤት ሄዶ ዕንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር በንዴት ጨጓራው እየነደደ አደረ። ጠዋት ሶስት ሰዓት አካባቢ ከተከራየበት አልጋ ቤት ወጥቶ ወደ ደጀኔ ግሮሰሪ ሔደ። ማርታ መመለሷን ሲጠይቅ በእዛው ማደሯን እና ወደ ግሮሰሪው ተመልሳ እንዳልመጣች ተነገረው። ቀኑን ሙሉ እዛው አካባቢ ሲያንዣብብ ዋለ።
የማርታ ዕጣ ፈንታ
ታደሰ በማርታ መታለሉ እያንገበገበው ንዴቱ ሳይበርድለት ዋለ። 10 ሰዓት አካባቢ ወደ ግሮሰሪው መምጣቷን ሰማ። በጃኬቱ የግራ ኪሱ ውስጥ ቢላዋ ከቶ ወደ ደጀኔ ግሮሰሪ ገባ። በሰዓቱ ማርታ አላየችውም። ከአንድ ወንድ ጋር ቁጭ ብላ ስታወራ፤ እርሱ በቅርብ ርቀት ኮርነር ስር ተቀመጠ። ቢራ አዞ እየጠጣ ቆየ። ትንሽ ቆይቶ የሚጠጣውን ከቢራ ወደ አረቄ አስቀየረ። ማርታ ገና ስላልመሸ እና ብዙም ጠጪ ስለሌለ አብራው ከተቀመጠችው ሰውዬ ጋር ተመስጣ ታወራለች።
ታደሰ በደንብ ሞቅ ሲለው እጁን በጃኬቱ የግራ ኪስ ውስጥ ጨመረ። የቢላዋውን እጄታ አጥብቆ ይዞ ተነሳ። ማርታ ከደንበኛዋ ጋር ተጠግታ ስታወራ፤ ታደሰ የያዘውን ቢላዋ ከኪሱ አውጥቶ እያሳያት ፊት ለፊቷ ቆመ። ማርታ በድንጋጤ ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ በያዘው ቢላዋ ሆዷን ወጋት። ማንም ሊከለክለው አልቻለም። ትከሻዋን፣ ደረቷን እና አገጯን ደጋግሞ በመውጋት እዛው ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጎ ሮጦ ወጣ። ታደሰ ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ እየሮጠ ከአካባቢው ራቀ። ሊይዘው የሞከረ አልነበረም።
ማርታ ማንም ሳይከላከልላት ገና በወጣትነት ዕድሜዋ በአጭሩ ተቀጨች። ሰዎች ተጯጯሁ። ገሚሱ ‹‹ፖሊስ ይጠራ፤ ሞታለች ኡኡኡ….››፤ ሲል ገሚሱ፤ ‹‹ሐኪም ቤት… እንውሰዳት፤ አልሞተችም…›› እያሉ ተተራመሱ። ‹‹አትንኳት በኋላ ችግር ነው›› እየተባለ ማንም ሳይጠጋት እንዲሁ ሲጯጯሁ በመሃል በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች ደረሱ። ታደሰ ከግሮሰሪው መሮጥ የጀመረ ጎሮ ፖሊስ ጣቢያ ሲደርስ ቆመ፤ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ገብቶ እጁን ሰጠ።
የፖሊስ ምርመራ
በሐምሌ 03 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 11፡30 ሲሆን፤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው አረቄ ሰፈር ደጀኔ ግሮሰሪ ውስጥ ወንጀል መፈፀሙን በአካባቢው በመዘዋወር ላይ የነበሩ ፖሊሶች ጥቆማ ሰጡ። የፖሊስ ምርመራ ቡድን ቦታው ላይ ሲደርስ የወጣት ማርታ ሕይወት አልፏል። የምርመራ ቡድኑ አስክሬኑን በጥንቃቄ በማንሳት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ላከ።
በአካባቢው ከወንጀሉ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በሙሉ ሰበሰበ። በሰዓቱ ወንጀሉ ሲፈፀም የተመለከቱትን ሰዎች ስም እና አድራሻ መዘገበ። ፖሊስ ባካሔደው የማጣራት ሥራ ተጠርጣሪ ታደሰ መላኩ ነዋሪነቱ ኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ሲሆን፤ የቤት ቁጥር አዲስ በሚል የተመዘገበ መሆኑን አወቀ። ሟች ማርታ በሴተኛ አዳሪነት እንደምትተዳደር አጣራ።
የምርመራ ቡድኑ ታደሰ መላኩ ሰውን ለመግደል በማሰብ የሴተኛ አዳሪነት ሥራ የምትሠራዋን እና የፍቅር ጓደኛው የሆነችውን ሟች ማርታ ታደሰን ጨካኝነቱን እና ነውረኛነቱን በሚያሳይ ሁኔታ ቢላዋውን በጃኬቱ በመያዝ ግሮሰሪ ከገባ በኋላ ሆዷን፣ ደረቷን፣ አንገቷን፣ ትከሻዋን እንዲሁም ክንዷን እና ፊቷን በተደጋጋሚ ወግቶ የገደላት መሆኑን የሚያሳውቅ ሙሉ ማረጋገጫ አገኘ።
የምርመራ ቡድኑ የወንጀሉን አፈፃፀም ሁኔታ የሚገልፁ እና ተጠርጣሪው መግደሉን በተመለከተ የሚመሰክሩ የ10 ሰዎችን ምስክርነት እንዲሁም ተጠርጣሪው ወንጀሉን እንደፈፀመ የሰጠውን የእምነት ክህደት ቃል አደራጀ። የሟች ማርታ ጓደኛ በሰጠችው የምስክርነት ቃል ላይ እንደተናገረችው፤ ሁለቱም አብረው ቆይተው አብረው እንደሚያድሩ ተነጋግረው ነበር። ይህንን ተከትሎ ታደሰ ደግሞ ግሮሰሪ አልጋ ተከራይቶ ሲጠብቃት፤ እርሷ ግን ወደ ሌላ ቦታ ሔዳለች። እየጠጣ ሲጠብቃት ቢያመሽም እንዳልመጣች እንዲሁም በዛ ተበሳጭቶ በማግስቱ መጥቶ በቢላዋ ወግቶ እንደገደላት ተናገረች።
ይህንን ምስክርነት እና ሌሎችም የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአስክሬን የምርመራ ውጤትን እና ገላጭ ፎቶግራፎችን ጨምሮ የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት አስተላለፈ።
የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ታደሰ መላኩ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን ተላልፎ ተገኝቷል በማለት፤ የወንጀሉ መነሻ ከእኔ ጋር ለማደር ተስማምተሽ ለምን ጥለሽኝ ሄድሽ የሚል መሆኑን ጠቁሞ፤ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ወንጀለኛ መሆኑን አረጋግጦ የቅጣት ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ሲል ክስ መሰረተ።
ውሳኔ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የዓቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ታደሰ መላኩን ክርክር ሲያዳምጥ ቆይቶ በግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ተከሳሽ ታደሰ መላኩ በሰው መግደል ወንጀል ጉዳይ ለቀረበበት ክስ ውሳኔ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ሕጉን እንዲሁም ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በ16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አሳለፈ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም